Saturday, March 16, 2013

በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

ቁጥራቸው በግምት ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የኢትዮጵያ መንግስት ያለዓግባብ አስሮ እያንገላታቸው የሚገኙትን የሃይማኖት መሪዎቻቸውንና እንዲሁም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በአስቸኳይ እንዲፈታ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ከቀትር ሰዓት በኋላ እዚህ ስቶክሆልም ከተማ በሚከኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ፊትለፊት አደረጉ። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ ሙስሊም ወገኖቻቸው ላይ የሚደርሰውን እንግልት፡ዝርፊያ እና ህገወጥ ብርበራ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁ ሲሆን መንግስት በዩኒቨርሲቲና በሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በመማር ላይ በሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውን ላይ እያደረሰ ያለውን ማዋከብና ማስፈራራት ከትምህርታቸው እያፈናቀለ ያለውን አፓርታዳዊ ተግባር እንዲያቆም ጠይቀዋል።
በእለቱ የእስልምና እና የክርስትና መሪዎች በየተራ ንግግር ያሰሙ ሲሆን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በእስልምናና በኦርቶዶክ ቤ/ክ ሃይማኖቶች ላይ እያደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት በማውገዝ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም የተቋውሞ ሰልፈኞቹ የጸረአሸባሪነት ህግ ከለላ በማድረግ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች፡የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ በአንድ ድምጽ ጠይቀዋል።
Ethiopian Muslims' Protest in Stockholm March 15, 2013. በእለቱ የስዊድሽ ሶሻል ዴሞክራትስ ፓርቲ ተወካይ ባደረጉት ንግግር ዛሬ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የዜጎች የመናገር የመጻፍ እና የሃይማኖት ነጻነት እንዲሰፍን ከሚታገሉ ወገኖች ጋር ያላቸውን የትግል አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ እያደረገ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አፈናና እስር በማውገዝ በሃገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ እስርቤቶች ያጎራቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የህሊና እስረኞች እንዲፈታ ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በጸረ ሽብር ክስ ተወንጅለው በእስር ላይ በመንገላታት ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ሌሎች የህሊና እስርኞች የሚዘክር ግጥም ቀርቧል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ እና ድምጻችን ይሰማ የሚለውንና ሌሎች የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት መንግስት በእምነት ነጻነት ላይ እያደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ እንዲያቆም በተለይም ጅሃዳዊ ሃረካት የተባለውንና በሰላማዊ ዜጎች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር ሆን ተብሎ በመንግስት ሃላፊዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውንና በኢቲቪ የተላለፈውን ፊልም አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። ቴዎድሮስ አረጋ መጋቢት
፳፻፭ ስቶክሆልም ስዊድን

No comments:

Post a Comment