Saturday, December 28, 2013

እኔ አላውቅም ፈራሁ ጁሃር (ከሄኖክ የሺጥላ)

ሄኖክ የሺጥላ
Poet Henok Yeshitela  የበደሌ ቢራ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 483 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ኢሉ-ኣባ-ቦራ ( Eloo The father of Holstein Friesian) ኢልባቡር ከተማ በሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ስኩዌር ሜትር ይዞታ ላይ ስራውን እንደ ኣውሮጳውያን ኣቆጣጠር በ1993 ማከናወን የጀመረ ትልቅ የቢራ ማምረቻ ድርጅት ነው።
ኢሊባቡር መልካ-ምድራዊ ኣቀማመጡም ሆነ ምድራዊ ልምላሜው፥ እንደ በቆሎ ፤ ገብስ፤ ጤፍ፤ የቅባት እሎች፤ ማር፤ ከነ ቦራ ደሞ ወተት፤ ቅቤ እና ወዘተ የሚዘራባት፤ የሚታጨድባት፤ የሚቆረጥባት፤ የሚታለብባት ሃገር እንድትሆን ኣድርጉዋታል።
ኢሊባቡርን የጽሁፌ መንደርደሪያ አደረኩ እንጂ ዋናው ነጥቤ እሱ አይደለም። ዛሬ መናገር ወይም መጻፍ የፈለኩት ቴዲ አፍሮ በቅርቡ በመላው ኢትዮጵያ የሙዚቃ ዝግጅቱን እንዲያሳይ ወኪል የሆነውን የበደሌ ቢራን ያለመጠጣት አድማ ( boycotting) በመላው ኢትዮጵያ ይደረግ ዘንድ አንዳንድ ግለሰቦች የጀመሩትን ነገር ሰምቼ፤ ለምን በደሌን፤ ለምን ቴድን የሚል ጥያቄ ለሚጠይቁ፤ መልስ የሚመስለኝን ለመተየብ፤ ከተቻለም ለማሳየት መሞከር በመሻቴ ነው ።
ቴዲ አፍሮ በቅርቡ በጋዜጣ ላይ ስለ አድዋ ድል በሰጠው አስተያየት የተቆጡ፤ የተቀየሙ ግለሰቦች፤ ቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” ብሎ ንጉስ ሚኒሊክን፤ ከዛም በላይ አድዋ ድልን በመዘከሩ የተበሳጩ የህብረተሰብ አካሎች፤ ቴዲ አፍሮ ከዚህ ቀደም “ጃ-ያስተሰርያል” ብሎ በመዝፈኑ ቂም የቁዋጠሩ ሰዎች፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን በ 1936 የኢጣልያንን የተለከለ የኬሚካል መሳሪያ መጠቀምን በመቃወማቸው፤ ኢትዮጵያን የዩናትድ ኔሽን ኣባል በማድረጋቸው፤ ቅራኔዎችን አብርደው ያፍሪካን ህብረት በመመስረታቸው፤ ለነዚህ ጉልህ አስተዋጾዎቻቸው በመዝፈኑ፤ ለነዚህ ለተጠቀሱት መልካም ስራቸው መታሰቢያ የጭንቅላቱ ውጤት የሆነውን ሙዚቃ በማበርከቱ፤ ቴዲ አፍሮ ፤ አቀንቃኝና አዝማሪ ፤ ገጣሚና ስዓሊ፤ ሃያሲና ደራሲ፤ ጸሃፊ ተውኔቱና ብላታው፤ አፉን በለጎመበት ዘመን፤ በብእሩ የታሪክ ጋሻ፤ በግጥሙ ለቆሰለ ታሪክ ማገገሚያ፤ በዘፈኖቹ ( ከማሊ ሱፊዎች ባልተናነሰ መልኩ) የነብስን ክር እየተጫነ ያላስለቀሰው፤ ያላስተከዘው፤ ሰው እንደሌለ የገባቸው ሰዎች፤ በይበልጥም የአድዋ ድል፤ የጥቁር አንበሳዎች ድል መሆኑን ያሳየበት በመሆኑ እና ይህም የሚያማቸው ሰዎች፤ ዛሬ በደሌ ቢራ ቴዲ አፍሮን ስፖንሰር ስላደረገ፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት አድማ ጠርተዋል። አሁን ቴዲ አፍሮን አብዶ በረንዳ (የጫት ማከፋፈያ በረንዳ ነው) ቢሆን ስፖንሰር ያረገው ምን ሊሉ ነበር።። ባረገው እና የተከታዮቻቸውን መልስ ባየን። አንድ ጊዜ ቆይ ጠብቁኝ ሳቄ መጣብኝ ያለው ተናጋሪ ማን ነበር።
አዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም (ጥቁር ሰው) የብዙዎቹን ኢትዮጵያዊያኖች ድምጽ ያስገኘለትን ያህል፤ ንጉስ ሚኒሊክ በድሎናል፤ ጡታችንን ቆርጦዋል፤ ወዘተ ወዘተርፈ ለሚሉት ደሞ፤ ከሚኒሊክ መፈጠር፤ ከታሪክ አንቅጽነቱና አኩሪ ገድሉ ጋር የጀመሩትን እጹብ ጸብ ውሃ የሚደፋበት በመሆኑ፤ ጠላት ሊያፈራበት እንደሚችል መገመት ብዙም አይዳግትም። እናም እነዚህ ሰዎች ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስኩት፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት አድማ እናድርግ እያሉ ነው። ልክ ናቸው፤ ህዝብ በጥላቻም በቢራም ሰክሮ እንዴት ይሆናል፤ ባንዱ ብቻ ይበቃልና።
በነገራችን ላይ ይህንን አድማ ለማስመታት ከሚራወጡት እና ከሚሯሯጡት ሰዎች መሃከል አንዱ ጁሃር መሀመድ መሆኑን ሰምቼ አፍሬ ጥፍሬ ውስጥ ልገባ ነበር። ባንድ ወቅት ይሄ ወጣት ፖለቲከኛ ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ እናቴ መንዜና የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነች አባቴ ደሞ ኦሮሞና ሙስሊም ነው ፤ ታዲያ ከኔ በላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ምንነት ኣለ ወይ” ብሎ ነበር። መልሱ ሊሆን ይሚችለው ጁሃርዬ በውነትም የለም፤ እንዳንተው አቶ መለስም እኮ የተላቀቀ ነገርን ማጣበቅ የሚችል (ኡሁ የሆነ) (UHU…glue) ደም ነበራቸው፤ ግን ደሙ ሳይሆን የደሙ ባህሪ ነው ወሳኙ ነገር። የተሸከምነው ደም ሳይሆን በውስጣችን ያፋፋነው ስብዕና ነው ማንነት ፤ ማንነት ስራ ነው እንጂ አንተ እንዳልከው የ-ኢ-ተጎራባች ዘር ደም ውህደት (ኬሚስትሪ ውጤት አይደለም)፤ ክርስቶስ (ኤሳው… ኣለይሁ ሰላም) በ-በረት ተወለደ ብለን እናምናለን፤ ግን እንደ ሰብኣዊ ፍጡር በ-በረት መወለዱ ሳይሆን ሰው ሆኖ ሲኖር ያደረገውን ነገር ነው የምናስበው፤ ስለ ነብዩ ሙሃመድ (ሰ.አ.ወ) ኣንድ ሙስሊም ሲያስብ ስለ ዘራቸው ሳይሆን ስለ ስራቸው ነው የሚያስበው ብዬ አስባለሁ ።
ባንድ ወቅት ይሄው ሰው፤ ፹ ከ ፻ የሚሆነው የሃገሬ እስላም ኦሮሞ ነው፤ እናም የኦሮሞ ህዝብን ኢምፓወር ማድረግ፤ እስልምናን ኢምፓወር እንደማረግ ነው አለን፤ ለመስማት አይደል የተፈጠርነው እናም ሰማነው፤ “በሜጫ” አለን ዝም ብለን ሰማነው፤ ቀጥሎም “ኢትዮጵያ አውቶ ኦፍ ኦሮሚያ” አለን እሱንም ሰማነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ኣውት ኣፍ ኦሮሚያን ወደ ፈርንጅኛ ስቀዳው ( the child give birth of her mother) ኣይመስላችሁም ? ለመተርጎም የተገደድኩት የመጀመሪያው ራሱ እንግሊዘኛ መሆኑን ስለተጠራጠርኩ ነው። ለነገሩ ስታንፈርድና ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ እኮ መፈክር አያስተምሩም።
እና ዛሬ በደሌ መጣ እና ወንድሜ ጁሃር ሰማኒያ ከመቶ ካለው ሃሳብ ጋ ግንባር ለግንባር ተጋጨ ( head on collusion) እናም ሁለት የሚጋጩ ነገሮችን እንግዲህ እናስተውላልን።
፩) መቼም ፹ ከመቶው እስላም ኦሮሞ ነው ብለኽን፤ አንተም በዘር ብቻ ሳይሆን በእምነትም ጭምር ጠበኽ፤ ኣልገባኝም ታዲያ እንዴት ነው፤ እነማን ቦይ ኮት እንዲያረጉልኽ ነው ጥሪውን ያቀረብከው፤ ፳ ፐርሰንቱ እስላም ያልሆነው ኦሮሞ ? ደሞ ከ ፹ ከመቶ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ውስጥም ቢሆን አዲስ የበደሌ አድመኛ ማግኘት ይቸግራል ብዬ አስባለሁ፤ ምክኒያቱም እነሱ ላንተ ሲሉ ሳይሆኑ ለዲናቸው ሲሉ ድሮም እንዲህ አይነቱን ነገር ይነኩት ነበር ብዬ አላስብም፤ በፍጽም አያደርጉትም፤ ታዲያ የማይጠጡ ሰዎችን ነው አድማ የጠራነው፤ ወይስ ሙሉ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ምሳሌ እንድትሆን ያደረገችህ የመንዜዋ እናትህን ዘመዶች፤ እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ሄኖክ ነው ያለኝ የልጅነት ጉዋደኛዬ፤ ባንድ ትልቅ የውሃ ጉድጉዋድ ውስጥ እንሹለክ ስለው። እኔ አላውቅም ፈራሁ ጁሃር።
ዛሬ ጀርመን ያላትን ቅርጽ እንድትጠብቅ ወይም እንዲኖራት ያደረገው ኦቶ ቮን ቢስ ማርክ፤ የደም ትግል ውጤት ነው። ታዲያ ጀርመኖች በቢስ ማርክ ተናደው ፒሊሲነርን (የጀርመን ታዋቂ ቢራ ነው) ቦይ ኮት እናርግ አላሉሉም። በፈረንሳይ እንዲህ የሚባል ታሪክ አለ፤ በአሜሪካም፤ ኣረ ሆመር በጥንታዊያኖቹ የግሪክ ዘመን ስለነበረው ጦርነትም ጽፎዋል፤ ስለ ስርኣቱ፤ ስለ አገማምኖን እና የወንድሙ መንግስት፤ ስለ ሄለናዊው ስርዓት፤ ከዚያም በሁዋላ እነ ዳንቴ ስለ ጻፉት ስለ ዲቫይን ኮሜዲ፤ ፍሬድሪክ ዊልሃልም ኒቺ ስለተራቀቀበት የማህበረሰብ ስነ ልቦና፤ እነ አልበርት ካሙ ስለጻፉለት የፈረንሳይ ማህበረስብ እና በየስራቶቹ ውስጥ ስለ ነበርው ፍዳ፤ እነ ልዮ ቶሎስቶይ በሰላ ብእራቸው ስለዘገቡት የሩሲያ የጭቆና ቦለቲካ፤ እነ ፓብሎ ፒካሶ ጉሬንሽያ ብለው ስለገለጹት የስፔን ከተማ ስለ ስንቱ ለዚህ ለወጣቱ ፖለቲከኛ እንንገረው እስኪ ባክህ ጁሃርዬ ገረፍ ገረፍ አርጋቸው (በቃ እንደውም ለዚህ ክረምት ለፐርሰናል ዲቨሎፕመንት…ትመለከታቸው ዘንድ እጠይቅሃለሁ (ማሳሰቢያ በኣብዛኛው በአማራ ጻሀፊ አይደልም የተጻፉት ቢሆኑም ደሞ ኣነተ ሃምሳ ፐርሰንት አማራ አይደለህ እንዴ፤ የምሬን እኮ ነው)
በታሪክ ላይ ጥላሸት መቀባት በፍጹም ለማንም አይሳካም፤ ወደድንም ጠላንም፤ ጠቅልለን የምንጎርሰውን እንጀራ የፈጠሩት አባቶቻችን ናቸው፤ ለሆዳችን ያለን ቅርበት ለታሪካችንም ይኑረን። ቴዲ እንዳለው ክፉውን በክፉ ለመመለስ ማሰብ ሌላ ክፉነት ነው። ሁለቱ ደሞች እንደ ደም ይሰሩ፤ ያስቡ ዘንድ ሰው እንሁን።