Tuesday, June 3, 2014

ሦስተኛዋን ‹‹እሁድ››- በአራዳ ምድብ ችሎት (ጽዮን ግርማ)



የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ስድስቱን ጦማሪያንና ሦስቱን ጋዜጠኞች በሰንበት ቀን ለሚሰየም ተረኛ ችሎት መቅጠሩን የተለመደ አድርጎታል፡፡ ከቀናት በፊት በሦስቱ ብሎገሮች አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ላይ በተሰጠው የዐሥራ አራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መሠረት የቀጠሮው ቀን ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር፡፡ ዛሬ በዚህ ፍርድ ቤት ተገኝቼ የነበረውን ሁኔታ መከታተል ባልችልም ምንጮቼ የነገሩኝን ዝርዝር እንዲህ ጽፌዋለሁ፡፡
ጠዋት
እንደተለመደው ኹሉ የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች፣ጓደኞች፣የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች የአራዳውን ምድብ ችሎት የጓሮ በር እያለፉ ወደ አሮጌው ፍርድ ቤት ግቢ መግባት የጀመሩት ጠዋት ሦስት ሰዓት ከመሙላቱ አስቀድሞ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከፍርድ ቤቱ ከፍ ብሎ በሚገኘው ማዕከላዊ ለሚገኙት እስረኛ ልጆቻቸው ቁርስ የማድረሻ ሰዓት ስለኾነ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲኖር ከማዕከላዊ በቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት ይመጣሉ፡፡ በዛሬው ችሎት ላይ ለመገኘትም ከቁርስ መልስ ሰብሰብ ብለው ነበር ወደ ፍርድ ቤት ግቢ የደረሱት፡፡
ፍርድ ቤቱ ሲደርሱ ግቢው በጸጥታ የተሞላ ነበር፡፡ አንድም የተከፈተ የችሎት በር አልነበረም፣ግቢውን ከሚጠብቀው አንድ ፖሊስ በስተቀር ሌላ ሰው የለም፡፡ ጠባቂው ፖሊስ ‹‹ዋናዎቹ ፖሊሶች›› ሲመጡ አንድ ላይ መሰብሰባቸው አይቀርም በሚል ይመስላል ወደ ፍርድ ቤቱ የሚገባውን ሰው በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስቦ እንዲቆም ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ሰዓቱ ረፈድ እያለ ሲመጣና ጸሐዩ ሲበረታ ግን ግቢው ውስጥ የቆመው ሰው ተበታትኖም ቢሆን ጥላ ፈልጎ እንዲቀመጥ ፈቀደ፡፡ የቀጠሮው ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ሁሉም አመጣጡ እንደገጠመለት እየተቧደነ ባገኘው ነገር ላይ ተቀምጦ ፖሊስ ሊጠይቅ ይችላል ያሉትንና ፍርደ ቤቱ ሊሰጠው ስለሚችለው ትእዛዝ ግምታዊ መላምቱን እያስቀመጠ ጭንቀቱን በተስፋ ለማራገፍ ውይይቱን ቀጥሏል፡፡‹‹ተጨማሪ ዐስራ አራት ቀን ሊጠይቁባቸው ይችሉ ይኾን?›› አንዱ ይጠይቃል፡፡ ‹‹የሽብር ተግባሩን ጠቅሰው ሃያ ስምንት ቀን ይጠይቁባቸዋል›› ሌላኛው ሰው አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል በፍርድ ቤት ጉዳዮች በቂ ልምድ ያለው አንድ የሕግ ባለሞያ፤‹‹መዝገቡ በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ባለፈው ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የሽብር ተግባርና የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ ስላደረገው ዛሬ መልሶ እሱን ማንሳት አይቻልም ፖሊስ ጥያቄውን እንደገና ማቅረብ ቢፈልግ እንኳን በይግባኝ እንጂ መልሶ በዚህ ችሎት የሚያቀርብበት ሥርዓት አይኖርም፡፡›› በማለት ሞያዊ አስተያየቱን ሰጠ፡፡ የሕግ ባለሞያው የተቀመጠበትን ዙሪያ ከበው የተቀመጡት ወዳጅ ቤተሰቦች አስተያየቱን ሰምተው ‹‹ቢበዛ ፖሊስ ሊጠይቅ የሚችለው ዐሥራ አራት ቀን ነው፤እሱንም ቢኾን የሽብር ተግባሩን ሳያካትት በማለት›› ተስፋን ለራሳቸው ሰነቁ፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩት ቀጠሮዎች ችሎቱ ሲሰየምበት ከነበረው ሰዓት እያለፈ ሲሄድ ሁሉም ሰው ግራ ተጋብቶ የነበረ ቢኾንም አምስት ሰዓት ሊሞላ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አንድ ዕድሜው ከሃያ አራት የማይዘለው ጎርመስ ያለ ወጣት ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ ገብቶ ተረኛ ኾኖ መመደቡንና ነገር ግን ችሎቱም አለመከፈቱን የጽፈት ቤት ኃላፊም አለማግኘቱን በመግለጽ የፍርድ ቤቱ ሠራተኛ የሚመስለውን አንድ ሰው ጠየቀ፡፡ ለችሎት ጸሐፊዋ ስልክ ተደወለላት፡፡ እርሷ እስክትመጣም አስቀድሞ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ሊቀርብ ከመጣው መርማሪ ፖሊስ ጋር ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡
ሠላሳ ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ እስረኞቹን ይዘው የመጡት ቁጡ (ከሌላው ጊዜ በእጅጉ የባሱ) የፌደራል ፖሊሶች ወደ ግቢው ገብተው ተበታትኖ የቆመውን ቤተሰብ እንደተለመደው ሰብስበው በአንድ መስመር አቆሙት፡፡ ማንም ሰው ፎቶ ማንሳት እንደማይችል፣ስልክን መነካካት ክልክል እንደኾነ በመግለጽ ማስጠንቀቂያ ሰጡ፡፡ ከፍርድ ቤቱ ግቢ ጀርባ ባለው መኪና ማቆሚያ ቦታ ለረጅም ሰዓት ተቀምጠው የቆዩትን ተጠርጣሪዎቹንም ይዘዋቸው ወደ ግቢው ገቡ፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላና በፍቃዱ ኃይሉ እንደተለመደው በሰንሰለት ታስረው ገቡ፡፡ ማኅሌት ፋንታሁን እጆቿ በሰንሰለት ባይታሰሩም አንገቷን በሐዘን ቀብራ ነበር ወደ ግቢው የገባችው፡፡ በአቤል ፊት ላይ የጥንካሬ መንፈስ ቢታይም የበፍቃዱ ዐይኖች መቅላት ለሊቱን በምርመራ ሳያድር እንዳልቀረ ይጠቁማሉ፡፡
የእጆቻቸው ሰንሰለት ተፈቶ ችሎት ከገቡ በኋላ፤ከችሎት ውስጥ የሚወጣውን ምላሽ ለመጠበቅ ቤተሰብ ትንፋሹን ውጦ በቆመበት መጠባበቅ ጀመረ፡፡እንደሌላው ጊዜ ከአንድ ተጠርጣሪ አንድ ቤተሰብ እንዲገባ እንኳን አልተፈቀደለትም ነበር፡፡ ችሎቱ ከተሰየመ ዐሥር ደቂቃ እንኳን በቅጡ ሳይሞላው ለዘለፋ እና ለቁጣ የተዘጋጁ የሚመስሉ የፌደራል ፖሊሶች ወደ ተሰበሰበው ሰው ቀርበው ‹‹ግቢውን ለቃችሁ ውጡ እዚህ መቆም አይቻልም›› በማለት ማመናጨቅና መገፈታተር ጀመሩ፡፡ ‹‹ጠበቃው እስኪወጣ እንኳን እንጠብቅ የሚባለውን ከእርሱ ነው የምንሰማው›› ሲል ቤተሰብ ተማጸነ፡፡ፖሊሶቹ ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ ኾን ብለው ሰዎችን ለማዋረድ የሰለጠኑ ይመስላሉ፡፡ ግፊያና ዘለፋውን ቀጠሉበት፡፡
አንዲት ሴት ፌደራል ፖሊስ እየተንደረደረች ወደ ተሰበሰበው ሰው ቀርባ ከፊት ያለውን ሰው መገፈታተር ጀመረች፡፡ ግፍተራው የበዛባት የበፍቃዱ ኃይሉ እህት ልቧ ወደ ታሰረው ወንድሟ ሄዶባት ቢያንስ ከችሎት ሲወጣ ለማየት እንድትችል ግፍተራውን እየተከላከለች ፍርድ ቤት ግቢው ውስጥ ቆሞ የመጠበቅ መብት እንዳላት በመግለጽ ለፖሊሷ ልታስረዳት ሞከረች፡፡ ፖሊሷ ግን ተቆጣች እጅግም ተናደደች፤‹‹የምን መብት ነው ያለሽ፤ውጪ ብዬሻለሁ ውጪ፤አንተ ዱላውን አቀብለኝ›› የሥራ ባልደረባዋ ዱላውን እንዲያመጣላት አዘዘችች፡፡ ያሁሉ ሰው በተሰበሰበበት ዱላ ተቀብላ ለመማታት ተጋበዘች፡፡ የበፍቃዱ እናት ግን አላስቻላቸውምና ልጃቸውን ለመከላከል ለመሃል ገቡ፡፡
ፖሊሷ ማንን ፈርታ እርሳቸውንም አብራ ገፈተረቻቸው ግቢውን ለቀው እንዲወጡ እያመናጨቀች ገፋቻቸው፡፡ የበፍቃዱ እናት የታሰረው ልጃቸውን ከኋላ ትተው ያልታሰሩትን ከፖሊስ ዱላ ለማስጣል እንባቸውን አረገፉት፡፡‹‹ዛሬ እናንተ ባለጊዜ ሆናችሁ ነው፤ፈጣሪ ፍርዱን ይሰጠናል›› በማለት ፍርዱን ከፈጣሪ ጠየቁ ፡፡ ሌሎችም አገዟቸው፡፡የእርሳቸው ለቅሶ ሌሎችን አስለቀሰ፡፡ ፖሊሷ ግን ዱላዋን ተቀብላ እያስፈራራች ይበልጥ ወደ ተጠጋች ሰዉ ግቢውን ለቆ የማይወጣ ከኾነ ዱላው የማይቀርለት መኾኑን በሚገልጽ አኳኋን እያመናጨቀች አባረረች፡፡ ራሳቸውን ከፖሊሷ ዱላ መከላከል እንደማይችሉ የገባቸው እናት በሁለቱ ልጆቻቸው ተደግፈው እየተላቀሱ ግቢውን ለቀው ወጡ ሌሎቹም ተከተሏቸው፡፡
ጠበቃው አቶ አመሐም ከችሎት ከወጡ በኋላ እንዳስረዱት ፖሊስ፤‹‹ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በወንጀል በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 59/2 መሰረት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀን በምርመራ ላይ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሚስጥራዊ በኾነ መንገድ በሕቡዕ በመደራጀት በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን የያዘውን መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ከሥልጣን ለማውረድ በማሰብ፣ ይህንንም ሐሳብ በውጭ አገር ከሚገኙ አሸባሪ ድርጅቶች ጋራ በመስማማትና አገሪቱን ለማተራመስ ትእዛዝ በመቀበል፣ትእዛዙን ለማሳካት የሚያስችላቸውን ገንዘብ በመቀበል፣እንዲሁም ስልጠና በመውሰድ በአገሪቱ ላይ ብጥብጥ ለማነሳሳትና ብጥብጡንም ለመምራት በመንቀሳቀስ የሽብር ተግባር ፈፅመዋል፡፡ በመኾኑም ይህን የሽብር ተግባር ለማጣራት እንዲረዳን በፀረ-ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 28 መሰረት ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን›› የሚለውን ቀደም ሲል አቅርቦት የነበረውን ማመልከቻ መልሶ አቀረበ፡፡
ጠበቃው በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በነበረው ቀጠሮ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን የቀጠሮ መዝገብ ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ለመቀየር አመልክቶ ውድቅ ተደርጎበታል፣ ፖሊስ ቀድሞ በተሰጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ይግባኝ ሊጠይቅ ይገባል እንጂ በተመሳሳይ ችሎት እና ጉዳይ ላይ በፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገን ማመልከቻ መልሶ ማቅረቡ ከሕግ አኳያ ተገቢ አይደለም ሲሉ መከራከሪያ አቀረቡ፡፡ ነገር ግን የፖሊስ ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቅዷል፡፡
በመጨረሻ ከዐሥራ አራት ቀናት በፊት በነበረው ቀጠሮ ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ችሎቱን ለመታደም የመጣውን ሰው ፖሊስ ከግቢው ውጪ አቁሞት ነበር፡፡ ኾኖም ተጠርጣሪዎቹ በመኪና ተጭነው ሲወጡ ከበር ላይም ቢኾን እጁን እያውለበለበ፣ስማቸውን እየጠራና እያጨበጨበ ሸኝቷቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይህም አልነበረም ማንም ሰው የውጭው በር ላይ እንኳን እንዲቆም አልተፈቀደለትም፡፡ ሁሉም በሐዘን እንዳቀረቀረ ወደ የመንገዱ ተበታተነ፡፡
ምራቂ ወሬ
‹‹መዝገቡ በጊዜ ቀጠሮ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ባለፈው ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የሽብር ተግባርና የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ ስላደረገው ዛሬ መልሶ እሱን ማንሳት አይቻልም ፖሊስ ጥያቄውን እንደገና ማቅረብ ቢፈልግ እንኳን በይግባኝ እንጂ መልሶ በዚህ ችሎት የሚያቀርብበት ሥርዓት አይኖርም፡፡›› በማለት ችሎቱ ከመሰየሙ አስቀድሞ ሞያዊ አስተያየት ሰጥተው የነበሩት የሕግ ባለሞያ ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ሲሰሙ ‹‹የፍርድ ቤቶቹ አሠራር በግልጽ ከሕጉ ጋር እየተጣረሰ ስለኾነ ከዚህ በኋላ የሕግ ባለሞያዎች ትንታኔ ዋጋ የሚያጡበት ጊዜ በጣም እየቀረበም ነው፡፡››ብለዋል፡፡
tsiongir@gmail.com
የበፍቃዱ ኃይሉ እናት በልጆቻቸው ተደግፈው ከዋናው ግቢ ከተባረሩ በኋላ የፍርድ ቤቱ ግቢ ጀርባ ካለው ጤና ጣቢያ በር በኩል ሲወጡ፡፡
Zone 9
ችሎቱን ለመከታተል የመጡት ወጣቶች ከበፍቃዱ ኃይሉ ቤተሰቦች ጋራ እየተላቀሱ በጤና ጣቢያው በር በኩል ሲወጡ ፡፡
Zone9

No comments:

Post a Comment