የዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ‹‹አብዮታዊ ሁኔታ›› ላይ ለመድረሷ በብዙሃን ዜጐች ዕይታም ሆነ፤ ሂደቱን በተከታተሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ምሁራን ምልከታ የማይታበል ሐቅ ሊሆን መቃረቡ በዚህ ተጠየቅ ለማነሳው አጀንዳ ገፊ-ምክንያት ነው፡፡ በአናቱም ባለፈው ሳምንት ‹‹የ‹ቀለም› አብዮት ናፍቆት›› በሚለው መጣጥፍ ላይ ለማሳያነት የጠቀስኳቸው ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ነገረ-ንዋያዊ ችግሮች ተደማምረው፣ ሀገሪቷን በርቀት እንደታዘብናት ሶቪየት ሕብረት፣ አሊያም በቅርበት እንዳስተዋልናት ሶማሊያ በመጪዎቹ ጥቂት ጊዜያት የመፈራረሷን አይቀሬነት ማስረገጣቸውን ልብ እንላለን፡፡ ከዚህ ክፉ የታሪክ ዕጣ ለመታደግም ከሁለት አስርታት በላይ ያስቆጠረውን ይሄን አሮጌ ሥርዓት መቀየር ብቻውን ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ዛሬ ግልፅ እውነታ ሆኗል፤ ምክንያቱ ደግሞ ለዘመናት በገዥነት የተንሰራፋው የፖለቲካ ባሕልም አብሮ ካልታደሰ ነገሩ-ሁሉ ‹‹ታጥቦ ጭቃ…›› ከመሆን አለመዝለሉ ነው፡፡
እናም ወደዚህ ከፍታ ለመሻገር ሶስተኛው አብዮት ብቸኛ መፍትሔ የመሆኑ ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፤ ይህ ታላቅ ንቅናቄ ‹‹የሕዳሴ አብዮት›› በሚል ስያሜ ቢጠቃለል፣ ሂደቱ አንድም ኢህአዴግን ከክፉ ስራዎቹ ከመግታት ባለፈ፣ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ መልኩ የማደስና የተረጋጋ የፖለቲካ ማሕበረሰብ መፍጠርን የመሳሰሉ ተልዕኮዎችን በቀላሉ ወደ መሬት ለማውረድ ያስችላል፤ ሁለትም ከለውጡ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ከስያሜው አንድምታ አንፃር እየቃኙ በቀላል መንገድ ለመተንተን ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አምኜም በአዲስ መስመር የሕዳሴን ታሪካዊ ዳራ፣ አተገባበር እና ተያያዥ ጉዳዮችን እየጠቃቀስኩ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
‹‹ህዳሴ›› ሲባል…
በ5ኛው ክፍለ ዘመን ከጀርመን የተነሱ ጎዝ፣ ቫንዳልና ቡርጉንዲያኖችን ጨምሮ ሰባት ጎሳዎች፣ በወቅቱ ከፊል አውሮፓን ያስተዳድር የነበረውን ልዕለ-ኃያል የምዕራብ ሮማ ኢምፓየር አንኮታኩተው ግብዓተ-ፍፃሜውን ዕውን አደረጉት፡፡ ይህም የኃያሉ አገዛዝ ፍፃሜ ፕላኔታችን በአዲስ የፖለቲካ ባሕል እንድትዋጅ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ከፈተ፡፡ የዚህ መነሾም አሸናፊዎቹ ጀርመናውያን ጎሳዎች የአስተዳዳሪነት ችሎታም ሆነ ልምዱ ስላልነበራቸው የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የሮማ ቤተ-ክርስቲያን እና ፊውዳሎቹ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ በመቀራመታቸው ነበር፡፡ መላ ግዛቱም ሥልጣኔ-ጠል (Barbarism) እየተባለ የሚጠራውንና እስከ 15ኛው ክፍለ ጊዜ ድረስ በዘለቀው ‹‹የጨለማው ዘመን›› ውስጥ ያልፍ ዘንድ ተገደደ፡፡ ይህን ተከትሎ ትምህርትም ሆነ መንግስታዊው አስተዳደር በኃይማኖታዊ ቀኖና እንዲበየን ተፈረደበት፡፡ በወቅቱ አብያተ-ክርስቲያናት በብዛት ከመታነፃቸው ባለፈ አይን የሚሞላ መሰረታዊ ልማት ባለመዘርጋቱ፣ ከተሞች እጅጉን ቆርቁዘው የገጠሩን ገፅታ እስከመላበስ ደርሰው ነበር፡፡ ከሁሉም የከፋው ደግሞ መመራመር፣ መጠየቅና አለማዊ እውቀትን መፈለግ ከደመ-ቀዝቃዛዎቹ ‹‹መንፈሳዊያን›› አስተዳዳሪዎች ዘንድ ምድራዊ ፍዳን ለመቀበል መዳረጉ ነበር፡፡
በዚህ መልኩ ክፍለ-አህጉሩ ሰባትና ስምንት መቶ የመከራ ዓመታት ካሳለፈ በኋላ፣ የጣሊያኖቹ ፍሎረንስ፣ ቬነስ እና ሮማ ከተሞች ከዘመኑ በተለየ እውቀት ፈላጊና አንሰላሳይ ልጆቻቸው መናጥ ጀመሩ፡፡ ይህንን የመነቃቃት መንፈስ በሥራዎቹ በማካተት የዘመኑ ዝነኛ ባለቅኔ ዳንቴ አሊጋሪ በቀዳሚነት ይታወሳል፡፡ በ15ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ደግሞ መነቃቃቱ መላ ጣሊያንን በማዳረስ በምርምር ውጤት (በሳይንስ) መቃብር ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን ኃይማኖታዊ አስተዳደር ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ አፈራረሰው፡፡ ይህ አይነቱ የለውጥ መንፈስ ከጣሊያን ባሻገር ከአልፕስ ተራሮች ጀርባ ባሉ የአውሮፓ ሀገራት ድረስ በመዛመቱም ታሪክ ይቀየር ዘንድ ግድ ሆነ፡፡ ለሁነቱም ዋናው ተዋናይ ሕዝባቸውን ከተዋጠበት የጨለማ ዳዋ ለማላቀቅ ሲሉ የጥንታዊያኑ ግሪክ እና ሮማ የተዘነጉ የአሰላሳዮችን የአእምሮ ውጤት መመርመር ቀዳሚ ስራዎቻቸው ያደረጉት የጊዜው ጠቢባን እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ባህል፣ ስነ-ጽሁፍ፣ ሞራል እና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ እውቀቶችን መልሶ በመመርመር ጠቃሜታውን ለይቶ ማሰራጨትን የቀን ተቀን ሥራ ማድረጋቸው የማታ ማታ ለስኬት አብቅቷቸዋል፡፡ እነሆም የታሪክ ምሁራን ‹‹ሕዳሴ›› (Renaissance) ብለው የሚጠሩት ይህንን ሁነት ነው፡፡
በርግጥም ሕዳሴ የታሪክ ሀዲድን ተከትሎ የኋሊት በመመለስ የማንፃት (የመታደስ) ተግባር የሚያከናውን የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም ጥንታዊውን ዘመን ዛሬ ላይ እንዳለ ማንበር ሳይሆን፤ የቀደመውን ሥልጣኔ የወደቀበትን ህፀፅ መርምሮ ለዘመኑ የሚበጀውን አንጥሮ በማውጣት፣ ያረበበውን ማሕበራዊ ፍዝነት እና ኋላቀርነት አንገዋሎ በመጣል ላይ የሚያተኩር ፍልስፍና መሆኑ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምዕራባውያን ለደረሱበት የሥልጣኔ ከፍታ ዋናው መሰረት የተጣለው በሕዳሴው ዘመን ስለመሆኑ ራሳቸው ይመሰክራሉ፡፡ ኮፖርኒከስ፣ ጋሊሊዮ፣ ቦይል፣ ሀአርቬይ፣ አይዛክ ኒውተን፣ ሊዎናርዶ ዳ ቪንቺ፣ ሚካኤል አንጀሎን የመሳሰሉ ጉምቱ ጠቢባን የሥራ ውጤትም አብርሆት (ኢንላይትመንት) የሚባለውን ዘመን ወልዷል፤ ይህም ወደ ኢንዱስትሪ አብዮት አሸጋግሮ ለዛሬው ዘመናዊነት መደላድልን ስለማመቻቸቱ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡
በወቅቱ የሕዳሴው መንገድ ቀያሽ ተደርጎ የሚጠቀሰው ገዥ-ሃሳብ፣ የሰውን ልጅ በቀዳሚነት በሚያጠናውና ሰዋዊነት (Humanism) ተብሎ በሚጠራው ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ይህ አስተሳሰብ በሀገረ-እንግሊዝ በተስፋፋበት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው ፀሐፌ-ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒር፣ ኃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን፣ ስሜት-ተኮር እንቅስቃሴዎችንና ሥነ-ምግባር ላይ ብቻ ያውጠነጥን የነበረውን የድራማ ዘውግ፣ ወደ አለማዊ ይዘትነት በመቀየር ለሀገራዊ ፍቅር መነቃቃት እና የአርበኝነት መንፈስን በማስረፅ ረገድ ወደር የማይገኝለት ሚና ለመጫወቱ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ ግንባር ቀደም ምስክሮች ናቸው፡፡ በጥቅሉ የ‹‹ሕዳሴ›› (Renaissance) ፅንሰ-ሀሳብ የግሪክና የላቲን ብሉይ መድብሎች ላይ ቆሞ ፍልስፍናን እና መሰል የእውቀት ዘርፎችን መተርጎምን የያዘ የብርሃን ንቅናቄ በመሆኑ፤ የግለሰብን አለማዊ ከፍታ ለማስረገጥ፤ የሰውን ልጅ ምክንያታዊነት፣ የምርምር ክሂልና የኪነ-ውበት ፈጠራ ማሳደግን ዋነኛ ማዕከሉ ያደረገ ብርቱ የለውጥ መንፈስ ነው ተብሎ ቢደመደም ማጋነን አይሆንም፡፡
የኢትዮጵያ ህዳሴ
በሚሊኒየሙ አከባበር ዋዜማ ይህንን ቃል በጥራዝ ነጠቅነት የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ መጠቀሙን ተከትሎ፣ ከክቡራን ሚንስትሮች እስከ የቀበሌ ካድሬዎች የንግግር መክፈቻና መዝጊያ ሆኖ ዛሬም ድረስ በማጭበርበሪያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫንም «የሕዳሴ ግድብ›› ሲሉ ሰይመውታል፤ ምንም እንኳ የትኛውን ያለፈ ታሪካችንን እንደሚያድስ አፍታተው ባይነግሩንም፡፡ ሰሞኑን የተከበረውን የግንቦት ሃያ በዓል በማስመልከት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ በወሬ ደረጃ የሚያውቀውን ገድል እየተደነቃቀፈ የተረከልን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ቢሆን ‹‹የግንቦት ሃያ ድል ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንድትመለስ /እንድትታደስ/ የጠቀመ ነው›› ከሚል መታበይ አልፎ፣ የትኛውን የገናናነት ዘመናችንን ለመመለስ እንደተቻለ ለይቶ አላስቀመጠልንም፡፡ በርግጥ እርሱ እያወራ የነበረው የአክሱም ስልጣኔን በተመለከተ ከሆነ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ታላቁ ስላቅ ተብሎ በታሪክ ማህደር ሊመዘገብ ይገባል፤ በተለይም የአቶ መለስ ዜናዊን ‹‹የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው?!›› ሽርደዳን ስናስታውስ፡፡ በተቀረ ‹‹ሕዳሴ›› ብሎ ለመሰየም በቅድሚያ መታደስ የሚገባው ጥንታዊ ሥልጣኔ ስለመኖሩ ማመን እንደሚጠይቅ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፕሬዚዳንት ለነበረ ሰው ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፡፡
በአናቱም ጀግናው ኢህአዴግ ከምንሊክ በፊት የነበረችዋን ኢትዮጵያ እንደማያውቃት ሲለፍፍ እና የኢትዮጵያ ታሪክን በ100 ዓመት ገድቦ፣ የቀደመው የሥልጣኔ አሻራ የአንድ ወይም የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ማሕበረሰብ ግንጥል ውበት እንደሆነ ለሃያ ሶስት አመት ሙሉ ሲሰብክ ኖሮ፣ ዛሬ ‹የጥንቱን ገናናነት እንመልሳለን› ማለቱ፤ ራሱ ካነበረው የሥርዓት አወቃቀር ጋር ፊት ለፊት እንደሚያላትመው የዘነጋው ይመስለኛል፡፡ ይህም ሆኖ ‹‹ስለሕዳሴ የማወራው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ አይደለም!›› ካለን ደግሞ፣ የኢትዮጵያን የ3ሺህ ዘመን ቀደምት ታሪክ በይፋ አምኖ መቀበሉን ያወጀ ያህል አድርገን ልንወስደው እንችላለን፤ ግና፣ ይህ አይነቱ አቋም ድንገት በሞቅታ የሚለወጥ ሳይሆን፣ ብዙ ማብራሪያዎችን እና ደም ያፋሰሱ ጠማማ ታሪኮችን የማቃናት ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ በተረፈ የሕዳሴው ልፈፋ በታሪክ ብያኔው ያኮረፉትንና ‹ቅድሚያ ኢትዮጵያዊነት› የሚሉትን ስብስብ በሀሳዊ የፕሮፓጋንዳ ማግኔት ወደፓርቲው ለመጎተት የሚጠቀምበት ተራ የማጭበርበሪያ ስልት ከመሆን የሚዘል አይመስለኝም፡፡
የሆነው ሆኖ በዚህ አውድ መከረኛይቷን ኢትዮጵያ ከአደገኛው ማዕበል የሚታደጋት ቀጣዩ ሕዝባዊ ንቅናቄ ‹‹የሕዳሴ አብዮት›› በሚል ማዕቀፍ ስር ይወድቅ ዘንድ ገፊ-ምክንያቱ፣ የሥርዓት ለውጥ ብቻውን ለሀገሪቱ ትንሳኤ በቂ አለመሆኑን አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ስለምን? ቢሉ፣ በተለይም ከ1983ቱ የመንግስት ቅያሬ በኋላ የተከሰቱ አስጨናቂ ችግሮች መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ዳግም የመታደስ (እንደገና የመወለድ) አስፈላጊነትን አማራጭ አልባ ምርጫ በማድረጋቸው ነው፡፡ በተለይም የብሔር ፖለቲካው የወለደው የጎሳ ክፍፍል፣ ከባህላዊ እሴቶች ማፈንገጥ፣ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል፣ የኃይማኖት መቻቻል ወደ ታሪክነት መቀየር፣ የህሊና ታማኝነት መደብዘዝ እና ከሰው ልጅ ይልቅ ቁስ መከበሩ… ከሞላ ጎደል አብዮቱን በታሪክ ማንፃት መካከል የማለፍ ተልዕኮ እንዲያነግብ ገፍቶታል፡፡ በተጨማሪም የቀድሞ የታላቅነት መገለጫችን የሆነው የአክሱም ሥልጣኔ ክቡድ መንፈስ ለዚህ ዘመን መዋጀት የሚበቃ ሽራፊ ምስጢረ-ጥበብን ሸሽጎ ስለመያዙ ከቶም ቢሆን ቅንጣት ታህል የማንጠራጠር መሆናችን ሕዳሴን አጀንዳ እንድናደርገው ያስገድደናል፡፡
ከላይ እንዳየነው የአውሮፓን ሥልጣኔ በፅኑ መሰረት ላይ ያስረገጡት አሰላሳዮቻቸው እንደሆኑ ሁሉ፤ በእኛም አውድ ሀሳቦቻቸውን ወደ አደባባዩ ተዋስኦ አብዝተን ልናካትትላቸውና የሕዳሴያችን ምሁራን ሊሆኑ ይገባል ብዬ የማምንባቸው ሶስት መምህራን አሉ፡፡ መስፍን ወልደማርያም፣ መሳይ ከበደና ተከስተ ነጋሽ፡፡ አዛውንቱ ጠቢብ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በተለይም ‹‹መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው፣ የኋላው መዘንጋቱ የችግሮቻችን ምንጭ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡ በገፅ 12 ላይም እንዲህ በማለት በቁጭት ይጠይቃሉ፡-
‹‹ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ሰረገላ ነበር፣ የመስኖ እርሻ ነበር፣ የግንብ ቤት ነበር፣ ሕዝብ የሚገበያየው በገንዘብ ነበር፤ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት ጋሪ ነበር፣ ድልድይና የግንብ ቤቶች ተሰርተው ነበር፤ የዚህ ሁሉ የሥራ ጥበብ ለምን ከሸፈ? የአክሱም ሀውልቶችን የመስራት ጥበብ ለምን ከሽፎ ቀረ? የላሊበላን ከድንጋይ የተፈለፈሉ አብያተ ክርስቲያናት የመስራት ጥበብ ለምን ከሸፈ? የጎንደርን ቤተ-መንግስቶች የመስራት ጥበብ ምን አክሽፎ አስቀረው? እነዚህ ሁሉ የድንጋይ ስራ ጥበቦች በሚታዩበት አገር በደሳሳ ጎጆ ውስጥ መኖር ከትውልድ ወደትውልድ የሚተላለፍ ባሕል መሆኑ በምን ምክንያት ነው?››
ቀድሞ ግራ-ዘመም የነበሩት የፍልስፍና መምህር ፕ/ር መሳይ ከበደ ደግሞ ሌላኛው የሕዳሴው ምሁር ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፤ በተለይም ከ40ዎቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር በተባረሩ ማግስት ባሳተሟቸው መጻሓፍት፣ የቀደሙ ሀገር-በቀል የኢትዮጵያ ሊቃውንትን ሙግቶች በማብራራት ይታወቃሉ፡፡ ‹ወደ ምንጫችን የመመለስን› ጥሪ የሚያስተጋቡት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ማጥ ለመውጣትም ሆነ ወደፊት እንድትገፋ፣ ለረዥም ዘመን ካስተናገደቻቸው ዕሴቶች መካከል ረብ ያላቸውን መመለስ እንደሚገባት አብዝተው ተከራክረዋል፡፡
አስመራ የተወለዱት የታሪክ አጥኚው ፕ/ር ተከስተ ነጋሽም ሌላው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የትምህርት ስርዓቱ ላይ ባደረጉት አበርክቶ በዚህ አውድ የማነሳቸው እኚህ ምሁር፣ እንደ ፕ/ር መሳይ ሁሉ፣ ዘመናዊው የትምህርት ስርዓት አውሮፓ ተኮር እና ኢትዮጵያ-ጠል በመሆኑ ወደፊት መራመድ እንዳላስቻለን ደጋግመው ከመናገር ባለፈ፤ ቋንቋ የሚሸከመውን ሀገራዊ ማንነት ከመረዳት አኳያ አማርኛን እና ኦሮምኛን የስርዓተ-ትምህርቱ ቋንቋዎች ማድረግ ብቸኛው ከውድቀታችን መውጫ መንገድ መሆኑን ያምናሉ፡፡ …በጥቅሉ እነዚህ አንጋፋ ጠቢባን (ያልጠቀስኳቸው ሌሎችም እንደሚኖሩ ሳልዘነጋ) አውሮፓውያን ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት ከጨለማ የወጡበትን ብልሃት መመርመርን ይበልጥ አጠንክረው በመከተል፣ ሀገር የመታደግ ተልዕኮዎቻቸውን ከዳር ያደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይሁናቸውና!
መጪው የሕዳሴ አብዮት በዋናነት የሚያተኩርበት ሌላው ጉዳይ፣ ከአራት አስርታት በፊት በያ ትውልድ ፈታኝ የትግል ጉዞ ላይ ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸውን እንስቶች የተኳቸው የዛሬዎቹ የፆታ አቻዎቻቸው ለምን ከእንቅልፍ በከበደ አርምሞ ውስጥ ሰጠሙ? የሚለው ነው፡፡ ከአውሮፕላን ጠላፊዋ ማርታ መብራቱና ታደለች ኪዳነማርያም እስከ የመኢሶኗ ወሳኝ መሪ ንግስት አዳነ፤ እንዲሁም ከእልፎቹ የኢህአፓ ትንታግ ጓዲቶች እስከ ወያኔዎቹ አረጋሽ አዳነ እና ቀሺ ገብሩ ያሉ ተዘርዝረው የማያልቁ የዚያ ዘመን የአናብስት እንስቶች እንቅስቃሴ እንደዋዛ አክትሞ፣ በብርቱካን ሚደቅሳ፣ ርዕዮት አለሙና ፈቲያ መሀመድን በመሰሉ ጥቂት ጀግኖች ተገድቦ መታየቱ፣ በቀድሞው ታሪክ መታደስን አማራጭ የለሽ ያደርገዋል፡፡ በርግጥ የእንስቶቻችንን ፊኒክስነት ለመመለስ ከጥንቱ ይልቅ የትላንቱ የእናቶቻችን ጊዜ በተምሳሌነቱ ተስተካካይ የለውም፡፡ እነርሱ በያ ትውልድ ተጋድሎ የጊዜውን ጎታች የፆታ አመለካከት በመጋፋትና የወንዶችን ትምክህታዊ ዓለም በመነቅነቅ ታሪክ ለመስራት የታደሉ ፈርጦች እንደሆኑ አስመስክረዋል፡፡
የእኔ ዘመን አብዮተኛ ሴቶችም፣ በኮታ ሳይሆን በእውነተኛው እኩልነት እንዲገለጡ ግዴታቸውን ከወዲሁ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ከወቅታዊው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር እኩሌታውን የሚይዙት እንስቶቻችን በነቂስ ያልተሳተፉበት አብዮት በየትኛውም መስፈርት ውጤታማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በግልባጩ እነርሱን በዕኩልነት ማካተቱ ካልተሳካ ለውጡ ሊዘገይም ሆነ ክፉ ጠባሳ ሊኖረው ስለሚችል፣ ‹‹ያለሴቶች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ሕዳሴ እውን አይሆንም!›› ከሚለው ዘመነኛ ኢህአዴጋዊ ቧልት እና ፕሮፓጋንዳ በተለየ መልኩ ተግባራዊ የሚሆን የንቃት ሕዳሴ ትኩረት ሊሰጠው ይገባዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ በ66ቱ እና በ83ቱ የአብዮት ሀዲድ ላይ የመጣችበትን የማሕበረ-ፖለቲካ ታሪኳን ግድፈቶችና ስኬቶች በምክንያታዊነት መመርመር ለሁለንተናዊ ዳግም ልደት (ሕዳሴ) እንድንዘጋጅ መደላድል የመፍጠሩ እውነታ ነው፡፡ ይህ የዳግም ልደት አብዮታዊ ጉዞ ደግሞ በዋነኝነት የሁለት ማሕበረሰቦችን ቅሬታ የሚያቅፍ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይኽን የምለው የሌሎቹን ዋጋ በመዘንጋት ሳይሆን፣ በቀዳሚነቱ ስለማምን ነው፡፡
የብሔር ጥያቄ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት ለመናድ ቅርብ የነበረባቸው ዘመኖችን ተመልክተናል፡፡ በዚህ መንገድ አልፈንም በዋናነት በአግባቡ መመለስ ካቃቱን ጥያቄዎች መካከል በኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚነሳው ዋነኛው መሆኑ አያከራክርም፡፡ ይህ ጥያቄ ጠርዘኛ ልሂቃኑ በሚያቀርቡት ልክ ባይሆንም፤ መሬት የረገጡ ማንነታዊ ቅሬታዎችን ተንተርሶ መነሳቱ ግን መካድ የለበትም፡፡ እናም ኢትዮጵያችንን በማደስ ጉዞ፤ ኦሮሞነት ከሀገሪቱ ምንነት ብያኔ የተነጠለ ሆኖ የመጣበትን የታሪክ አጋጣሚ ሂደት በመግታት፣ የብሔሩን መለዮዎች የኢትዮጵያዊነት ብያኔ ገዢ መተርጎሚያና መዳረሻ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሌላኛው ጭብጥ ደግሞ የኢትዮጵያን እስልምና ነባራዊነት ማፅናት ነው፡፡ ኃይማኖቱም ሆነ ተከታዮቹ በአፄያዊዎቹ አፈና ውስጥ ለሺ ዓመታት የመቆየታቸውን እውነታ ተቀብለን፤ በኢትዮጵያዊነት ትእምርታዊ ገፆች ውስጥ ቀዳሚ አዋጭነታቸውን መቀበል የመታደሳችን ግብ ሊሆን ይገባል፡፡
ለነዚህና ለሌሎች መዘርዘር ለማይቻሉን የሀገሪቷ መከራዎች፣ መውጫው ኢትዮጵያን በማደስ የሚደመደም አብዮት ከሆነ ዘንዳ፣ የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ከዋነኛ የሽግግር ሂደቶች መካከል ከፊት የሚቆም እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በእርግጥ ርዕሰ-ጉዳዩ በተነሳ ቁጥር፣ ‹ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው?› እያለ የሚቀልድ ኢህአዴግ መራሹን መንግስት የመሰለ ቢኖርም፤ እየመጣ ካለው መዓት ሀገሪቷን ለማዳን፣ ብሔራዊ እርቅ ምቹ ድልድያችን መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በበላይነት የሚዘውሩት ልሂቃንን በአንድ የጋራ መድረክ ላይ ማሰባሰብ፣ በቀጣይ እንድትኖረን በምንሻት ሀገር ምንነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚያርፉ ተመጋጋቢ አመለካከቶችን ለመቅረፅ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
የሆነው ሆኖ ይህን ተምኔት የመሰለ፣ ነገር ግን ሊከወን የሚችል የሕዳሴ አብዮት ያለእንቅፋት ለማሳለጥ፣ በቅድሚያ ገዥዎቻችን ‹በአንድ ክፉ አጋጣሚ ስልጣኑን ብናጣ ያበቃልናል› ከሚለው ነቢባዊም ሆነ ተጨባጭ ስጋት እንዲላቀቁ ዋስትና መስጠት ላይ መግባባት የግድ ይላል፡፡ በመገዳደል ከተበከለው የግራ-ቀኝ ፖለቲካ ለመንፃት፤ ከነነውረኝነታቸው ሀገሪቷ የእነርሱም እንደሆነች አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡ በመጪዋ ኢትዮጵያ አንዱ ልዩ ቀናዒ፣ ሌላኛው ደግሞ ተጠርጣሪ እንደማይሆንባት መተማመን፣ ለሕዳሴው የሚኖረንን ተስፋ ያጎለብታል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
(የሕዳሴው አብዮትን ማስፈፀሚያ ሃሳብን በተመለከተ ሳምንት እመለስበታለሁ)
Source Ethiomedia

No comments:
Post a Comment