ከዚህ አንፃር በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሚና ምን ሊሆን ይገባል?
በግንቦት 7 እምነት በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በድጋፍ ሰጭነት ሳይወሰኑ የትግሉ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች መሆን ይኖርባቸዋል። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በወያኔ ጥቅሞችና ተቋማት ላይ በማመጽ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አርዓያ መሆን ይኖርባቸዋል።
በዚህ ረገድ የተጀመሩ አበረታች ጥረቶች አሉ፤ ለምሳሌ:
- ወያኔ ሙስሊሞችን ከክርስቲያኖች ለማጣላት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን “እንቢ አንጣላልህም” ያሉት መሆኑ የሚያኮራ ነው። ወያኔ ከጠበቀው በተቃራኒ የሁለቱም ሃይማኖቶች መሪዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ ሲመክሩ መታየቱ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው። አብሮነታችንን ማጎልበትና ይህንን በአደባባይ፣ በአዳራሾች፣ በቴሌቪዥን መስኮቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳየት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ውጭ የተጀመረው አገር ቤት መዳረሱ የማይቀር ነው። ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርብናል።
- ወያኔ በአባይ ግድብ ስም በውጭ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በርከት ያለ ገንዘብ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን “ከአባይ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይገደብ” “ከአባይ በፊት ሙስና ይገደብ” እያሉ ወዋጮዎቹን እንቢ ብለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን የታየው ጽናት በጣም አበረታች ነው። የወያኔ ሹማምንት በአባይ ጉዳይ እንኳንስ ገንዘብ ስብሰባም ሊሰበሰቡ አልቻሉም። ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
- ኢትዮጵያዊያን በስፖርትና በኪነጥበባት መስኮች የሚያደርጓቸው መሰባሰቦች ለትግሉ ትልቅ እገዛ ይሰጣሉ። የኢትዮጵያ ስፓርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA) ከወያኔና ከወያኔ ሸሪክ ቱጃር ጋር ያደረገው ትንንቅ የሚያኮራ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን አገር፣ ነፃነት፣ ክብር ይበልጥብኛል ብለው የቀረቡላቸውን አጓጊ ማባበያዎችን “እንቢ” ብለዋል። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
- ባለፈው ዓመት ጋዜጠኛ አበበ ገላው በመለስ ዜናዊ ላይ፤ ዘንድሮ ደግሞ ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድና አቶ መስፍን የዘረኛው ወያኔ ግንባር ቀደም አስተባባሪ በሆነው ስብሀት ነጋ ላይ ያሰሙት ተቃውሞ በጣም የሚደገፍና በውጭ አገራት የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ባህል ሊሆን ይገባዋል።
- በስዊድን የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች የጀመሩት እና በኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ተሳትፎ እየተካሄደ ያለው የወያኔ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ የማቅረብ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
- በአገራችን ውስጥ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ ከፈለግን ወያኔን ማስደንገጥ፣ ማሸበር፣ ካስፈለገም ማስወገድ የሚችል የአመጽ ኃይል መኖሩ ወሳኝ ነው። እንዲህ ዓይነት የወገን ኃይል ከጀርባው መኖሩ ሲሰማው ነው ሕዝብ ለእንቢተኝነት የሚነሳሳው። በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ኃይል ቢቻል መቀላቀል፤ ካልተቻለም በአባላት ምልመላ፣ በፋይናንስ፣ በሎጂስቲክስና ዲፕሎማሲ መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ከሁሉ የላቀ የእምቢተኝነት መገለጫ ነው።
- ትግሉ እየመረረ መሆኑ በመረዳት በርቀት ሆነን ከመብሰክሰክ በትግል ላይ ያሉትን ድርጅቶች መቀላቀል ሌላው አሁኑኑ ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው። ድርጅቶች “አይረቡም” ብለን ስላጣጣልናቸው አይጠናከሩም። ድርጅቶችን ማጠናከርና ማዘመን ያለብን እኛው ነው። መሪዎችን ማውጣት ያለብን እኛው ነው። እስካሁን ድርጅቶችን ያልተቀላቀልን ካለን መቀላቀልና ትግሉን ማጧጧፍ ይኖርብናል።
- በየተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወያኔን “እንቢ” እንበል። “እንቢ” የማለትን አጋጣሚ ማሳለፍ የለብን። “እንቢ” ማለት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ብዙዎች ናቸው። ለምሳሌ: -
ሀ) ወያኔ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን አዲስ የገንዘብ ማለቢያ ለማድረግ አቅዶ ተነስቷል። ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶችን በ2 ዓመት ጨርሼ አስረክባለሁ በሚል ማባበያ በውጭ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ለመሰብሰብ ዝግጅቱን አጠናቋል። ይኸንን ነገር አጠንክረን “እንቢ” ማለት ይኖርብናል። “ለኛ ቤት ከመሰጠቱ በፊት፤ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን መወደቂያ ያግኙ” ማለት ካልቻልን በራሳችን ማፈር አለብን። የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታትን አምባገነኖችን በገንዘብ አትደግፉ እያልን እኛ ራሳችን ወያኔን በገንዘብ የምንደግፈው ከሆነማ ከነሱ ብሰን መገኘታችንን እንወቀው።
ለ) ወያኔ በስደተኛ ስም በመካከላችን የሰገሰጋቸውን ካድሬዎችን የማጋለጥ ዘመቻ ማፋፋም አለብን። የወያኔ ደጋፊዎችን በኤርትራ ስደተኞች ስም እንደሚገቡ መረጃዎች አሉ። በደል ደርሶብናል ብለው መንግሥታትን አሳምነው የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ አጠቃን ካሉት አገዛዝ ጋር የሚሠሩ መሆናቸው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን አጠናቅረን ለየሀገሩ መንግሥታ ማቅረብ እንደ አቢይ ሥራ መያዝ ይኖርብናል።
ሐ) የወያኔ ባለሥልጣናት የሚገዟቸውን ቤቶች፤ የሚያስተዷድሯቸውን ቢዝነሶች እያደንን ማጋለጥ ይኖርብናል።
መ) የወያኔዎች ሹማምንት በአሜሪካና አውሮፓ በነፃነት ሊዘዋወሩ አይገባም። በሄዱት ሁሉ ተቃውሞና ውርደት ሊከተላቸው ይገባል።
ሠ) የወያኔ ቢዝነሶች ላይ ማዕቀብ ማድረግን (ቦይ ኮት) መልመድ አለብን። ጥረቶቻችንን በፈጠራ ከደገፍን ወደ አገር ቤት የምንልከው ገንዘብ የወያኔ የውጭ ምንዛሬ ረሀብ ማስታገሻ የማይሆንበት መንገድ መሻት አለብን።
ረ) ለወያኔ ባለሥልጣኖች ዲግሪ የሚያድሉ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆችን ማዋረድ መጀመር አለብን። ስምንተኛ ክፍል እንኳን በወጉ ላልጨረሱ ሰዎች የማስትሬት ዲግሪ እንደሰጡ ማሳወቅ የኛ ኃላፊነት መሆን አለበት።
በግንቦት 7 እምነት ትግሉ በሁሉም ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያዊያን በያለሉበት ቦታ በተደራጀና በተቀናጀ መልክ ወያኔን ፊት ለፊት ከተጋፈጥን የድላችን ቀን እናቀርባለን።ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
No comments:
Post a Comment