Tuesday, November 11, 2014

ፓርቲዎች ለሃይማኖት ተቋማት ጥሪ አቀረቡ


ጥቅምት (ሠላሳቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ››በሚል መርህ ትብብር  የመሰረቱት 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀደም ብለው ባሳወቁት የአንድ ወር መርሃ ግብር መሰረት የጀመሪያውን ጥሪ ለሃይማኖት ተቋማት አድርገዋል።
ፓርቲዎቹ አገራችንና ህዝቧ በተፈጥሮ ሚዛን መዛባት በሚከሰትበትም ጊዜ ሆነ በአገዛዝ ሥርዓቶች ምክንያት በችግር ውስጥ በሚወድቁበት ጊዜ የኃይማኖት  ተቋማትና ምዕመናን ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተው፣ ዛሬ ላይ እነዚህ የሞራልና ሥነ-ምግባር እሴቶች እየተናዱ በመሄዳቸው ዜጎች ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ
ምስቅልቅል ተጋልጠዋል፣ የአገር ፍቅር ስሜት በጥያቄ ውስጥ ወድቋል ብለዋል። በመቻቻል ፋንታ ግጭትና መፈናቀል በአራቱም አቅጣጫ ህዝብን ለሥቃይና ለሥጋት ዳርጓል የሚሉት ፓርቲዎቹ፣  የህግ ‹‹አምላክ›› ክብር እያጣ ፍትህ እየተዛባ ፣ ወህኒ ቤቶች በታሳሪዎች እየተጨነቁ፣ የምግብ ተረጂውና የጎዳና ላይ
ተዳዳሪው ዜጋ ቁጥር እየተበራከተ በአጠቃላይ የህዝባችን ኑሮና ህይወት፣ የአገራችን ሠላምና መረጋጋት ፈታኝና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑም ገልጸዋል።
” ተቃዋሚዎች እና ገዢው ፓርቲ በአገራችን ጉዳይ ላይ ጨፍ እና ጫፍ መቆማቸውን  በመግለጫቸው የገለጹት ፓርቲዎች፣ በተለያየ ምክንያት በሁለት ጠርዝ ላይ የቆሙ ኃይሎች ወደ ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲመጡ፣ በህዝብ ውስጥ የሚታየው የሞራልና ሥነምግባር ጉድለት እንዲቃናና የመቻቻልና መተሳሰብ
ስሜት እንዲያንሰራራ   የዜጎች ሥቃይና ሥጋት ተወግዶ በተስፋ እንዲሞላ ፣ በአገራችን መረጋጋትና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ዜጐች ይጠልዩ ዘንድ ጠይቀዋል አንዲሁም ቀጣይና ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን፣ አብሮነታችንና አንድነታችን እንዲጠናከር፣ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲለመልምና ለሉዓላዊነታችን ያለን ቀናዒነት
እንዲጠናከር በሰንበትና የጁምኣ ቀናት በጋራ እንዲሁም በየግል የዘወትር ጸሎት ፈጣሪ አምላክን በመለመን ለተያያዝነው አገራዊ ዓላማና የጋራ ጥረት ድጋፋችሁን እንድታደርጉ ” እንጠይቃለን ብለዋል።
9ኙ ፓርቲዎች ለአንድ ወር በሚካሄደው የትግል መርሃ ግብር፣ የቤት ውስጥ ስብሰባዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ለአንድ ሙሉ ቀንና ሌሊት የሚቆይ የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጅተዋል።

No comments:

Post a Comment