Friday, July 25, 2014

የአምባሳደር ገነት ዘውዴ የልቅሶ ታሪክ ጅማሬ በእግዜሩ አማካኝነት ነበር

ኤርምያስ ለገሰ “የመለስ ትሩፋቶች” በተባለው መፅሃፉ አዲስ አበባን በስውር ሲቆጣጠሩ ከነበሩት ቁልፍ የህወሓት ካድሬዎች አንዱ ስለሆነው ገብረእግዚአብሔር (በቅፅል ስሙ “እግዜሩ”) ከፃፈው ውስጥ የሚከተለውን ቀንጭቤ ላካፍላችሁ ወደድኩ ።
.<<እግዜሩ ትላልቅ የሚባሉ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ሳይቀር ደም እንባ አስለቅሷል። የአምባሳደር ገነት ዘውዴ የልቅሶ ታሪክ ጅማሬ በእግዜሩ አማካኝነት ነበር።
እንዲህ ነበር የሆነው።

በምርጫ 92 በወረዳ 21/22 ኢህአዴግን ወክላ ለፓርላማ እጩ ሆና የቀረበችው የትምህርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ነበረች። እግዜሩ ደግሞ ምርጫውን በበላይነት ከመምራት በተጨማሪ በዚሁ ወረዳ ለከተማ ምክር ቤት እጩ ሆኗል። ምርጫው ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት የሁሉም ወረዳ እጩዎችን የስራ ስምሪት ለመስጠት ሜክሲኮ ዞን ጽ/ቤት ጠርተናቸው ነበር። ወይዘሮ ገነት ሀገር ሰላም ብላ በስብሰባው ታድማለች። ጠንከር ያሉ የግምገማ ነጥቦች ሲነሱ እሷም ፀሀዩ መንግስታችንን እንዲጠላ ያደረጉት የበታች ካድሬዎች ናቸው የሚል ወቀሳ አዘል አስተያየት ትሰጣለች። በንግግሯ የተበሳጨው እግዜሩ፣
“… ገነት እኔ ህይወቴን ሙሉ ከህዝብ ጋር እየተገናኘው የድርጅትና ፕሮፐጋንዳ ስራ ሰርቻለው። የህዝብ ሀሳባ አዳምጫለሁ። እውነቱን ንገረኝ ካልሽ እንዳንቺ ህዝብ የሚጠላው ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም!፣ ከሁሉም የሚያሳዝነው ስትወድቂ እኛንም ይዘሽ መገንደስሽ ነው!” አላት።
ክብርት ሚኒስትሯ ተንሰቅስቃ አለቀሰች።ልቅሶው ሲበርድላት፣
“እኔ የኢህአዴግን የትምህርት ፓሊሲ በቁርጠኝነት ከማስፈፀም ውጭ ምን ያደረኩት ነገር አለ? ፓሊሲው ትውልድ ገዳይ እንደሆነ እየገለፀ ያለው ህዝቡና ምሁራኖች ናቸው። እኔ ፓሊሲ የመቀየር ስልጣን የለኝም! … ስለዚህ ህዝቡ የጠላኝ በፓሊሲው ምክንያት ነው። ርግጥ ከኢህአዴግ በተቃራኒ የቆመው ዶክተር በየነ ጴጥሮስ “ዮዲት ጉዲት!” የሚል ስያሜ ሰጥቶኝ በህዝቡ ጥላቻ ላይ ቤንዝን ጨምሯል።” የሚል አስገራሚም አነጋጋሪም ምላሽ ሰጠች።
ክብርት ሚኒስትሯ በፓሊሲው ትውልድ ገዳይነት ላይ ጥርጥር የላትም። ባለስልጣናት ልጆቻቸውን ከተቻለ እንደ ሽማግሌው ስብሀትና አርከበ እቁባይ ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ ውጭ ሀገር ፣ካልተቻለ ደግሞ የሀገሪቷን የትምህርት ስርአት በማይከተሉ የሀገር ውስጥ ምርጥና ውድ ትምህርት ቤቶች እንደምናስተምር ታውቃለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አስረኛ ክፍል ማለቁ ህብረተሰባዊ ውግዘት እየደረሰበት እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ነው። ዪንቨርሰቲ ከሚማሩ ተማሪዎች ስማቸውን በአግባቡ መፃፍ የማይችሉ መኖራቸው ሀቅ ነው። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቃትና አለም አቀፍ ተቀባይነት ቁልቁል ወደ ታች አየተምዘገዘገ እንደሆነ የእለት ሪፓርቷ ሆኗል።>> 

No comments:

Post a Comment