ወንድሙ መኰንን – ከብሪታኒያ ሚያዝያ ፴ ቀን ፪ሺ፭ ዓ. ም (7 June 2014)
ወያኔ አሁን ደኅና ልማታዊ መነኵሴ አገኘች! ጎሽ! የለንደኑ ኤምባሲዋ፣ አዲሱን ወዶ-ገባ ለግንቦት ፳ አሰልጥና አስመረቀች! በድንኳን ባደረገቸው ድግስ ላይ በግልጽ ለዕይታ አበቃች። ማብቃቷንም በራሷ የሚዲያ መረብና (http://www.ethioembassy.org.uk/news_archive/Ginbot-20_celebrated_in_London.pdf) እና በዓይጋ ድረ-ገጿ በተነች። “አባ” ግርማ፣ የለንደኗን ርዕሰ አድባራት ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሕንጻና ንብረቷን፣ እጅ መንሻ አድርገው በማቅረባቸው፣ አሁን የወያኔ ባለውለታ አሽከርነታቸውን አረጋገጠዋል። እንዲያ ነው እንጂ! ማጥ ውስጥ ከወደቁ አይቀሩ በቅጡ መንከባለል ይሻላል። ለወያኔ አድረዋል ስንል፣ “ስም አጥፊዎች” ተባልን። አሁን ደጋፊዎቻቸው ምን ይበሉ? በየሳምንቱ፣ የጥበቃ ዘበኞችን ቀጥራ ስታስጠብቃቸው የነበረችው በከንቱ አልነበረም። በነዚህ ፈርንጆችና ሶማሌ እንግዶች መሀል የሚታዩት ሁሉቱ ከሀዲ ግርማዎች ናቸው – ግርማ ከበደና፣ ግርማ ቡፋ ይባላሉ! ተዋወቋቸው!
እዚያም ሂደሽ በላሽ! እዚህም መጥተሽ በላሽ!
ሰው ታዘበሽ እንጂ ሆድሽን አልሞላሽ!
ሰው ታዘበሽ እንጂ ሆድሽን አልሞላሽ!
የሆድ አደሮች ሕሊና ግርም ነው የሚለኝ። ምንም ባወጣው-ባወርደው፣ ልደርስበት አልቻልኩም። ሕሊናቸው የሚመራው፣ በአዕምሮአቸው ሳይሆን በሆዳቸው መሆን አለበት ልበል? እኚህ ሰው፣ ከዚህ በፊት፣ ጸረ-ወያኔ ነኝ ብለው በመቅረባቸው፣ ወያኔ ገዳሞቻችንና ቤቴክርስቲያኖቻችን ላይ የምታደርገውን ግፍና በደል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመቃወማቸው፣ የሕዝቡን አመኔታና ከበሬታ አገኙ። በሔዱበት ሁሉ የክብር ቦታ ተሰጣቸው። ሬስቶራንት ከሔዱ፣ አንዲት ሳንቲም ሳይክፍሉ የሚመገቡ ተወዳጅ “አባት” ተበለው ነበር። እስቲ እግዚአብሔር ያሳያችሁ፣ እንደዚያ የወደዳቸውንና ያከበራቸውን ሕዝብ፣ ለጠላቱ አሳልፈው ለኩርማን እንጀራ ሲሸጡት ምን ይባላል? ሕሊና ቢኖራቸው፣ እንዲህ በየወያኔ ድግሱ እየዞሩ መብላት ቀርቶ በሰላም ተኝተውም የሚያድሩ አይመስሉኝም ነበር። “እሳቸው እልኸኛ ናቸው እንጂ፣ ከወያኔ ጋር አይሰለፉም” ከሚሉት ምዕምናን መሀል አንዱ ነበርኩ! ወይኔ ሰውዬው! አሁንም ተሸወድኩ። ሰውን በሰውነቱ ስለማምን ነው በየጊዜው ጉድ የምሆነው! ሰው ግፍ ሠርቶ በሰላም ይተኛል? ምን ዓይነቶቹ ጉዶች ናቸው፣ ሆድ-አደሮች? እስካሁን ያየኋቸው ሆዳ-አደሮች፣ ክርስቶስን ከሸጠው ይሁዳ ጀምሮ፣ ሰሎሞን ተካልኝንም በሉ፣ “አባ መላ” የሚባለውን ገበየሁ ባልቻ፣ አሁን ደግሞ የለንደኑ ግርማ ከበደ (ዕውነተኛ ስማቸው “ግሩም”) 1800 ዙረው የክሕደት አክሮባት ሲሠሩ፣ አለማፈራቸው፣ ሊዋጥልኝ ያልቻለ ጉድ ነው። ምናልባት የቁጥር እንጂ የሥነ-አዕምሮ ባለሙያ ባለመሆኔ አልገብቶኝ እንደሆን! እራሴን በነሱ ቦታ አስቀምጬ ስገመግመው ሁሌ ይሰቀጥጠኛል! ስለነሱ አፈርኩ!
የታወቁት የፖሊቲካ ግልሙትና (ይቅርታ ለእንግሊዚኛው “political prostitution” ለሚለው ቃል በ”ሸ” የሚጀምር አማርኛ ቃል ቢኖርም፣ መጠቀም ስለከበደኝ ነው) ተዋኒ ፍጡሮች፣ አስገራሚ አክሮባት/መገለባጥ ግብራቸው ነው። መቼም በተለምዶ “ትያትር”/ድራማ የሚባለውን ተውኔት ሲተውኑ ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ሁነው ነው ቁጭ የሚሉት። “ወይ-ያኔ! ወይ-ያኔ! አንተን አንተን አያርገኝ የዚያን ቀን መጥኔ” ሲለን ስንቶቻችን ነን ከመቀመጫችን ተንስተን “ሰሎሞን! ሰሎሞን!” ብለን ላንቃችን እስኪነቃ የጮኽነው? አሁን ያን ሰሞን፣ አባ መላ የተባለው ጉድ “ወያኔን ክጄ ከተቃዋሚው ጎራ ተቀላቅዬአለሁ” ሲለን ስንቶቻችን ነን የክብር ቦታ የሰጠነው? አዪዪዪዪዪ! ተመልሶ ገባ!
እስቲ ግሩም ጸረ-ወያኔ ሁነው የከየኗትን ተውኔት ላስታውሳችሁ! የዘመኑ ቪዲዮና ሞኝ የያዘውን አይለቅም አይደል!
“ገዳማትን መንካት ማለት ኢትዮጵያን መንካት ነው! ወያኔ ገዳሞቻችንን አትንካ” ብለው ላንቃቸው እስኪነቃ እንዳልጮኹ ተገልብጠው የወያኔን 23ተኛ የጨለማን ዘመን አክባሪ ሁነው ተገኙ! እንኳን ለዚህ አበቃዎት “አባ” ተባዩ ጉድ!
የወያኔ የታማኝነት ባጅ ያገኙበትን ሌላ አጭር ግን በጣም አስገርሚ ተውኔት እስቲ እናስታውስ! አሁን እኚህ ናቸው መነኵሴ!
ወዶ-ገባ ልብሱ ዳባ ይባላል። አሁን ወያኔ እንደፈለገችው ልታሽከረክራቸው ትችላላች። ግን የግሩም አወዳደቅ ከባድ እንደሚሆን አትጠራጥሩ። እህታችን፣ ገጣሚ አበባ አመዴ እንዲህ ብላ ነበር፡
እላይ ቤት እታች ቤት፣ ስትይ አገኝ አገኝ
ጅብ አህያ ለምዷል፣ እኔ አንቺን አያርገኝ።
ጅብ አህያ ለምዷል፣ እኔ አንቺን አያርገኝ።
እኚህ ሰው “ሕዝብ ምን ያውቃል። እንደነዱት የሚነዳ ከብት ነው” ብለው ሕዝብ ሲንቁ በጆሮዬ ሰምቼአቸውለሁ። የቀበሮ ባሕታዊው፣ ወያኔ ሲወድቅ አብረው እንደሚንኮታኮቱ አትጠራጠሩ! እኚህ እግዚአብሔርም ላይ፣ ሕዝብም ላይ ግፍ የሠሩ የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ግለሰብ ለብዙ ሥቃይ ዳርገውናል። ከዚህ በኋላ፣ እኚህን ሰው፣ ወያኔ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሳይሆኑ እንደ ከግዑዝ አካል ዕቃ ተጠቅማ ትተፋቸዋለች። ለመሆኑ፣ ይኸ አክሮባት ሠርቶ ወያኔ ሥር ጎንበስ-ጎንበስ ማለት የቱን ዕቃ ለማንሳት ይሆን? ለመሾም-ለመሸለም? ይቅርብዎት “አባ!” የወያኔ ሹመት ምን ማለት እንደሆነ ሟቹ ጣዖታቸው መልስ ነግሮን አሸልቧል! “የወያኔ ሹመት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው! ሽልብ ሲያደርግ ዱብ!”
ለምንኵስና ሕዝባችን ያለውን ክብር በማወቅ፣ “መነኵሴ ነኝ” ብለው የቀረቡን ግሩም፣ በሶልዲ ሸጡን! ትላንትና “ወያኔ! የዋልድባን ገዳማት አትንካ፣ የአሰቦትን ገዳም አትንካ፣ የዝቋላን ገዳም አትንካ” ብለው “ያዙኝ ልቀቁኝ” ሲሉ የነበሩት የቀበሮ ባኅታዊ፣ የለንደኗን ደብር ሳይቀር ለዕጅ መንሻ፣ ሕዝቡን ቀንሰው፣ አቅረበዋት በትነውን ከወያኔ ሰይጣኖች ጋር ግንቦት ፳ ለማክበር ድግሷ ላይ በኩራት ተገኙ! እነሆ ሕጻኑ፣ ሴቱ፣ ወንዱ ሽማግሌውና ወጣቱ፣ ውጭ ጸሐይና ውርጩ እየተፈራረቀበት፣ ይንከራተታል። እሳቸው ግን እነሆ በግልጽ ከወያኔ ጋር አዲስ ፍቅር ጀምረዋል። አዲስ ፍቅር ያመናቅር! ይመቻችሁ! ከርታታው የቤተክርስቲያኗ ምዕምን ግን ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ ከጀምረ ሁለት ዓመት ሊያስቆጥር ምንም አልቀረውም። ሕገ-ወጡ የወያኔ ጳጳስ፣ እንጦንስም በጉልበታቸው፣ ያለምንም ሀፍረት፣ በወያኔ ቅጥረኛ ዘበኞች ታጅበው የቤተክርስቲያናችንን ቁልፍ ከግሩም ተረክበው፣ በሯን ገፍትረው ከፍተው ገብተዋል። አልፈው ተርፈውም፣ አንድ ከሕዝቡ ጋር የሚንከራተቱትን ካህን ሕዝቡን እንዳያገለግሉ ለመገዘት ዳድቶአቸዋል። ጻዲቅ ቢሆኑ እንኳን ባማረባቸው። እንደ የወያኔዎች ባለሟሎች “ሕግ እንዳንተላልፍ” ተመክረን፣ በትዕግስት አንጡራ ገንዛባችንን አንጠፍጥፈን፣ የገዛናትን ቤተክርስቲያናችን ለስኳተርስ ትተንላቸው ምዕምናኑ ውጪ ቁመን እግዛብሔርን በማምለክ ላይ እንገኛለን። አልሆነላቸውም እንጂ ከዚያም ሊያባርሩን ዳድቶአቸው ነበር። ልብ እንቅርት ይመኛሉ ነው የሚባለው? ቢሆንም የለንደን ኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ትግል፣ አልተቋረጠም። ቀጥለንበታል! ወያኔና የቀበሮ ባሕታውያን እንዳዋረዱን፣ እግዚአብሔር በሕግ ፊት ያዋርዳችዋል።
በዓለም ተበትናችሁ የምትኖሩ፣ ወገኖቻችን፣ በያላችሁበት በጸሎት አትርሱን። ፍርድ ቤት ስንደርስ ለሚያፈልገን ሁሉ ከጎናችን ቁሙልን! የወያኔን ዓላማ ለንደን ላይ ድባቅ መምታት ማለት ሌላ ቦታ እንዳይሞክር አከርካሪውን መስበር ማለት ነው! ከዚህ በፊት ወያኔ እንዴት አድርጎ የቀበሮ ባህታውያንን አሰልጥኖ እንዳሰረገብን በሰፊው ጽፌአለሁ። ዞር ዞር እያላችሁ፣ አካባቢአችሁን እዩ! የቀበሮ ባሕታውያንን ከመሀከላችሁ ከተሰገሰጉ በዓይነ-ቁራኛ ተከታተሉአቸው። ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲንገበገቡ ትነቁባቸዋላችሁ! ለንደንን ያያችሁ ተቀጡ! ሀሳዊ መነኵሴ ጎንበስ-ጎንበስ ካለ ነገሩ ‘ዕቃ ለማንሳት” ነውና ጠንቀቅ በሉ። ዕውነተኛ አባቶችን በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁና፣ አይጭነቃችሁ!
እግዚአብሔር የግሩምን መጨረሻ ያሳየን! አሜን!
እግዚአብሔር የግሩምን መጨረሻ ያሳየን! አሜን!
No comments:
Post a Comment