Friday, March 28, 2014

ፓስፖርት ሸርካቹ ወይም ቀዳጁ መንግሥት


ሰሎሞን ታምሩ ዓየለ
መጋቢት 18 2006 ዓም
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በመጋቢት 12 2006 ዓም በሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የጉዞ ሠነድ ለይ ጉዞውን ወደ ምድረ አሜሪካ ለማድረግ የነበረውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የተደረገውን የወረደና የዘቀጠ፤ ጥላሸት ያነጠፈበትና ሸረሪት ያደራበት  በዝምታና በተንኮል የተውተበተበውን ስንኩል የመንግስትን ቁሻሻ አሰራር ለማውገዝና ድርጊቱን ፈጻሚ ሰዎችም በህግ እንዲጠየቁና በዋናነት የዜግነት ድርሻዬን ለመጠየቅ ነው። መንገድና ድልድይ ሰራሁ፤ ት/ቤት፤ የመኖሪያ ሕንጻ፤ ግድብ፤ መስኖ፤ የሃይል ማመንጫ፤ ስኳር ፋብሪካ፤ ትልልቅና ግዙፍ የሆኑ የኢንጂነሪንግ ተቋሞችን ገነባሁ፤ ሰፋፊ እርሻ እያስፋፋሁ ነኝ የሚል መንግስት ድንገት ምን ቢነካው ነው እንዲህ ወርዶ ወረቀት የሚቀድ? አንድ ግለሰብስ ይሄን ያህል ምን አስፈራው? ትናንት የተመሰረቱበትን በዐል ሲያከብሩ ” ኮሌኔል ማራኪና ደርጊ ማራኪ” እያሉ በድላቸው ፈንጠዚያ  ወደ ሰማይ ላይ ሲዘሉና ሲጨፍሩ የነበሩ ሰዎች እንዴት እንዲህ ከመቅጽበት ወርደው የመንገደኛን የጉዞ ሰነዱን በመንጠቅ ወረቀት በመቅደድ ያንገላታሉ? ለመሆኑ ከነሱ በፊትስ ከአገር መውጫ ቪዛ ለማግኘትስ የአገሪቱ የሰደተኞችና የቪዛ አገልግሎት መስጫን በሰላም ያለፈና የአሜሪካን ኤምባሲ ለቪዛ ያለፈ ፓስፖርት እንዲህ በጋጠ ወጦቹ ደህንነት ተብዬዎች ከመቅጽበት ወረቀቱ ሲጎድል አያስገርምንምን?
በመሰረቱ መንግስት የሚባለው ፖለቲካዊ ተቋም በምርጫም፤ በቅርጫ፤ በጡጫም ሆነ በጠመንጃ  መጣ የሚፈጽማቸው ተግባራቶች አሉት። በዋናነት የአገሩን ግዛት ሉዓላዊነት ማስከበርና ሕዝብ በውጭ ወራሪ ሃይሎች ጥቃትና ወረራ እንዳይፈጸምበት፤ ህግና ሥርአት ደንብና ትዕዛዝ በማዘጋጀት ካለምንም አድልዎ ለዜጎች ፍትህና ርትዕ ማጎናጸፍ፤ የሃገሪቱን የተፈጥሮ ሃብቶች ለሕዝብ ዕድገትና ልማት ማዋል መጠበቅና መንከባከብ፤ የተሟሉ ሕዝባዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ( ስራ መፍጠር ትምህርት ማስፋፋት ጤና መጠበቅና ሽፋን መስጠት  የባህልና ስፖርት መዝናኛ  ማበልጸጊያዎችን የመጓጓዣ አገልግሎቶችን ማስፋፋትና ማቅረብና) ሌላም ሌላም ናቸው። ጠቅለለ ባለ አነጋገር መንግስት ከሕዝብ፤ ለሕዝብና በሕዝብ መሰረታዊ ተፈጥሮአዊ፤ ታሪካዊና በህላዊ እሴቶች ላይ ከተመሰረተ  የጸናና የሕዝብ መንግስት ይሆናል። ለዚህም መሰለኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስት ምንድር ነው ብለህ ብትጠይቀው መንግስት ሕዝብ ነው ብለው አባቶቻችንና እናቶቻችን ትርጉሙን የሚሰጡት። ዛሬ ግን ደረጃውን ዝቅ አድርጎ ፓስፖርት ቀዳጂና ሸርካች ተቋም መሆኑን አልሰሙም። አብዛኛው የአኅጉራችን አፍሪካና የኛው መንግስት ግን ሲተረጎሙ ከመንግስት ዋና ተግባሮች መቶ በመቶ በተቃራኒው የቆሙ ናቸው። ግፍ፤ ፍትህ አልባነት፤ ሙስና ሲያስፋፉ፤ ውረደትና ቅሌት የተሞላበት ተግባር በተደጋጋሚ ሲፈጽሙ ነው የሚታይ። ደግሞ ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ጸረ ሰላም፤ ጸረ ልማት፤ ጸረ ሕዝብ፤ ሸብረተኛ እያሉ ሲፈረጁ እንኳን ለአፍታ አያፍሩም።  የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ ተብሎ የለ ።ስሟን ለሰው አወረሰች አሉም ይባላል።
ይህንን ሳስብ አንድ ተመሳሳይ የሆነና የወረደ ተራ ውስልትናና በሙስና የተውተበተበ አገር ጨዋታ ትዝ አለኝና ምንአልባት በኔ ዕይታ ድርጊቱ አንድ የሆነብኝን ነገር ግን ግዝፈቱ ከኛ ሰዎች ተግባር በአፈጻጸም ስልቱ ዝቅ የሚለውን ጨዋታ ልቅደድላችሁ። ይህንን ድርጊት የተፈጸመበት ሰው በስራ ላይ እያለ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ በሕይወት የለም (ነፍስ ይማር)። አገልግሎቱን የሚሰጠው መ/ ቤቱ ለአጭር ጊዜ ሥልጠና በናይጄርያ አገር በኢባዳን ከተማ በሚገኘው የትሮፒካል አገሮች የእርሻ መካነ ጥናት ተቋም ባዘጋጀው የሙያ ማዳበሪያና ማሻሻያ ኮርስ ላይ እንዲሳተፍ ዕድሉን ይሰጠውና የጉዞ ሰነዱን ከጠናቀቀ በኋላ በረራ ወደ ሌጎስ ያደርጋል። ከዚያም እንደደረሰ ተርሚናሉን ከመልቀቁ በፊት ግን ያልጠበቀው ሁኔታ ተፈጠረ። የተለየ ሳይሆን በምግባረ ብሉሽነታቸው የሚታወቁቱ የናይጄ ሪያው ፓስፖርት ተቆጣጣሪዎቹ ለራሳቸው የፈጠሩት ንቅዘት የተሞላበት አሰራር ሰለባ መሆኑ ነው። ተቆጣጣሪው እንዲህ አለው። “One paper is missing from your passport.” ለጊዜው የተደናገጠው የሥራ ጓደኛዬና የችግሩ ተጠቂ ግን የገዛ ፓስፖርቱን ካለማመን ደጋግሞ ቢፈትሽም የተሟላ ሆኖ ስላገኘው ክርክሩን ይጀምራል ፤ ሙከራው ግን አልተሳካም። ወደ ጎን በተዘጋጀለት ማረፊያ እንዲቀመጥ ይታዘዝና የሚሆነውን ሲጠብቅ ሁኔታውን በጎን ትከታተል የነበረች ወይዘሮ / ወይዘሪት ጠጋ ብላ የጎደለውን ወረቀት ዋጋ ነገረችውና ለመንገድ ተመንዝራ በኪሱ ከያዛት የአረንጓዴ ኖት $20 በፓስፖርቶቹ ቅጥል መሃል አድርጎ እንደገና ወደ ተቆጣጣሪው ብቅ ያለው ወንድሜ “now, it is okay!” የሚል መልስ እንዳገኘና መግቢያውን ይዞ ወደ ስፍራው እንደ ሄደና ሥልጠናውን ለመሳተፍ እንደቻለ አጫውቶኛል።
የናይጄሪዎቹ ሙስናና ንቅዘት የፈጠረው አሰራርን ወንድሜ በትንሽ ገንዘብ ፈታው። የኞዎቹ ግን ከሕግ በላይ ሆነውና ማን ከኛ በላይ አለ በሚል ይመስላል የፈለጉትን ያደርጋሉ። እንኳን አይደለም ፓስፖርት ወረቀት መቅደድና መሸርከት ይኽው የአገርስ ድንበር መሬት ለሌላ ባእድ አገር አሳልፎ ለመስጠትእየቀደዱና እየቀረደዱ አይደለምን? ሕዝቡንስ በርሃብ አለንጋና በኑሮ ውድነት እየገረፉት አይደለምን? በፍትህና ርትዕ እጦት የተነሳ ሕዝቡ ከመክሰስ፤ መከሰስን የመረጠበት ወቅት አይደለምን የምንገኘው? በልማትና በዕድገት ስምስ ከተሞቻችን በሰይጣናዊ ምግባርና አገልግሎት እየተሞሉና እየደመቁ አይደለምን? እነሱ በቅጡ ሳይማሩና ከመጽሃፍ ሳይታገሉ ቤታቸው ቁጭ ብለው ባገኙት ዲፕሎማና ዲግሪ አለቃና ስራ መሪ ሆነው፤ የተማሩትና ከመጽሃፉ የታገሉት ኮብል ድንጋይ አንጣፊ ስራ ተፈጥሮላቸው የለምን? ሃይማኖት የለሽስ ሆነው ይኽው የእስልምናውንና የኦርቶዶክሱን ሃይማኖት እያመሱትና እየገለባበጡት አይደለምን? ይኽው የአንድ አገር ሕዝብ አንድ አድረገው መግዛትና በፍትህ ማስተዳደር ሲገባቸው በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በፖለቲካ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት፤ በመደብና በሌላም ሕዝብን ይከፍልልናል ብለው በሚያምኑት መንገድ ሁሉ በመክፈል ለግጭቶች ምክንያት አልሆኑምን? የመንግስት ሥልጣንስ ዋና ባለቤት በመሆን የመንግስት ዋና ዋና ተቋሞች ውስጥ ግምባር ቀደም ተሿሚዎችና አዛዥ፤ ናዛዥ አልሆኑምን? የነሱን ፖለቲካ ያልተቀበለውንና ያልደገፈውንስ የተማረና ልምድ ያካበተውን በግምገማ ስም ስራውን እንዲለቅ፤ ከፍ ሲል ደግሞ ከአገሩ እንዲሰደድ አላደረጉትምን?
በመጨረሻም ዛሬ በፓስፖርት የጀመረው የመረጃ ቀደዳስ ነገስ በሌሎቹ  ጋጠ ወጦቹ የደህንነት ሰዎች በሌሎቹ የአገሪቱ ዜጎች የማይደገምበት ምንስ ዋስትና አለን? በእርግጥ የመታውቂያችን፤ የልደት፤ የጋብቻ፤ የንብረት፤ የትምህርትና ሌሎችም ሰነዶቻችን በመንግስት ሰዎች ስንኩልና ዕኩይ ምግባር ለአንዴና ለመጨረሻ ላለማግኘታችን ማስረጃችን ምንድር ነው? ይህም በመሆኑ ድርጊቱን የፈጸሙት ስርዓተ አልበኞቹና ጋጠ ወጦቹ የደህንነት የመንግስት ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡና ከዚህም ተግባራቸው ለወደፊቱ እንዲታቀቡ የም/ቤቱ ተወካዮች፤ የሚንስትሮች ም/ ቤት፤ የፍትህ ሚኒስቴር፤ ፖሊስና ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን ትኩረት ችረው ውሳኔአቸውን ለሕዝብ እንዲያሳውቁ አጥብቄ እጠይቃለሁኝ። የደንበኞቹን ፍላጎ ት ለማርካት ሌት ተቀን የሚማስነው የኢትዮጵያ አየርመንገድስ ምነውዝም አለ ? ድርጊቱ የተፈጸመው በድርጅቱ ግቢም አይደል? ደንበኛ በስንኩሎች ሴራ ተመንገዱ ሲስተጓጎል ዝም ነው መልሱ? ድንቄም የመንገደኛን ምቾት ጠባቂ!! አልሰማንም እንዳይሉ የአሜሪካው ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል፤ የጀርመኑ ዶቼ ወሌና የኢሳትና የኅብር ሬዲዮ እንግዳ ሆነው የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/ መንባበር ቃለ መጠይቅ መስጠታቸው ተደምጧል፤ ተዘግቧል።

No comments:

Post a Comment