Saturday, March 22, 2014

(ሰበር ዜና) ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት የእሳት አደጋ ደረሰበት (ተጨማሪ ወሬዎች አግኝተናል)

(EMF) በብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ላይ “የእሳት አደጋ ደረሰበት” የሚል ወሬ ከአዲስ አበባ ሰምተናል:: የአደጋውን ትልቅነት ወይም አነስተኛ መሆን ገና አላረጋገጥንም:: ቢሆንም አራት ኪሎ አካባቢ ግርግር ተነስቷል:: ይህ ማተሚያ ቤት ከማተሚያነቱም በላይ በ7ኛ ፎቁ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ሲያትማቸው የነበሩ ጋዜጦችና ጥንታዊ ህትመቶችን በቅርስነት የያዘ ነው:: በአገሪቱ የሚገኘው ይህ አንጋፋ ማተሚያ ቤት በቅርቡ፤ ለሌሎች አፍሪካ አገራት የገንዘብ ህትመት ለመጀመር አለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ ይታወሳል:: ሁኔታውን ተከታትለን እናቀርባለን::አሁን የደረሰን ዘገባ እንዳመለከተው ከሆነ; የ እሳት አደጋው በቁጥጥር ስር ውሏል:: ሆኖም አደጋውን ማን እንዳደረሰው እና የአደጋውን መጠን በዝርዝር አላወቅንም::
አሁን 10:00 AM EST ላይ… ተጨማሪ ወሬዎች አግኝተናል
አደጋው የተፈጠረው በብርሃን እና ሰላም የምድር ቤት ወይም የጋዜጣ ማተሚያ ውስጥ ነው:: ይህ የምድር ቤት በአብዛኛው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚታተምበት ክፍል መሆኑ ይታወቃል:: እሳቱም በግልጽ የሚታየው ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በጀርባ ወይም ወይም በጓሮ በኩል ነው:: በጀርባ በኩል ሆኖ የእሳት አደጋውን በቅርብ የተከታተለው ሰው እንደነገረን ከሆነ… እሳቱ ከተነሳ በኋላ ሁለት ግዜ የፍንዳታ ድምጽ ተሰምቷል, የኤሌክትሪክ ሃይል ሙሉ ለሙሉ ከአካባቢው እንዲጠፋ ተደርጓል, አሁን ግቢው እና አካባቢው በፌዴራል ፖሊስ ተከቦ በርከት ያሉ የእሳት አደጋ መኪናዎች እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረታቸውን ቀጥለዋል:: እሳቱም በቁጥጥር ስር የዋለ ይመስላል… ብለውናል::
በዚህ አጋጣሚ ስለብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ግንዛቤ እንዲኖራቹህ ቀደም ታሪኩን ከዚህ በታች ለህትመት አብቅተናል::
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት እ.ኢትዮ.አቆጣጠር ታህሳስ 23 ቀን 1917 ዓ/ም በአንዲት “ብርሃንና ሰላም” በተሰኘች አነስተኛ ጋዜጣ ሕትመት ሥራውን ጀመረ። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መጻሕፍት ፣ ጋዜጦች ፣ መጽሔቶችና የምስጢራዊ ሕትመት ሥራዎች በተለያዩ ቋንቋዎች እያተመ ይገኛል። ማተሚያ ቤቱ በርካታ የመንግሥት እና የግል ጋዜጦችን የሚያትም ሲሆን ፥ በተጨማሪም በየዓመቱ በርካታ የፈተና ሥራዎችን በማተም ይታወቃል።
Berhan ena Selam Building
Berhan ena Selam Building
ጥንታዊ ኢትዮጰያውያን ሊቃውንት የሚጽፏቸው መጻሕፍት ለሕዝብ የሚቀርቡት ብራና ተፍቆ ፣ ቀለም ተቀምሞ በእጅ ተፅፎ ነበር። በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመረው የዘመናዊ ሕትመት ሥራ በሀገሪቱ ቁጥራቸውና መጠናቸው በርከት ያሉ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች፣ መጻሕፍት፣ እንዲሁም ሌሎች የሕትመት ውጤቶች መታተም በመጀመራቸው የትምህርትና የሥልጣኔ መሰፋፋት ላይ የበኩሉን ሚና መጫወት ጀመረ።
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትም ምሥረታ ዋና ዓላማ የአገሪቱን መንፈሳዊ መጻሕፍት በብዛት እና በዘመናዊ መልክ ከእጅ ጽሑፍ ወደ ሕትመት ለማሸጋገር ሲሆን፤ ምሑሩ ተክለጻድቅ መኩሪያ (፲፱፻፷፩ ዓ/ም)፣ ማተሚያ ቤቱ መስከረም ፫ ቀን ፲፱፻፲፬ ዓ/ም መቋቋሙን እና ብዙ ሥጋዊና የመንፈሳዊ መጻሕፍት እንዲሁም ምክርና ተግሣጽ፣ የለት ወሬ፣ የሹም-ሽር አዋጆችን ያትም እንደነበር ዘግበዋል። [1] በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት መምህር መኩሪያ መካሻ፤ “የፕሬስ ታሪክ” በተሰኘ ጽሑፋቸው ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ፣ ራስ ተፈሪ መኮንን በ፲፱፻፲፫ ዓ/ም የማተሚያ መሣሪያ አስመጥተው “ትንሹ ግቢ” (በኋላ ገነተ ልዑል — አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ይባል በነበረው መኖሪያቸው ውስጥ አስተክለው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተባለውን እንደመሠረቱ ዘግበዋል። [2]
ከሁለት ዓመት በኋላ በ፲፱፻፲፭ ዓ/ም አራት ተጨማሪ ማተሚያዎች ተገዝተው ከተተከሉ ከአንድ ዓመት በኋላ ሣምንታዊው ‘ብርሃንና ሰላም’ የተሰኘው ጋዜጣ እየታተመ፣ አስቀድሞ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከተጀመረችው ‘አዕምሮ’ ጋዜጣ ጋር እስከ ጠላት ወረራ ዘመን ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ይሠራጩ ነበር።
የወቅቱ ማተሚያ መሣሪያዎች በእግር እየተረገጡ የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች ሲሆኑ የሠራተኞቹ ቁጥር ከሰባት እስከ አሥራ-ሁለት እንደነበር ተዘግቧል። ራስ ተፈሪም አልፎ-አልፎ በብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ይረዱ እንደነበረና ጽሑፎቻቸውንም ለሕትመት ያበቁ እንደነበር ተምዝግቧል።
ከጠላት ወረራ ወዲህ[ለማስተካከል]
በ፲፱፻፴፫ የፋሺስት ኢጣልያ ኃይል ተሸንፎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዳግም ሲቋቋም “ባንዲራችን” የተባለ ጋዜጣ እና ቅዳሜ ፣ ግንቦት ፴ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም በይፋ ሥራ ጀመሮ የመጀመሪያ እትሙን በ፲ ሺ ቅጅ ለአንባብያን ያበቃው አዲስ ዘመን (ጋዜጣ) የሚታተሙት በዚሁ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ነበር።
የዘውድ ሥርዓት አብቅቶ የ፲፱፻፷፮ቱ ዓብዮት ከታወጀ በኋላ የግል ማተሚያ ቤቶችን በሙሉ በመንጠቅ የብሔራዊ ንብረት ከማድረጉም ባሻገር፤ የግል ጋዜጣዎችንና መጽሔቶችን በሙሉ ከለከለ። በዚህ ፖለቲካዊ መንስዔ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከቀድሞው የበለጠ፤ በመንግሥት ሥር የሚተዳደርና ለሕትመት የተፈቀዱትን ጋዜጣዎች፤ መጽሔቶች፤ መጻሕፍት እና ሌላም የሕትመት እሴቶችን ከሞላ ጎደል አጠቃሎ ያዘ።
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ጊዜ ከ፰መቶ በላይ የሚቆጠሩ ሠራተኞችና በዘመናዊ መሣሪያዎች የቅድመ-ሕትመት ፣ የሕትመትና የድህረ-ሕትመት አገልግሎት ላይ የተሠማራ ድርጅት ሲሆን ንብረትነቱም፤ አስተዳደሩም ሆነ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂነቱ የመንግሥት ነው። ስለሆነም የመንግሥትን ፖለቲካዊ አቋም፣ በተለይም መንግሥት የማይፈልጋቸውን የግል ፕሬስ ድርጅቶችን እና ሌሎች ለሕትመት የሚቀርቡ ዝግጅቶችን ያሰቃያል፤ የነጻ ፕሬስን መንፈስ ያቀጭጫል፤ ተቀናቃኝ የግል ማተሚያ ቤቶች ስለሌሉበትም እንዳሻው ፈላጭ ቆራጭነትን ያካሂዳል የሚሉ ነቀፋዎች በብዛት ይሰነዘሩበታል።
ዝርዝር የመረጃ ምንጭ: ዊኪፒዲያ

No comments:

Post a Comment