Thursday, December 26, 2013

ለርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትና ወዳጆች፤ እንዲሁም በመላው UKየምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሁሉ

ቀን፡ 23/12/2013
በስደት ላይ በሚገኘው ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ጥረት፤ ድካምና ተጋድሎ አማካኝነት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዘረጋው የጎሳ ፖለቲካ ተጽዕኖ ሥር ሳትወድቅ በአስተዳደር ራሷን ችላ በመመራት ለከፍተኛ የዕድገት ደረጃ የበቃችው አንጋፋዋ የለንደን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ለወያኔ ባደሩ ጥቂት ባንዳ ካህናትና ተከታዮቻቸው አማካኝነት ገንዘብና ጉልበታቸውን አስተባብረው፤ ጥረውና ግረው የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት ካደረጓት አባላቷ ተነጥቃ የወያኔ አገዛዝ ሹመኞችና ደጋፊዎች ንብረት እንድትሆን የሚካሄደው ጥረት ቀጥሎ ይገኛል።Reese Adbarat Saint Mary of Debre Tsion Ethiopian Orthodox Church
ቀደም ሲል እነዚሁ ከሃዲ ካህናትና ተከታዮቻቸው ወያኔ ከጎሳው መርጦ ከሾማቸው ከአቡነ እንጦስና ከነ መጋቢ ተወልደ ጋር ግንባር በመፍጠር በ12 October 2013 ሁለት ጳጳሳትን ከኢትዮጵያ በማስመጣት ቤተ ክርስቲያኗን በወያኔ አገዛዝ ሹመኞችና ደጋፊዎች ቁጥጥር ሥር ለማዋል ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ይህ ሙከራቸው ግን ስደተኛው ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝቤ ላይ የምትፈጽሙት ግፍ፤ በደልና ፍትሕ አልባነት አልበቃ ብሏችሁ በዚህ ነጻነትና ፍትሕ በሰፈነበት ሃገር ደግሞ ተመሳሳይ ድርጊት እፈጽማለሁ ብላችሁ አታስቡ በማለት ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃውሞ በማድረግ ሙከራቸውን ሊያከሽፈው ችሏል።
ከዛም በመቀጠል የከሃዲዎቹ መሪ የሆኑት አባ ግርማ ከበደ አዲስ አበባ ድረስ በመሔድ ከወያኔ አገዛዝ ባለሥልጣኖችና የደህንነት ሰዎች ጋር በመምከር ለንደን በሚገኘው የወያኔ ኤምባሲና ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሃ.ት) ጽሕፈት ቤት እየተረዱ የጀመሩትን ተግባር እንዲያጠናቀቁ መመሪያ ተቀብለው ተመለሱ።
አባ ግርማ ከበደም ለወያኔ አገዛዝ ያላቸውን ታማኝነት ለማረጋገጥ ሲሉ ዜና ቤተ ክርስቲያን ለተሰኘው መጽሄት ለንደን ላይ የሚያስቸግሩኝ ግንቦት ሰባትና ቅንጅት ናቸው የሚል ክስ በማቅረብ ከነዚህ ሁለት ድርጅቶች ጋር ለሚያደርጉት ትግል ወያኔ ከጎናቸው እንዲቆምላቸው መጠየቃቸውን መጽሄቱ በእትሙ ላይ ካሰፈረው ለመረዳት ተችሏል።
በዚህ ድጋፍና መበረታታት በመታገዝ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እነዚህ ባንዳ ካህናትና ተከታዮቻቸው የሃገሪቱን ሕግም ሆነ የቻሪቲን ሕግና መመሪያ አንቀበልም በማለት በኤምባሲ ተወካዮችና ለንደን ከደረሱ ካለፈው 7 ጀምሮ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ደጃፏን ረግጠው በማያውቁት አቡነ እንጦስ አማካኝነት በ29/12/2013 ቤተ ክርስቲያኗን ከፍተው ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ይፋ ማስታወቂያ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ።
ከዚሁ ጋርም በኤምባሲና በወያኔ ጽ/ቤት አስተባባሪነት በለንደን ያሉና ከለንደን ውጪ ያሉ የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባላት ተጓጉዘው መጥተው ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በብዛት በመገኘት ቤተ ክርስቲያኗን በወያኔ አገዛዝ ሹመኞችና በኤምባሲ ተወካዮች ቁጥጥር ሥር ለማዋል ኃይልና ጉልበት እንዲሆኗቸው ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን አቡነ እንጦስ በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት ለተሰበሰበው ሕዝብ ይፋ ቅስቀሳ አድርገዋል።
ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ ግን ለአካባቢው ፖሊስ የተሰጠው ምክንያት የጸሎትና የአምልኮት መብታችንን ይከበርልን ዘንድ ቤተ ክርስቲያኑን ስንከፍት አስፈላጊው ትብብር ይደረግልን የሚል በመሆኑ ፖሊስ ያሉትን አምኖ ተቀብሎ ትብብር ሊያደርግላቸው እንደሚችል ይገመታል።
በለንደንና በመላው UK የምትገኙ ውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችና የማርያም ወዳጆች ሁሉ፡
መብትና ነጻነት ያለትግል፤ ድካምና መስዋዕትነት አይገኝምና ዛሬ የእምነትና የነጻነት ምልክታችን የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስደተኛው ኢትዮጵያዊ ሃብትና ጉልበቱን አስተባብሮ የንብረት ባለቤት ባደረጋት ማግስት የወያኔ ሹመኞች የውስጥ ባንዳዎችን በመሣሪያነት ተጠቅመው የሃይማኖቱን ማዕከል፤ ሃብትና ንብረቱን ነጠቁት ማለት ነገ በስደቱ ዓለም ነጻ የኮሚኒቲ ማዕከል፤ የፖለቲካ ተቋም፤ መኖር ቀርቶ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ በግል ሰብ ሳይቀር በነጻነት ሃገር መብትና ነጻነትን አሳልፎ ለመስጠት ትለቁ በር ከፋች ስለሆነ ሁሉም የማርያም ወዳጅና ነጻነት ወዳድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ በ29/12/2013 ከ0800 ሰዓት ጀምሮ በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት ቤተ ክርስቲያኑን እንዲከላከልና በስደት ሃገር የተጎናጸፈውን መብትና ነጻነቱን እንዲያስከብር በእመቤታችን በቅድስት ማርያም ስም ጥሪአችንን እናቀርባለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
http://londondebretsion.org/ ተከታተሉን
ourchurchdebretsion@gmail.com ኢ-ሚየል መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

No comments:

Post a Comment