Sunday, December 8, 2013

ኔልሰን ማንዴላ እና ኢትዮጵያ!!

ተጨማሪ ማስታወሻዎችና ከኢትዮጵያ የወሰዱት ሽጉጥ መጨረሻ

የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በ95 አመታቸው ከዚህ አለም ሲለዩ፤ የተለያዩ አገሮች እንደየራሳቸው ግንኙነት የራሳቸውን ታሪክ ሲያወሩ ነበር። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ሃዘናቸውን ሲገልጹ ከማንዴላ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመግለጽ ነበር። እኔ በምኖርበት አትላንታ ከተማ ዜናው ሲቀርብ፤ ኔልሰን ማንዴላ አትላንታ በመጡበት ወቅት፣ ከነአንድርው ያንግ ጋር ሆነው የማርቲን ሉተር ኪንግ ማዕከልን ስለመጎብኘታቸው ነበር – ዋናው ዜና። ሁሉም አገር ስለማንዴላ የየራሱ ትዝታ አለው። ኢትዮጵያውያንም ስለኔልሰን ማንዴላ የራሳችን ታሪክ እና ትዝታ አለን። እናም ማንዴላ የዛሬ 51 አመት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ስለነበረው ጉዳይ በማውጋት ታሪካችንን እንጀምራለን።
Nelson Mandela, the revered statesman who emerged from prison after 27 years
በዳዊት ከበደ ወየሳ
Nelson Mandela and Col Tadesse
የኔልሰን ማንዴላ አሰልጣኝ ከነበሩት መካከል፣ ኮሎኔል ታደሰ አንዱ ነበሩ። ይህ ፎቶ ማንዴላ እና ኮ/ል ታደሰ (በሗላ ጄነራል) ለመታሰቢያ የተነሱት ነው
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ በ1962 ዓ.ም አራተኛው የፓን አፍሪካ ስብሰባ በኢትዮጵያ እንዲደረግ ጃንሆይን ፍቃድ ጠየቁ። ጃንሆይ በጉዳዩ ተስማሙና በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም የአፍሪካ ታዋቂ የነፃነት ታጋዮች ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ከእነዚህም መሃከል ሚስተር ኦሊቨር ታምቦ፣ ሚስተር ሮበርት ሙጋቤ፣ ሚስተር ኬኔት ካውንዳ እና ሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ይገኙበታል። (በኋላ ላይ እነዚህ ወጣት ታጋዮች የየአገራቸው ፕሬዘዳንት ሆነዋል) ይህ ጉዞ በተለይ ለኔልሰን ማንዴላ በህይወታቸው ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጡት ነው።
ኔልሰን ማንዴላ እንደጻፉት…. ስለቼ ጉቬራ፣ ማ ኦ እና ፊደል ካስትሮ ስራዎች አነበብኩ። ለህዝባቸው ነጻነት ያደረጉትን ትግል ተመለከትኩ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያውያን የደፈጣ ተዋጊዎች፤ ሙሶሊኒ ያስታጠቃቸውን የጣልያን ወታደሮች ድል ያደረጉበትን ታሪክ ለማወቅ በጣም ጓጓሁ። በመሃል ደግሞ ድርጅታችን ከሰላማዊ ትግል ጋር የትጥቅ ትግል ማድረጉ ስለታመነበት፤ እኔ ይህን ጉዳይ እንድመራ ትዕዛዝ ተሰጠኝ። ይህ የህቡዕ ጦርም ኡምኮሆንቶ ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ። ኡምኮሆንቶ ማለት፤ የጦር ጫፍ ማለት ሲሆን፤ አፍሪካውያን ለነጻነታቸው ሲዋጉ የቆዩት በጦር ስለሆነ ነው።
እናም ድሮ አቢስንያ ተብላ ወደምትጠራው የአሁኗ ኢትዮጵያ ለመሄድ ተዘጋጀሁ። ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ደት በፊት የነበረች አገር ናት። እንዲያውም ከንጉሥ ሰለሞን እና የሳባ ንግስት የሚወለደው ቀዳማዊ ምኒልክ አገሪቱን መርቷል። ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ በአውሮፓውያን ብትወረርም፤ ሁልጊዜ ህዝቡ ጦርነት እያደረገ ያሸንፋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት እና ብሄራዊ ስሜት የተወለደባት አገር ናት። ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለየ መልኩ ወራሪዎችን ሲዋጉ ቆይተዋል። ዳግማዊ ምኒልክ ጣልያኖችን ድል አድርገው ቢመልሱም፤ ጣልያን ለሁለተኛ ግዜ አገሪቱን በወረረች ግዜ ግን ሁኔታዎች የከፉ ነበሩ።
ሙሶሊኒ የጣልያን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ጦርነት ሲያደርግ የ17 አመት ልጅ ነበርኩ። ድርጊቱ ፋሽስቶችን እስከመጨረሻው እንድጠላቸው ነበር ያደረገኝ። ምንም እንኳን ንጉሥ ኃይለ ስላሴ በጦርነቱ ምክንያት አገር ለቀው ቢሄዱም፣ ህዝቡ በአርበኝነት እየተዋጋ አገሪቱ በ1941 እንደገና ነጻነቷን አስመልሳለች። ኢትዮጵያ በኔ ውስጥ ሁልጊዜ ልዩ ስፍራ አላት። የአፍሪካዊነት የዘር ሃረግ ግንዴ የተተከለባት አገር ትመስለኛለች።
ከአክራ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ባደረግንበት ወቅት ስሜታዊ ያደረገኝ ጉዳይ ተፈጠረ። ከአክራ ወደ ካርቱም መጥተን፤ ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ገባን። ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስንገባ፤ ፓይለቱ ጥቁር መሆኑን አይቼ ደነገጥኩ። በህይወቴ ሙሉ ጥቁር ሰው አውሮፕላን ሲነዳ አይቼ ስለማላውቅ ተሸበርኩ። ‘ጥቁር ሰው እንዴት አውሮፕላን ሊነዳ ይችላል?’ እያልኩ ደጋግሜ ራሴን ጠየኩ። በኋላ ግን ሲገባኝ፤ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርአት አስተሳሰባችንን ጭምር ቀይሮታል። ሳናውቀው አፍሪካዊ ዝቅ ያለ እና አውሮፕላን ማብረር የሚችለው ነጭ ብቻ ነው’ የሚል ስሜት እንዲያድርብን ሆኗል ለካ። አውሮፕላኑ በሰማይ ላይ ማንዣበብ ሲጀምር ጭንቀቴን ትቼ ስለኢትዮጵያ መልክዐ-ምድር ማንበብ ጀመርኩ። በመንገዳችን ላይ የማስብ የነበረው… ኢትዮጵያውያኑ በነዚህ ተራሮች እና ጫካዎች ውስጥ ተደብቀው እንዴት ከጣልያን ጋር የደፈጣ ውጊያ ያደርጉ እንደነበር ነው።
ጥቂት አስፋልት መንገድ ያላት አዲስ አበባ፤ ከመኪኖች ይልቅ በግ እና ፍየል በየመንገዱ ሞልተው ይታያሉ። ቤተ መንግስቱ፣ እኛ ያረፍንበት ራስ ሆቴል፣ እንዲሁም ሌሎች ህንጻዎቿ ከጆሃንስበርግ የህንጻ ጥበብ ጋር ሲተያይ ብዙም አይማርክም። በዲሞክራሲም ቢሆን ኢትዮጵያ በምሳሌ ተርታ የምትሰለፍ አገር አይደለችም። ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም በንጉሱ ብቻ የምትመራ አገር ናት።
ከአፍሪክ ኮንፈረንስ መክፈቻ በፊት ወደ ትንሿ ከተማ፣ ደብረ ዘይት ሄደን ነበር። በከተማው አንድ አደባባይ አለ። እዚህ አደባባይ ላይ ከነበረው ድንጋይ ላይ እኔና ኦሊቨር ቁጭ ብለናል። ድንገት ግን ከርቀት የሙዚቃ ድምፅ ሰማን። ወደኛ ሲቀርብ የጥሩንባ እና የድራም ድምጽ እንዳለበት አወቅኩ። በኋላ ላይ እንዳየሁት ለካስ ወታደራዊ የሙዚቃ ባንድ ኖሯል። ከሙዚቃው ባንድ ቀጥሎ የብዙ ሰዎች እግር መሬቱን እየደቃ ሲመጣ ሰማሁ። በመቶዎች የሚቀጠሩ ጥቁር ወታደሮች ናቸው። ከፊት የሚመራቸው መኮንን የሚያብረቀርቅ ሰይፍ ይዟል። ወታደሮቹ የተወለወለ ጠመንጃቸውን እንደያዙ በልዩ ስሜት ይራመዳሉ። ፊት መሪያቸው ድንገት በአማርኛ አንድ ነገር ሲነግራቸው፤ ሁሉም እኩል አንድ ድምጽ አሰምተው፤ ፊታቸውን ወደ ንጉሥ ኃይለ ስላሴ አዙረው ሰላምታ በመስጠት አለፉ።
በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁር ሰው የሚመሩ ጥቁር ወታደሮች ተመለከትኩ። የተሰበሰቡት ሰዎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው። ሁሉም ጥቁሮች ናቸው። ራስ የሚያዞር ስሜት ውስጥ ገባሁ። አንድ ቀን አገሬ ውስጥ እንዲህ አይነት ነጻነት እንደምመለከት ተስፋ ከማድረግ ሌላ የምለው ነገር የለም ነበር።
የኔልሰን ማንዴላን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ያሰናዱት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ። በወቅቱ በአፓርታይድ የዘረኝነት ቀንበር ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ዜጎችዋ ያለፈቃድ አገሪቱን ለቀው እንዳይወጡ የሚያዝ ህግ አውጥታ ነበር። ይህ ህግ ለኔልሰን ማንዴላ ጉዞ አስቸጋሪ  ሁኔታን ፈጠረ። በመሆኑም አቶ ከተማ ይፍሩ ለኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልፅ ፓስ ፖርት ካዘጋጁላቸው በኋላ ነበር፤ በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፤ ወቅት ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።
በወቅቱ ለኔልሰን ማንዴላ የተዘጋጀው ፓስፖርት ላይ ማንዴላ እንደጋዜጠኛ ሆነው፤ ስማቸው ዴቪድ ሞሳማይ ተብሎ ነበር የተጻፈው። ስሙን የተጠቀሙት ደቡብ አፍሪካ እያሉ አብሯቸው ከነበረው ጓደኛቸው ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ስለነበረው ጉዞ እናውጋ። ኔልሰን ማንዴላ Long Walk To Freedom” በሚለው መፅሃፋቸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አየር መንገድ ድረስ መጥተው እንዴት እንደተቀበሏቸው ገልፀዋል። እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ ኔልሰን ማንዴላ…
ለንደን የነበሩትን ጓደኞቼን በወዳጅነት ስሜት ተሰናብቼ ወደ አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ ተጓዝኩ። እስካሁን ባለው ህይወቴ ለማላውቀው ወታደራዊ ስልጠና ነው የምሄደው። የስድስት ወር ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ በያዝኩት ፕሮግራም መሰረት ነው ወደ ኢትዮጵያ የምጓዘው። አዲስ አበባ ስደርስ መጀመሪያ ተቀብለው ያነጋገሩኝ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከተማ ይፍሩ ነበሩ። ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። ከዚያም “ኮልፌ” ወደሚባለው አንድ የከተማው ክፍል ወሰዱኝ።
የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ የሚሰለጥነው እዚህ ኮልፌ የሚባለው ሰፈር ነው። የባታሊዮኑ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው ከዚህ ነው። አኔ ወታደራዊ የሳይንስ ጥበብ እንድማር የተመደብኩበትም ስፍራ እዚህ ነው። እስካሁን ባለኝ ልምድ ጀማሪ ቦክሰኛ ከመሆን ውጭ ስለጦር ሜዳ ፍልሚያ የረባ እውቀትም የለኝም። አሰልጣኜ መቶ አለቃ ወንድሙ በፍቃዱ ይባላል። በጣልያን ወረራ ግዜ የደፈጣ ተዋጊ የነበሩ ልምድ ያላቸው ወታደር ናቸው።
በአዲስ አበባ መውሰድ የጀመርነው የስልጠና ፕሮግራም ጥብቅ ነው። ከጠዋቱ 2፡00 ሰአት እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ ስልጠና ላይ እንቆያለን። ከዚያ የምሳ ሰዓት ነው። ከዚያ ከሰዓት ከ8፡00 እስከ 10፡00 ስልጠናው ይቀጥላል። ከ10፡00 ሰዓት በሁዋላ እስከምሽቱ ድረስ ስለ ወታደራዊ ሳይንስ የንድፈ ሃሳብ ገለጻ ይደረግልናል። ይህንን ስልጠና የሚያደርጉልን ኮሎኔል፤ የፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ናቸው። በንጉሱ ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲከሽፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በስልጠናው የአውቶማቲክ መሳሪዎች እና የሽጉጥ አጠቃቀምን ተማርኩ።
መጀመሪያ ኮልፌ ከዚያም ከኮልፌ 50 ማይልስ የምትርቅ ቦታ ከወታደሮቹና ከንጉሱ የክብር ዘበኛ አባላት ጋር ሄጄ የኢላማ ተኩስ ተለማመድኩ። የሞርታር ተኩስና እንዲሁም የቦንንብ አሰራሮችን፤ ፈንጂዎችን የማክሸፍ ዘዴንም ተማርኩ። አሁን እያደር ወታደር እየሆንኩ ስሄድ ይታወቀኛል። እንደ ወታደር ማሰብ ለመድኩኝ። ወታደር መሆን እንደ ፖለቲከኛ ከማሰብ የሚለይበት የራሱ መንገድ አለው።
እዚህ ቦታ ላይ በጣም የወደድኩት ጠዋት ተነስተን የምናደርገው የማለዳ ጉዞ ነው። ጠመንጃ፣ ጥይትና ጥቂት ውሃ እንይዛለን። እናም በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ ያንን ርቀት ተጉዘህ የታዘዝከውን ፈፅመህ መድረስ አለብህ። በዚህ ወታደራዊ ጉዞ የአገሪቱን ገጠራዊ ክፍሎች ለማየት እድሉን አገኘሁ። የመሬቱ አቀማመጥ በጣም ቆንጆ ነው። ጥቅጥቅ ያለ ደንና ከፍተኛ ቦታዎችን አየሁ። ገጠሩ በጣም ሁዋላ ቀር ነው። ሰዎች በእንጨት መቆፈሪያ ነው የሚያርሱት። ምግባቸውም ትንሽና በቀላሉ የሚዘጋጅ ነው። እቤት የሚጠመቅ ቢራ ወይም ጠላ አላቸው፤ ኑሯቸው እዚህ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ መከረኞች ጋር ተመሳሳይ ነው። መቼም ደሃ ሰዎች የትም ቢኖሩ ኑሯቸው አንድ አይነት ነው፤ ብዙም አይለያዩም።
በስልጠናዬ ወቅት ኮሎኔል ታደሰ ብዙ ጉዳዮችን እያነሱ ያስተዋውቁኛል። ስለ ደፈጣ ውጊያ፤ ሃይል እንዴት ማዋቀር እንደሚቻል አንድን ጦር እንዴት ማዘዝና መምራት እንደሚቻል፤ በጦር ውስጥ ወታደራዊ ስነ ስርአትን ለማስፈን ምን ማድረግ እንደሚገባ ያስተምሩኛል።
አንድ ምሽት እራት ላይ ለደቡብ አፍሪካ ትግል ምን አይነት ጦር እንደሚያስፈልገንና የሰራዊቱ ባህሪ ምን መሆን እንዳለበት አጫወቱኝ። “ይኸውልህ ማንዴላ… አንተ የምትመሰርተው ነፃ አውጪ ሃይል እንጂ መደበኛ ጦር አይደለም። የናንተን ጦር ሰዎች የምትቀርፅበት ስልት ከመደበኛው ጦር አሰራር የተለየ ነው። አንተ መመስረት ያለብህ ነፃ አውጪ ጦር ነው። በትግል ላይ ስትገባም የምትመራቸው ተከታዮችህ ፍፁም እርግጠኝነት እንዲሰማቸውና ሁሉም ሃሳብህን እንዲከታተሉ ማድረግ መቻል አለብህ። ይህ በመደበኛው ጦርም ውስጥ ያለ ነው። ከስራ በሁዋላ በእረፍት ሰዓትህ ማድረግ የሚገባህ ግን ከመደበኛው ደንብ ውጪ ይለያል። አንተና የመጨረሻው ተራ ተዋጊ እኩል መሆናችሁን የሚያሳይ አቀራረብ ሊኖርህ ይገባል። የሚበሉትን ትበላለህ፤ የሚጠጡትን ትጠጣለህ። ምግብህን ወደ ግል ክፍልህ መውሰድ የለብህም። እራስህን ገለል አታድርግ፤ እዚያው አብረሃቸው ሁን።” አሉኝ። የኮሎኔልን ሃሳብ ተረድቻለሁ። ሃሳቦቹ የሚደነቁና መልዕክት ያዘሉ ናቸው። እንደነዚህ ያሉ ቁም ነገሮችን በየፕሮግራሙ መሃል ይነግሩኝ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለስድስት ወር ስልጠና ነው። ስምንት ሳምንት እንደሆነኝ ግን ከድርጅቴ ‘የአፍሪካ ኮንግረስ’ አንድ የቴሌ ግራም መልዕክት ደረሰኝ። ባስቸኳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንድመጣ የሚጠይቅ ነው። የዚያን ጊዜ የነፃነት ትግሉ መፋፋም ጀምሯል። እናም የግንባሩ አዘዥ እዚያው ቦታው ላይ መገኘት ስላለበት ነው የጠሩኝ። ኮሎኔል ታደሰ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የምሄድበትን መንገድ ቶሎ አዘጋጁልኝ። ስንሰነባበት አንድ ሽጉጥና ሁለት መቶ ጥይት ስጦታ አበረከቱልኝ። ስለ ስልጠናውም ሆነ ሰጡኝ ትምህርት ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ገለጽኩና ጉዞዬን ጀመርኩ። መሳሪያ ተሸክሞ ረዥም መንገድ መጓዝን ብለማመድም የተሰጠኝ መሳሪያ ከባድ ነው። ሁለት መቶ ጥይት ጀርባ ላይ መታጠቅ ህጻን ልጅ በጀርባ እንደማዘል ነው የሆነብኝ።
ኔልሰን ማንዴላ ደቡብ አፍሪካ ከገቡ በኋላ ሽጉጡንና ጥይቶቹን ለአንድ ለሚያምኑት የኤ.ኤን.ሲ አባል አሳዩት። የት እንደደበቁት ግን ማንም አያውቅም። (የሽጉጡን መጨረሻ በስተበኋላ ላይ እመለስበታለሁ)
ኦገስት 5 ቀን፣ 1962 ላይ… ኔልሰን ማንዴላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከገቡ ጥቂት ሳምንታት በኋላ ጥብቅ ፍተሻ ተደረገባቸው። ከጦር መሳሪያው በስተቀር የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልጽና የአቶ ከተማ ይፍሩ ፊርማ ያለበት ፓስፖርት ተገኘባቸው። በኢትዮጵያ መቆየታቸውን የሚገልጽ የጃንሆይ ማስታወሻና የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ አነስተኛ ፎቶ ነበር። እነዚህን ጨምሮ 173 መረጃዎች በሪቮንያ የአፓርታይድ ችሎት ላይ ቀረበባቸው – 1963።
እነዚህና ሌሎች መረጃዎች በሪቮንያ ፍርድ ቤት ቀርቦ በኔልሰን ማንዴላ ላይ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው፤ በዚሁ አመት በ1963 ሮቢን ደሴት ላይ ወደሚገኘው ወህኒ ተወረወሩ።
ከብዙ ውጣ ውረድና የ27 አመታት ትግል በኋላ ማንዴላ ከእስር ተፈቱ። እናም ከእስር በኋላ መጀመሪያ ከጎበኟቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። በፓስፖርታቸው ላይ ያሉት የመጀመሪያ ቪዛዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። መጀመሪያ ከጎበኟቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆነች። በኋላ ላይ በመጽሃፋቸው ላይ ሲጽፉ፤ “ኢትዮጵያ በኔ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላት። በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ያደረኳቸው ጉብኝቶች ቢደመሩ እንኳን፤ በኢትዮጵያ ከነበረኝ ቆይታ አይበልጡም።” በማለት ለኢትዮጵያ ያላቸውን ልዩ ስሜት ገልጸዋል። (በነገርዎ ላይ የኔልሰን ማንዴላን የህይወት ታሪክ የሚገልጽ፤ ትልቅ ፊልም ተሰርቷል)
Nelson Mandela with Mengistu Haile Mariam
ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በሗላ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በወቅቱ ፕ/ት መንግስቱ ሀይለማርያም አቀባበል ሲያድርጉላቸው
ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በወቅቱ እነ ጄነራል ታደሰ ብሩ በህይወት አልነበሩም። ጊዜውም ተለውጧል። ቆየት ብሎ ኔልሰን ማንዴላ በህይወት ካገኟቸው ሰዎች መካከል አቶ ከተማ ይፍሩ አንዱ ነበሩ።
ከሰላሳ አመት በፊት  አብረው የተነሱት ፎቶ ማንዴላን ለእስር እንዳላበቃቸው፤ አሁን ግን በነፃነት እንደገና ተገናኝተው የመታሰቢያ ፎቶ ለመነሳት በቁ። (አቶ ከተማ ይፍሩም ከጥቂት አመታት በፊት አልፈዋል)
ከመሰናበታችን በፊት… የሽጉጡን ነገር እንጨዋወት። ኔልሰን ማንዴላ ከኢትዮጵያዊው በወቅቱ ኮ/ል ታደሰ ብሩ (በኋላ ጄነራል) የተቀበሉትን ሽጉጥ፣ 200 ጥይት እና የወታደር ዩኒፎርም ሊሊስሊፍ በተባለው እሳቸው ከመታሰራቸው በፊት ይኖሩበት በነበረው ቦታ ቀብረውት ኖሯል።
ማንዴላ ከተፈቱ በኋላ ይህንን ስፍራ ለመጎብኘት ሄዱ። ከዚያም ለብዙ አመታት በትግሉ ውስጥ የነበረውንና እዚህ ስፍራ የሚኖረውን ባልንጀራቸውን፤ “ሽጉጡስ?” ሲሉ ጠየቁት።
ሰውየው በማንዴላ ድንገተኛ ጥያቄ ተደናግጦ፤ “የምን ሽጉጥ?” አለ። ኣካባቢው የነበሩ ሰዎች በሙሉ በሁኔታው ግራ ተጋብተዋል። “ድሮ የምንጠቀምበት ኩሽና የታለ?” አሉ። ባልንጀራቸው አሁን ህንጻ ወደተሰራበት የድሮው ኩሽና ወሰዳቸው።
“ከዚህ ኩሽና ሃያ እርምጃ ላይ ነው፤ ሽጉጡንና ጥይቶቹን የቀበርኳቸው” አሉና ሃያ እርምጃ ለመራመድ ተዘጋጁ። ሆኖም ሃያ እርምጃ ከመሙላቱ በፊት አንድ ትልቅ ግንብ ከፊታቸው ተደቀነ። ከግዜ በኋላ መሬቱን ገዝቶ፣ ቤት ሰርቶ የሚኖረው የቦቢ ላንሃም የድንጋይ ግንብ ነው። ስለዚህ ማንዴላ ከመታሰራቸው በፊት የቀበሩት ሽጉጥ፤ አሁን በሌላ ሰው ግቢ ውስጥ እንደሚገኝ ይገመታል።
የቤቱ ባለቤት የሆነው ቦቢ ላንሃም ግቢው እንዲቆፈር ቢጠየቅ፤ “265ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ከከፈላችሁኝ ብቻ ነው የምፈቅድላችሁ” አላቸው። ገና ለገና መኖር አለመኖሩ ላታወቀ ሽጉጥ ይህን ሁሉ አንከፍልም ብለው ነገሩን ተዉት።
ሆኖም ኔልሰን ማንዴላ ከመሞታቸው ሁለት አመታት በፊት “ሽጉጡ ተገኘ?” ብለው ጠይቀው፤ አለመገኘቱ ተነግሯቸው በወቅቱ አዝነው እንደነበር ተገልጿል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአገሪቱ ቅርስ ጠባቂ ሙዚየም በጉዳዩ ውስጥ ራሱን በማስገባት የባለቤትነት ጥያቄ አቅርቦ የኔልሰን ማንዴላ ቤተሰቦች በመቃወማቸው ነገሩ አወዛጋቢ እንደሆነ ቆይቷል። ይህ ሽጉጥ ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ ሳይወጣ 2 ሚሊዮን ዶላር ተገምቶ ነበር። አሁን ከማንዴላ ሞት በኋላ ደግሞ ዋጋው በ እጥፍ ሊጨምር ይችላል። የሆኖ ሆኖ ግን ከቦቢ ግቢ በቀር የ-ሊሊስሊፍ ግቢ ተቆፍሮ እስካሁን ምንም አልተገኘም።
በመጨረሻም በዚህ እንሰናበት።
የኔልሰን ማንዴላ የልደት ቀን ሲመጣ፤ ተማሪዎችን ጨምሮ ህዝቡ በሙሉ ልደታቸውን ያከብራል። ለኔልሰን ማንዴላ ትልቁም ትንሹም “ማዲባ ሃላላ፣ እንወድሃለን አባባ” እያሉ ይዘምሩላቸዋል። እኛም “ማንዴላ እንኳን ተወለዱልን” ለማለት በልደት ቀናቸው አገር ምድሩ የሚያዜምላቸውን መዝሙር እንጋብዛቹህ።
Madiba, Halala
Happy birthday to you!
Happy birthday to you!
Happy birthday dear Tata!
We love you Tata
We love you Tata
Nelson Mandela. Ha hona
Ya tshwanang le wena (there is no like you)
Yeep yeep!
Hooray!
እኛም በዚሁ ስንሰናበት፤ አንድ ነገር ለማለት ወደድን። አሁን የውሸት ወይም ድራማዊ ለቅሶ ሳይሆን፤ የእውነት ሃዘን የምናይበት ጊዜ ይሆናል።
ነፍስ ይማርልን!

No comments:

Post a Comment