Saturday, November 23, 2013

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰሜን አሜሪካ፣ ነፃነት ያለ ደም …. ክብርስ ያለ መስዋዕትነት እንዴት ሊገኝ ይችላል?

ነፃነት ያለ ደም …. ክብርስ ያለ መስዋዕትነት እንዴት ሊገኝ ይችላል?
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰሜን አሜሪካ
በሳውዲት አረቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ እየተካሄደ ያለውን አሰቃቂ ግድያና ሰቆቃ አጥብቆ ያወግዛል !
አድዋ ላይ የፈሰሰው ደም ፣ በማይጨው የተከሰከሰው አጥንት ፣ በመተማ ግንባር ላይ የተቀላው አንገት ፣ በዶጋሊ በደም የተፃፈው ጀግንነት …… ለግል ታሪክ ማዳመቂያ ሳይሆን እኛ ኢትዮጵያኖች በገዛ አገራችን በባርነት ቀንበር ስር እንዳንማቅቅና በነፃነት ተከብረንና ኰርተን እንድንኖር አድርጐናል ።
ዘርዓይ ደረስ ለአገሩ ባንዲራ የከፈለው መስዋዕትነት …. አብዲሳ አጋ ያስመዘገበው ወደር ያልተገኘለት ጀግንነት …. አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በየካቲት አስራ ሁለት ጀነራል ግራዚያኒ ላይ የቃጡት ጥቃት ፣ አቡነ ጴጥሮስ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ክብር ሲሉ ነፍሳቸውን መስጠታቸው እኛ ልጆቻቸው ፣ የልጅ ልጆቻቸው ባለ አገርና ያልተገደበ ነፃነት እንዲኖረን ነበር ።
የኦጋዴንን ድንበር ሰብሮ በመግባት …… ልጆቻችንን ፣ ሚስቶቻችንና እናቶቻችንን እፊታችን ስር ሊደፍርና ሊያዋርድ የመጣውን እብሪተኛ ጦር እውነተኛው ኢትዮጵያዊው ሰራዊት በሰማይ ፣ በባህርና በምድር ተሞ ድባቅ መምታቱ ባንዲራችንን የሰንደቆች ሁሉ አውራ አድርጓት ኖሯል ።
ታዲያ ዛሬ ያ ! ሁሉ የዜግነት ክብር እንዴት ተናደ ? ዜጐቻችን ባባህር ሲያቋርጡ የአሳ ነባሪ እራት ለምን ይሆናሉ? እህቶቻችን የፈላ ዘይትና ውሃ በአካላቸው ለምንስ ተቸለሰባቸው ? ከፎቅ ላይ እራሳቸውን እያምዘገዘጉ ለምን ጣሉ ? በጠራራ ፀሃይ በመሃል ከተማ ውስጥ የድረሱልኝ እሪታ እያሰሙ እንደ በግ መሬት ለመሬት ሲጐተቱና በመኪና መስኰት እንደወረቀት እያጣጠፉ በግድ ሲጭኗቸው በገሃዱ አለም ለምን አየን ? ሳውዲት አረቢያ ለዜጐቻችን የምድር ሲዖል ለምን ሆነች ? ወንድሞቻችን እንደ ረከሰ ውሻ ያለርህራሄ ተቀጥቅጠው ሲሞቱ በዓይናችን በብረቱ አየን ። ሰንደቅ ዓላማችንን በአናቱ ላይ ያሰረው ወንድማችን እንዲሁ ምህረትን እንደተማፀነ ነፍሱ ከስጋው ስትለይ በሰቀቀን ተመለከትን …… ገዳዮቹ ውሻው አበሻ (ኢትዮጵያዊ) ሞቷል እያሉ ሲሳለቁበት እርር ድብን እያልን ተከታተልን ።
እህቶቻችን አይናችን ፊት በጐዳና ላይ ለአምስትና ለአሥር ሆነው ሲደፍሯቸው ተጐልተን እያየን በቁጭት አነባን ።
አባችቶቻችን ያቆዩልንን አኩሪ ነፃነት መጠበቅ አቅቶን በባርነት በተሸጥንበት አገር የውሻ ስም ተሰጥቶን የውሻ ሞት ሞትን ። ከዜጐች ሁሉ መጨረሻ የተናቅንና የተዋረድን ሆንን ።
እነሆ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰሜን አሜሪካ ይህንን በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን አሰቃቂ ፍጅት አጥብቆ እያወገዘ ፤ ለዚህ ሁሉ ውርደትና ሥቃይ የዳረገንን ዘረኛ መንግስት ተጠያቂ ያደርጋል ።
የኢትዮጵያ ሰራዊት ሆይ ስማ ! አገርህ ኢትዮጵያ ናት ፣ ህዝብህ ኢትዮጵያውያን ናቸው ።
የኢትዮጵያ ሰራዊት እንጂ የዘረኞች የግል ዘበኛ አይደለህም ።
ህዝብህ ተዋርዷል ! ዜግነትህ ከእንስሳ ባነሰ በቁሻሻ ላይ ተጥሏል ። እናትህ ፣ አባትህ ፣ ወንድምህና እህትህ ከለላና መከታ አጥተው ደማቸው በየጐዳናው እየፈሰሰ ይገኛል። የህዝብህን ዋይታ ስማ !
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰሜን አሜሪካ

No comments:

Post a Comment