Thursday, November 28, 2013

ኢንቨስትመንት፤ “ከዝንጀሮ” ፖለቲካ ጋር ምን አንድ አደረጋቸው?

                   

በሕገ ወጥ መንገድ ሀገሬ ገብተዋል በማለት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ በስራ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ላይ በሳዑዲ አረቢያ ምድር ከተፈጸመ ሳምንት አለፈው። ሰብዓዊነት የጎደለው የሰው ህይወት ማጥፋት፣ የአካል ማጉደል እና የስነ ልቦና ድቀት በዜጎቻችን ላይ ሲፈጸም የዓለም ሕዝብን ያሳዘነ ተግባር ነበር። በተለይ የኢትዮጵያን መንግስት እና ሕዝብን ክፉኛ ያስቆጣ ፀያፍ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነበር። አሁንም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ በፈጸመው ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በይፋ ይቅርታ የጠየቀበት ሁኔታ አለመኖሩ የሚያስቆጭ ነው።
በዚህ ጽሁፍ ሳዑዲ አረቢያ ከሕዝቧ ሥነ-ሕዝብ (ዲሞግራፊ) አንፃር እየቀረበ ያለው የመከራከሪያ ነጥቦች ምን ይመስላሉ? የሰነድ አልባ ስደተኞች ፍልሰት መነሻዎች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ምን ይመስላሉ? የስደት የፖለቲካ ቀውሶች በምን መልኩ ሊታዩ ይገባል የሚለውን ለመመለስ ይሞክራል።
የሳዑዲ አረቢያ ዲሞግራፊ ምን ይመስላል?
እ.ኤ.አ. አፕሪል 2010 በሳዑዲ አረቢያ በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ አጠቃላይ የሕዝብ ብዛታቸው 27 ሚሊዮን 136 ሺህ 977 ነው። ከዚህ ውስጥ 18 ሚሊዮን 707 ሺህ 576 የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያላቸው ሲሆን 8 ሚሊዮን 429 ሺህ 401 የሳዑዲ ዜግነት የሌላቸው በሳዑዲ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።
tied
በእድሜ መዋቅር ሲተነተን፤ ከዜሮ እስከ አስራ አራት ዓመት፣ ሰላሳ ሁለት ነጥብ አራት ከመቶ (32.4%)፤ ከአስራ አምስት እስከ ስልሳ አራት አመት፣ ስልሳ አራት ነጥብ ስምንት ከመቶ (64.8%) እንዲሁም ከስልሳ አምስት ዓመት፣ በላይ ሁለት ነጥብ ስምንት ከመቶ (2.8%)ናቸው። የአጠቃላይ የሕዝቡ አማካኝ እድሜ 25.3 ነው። ከዚህ ውስጥ የወንዶች አማካኝ እድሜ 26.4 ሲሆን የሴቶች አማካኝ እድሜ 23.9 ነው። የሕዝብ እድገቱ በዓመት 1.536 ከመቶ ነው።
የመኖሪያ ዕድሜ ጣሪያቸው ሴቶች 75.9 ሲሆን የወንዶቹ 71.93 ናቸው። ሰማንያ አምስት በመቶ በከተማ ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ነው። የሕዝቡ ስብጥር ዘጠና ከመቶ (90%) አረብ ሲሆን የተቀረው አፍሮ አረብ ነው። በሃይማኖት ደረጃ ሰማንያ አምስት ከመቶ ሱኒ ሲሆኑ አስራ አምስት በመቶ የሚሆኑት ሺአት ናቸው። የሳዑዲ መንግስት በመካና መዲና ከተሞች ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች እንዲገቡ አይፈቅድም።
በሳዑዲ አረቢያ ግዛት ውስጥ በተለይ ከኤዢያ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዲሽ፣ ኢንዲኔዢያ እና ፊሊፒንስ በብዛት ይገኛሉ። ከምዕራቡ ዓለም በብዛት ባይሆኑም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ሲሆን አኗኗራቸው ግን በግል በተዘጋጁ ማረፊያዎች ውስጥ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ8 ሚሊዮን 429 ሺህ 401 (ከስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ሺ ሃያ ዘጠኝ አራት መቶ አንድ) የሳዑዲ ዜግነት ከሌላቸው ነዋሪዎች መካከል 350ሺ ኢትዮጵያዊያን በሕጋዊ መንገድ ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ ከ60 እስከ 80ሺ ሰነድ አልባ ስደተኛ (undocumented immigrant) ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እንደሚገኙ ይገመታል።
ከላይ ከሰፈረው የሳዑዲ አረቢያ ዲሞግራፊ አንፃር አብዛኛው የሳዑዲ አረቢያ ዜጋ ወጣቶች መሆናቸውን መረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ለእነዚህ ወጣቶች ስራ ማቅረብ ያቀተው ንጉሳዊ አገዛዝ እንደአማራጭ የወሰደው የስደተኛውን ቁጥር መቀነስ ነው። በተለይ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከሀገሩ በከፍተኛ ፍጥነት እያስወጣ ይገኛል። ይህ ተግባራቸው ከሉዐላዊነት አንፃር እንደመብት ቢወሰድም የስደተኞችን ሰብዓዊ ክብር መንካትና ለሕልፈት መዳረጋቸው ዓለም ዓቀፍ ውግዘት ያስከተለባቸው ተግባር ሆኖ አልፏል።
ሰነድ አልባ ስደተኞ ከኢኮኖሚ ሞዴል አንፃር
የስደተኞች አጠራር በራሱ አከራካሪ ነጥቦች አሉት። እነሱም ሰነድ አልባ ስደተኞች (undocumented immigrants) እና ሕገ ወጥ ስደተኞች (illegal immigrants) ሲሉ ይጠሯቸዋል። ሕገ ወጥ ስደተኞች ተብለው የሚጠሯቸው የአንድ ሀገር የደህንነት ሕግ በመተላለፍ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ በመሆናቸው ሲሆን፤ ሰነድ አልባ የሚባሉት ደግሞ በሰነድ አንድ ሀገር ውስጥ ገብተው ሆን ብለው ሰነዳቸውን በመጣል ወይም ከተሠጣቸው የጊዜ ገደብ በማሳለፍ ከሰነድ ውጪ በአንድ ሀገር ውስጥ በስደት ለመቀመጥ የሚሹትን የሚመለከት ነው።
ከኢኮኖሚ ሞዴል አንፃር፤ የኒዮ ክላሲካል ሞዴል ለስደት የሚሰጠው መሰረታዊ መነሻ ‘push-pull’ incentive በሚል ነው። ይህ ማለት ጥገኝነት የሚሰጠው ሀገር ውስጥ ያለውን የህይወት ደረጃ ከሚሰደዱበት ሀገር በአንፃራዊነት በመውሰድ የሚሞግቱበት አቀራረብ ነው። ለተሻለ ጥቅም ፍለጋ የሚደርግ ፍልሰት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ሌላው ነፃ የንግድ ቀጠና በምክንያትነት ያነሳል። ግሎባላይዜሽን የፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድል ዓለም ለነፃ የንግድ ስርዓት እንድትጋለጥ ዳርጓታል። በዚህም የተነሳ ይህ ነፃ የንግድ ስርዓት ለእርሻ እና ዕውቀት ለማይፈልጉ ትንንሽ ስራዎች ብዙ ሰዎች ከሀገር ወደ ሀገር እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗቸዋል። በተለይ የቀን ሠራተኛ የሚፈልጉ የበለጸጉ ሀገራት ይህን መሰል የሰው ኃይል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ በመፍጠር ከሀገር ወደሀገር ያስኮበልላሉ።
ሌላው መዋቅራዊ የበለፀጉ ሀገራት ፍላጎት አንድም የስደት ምንጭ ነው። “structural demand in developed states” በበለጸጉ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ለመስራት በማይፈልጓቸው ወይም በማይሰማሩበት የስራ ዘርፎች በማደግ ላይ ካሉ ሀገሮች በመውሰድ የሚፈልጉትን ስራዎች ያሰራሉ። ይህን የስራ ክፍተት ለመሙላት በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ስደትን በአማራጭነት ይወስዱታል።
ድህነትም ሌላው የስደት አንዱ ምንጭ ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ በሚፈጠር ስር የሰደደ ድህነት ዜጎች ወደ ሌላ ሀገር እንዲሰደዱ አንድ ምክንያት ነው። በተለይ ድህነት በተንሰራፋበት ሀገር ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ሲኖር ነገሮች ሁሉ ወደከፋ ሁኔታ ይቀየራሉ። ይህን መሰል ሁኔታን ለማምለጥ ስደት በአንድ አማራጭነት ይቀርባል። ሌላው የተበታተኑ ሰዎች ወይም ቤተሰቦች አብረው ለመኖር ካላቸው ፍላጎት (family reunification) የተነሳ በአንድ ለመሰብሰብ በሚያስችላቸው ሀገር ውስጥ ለመሰባሰብ በሚያደርጉት ጥረት ስደትን በአንድ አማራጭነት ይወስዱታል።
ሌላው ጦርነት በምክንያነት ይወሰዳል። በአንድ ሀገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድ ዜጎች ከጦርነት ለማምለጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይሰደዳሉ። በሚኖሩበት ሀገር በፖለቲካ ወይም በሃይማኖት ወይም በዘር ወይም በተለያዩ ችግሮች ለአደጋ ሲጋለጡ ዜጎች ስደትን በአንድ አማራጭነት ይወስዱታል። በዚህ አይነት ሁኔታ በአንድ ሀገር ውስጥ ሲሰደዱ ከስራ ፈላጊነት ወይም ከተራ ጥገኝነት ጥያቄ ባሻገር የፖለቲካ ጥገኝነት ያነሳሉ።
ሌላው ዜጎች፤ ዜግነታቸው በአምባገነን መንግስታት ሲነጠቅ ወይም ሲሻር ወደ ሌላ ሀገር ለመሰደድ ይገደዳሉ። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት በማይናመር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የሮሂነረገሬያ ብሔሮች በማይናመር መንግስት ሙሉ ለሙሉ ዜግነታቸው በመገፈፉ ሀገር አልባ አድርጐ በትኗቸዋል። በተለያዩ ቦታዎች ተሰደው ቀርተዋል።
የስደት የፖለቲካ ቀውሱ እንዴት ሊያዝ ይገባል?
ከላይ በአሃዝ እንደተቀመጠው በሳዑዲ አረቢያ 350ሺ ኢትዮጵያን በሕጋዊ መንገድ ተቀጥረው ስራቸውን እየሰሩ እንደሚገኙ ይገመታል። በሕገወጥ መንገድ አስከ 80ሺ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። እስከ ትላንት ድረስ ከ37ሺ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵዊያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። በቀጣይ የቀሩት ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሁን የተፈጠረው ችግር ለመፍታት የመጀመሪያው አማራጭ ሁሉንም ነገር በሰከነ መልኩ መመልከት እና አማራጮቹን ማየት ነው። ነገሮች ሁሉ ብስለት ከጎደለው እርምጃ ሊፀዱ ይገባል። ይህም ሲባል ሁሉም የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሕጋዊ መንገድ እየሰሩ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ ከማኛውም የስነ ልቦና እና አካላዊ ጥቃት የሚጠብቅ መሆን አለበት። እንደሙሴ ጊዜ አይን ያጣ አይኑን የሚባልበት ዘመን በዘመነ ስልጣኔ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።
በተለየ በሳዑዲ ዓረቢያ በወገኖቻችን ላይ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ በአገራችን የሚገኙ የሳዑዲ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድና በዚህም የገደለ፣ ይገደለ የሚለው የሀሙራቢ ሕግ እንዲተገበር የሚናፍቁ ወገኖች አልፎ አልፎም ቢሆን ኃላፊነት የጐደለውን ኀሳባቸውን በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ለማሰራጨት ሲሞክሩ መስተዋላቸው አልቀረም።
የክብር ዶ/ር ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ኢትዮጵያ የተወለዱባት፣ የተማሩባት አገራቸው መሆኗን እንኳን በመካድ ከሳዑዲ ችግር ጋር ነገሩን በማቆላለፍ በሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው የከፈቱትን የሥራ ዕድል ዘግተው እንዲወጡ የሚወተውቱ እንዳሉ ታዝበናል። ሼህ መሐመድ ሐብታቸውን በማፍሰስ ሥራ ከመፍጠር ባሻገር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በግብርና ታክስ መልክ ለአገሪቱ በማስገባት እያደረጉ ያሉትን አስተዋፅኦ እንኳን ግምት ውስጥ አለማስገባት መከራከሪያ ነጥባቸውን ምክንያት አልባ ማድረጉ አሻሚ አይደለም። የክብር ዶ/ር ሼህ መሐመድ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያላቸውን ጠቅላላ ኩባንያዎች ብዛት ከ70 በላይ የደረሰ ሲሆን፤ ጠቅላላ ኢንቨስትመንታቸውም ከአምስት ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ወገኖቻችን ከሳዑዲ ማባረር እኚህን ባለሃብት ከማባረር እኩል ለማየትና ለማነፃፀር መሞከርም መነሻው ከወገናዊነት የመነጨ ሳይሆን የታመቀ የራስ ፍላጐትን ለማስፈፀም ያስመስላል። አሁንም ቢሆን ተፈናቅለው ለመጡ ወገኖቻችን የክብር ዶ/ር ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ድጋፍ እንደማይለያቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህን ሊያደርጉ የሚችሉበት መሠረታዊ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በስሎ በሚገኝ አጀንዳ ላይ በመንጠላጠል የኢንቨስተሮችን ስም የፖለቲካ አጀንዳ ማወራረጃ ማድረግ ሃላፊነት የተሞላት ተግባር አድርጎ መቀበል አደገኛ ነው። ሁሌም የበሰለ ነገር ብቻ እንደ ዝንጀሮ ማደን ለማን እንደሚጠቅም አዳኙ ብቻ ነው የሚያውቀው። ሕዝባዊ መሰረት ጥሎ ገዢ ፓርቲን መታገል በራሱ አንድ መንገድ ሆኖ ሳለ ሀገራቸውን ጠቅመው ለብዙ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ የሀገሪቷ አንጡራ ሃብት የሆኑ ኢንቨስተርን የጦስ ዶሮ ለማድረግ መመሞከር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
ስለዚህም እንደዝንጀሮ ሁሌም የበሰለውን ከማደን ሕዝባዊ መሰረት ያለው የፖለቲካ ትግል ውስጥ መግባት አጥብቆ ይመከራል።
Source/http://ethioforum.org/

No comments:

Post a Comment