Tuesday, October 29, 2013

የአቶ መለስ ዜናዊ “ያልተገለጡ ገፆች”

    
220px-Meles_Zenawi_-_World_Economic_Forum_Annual_Meeting_2012

ከበትረ ያዕቆብ
ዉድ የሀገሬ ልጆች ከሁሉም በማስቀደም እንደምን ናችሁ ? ደህና ናችሁ ? 2006 እንዴት ይዟችኋል ? ስል የጠበቀ የወዳጅነት ሰላምታየን ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ እዚህ ላይ ይህ ሰዉ ምን ነካዉ!? ባልተለመደ መክኩ ሰላምታ አበዛሳ !? ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም አትፍረዱብኝ፡፡ “አሸባሪ ፣ አክራሪ ፣ ጅሀዳዊ ፣ ተለጣፊ ፣ ነጭ ለባሽ”… ወዘተ የሚል ቅፅል ስም ለሀገር ወዳድና ለመብታቸዉ መከበር ድምፃቸዉን ለሚያሰሙ ሁሉ በጅምላ እየተሰጠ ዜጎች በሀሰት በሚወነጀሉበት ሀገር ፤ በእያንዳንዷ ቀን እንደ መልካም ተግባር መሰል ዜጎችን ጠልፎ ለመጣል የተንኮል ወጥመድ ሲጠመድ በሚዋልበት ጊዜ ፣ ንፁህ ዜጎች በግዳጅ ያልፈፀሙትን ኃጢያት እንዲናዘዙ በሚገደዱበት ዘመን ፤ በልቶ ማደር ፍፁም በከበደበት በዚህ የጭንቅ ወቅት አጥብቆ ደህንነትን መጠየቁ ተገቢ ሆኖ ስለታየኝ ነዉ፡፡ እንደዉም ከዚያም በላይ ብዙ ብል እንኳ የሚበዛ አይመስለኝም፡፡ የሆነ ሆኖ ለሰላምታ ያህል ይህን ካልኩ ወደ ዋናዉ ርዕሰ ጉዳየ በቀጥታ ልለፍ፡፡
እንደሚታወቀዉ ምንም እንኳን የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሰራቸዉ በጎ ስራዎች ይልቅ ያጠፋዉ ለሚዛን የከበደ ቢሆንም ህልፈቱን ተከትሎ በፓርቲዉና በዙሪያዉ በተሰባሰቡ ጥቂትጥቅመኛ የህብረተሰብ ክፍሎች እስከዛሬ ያለ እረፍት እየተወደሰ ይገኛል፡፡ ጀግና ፣ የልማት አርበኛ ፣ የዲሞክራሲ ዘብ ፣ የአፍሪካና የዓለም ምርጥና ድንቅ ባለራዕይ ፣ አስታራቂ አባት ፣ የሰላም ሰባኪ ፣ ብልህ ሽማግሌ ፣ ጥበበኛ ፣ መለኛ ፣ የደሀ ተቆርቋሪ ፣ የፍትህ ሰዉ ፣ ፈላስፋ ….ብዙ ብዙ እየተባለና በርካታ ከንቱ ዉዳሴ እየተዥጎደጎደለት ነዉ፡፡ ሀሰተኛ ታሪክ እንደ ልብ ወለድ እየተፃፈለትና እየተተረከለትም ይገኛል፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ አንድ በየኢትዮጵያ ቴሌቭዥን “ያልተገለጡ ገፆች” በሚል በቀረበ ዘጋቢ ፊልም የሰዉየዉ ታሪክ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከምንኮራባቸዉ የዘመነ አድዋ ጀግኖች ታሪክ ጋር ተነፃፅሮ የቀረበ ሲሆን ፤ “ኢትዮጵያን በብቃትና በታማኝነት ያገለገለ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መሪ” ተብሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን አንድ ጉዳዮን የሚያዉቅ ወዳጄ ፊልሙ በተለያዩ የሀገር ዉስጥ ቋንቋዎች ሰፋ ባለ መልኩ ዳግም እየተዘጋጀ እንደሆነ ሹክ ብሎኛል፡፡ እንዳጫወተኝ እነዚህ ፊልሞች ለህዝብ እይታ በቅርቡ ይቀርባሉ፡፡
ኢህአዴግ/ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እዉነተኛ ታሪክ በማድበስበስ ህዝብን ለማሳሳት እያደረገ ያለዉ ሙከራ መጠነ ሰፊ ነዉ፡፡ ከቴሌቭዥንና ራዲዮ ባሻገር ከእዉነት የራቁ አሳሳች ታሪኮች በተለያዩ ድህረ ገፆች አማካኝነትም ለህዝብ እየቀረቡ ይገኛል፡፡ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪም በተለያዩ የዉጭ ቋንቋዎች መሰል ታሪኮች እንዲሰራጩ በመደረግ ላይ ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያየ አንድ የዉጭ ዜጋ የሆነ ወዳጄ በፕሮፖጋንዳዉ አለቅጥ መለጠጥና እየተሰራጩ ባሉት ታሪኮች ተደንቆ “መንግስታችሁ ስራ አጣ እንዴ!?..” ሲል በቅርቡ ተርቦኛል፡፡ አያይዞም “እንዴት ነዉ እኛ የማናዉቀዉ መለስ ዜናዊ የተባለ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበራችሁ?” ሲል ፈገግ አድርጎኛል፡፡ እንደማስበዉ ኢህአዴግ/ህወሓት ለምን የመለስን ታሪክ ማሰማመር እንደፈለገ ለብዙዎች ሚስጥር አይመስለኝም፡፡ እንደሚታወቀዉ ሰዉየዉ የዚህችን አገር የፖለቲካ መዘወሪያ ለ21 አመታት ያለተቀናቃኝ በጫንቃው የተሸከመና በሁሉም ነገር ላይ አራጊ ፈጣሪ የነበረ እንደመሆኑ የእርሱ ታሪክ የገዥዉ ፓርቲ እንዲሁም የሌሎች አመራሮች ታሪክ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነዉ፡፡ ስለሆነም ስልጣኑን ተቆጣጥሮ የቀጠለዉ ፓርቲና አመራር ለራሱ የተሻለ ገፅታ ለመስጠት የግድ የሰዉየዉን መልካም ያልሆነ ታሪክ ማስተካከል አለበት ማለት ነዉ፡፡ እንግዲህ አሁን እየተደረገ ያለዉም ይህ ይመስለኛል፡፡
ዉድ አንባብያን እንግዲህ እኔም ይህችን ፅሑፍ ለመፃፍ ምክንያት የሆነኝ ይህ ኢህአዴግ/ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እዉነተኛ ታሪክ በማድበስበስ ህዝብን ለማሳሳት እያደረገ ያለዉ ሰፊ ሙከራ ሲሆን ፤ እዉነቱ ይፋ ወጦ የህዝብ መወያያ ሊሆን ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የሰዉን እዉነተኛ ታሪክ (ያዉም ሀገርን ያህል ትልቅ ነገር ለረጅም ጊዜ የመራን ሰዉ) ሰርዞና ደልዞ ለህዝብ ማቅረብ በጣም አደገኛ ዉጤት የሚያስከትል ተግባር ነዉና፡፡ እንዲህ አይነት ተግባር ሰዎች በሰሯቸዉ ስህተቶች ተወቃሽ እንዳይሆኑና ትዉልድም ከታሪክ እንዳይማር የሚያደርግ ፣ ተተኪ ወጣቶች ትናንት አባቶቻቸዉ ባለፉበት የስህተት ጎዳና ደጋግመዉ እንዲያልፍ በር የሚከፍት ነዉ፡፡ ስለሆነም ሊደበቅ እየተሞከረ ያለዉን የአቶ መለስን ማንነት በዚች አጭር ፅሑፌ በትንሹም ቢሆን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ሰዉየዉ በስልጣን ዘመኑ በማናለብኝነት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈፀማቸዉን ወንጀሎች በመዘርዘር ለሕዝብ ዳኝነት እተወዋለሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ለግንዛቤ ያህል የሰዉየዉን የህይወት ታሪክ ጠቅለል ባለ መልኩ አስቀምጨ ልለፍ፡፡
እንደሚታወቀዉ የትናንቱ ለገሰ ዜናዊ የዛሬዉ አቶ መለስ ዜናዊ በወርሃ ግንቦት 1947 ዓ.ም ነበር በአድዋ ከተማ የተወለደዉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአድዋ ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጀኔራል ዉንጌት አጠናቋል፡፡ ከዚያም ከፍተኛ ዉጤት በማስመዝገብ አዲስ በበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ለማጥናት መግባት የቻለ ቢሆንም ብዙም ሳይገፉበት ነበር ወታደራዊዉን አምባገነን የደርግ ስርዓት ለመታገል ወደ በረሀ የወረደዉ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ያለዉ ጭቆና የብሔር ጭቆና ነዉ የሚል እምነት የነበረዉ ወጣቱ ታጋይ ፤ መፍትሄዉ ትግራይን ከቀረዉ የኢትዮጵያ ክፍል በመገንጠል የትግራይን ሪፐብሊክን መመስረት ነዉ የሚል ፅኑ እምነት ነበረዉ፡፡
በትግሉ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ በተለያዩ ከፍተኛ የሀላፊነት ደረጃዎች ህወሀትን በሙሉ አቅሙ ያገለገለ ሲሆን ፤ በድርጅቱ ዉስጥ ከነበረዉ ቁልፍ ሚና አኳያ የትግሉ አርክቴክት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አቶ መለስ በ1983 ትግሉ በድል ሲጠናቀቅ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሆን የቻለ ሲሆን ፤ ቆይቶም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሸጋገር እስከ እልፈተ ሞቱ ሀገሪቱን ያለአንዳች ተቀናቃኝ በማንአለብኝነት መምራት ችሏል፡፡
1. የኤርትራ መገንጠል
አቶ መለስ ዜናዊ 21 ዓመት መዝለቅ በቻለዉ ያስተዳደር ዘመኑ በሀገርና ህዝብ ላይ ከባድ ወንጀሎች ፈፅሟል ፤ እነርሱም በተለያዩ የታሪክ መፅሐፍት ላይ በዝርዝር ተጠቅሰዉ ይገኛል፡፡ ሰዉየዉ ከፈፀማቸዉ እነዚህ ወንጀሎች መካከል በዋነኝነት ተጠቃሹና በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥም ሁሌም የሚታወስበት በግብፅና በአንዳንድ የአረብ ሀገራት አጋዥነት ኤርትራን እንድትገነጠል ማድረጉ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ ምንም እንኳን የበርካታ የህወሀት አመራሮች እጅ በዚህ ወንጀል ዉስጥ ቢኖርበትም የአንበሳዉን ሚና የተጫወተዉ እሱ ነበር ለማለት የሚያስደፍሩ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡
በርካታ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት የኤርትራ መገንጠል ህግን እና ህጋዊ አካሄድን ያልተከተለ ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያን ጥቅም ከግምት ዉስጥ ያላስገባ ፤ የአረቦችን ፍላጎትና የኢሳያስን ገደብ የለሽ የስልጣን ጥም ለማሟላት ሲባል ብቻ ሆን ተብሎ የተደረገ ነበር፡፡ በወቅቱ በርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን (ለቁጥር የሚታክቱ ኤርትራዉያንም ጭምር) ድርጊቱን በመቃወም ድምፃቸዉን ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ፤ ለነርሱ የአቶ መለስ ምላሽ ስድብ ነበር፡፡
በትግል ወቅት አቶ መለስ የኤርትራ ባለቤት ነን ከሚሉት የሻብያ መሪዎች በላይ ስለኤርትራ መገንጠል ያቀነቅን ነበር፡፡ ተስፋ ወደ መቁረጡ በተቃረቡበት ወቅትም “አይዟችሁ ኤርትራን በቅርቡ ከኢትዮጵያ ትገነጥላላችሁ ፣ በርቱ” እያለ ከመደገፉ ባሻገር ትግላቸዉን የሚያግዝ አስትራቴጅክ መፅሐፍም ፅፎ አበርክቶላቸዋል፡፡ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ከተገነጠለች በኋላም አለም እንደ ሀገር ይቀበላት ዘንድ እንደ መለስ ወዲያ ወዲህ ያለ የለም ማለት ይቻላል–ኢሳያስ አፈወርቂም ቢሆን እንኳ፡፡ በዚህም ምክንያት የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በነገሩ ግራ እስከመጋባት ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንዳንዶችም የሰዉየዉን ኢትዮጵያዊነት እስከመጠራጠር ደርሰዉ ነበር፡፡
2. የኢትዮጵያ የባሕር በር (አሰብ)
አሰብ በታሪክና በህግ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የበሀር በር የመሆኗ ጉዳይ አሌ የማይባል እዉነት ነዉ፡፡ ይህንንም በርካታ ምሁራን ሰነድ እያጣቀሱ ደግመዉ ደጋግመዉ በግልፅ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ ዜናዊ እዉነቱን እያወቀ (ለእርሱ ብቻ ግልፅ በሆነ ምክንያት) ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ሀብታችንን ከእጃችን አይናችን እያየ እንዲያመልጥ አድርጓል፡፡ ይህም የብዙ ኢትዮጵያዉያንን ልብ የሰበረና እስካሁን እንቆቅልሹ ያልተፈታ ጉዳይ ነዉ፡፡
አቶ መለስ አሰብን በተመለከተ ጥፋት ያጠፋዉ ከአንድም ሁለት ሶስቴ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ጥፋት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ወደቡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲጠቃለል ማድረግ እየተቻለ (ህጉም እየፈቀደልን) ለኤርትራ መሰጠቱ ነዉ፡፡ በወቅቱ ለምን የሚል ተቃዉሞ ሲነሳ አቶ መለስ ይግረማችሁ ብሎ ለኤርትራ ሽንጡን ገትሮ በመከራከር ኢትዮጵያ ጥንታዊ የባህር በሯን በተመለከተ አንድም ጥያቄ እንዳታነሳ አድርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1989ዓ.ም የኤርትራን ዉረራ ተከትሎ ኢትዮጵያ አሰብን በእጇ የምታስገባበት ሌላ እድል ተፈጠሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያላደላት ሀገራችን የዚያን ሁሉ ልጆቿን ህይወት ገብራ ጦርነቱን በድል አድራጊነት ብትወጣም በአቶ መለስ ትዕዛዝ ወደ አሰብ ድርሽ እንዳትል ተደርጓል፡፡ ከዚህም በኋላ የአልጀርስን ድርድር ተከትሎ ብዙ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ተስፋ ሳይቆርጡ መንግስት ወደቡን በተመለከተ ለአደራዳሪዉ አካል ጥያቄ እንዲያነሳ ከመማፀን ባሻገር ለድርድሩ የሚረዱ ጠቃሚ የታሪክ ፣ የህግና የፖለቲካ መረጃዎችን በዝርዝር ማቅረብ ችለዉ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ የፈየደዉ አልነበረም፡፡ የሆነዉ የብዙዎችን አንገት ያስደፋ ነበር፡፡ አቶ መለስና ግብር አበሮቻቸዉ ከኤርትራ ጎን ቆመዉ ለኤርትራ ጥቅም በመከራከር በገንዘብ የማይተመነዉን እጅግ ጠቃሚ የሀገር ሀብት ለኤርትራ አስረክበዉ ተመለሱ፡፡ እነዚህን በሀገርና ወገን ላይ የተፈፀሙ ክህደቶችና ወንጀሎችን በተመለከተ ዶክተር ያዕቆብ አሰብ የማናት በተሰኘዉ መፅሐፋቸዉ ላይ በደንብ አንድ ባንድ ያብራሩዋቸዉ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ማግኘት የሚፈልግ ሰዉ መፅሐፉን ማንበብ ይቻላል፡፡
ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአለም ወደብ ከሌላቸዉ ጥቂት ሀገራት ዉስጥ ትልቋና ብዙ ህዝብ ያላት ስትሆን ፤ በየቀኑ ከ4 ሚሊዩን ዶላር በላይ ለጅቡቲ የወደብ ክራይ እንድትከፍል ተገዳለች፡፡ ይህም የሁላችንን ኪስ የሚፈታተን ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደብ አልባ መሆናችን ሙሉ በሙሉ በሌላ አገር ላይ ጥገኛ እንድንሆን ምክንያት የሆነ ሲሆን ፤ የደህንነት አደጋም ጋርጦብናል፡፡ የአለማችን ዋና እስትራቴጅክ አካባቢ ከሆነዉ የቀይ ባህር አካባቢ መራቃችንን ተከትሎም በዲፕሎማሲዉ መስክ የነበረን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እጅግ ተዳክሟል፡፡
3. የባድመ ጦርነት
ሻቢያ በ1989 ዓ.ም በድፍረት ድንበር ተሻግሮ ኢትዮጵያን መዉረሩ በተሰማ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ነበር በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵዉያን ለነፍሳቸዉ ሳይሳሱ የአገራቸዉን ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ ጦር ግንባር የተመሙት፡፡ ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጦርነቱን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን እግረ መንገዷንም ሌሎች ጥቅሞቿን ታስጠብቃለች የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ በተለይም አሰብ እንደገና በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ የመግባቱ ጉዳይ ላይ ማንም አልተጠራጠረም፡፡ ሆኖም ግን በጣም ዘግናኝ ከሆነ ጦርነት በኋላ የመከላከያ ሰራዊታችን ወደ መሀል ኤርትራ መገስገስ ሲጀምር አቶ መለስ ዜናዊ በአስቸኳይ እንዲመለስ ትዕዛዝ በመስጠት ለወገኖቻችን ህይዎት መጥፋት ምክንያት የሆነዉን የሻብያ መንግስት ታደገ ፤ የዚያን ሁሉ ወጣት ኢትዮጵያዊ ህይወት ትርጉም አሳጣ ፣ ተሳለቀበት፡፡
በዚህም ያልተገታዉ አቶ መለስ ዜናዊ በአልጀርሱ ድርድር ላይ ሌላ አሳፋሪ ተግባር ፈፀመ፡፡ ተገቢነት የሌላቸዉና ፍርስ የሆኑ የ1900 እና የ1902 የቅኝ ግዛት ዉሎችን ለድርድር በመምረጥ የሻቢያን ህልም እዉን አደረገ፡፡ የዚያ ሁሉ ወጣት ደም የፈሰሰለትን ባድሜን ፣ ኢሮብን እና ፆረናን ለሻቢያ አስረክቦ በዶ እጁን ተመለሰ፡፡
4. የመተማ መሬት
አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣን ዘመኑ በሀገር ላይ ከፈፀማቸዉ ወንጀሎች መካከል አንዱና የቅርብ ጊዜዉ የመተማ ጉዳይ ነዉ፡፡ ሰዉየዉ የተጠናወተዉ ሀገርን እየቆረሱ ለባዕዳን የመስጠት አባዜዉ አለቀዉ ብሎ ሰፊ የመተማን ለም መሬት ከኢትዮጵያ ህዝብ እዉቅና ዉጭ ሸንሽኖ ለሱዳን ያስረከበ ሲሆን ፤ ይህንን ተግባሩን በተቃዎሙት የአካባቢዉ አርሶ አደሮች ላይም ብዙ በደል ፈፅሟል፡፡ በቅርብ የወጡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ሰዓት መንግስት ለህዝብ በግልፅ ባላሳወቀበት ሁኔታ ኮሚቴ በማቋቋም አዲሱን ድንበር የማካለል ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
5. ታሪክ ማጠልሸት
አቶ መለስ ዜናዊ ከሚታወስባቸዉ ተግባራቶቹ መካከል ከታሪክ ጋር የነበረዉ መረን አልባ ቅራኔ ነዉ፡፡ ይህ ሰዉ የ5 ሽህ ዓመት ታሪክ ባለቤት የሆነችዉን ሀገራችንን የመቶ ዓመት ዕድሜ ባለቤት ናት ከማለት ጀምሮ በርካታ የታሪክ ክህደት ፈፅሟል፡፡ ለእርሱ ሰንካላ የፖለቲካ ፍልስፍናና እረጅም የስልጣን እድሜ ያመቸዉ ዘንድ የፈለገዉን ታሪክ ሰርዟል ፣ ደልዟል፡፡ ያሻዉን ታሪካችን ነዉ ሲል ተከራክሯል፡፡ የአክሱም ታሪክ ለወላይታዉ ምኑ ነዉ …ወዘተ ሲል በሀገርና በህዝብ ላይ ቀልዷል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአለማችን ከሚገኙ ጥቂት ቀደምት ታሪክ ካላቸዉ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት የምትጠቀስ ናት፡፡ ከዚህም ባለፈ የሰዉ ልጅ መገኛ መሆኗ ልዩ ያደርጋታል፡፡ የሚገርመዉ ይህን ታሪካችንን በርካታ ምሁራን የመሰከሩለትና በምርምር የተረጋገጠ በመሆኑ ጠላቶቻችን እንኳን የሚቀበሉት ነዉ፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ እዉነት ለአቶ መለስ አልሰራም፡፡
6. ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማዳከም
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፡፡ እነዚህ የተለያየ ባህል ፣ ቋንቋና ሐይማኖት ያላቸዉ ህዝቦች ለበርካታ ዘመናት በአብሮነት ተከባብረዉና ተዋደዉ ኖረዋል፡፡ በአንድነት የደስታ ዘመናትን እንዳሳለፉ ሁሉ በርካታ አሳዛኝ ጊዚያትንም ተጋርተዋል፡፡ ተጋብተዉ ወልደዋል ፣ ከብደዋል፡፡ አብረዉ የዉጭ ጠላትን በደምና ባጥንታቸዉ ተከላክለዋል ፤ ደማቅ ታሪኮችን ሰርተዋል፡፡ ሆኖም የአቶ መለስን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ይህ ኢትዮጵያዊ አንድነት ችግር ላይ የወደቀ ሲሆን ፤ ዛሬ እየተባባሰ መጦ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ደህንነት ላይ ጥላ አጥልቶበታል፡፡
አቶ መለስ ሲመቸዉ አንዱን ብሔር ጨቋኝ አንዱን ተጨቋኝ አድርጎ በማቅረብ እንዲሁም አንዳንድ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የተከሰቱ ያለፉ አለመግባባቶችን እየነቃቀሰ ህዝቦች በተለመደዉ አብሮነት እንዳይቀጥሉ በርካታ ጥረት አድርጓል፡፡ አንድ የሚያደርጉንን የጋራ እሴቶቻችንን በማደብዘዝ በመሀከላችን ልዩነት እንዲፈጠር ተግቶ ሰርቷል፡፡ ይህንን ሁሉ ያደርግ የነበረዉ ደግሞ ያን የሚሳሳለትን ስልጣን ለማስጠበቅ ብቻ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሀገሪቱ ፍቱን ነዉ ሲል የፈለሰፈዉ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝምም ቢሆን ከመስማማት ይልቅ አለመስማማትን እያጎለበተና ሌላ መዘዝ እያመጣብን ይገኛል፡፡
7. ምርጫ 97
እንደሚታወቀዉ ህወሀት/ኢህአዴግ ወደስልጣን ከመጣበት 1983ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያዉያን በአቶ መለስ ትእዛዝ በግፍ ተጨፍጭፈዋል ፣ በወጡበት ቀርተዋል፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ተደብድበዋል ፣ ታስረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል በጋምቤላና በሶማሊያ ክልል የተፈፀሙትን መመልከት በቂ ነዉ፡፡
ምርጫ 97ን ተከትሎ ድምፃችን ይከበር በሚል አደባባይ በወጡ ንፁሐን ዜጎች ላይ የተፈፀመዉ ዘግናኝ ወንጀል አንዱ በአቶ መለስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተፈፀመ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነዉ፡፡ በወቅቱ ስልጣኔ ለምን ተነቀነቀ በሚል አዉሬ የሆነዉ አቶ መለስ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በእርሱ እዝ ስር እንዲሆን በማድረግ በሰጠዉ መመሪያ መሰረት በአዲስ አበባ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ፣ ህፃናትና አዛዉንት የጥይት ሲሳይ ሆነዋል፡፡
እንደ ማጠቃለያ
አቶ መለስ ዜናዊ በሀገርና ህዝብ ላይ የፈፀመዉን ወንጀል ዘርዝሮ ለመጨረስ ይከብዳል፡፡ ሀገርን ከመካድና ከመናድ ባሻገር በርካታ ግፍ ፈፅሟል፡፡ ዜጎችን አስጨፍጭፏል ፤ በግፍ ንፁሀንን በእስር ቤት አሳጉሯል ፤ ምስኪን ደሀ ቤተሰቦችን ከቀያቸዉ አስፈናቅሏል ፤ የሀገርና የህዝብን ሀብት አስመዝብሯል ፣ መዝብሯል፡፡ እንግዲህ ይህ ነዉ የአቶ መለስ ዜናዊ ትክክለኛ ማንነት ፤ ይህ ነዉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአፍታም ሊዘነጋዉ የማይገባዉ ነጥብ፡፡

No comments:

Post a Comment