Monday, July 8, 2013

በዘር እንዳትመነዝሩኝ (ከዘካሪያስ አሳዬ)


የጓደኛችን ቋንቋው፣ ዘሩ፣ ሃይማኖቱና ፖለቲካዊ አመለካከቱ ምን ያደርግልሃል? ደጋ ውስጥ ቢፈጠር ቆላ፣ ወይናደጋ ቢወለድ ተራራ ጫፍ ላይ፤ አንዴ ተፈጥረናልና ሰው ስለመሆናችን ብቻ ማሰቡ ይበልጣል።
Zekarias Asaye, Ethiopian blogger in Norway
ዘካሪያስ አሳዬ
የዘር አድልዎ ፖሊሲ ምልክቶቹን ፣ በሃገራችን ፣ በአንዳንድ በተቃዋሚው አካባቢ ባሉም ምሁራንም ጭምር ፣ በአንዳንድ ድህረ-ገጾችና የፓልቶክ የመወያያ ክፍሎች ሲሰሙና ፣ ሲንጸባረቁ ያየሁትን አደገኛ አዝማሚያ፣ ስጋቴን ለወገኖቼ ለማካፈል እንጂ ፣ ባለሙያው ሆኜ አንባቢያንን ለማስተማር አይደለም፡፡
የናዚዝም ፣ ወይም እራሳቸውን የአርያን ማስተር ሬስ (Aryan master race ) ብለው የሚጠሩት ዘርኞች ዋና መለያ አካሄዳቸው ፣ የሌላውን ሰው ሕልውና መካድ ፣ በሕዝብ መሃል ያለውን ታሪካዊ ትስስርን አለመቀበል ፣ ከአንድነቱ ይልቅ በልዩነቱ ላይ ማተኮር ፣ በሕዝቦች መሃል አጥር ማጠር ፣ የግንኙነቱን ድልድይ ማፍረስ ፣ በሰዎች ልጆች መሃከል ሰፊ የማበላለጥና ፣ ሚዛኑ የተንሻፈፈና ቅጥ ያጣ የወገንተኛነት አካሄድ ማስፋፋት ነው ፡፡
ይህ አይነት ግልጽ የዘረኛነት አካሄድ ፣ ትላንት የወያኔው መሪ ፣ “ ከወርቅ ዘር በመወለዴ እኮራለሁ “ ያሉን ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የማበላለጥ ዘረኛ ዓላማ ስንቃወም ሰንብተን ፣ ዛሬ ደግሞ ፣ አውቀው ሆነ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ሳያጤኑት ፣ እንደዚህ አይነት ከፋፋይ ፣ የፋሺስት ዘረኛ ፖለቲካዊ ቋዋንቋ ማሰማት የጀመሩትን ፣ ቁጭ ብሎ ማዳመጥ እየተለመደ መምጣት ጀምሮዋል ፡፡
ዛሬ ከአንዳንድ ተቃውሞን እናስተባብራለን ከሚሉ ፣ ሊያስወግዱ ከሚፈልጉት ስርዓት ባልተለየ መንገድ እየተጓዙ ፣ ቆመንለታል የሚሉት ሕዝብ ያልጠየቃቸውን ፣ እሱ ከሌላው የምበልጥ ነኝ ያላለውን ፣ እሱ ያልፈለገውን በስሙ እንወክለዋለን እያሉ ፣ በሕዝባችን መሃል ፣ ጥላቻንና ፣ መራራቅን የሚጋብዝ ፣ አላስፈላጊ ማበላለጥ ፣ ባልተለመደ መልኩ ሲካሄድ ስንሰማ ፣ ከማሳዘኑም በላይ እያሰጋን ሄድዋል ፡፡
በአንድ የታሪክ ሂደት አስገዳጅነት በተከሰተ ሁኔታም ይሁን ፣ ተፈጥሮ በቸረው ልዩነት ፣ እንደ ጌጣችን ልናየው ፣ የሚገባን ታሪካችንን ፣ አንዱ ከሌላው ፣ የተመረጠ ፣ የተሻለ ፣ ቆንጆ ፣ ጸጉረ ዞማ ፣ አፍንጫ ሰልካካ ፣ ጎበዝ ተዋጊ ፣ ታላቅ ሕዝብ ፣ ወርቅ ሕዝብ …….ወዘተ የመሳሰሉ ፣ በጣም ኋላ ቀር የሆኑ ዘረኛ ፣ ቅጽላዊ ማበላለጦችን በሕዝባችን መሃል ፣ በአለንበት በሃያ አንደኛው ዘመን ማዳመጡ ጆሮ ያሳምማል ፤ አንገት ያስደፋል ፣ ተስፋ ያጨልማል ፡፡ ይህ አይነት አላስፈላጊ ወገንተኝነት ፣ ቆመንለታል ለሚሉት ክፍል ከሌላው ወገኑ እንዲነጠልና ፣ የጥቃት ኢላማ እንዲሆን ከመርዳት ባሻገር የሚጠቅመው ነገር የለም ፡፡
በእርግጥ በማንኛውም ወገናችን ላይ በተናጠል የሚደርሰው ፣ በጎም ይሁን ጉዳት የጋራችን መሆኑን መቀበል አለብን፡፡ የማንኛውም ክፍል ወጋናችን በተናጠልና በተራ በሚደርስበት ፣ መሰቃየት ፣ መታሰር፣ መፈናቀል ፣ መጋዝ ፣ መዋረድ ፣ ለሌላውም ህመም ሆኖ ሲሰማው ኖርዋል ፡፡ ለመፍትሄውም አብሮ ተዋድቋል ፣ ታግሏል ፣ አብሮ በደም የተሳሰረ አንድነት ገንብቷል ፡፡ ያም እየተደናቀፈም ቢሆን ወደፊት ይቀጥላል ፡፡
በተለምዶ ፣ በአባቴ የትውልድ ሃረጌ የዚህኛው ዘር ነኝ ፣ በእናቴ የዚያኛው የእከሌ ወገን ነኝ እንደምንለው ሁሉ ፣ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን ከአማራውም ፣ ከኦሮሞውም ፣ ከሃዲያውም ከሁሉም የሐገራችን ሕዝብ ጋር ትስስር ስላለን ፣ የትኛውም ወገናችን ፣ በተናጠልም ይሁን በጋራ ለሚደርስባቸው ጥቃት፣ የራሳችን ጥቃት መሆኑ ተሰምቶን፣ ከማንኛውም የተገፋ ወገናችን ጎን ቆመን ጥቃቱን በጋራ ልንከላከል ይገባል ፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ሁላችንንም የሚያገናኝ ማእከል ነው ካልን ? እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ዶርዜነት አለብኝ፣ በኢትዮጵያዊነቴ አፋርነት አለብኝ ፣ በኢትዮጵያዊነቴ አማራነት ፣ በኢትዮጵያዊነቴ ኦሮሞነት ….ወዘተ አለብኝ ብለን አምነን ፣ በተግባር በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ አብረን ተደጋግፈን ስንቆም ነው ፣ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነታችንን በተግባር የምናስመሰክረው፡፡
አንዳንዴ ሰዎች እራሳቸው ባልመረጡት መንገድ እንዲሄዱ ፣ ስለሚገፉ ፣ ሰዎች በተናጠል ለሚደርስባቸው ጥቃት እራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ፣ የሌላውን ህልውናና ፣ መብት እስካልተጋፉና ፣ ላጠቃላዩ ሕብረት ችግር እስካልሆኑ ድረስ ፣ በሚያመቻቸው መንገድ የመታገል መብታቸውን መቀበል ብቻ ሳይሆን ማገዝና ፣ ከጎናቸው ሆኖ ብቻቸውን አለመሆናቸውን ማሳየት ወገናዊ ግዴታ ነው ፡፡
ይህ አይነት ወገናዊ ትብብር ፣ ለየብቻ መፍትሄ ፍለጋን ለማበረታት ሳይሆን ፣ የላላውን ለማጥበቅ ፣ የራቀውን ልብ ለማቅረብ ፣ የተጎዳውን መንፈስ ለመጠገን ፣ ይበልጥ የሚያስተሳስረን ፣ በሂደት የገነባነውን በጎ ትሪካችንን የሚንከባከብና ፣ የማይጠቅመንን አስወግደን ለሃገራችን አንድነትና ፣ ለሕዝቦቿ እኩልነት ለሚደረገው ትግል ጽኑ የአንድነት መሰረት እንደሚገነባ በማመን ነው ፡፡
ለሰባዊ መብቶች (human rights)መቅደም ስንታገል ፣ ዘር ፣ ሃይማኖት ፣ ቀለም ፣ ጾታ ፣ ታላቅነት ፣ ጀግነት ፣ የመሳሰሉትን “እንደ መለኪያ “ አስቀምጠን ሳይሆን ፣ ወይም በቡድንና ፣ በግለሰብ የተደራጁና ያልተደራጁ በሚል ስሌት ከፋፍለን ሳይሆን ፣ በዚህ ምድር ላይ ለተፈጠረ ፣ ለሰው ልጅ የተሰጠው ተፈጥሮዋዊ መብቱ የተጣሰ በመሆኑ ብቻ ነው ፡፡
በሌላው ወገናችን ላይ የሚደርሰው፣ እስር፣ እንግልት ፣ መፈናቀል ፣ የሚሰማን ፣ የእኛ በምንለው ላይ ብቻ ሲደርስ ከሆነ ? የሌላው ወገናችን ስቃይና መከራ ፣ እንደራሳችን የማይሰማን ከሆነ ? ሕዝባችንን ያስተሳሰረውን ሰንሰለት እየበጣጠስን ፣ ለጎጣችን ፣ ለመንደራችን ፣ ብቻ የምንጨነቅ ከሆነ፣ በእውነት እንደ ናዚዎቹ ፣ በዘረኞች በሽታ እንደተለከፍን መቀበል አለብን ፡፡
ትላንት ያልተመችን ፣ ሌሎች ብቻቸውን የሄዱበት ጸረ አንድነት የጥፋት መንገድ ነበር ብለን አሁንም የምናምን ከሆነ ? ፣ ይህንን አካሄድ እኛ ስንደግመው ልክ የሚሆንበት መንገድ ስለሌለ ፣ የምንከተለው የትግል አቅጣጫ ፣ ለጋራ ችግራችን ወደ የጋራ መፍትሄ የሚያደርሰ መንገድ የሚያመቻችልን እቅድ ስንነድፍ ነው ፡፡ በጋራ ታግለን ፣ የምናመጣው ሰላም ፣ ዕድገትና ፣ ፍትህ የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የብዙውን ፣ አለ የምንላቸውን ችግሮቻችንን መፍቻ ቁልፍ ስለሆነ ፣ በየትኛውም አቅጣጫ የምናደርገው ግፊት ፣ ወደ እዚህ አቅጣጫ አቅርቦ የሚያሰባስበን መሆን ይኖርበታል፡፡
የሕዝባችን ጥያቄም ባይሆን ፣ ለረዥም ጊዜ ፊደል በቆጠረው ጎጠኛ (elite) እንወክለዋለን ብለው ወደ ሕዝባችን በሚገፉት አጀንዳ የተጎዳው አንድነታችንን ለመጠገን ፣ በተመሳሳይ መንገድ በእልህ መሄድ ፣ እነሱን መተባበር እንጂ ለሃገር እንደማይጠቅም መታወቅ አለበት ፡፡ በእልህ የሚወሰድ አቅዋም ፣ ለማንኛችንም የሚበጅ አይሆንም ፣ ይበታትነናል፣ በዚህ ደግሞ ማንም አይጠቀምም ፡፡ በሳይንስ እንደተረጋገጠው ፣ ስሜታዊነት ሚዛኑ በዝቶ ካጋደለ ፣ ዕውቀት ወይም ጥበብን የያዘው የአዕምሮ ክፍላችን ስራውን ይቀንሳ፡፡(when emotions is high intelligence is low) የዚህም ውጤት የሚያስከትለውን አደጋ ለማስረዳት አንባቢዎቼን መናቅ ይሆንብኛል ፡፡
ወደድንም ጠላንም የመገንጠልን ዓላማ በሚገፉ ጎጠኛ ኢሊቶችና ፣ በሥርዓቱ ተባባሪነት ይገፋ የነበርው የዘረኞች ዓላማ ፣ ወደ ሕዝባችን እየገባ ፣ ከምንገምተው በላይ እየተራባ ፣ በብሔራዊ አንደንታችን ላይ አደጋ እንዳንዣበበ ያስተዋሉት ጥቂቶች ናቸው ፡፡ የአንድነቱ ደጋፊዎች ነን ከምንል ፣ የጎጥ ፖለቲካ አራማጆች በተሻለ እይተደራጁ ፣ እየተሰባሰቡ እንደሆን መካድ የዋህነት ነው ፡፡
ሕዝብ ደግሞ ፣ መሪ እስከሌለውና ፣ አደራጅቶ ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚመራው እስከሌለው ድረስ፣ ቁጥሩ ስለበዛ ምንም ሊሰራ አይችልም ፡፡ በተግባር የምናየውም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝባችን ብቻውን እንደተውት ነው፡፡ በዚህ ላይ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ በቀጣይነት በሚፈስለት ጥንፈኛ አመለካከት አይሳሳትም ማለት አይቻልም ፡፡ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚ ፣ ሕዝብ የተሳሳተ አቅዋም ሊወስድ እንደሚችል በተደጋጋሚ ታይቷል ፡፡
በእነዚህ ጎጠኛ አስተሳሰብ ባላቸው የሚገፋውን የዘረኝነት ጥፋት ፣ እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ አቅዋም እንደሆነ አድርገን ተስፋ ቆርጠን ፣ በወገኖቻችን ላይ ዕምነት ማጣት የለብንም ፡፡ እንደዛ ማመን የጀመርን ከሆነ ፣ ለጎጠኞች እጅ እየሰጠን እንደሆነና ፣ እኛም የችግሩ ተባባሪ መሆን እንደጀመርን ማመን አለብን ፡፡ በሕዝባችን የሚቀርበው መሰረታዊ ጥያቄና ፣ የተማረው (ኢሊት) በሚፈጥረው ችግር መሃከል ያለውን ልዩነት ማስመር ካልቻልንና ፣ ሁለቱን ካምታታን ፣ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እንዳይወስደን መጠንቀቅ አለብን ፡፡ እየመጣ ያለውን ችግር አቃለንም ሆነ አጋነን ሳናየው ፣ እንደ ሁኔታው ቅደም ተከተል ተደራጅተን ልንታገለው ይገባል፡፡
ያለው አገዛዝ ፣ የጎጠኞችን ፍላጎት በእጥፍ አጩሆ የሚያደነቁረን እንጂ ፣ የአብዛኛውን ፣ አንድነቱን የሚፈልገው ሕዝባችን ድምጽ ስለታፈነ ፣ ባለመስማታችን ልንጠራጠር አይገባም ፡፡ የሕዝባችንን እውነተኛ ፍላጎት በተለያየ አጋጣሚ ቀዳዳ ሲያገኝ አሳይቶናልና ፣ አሁንም ምንም የተለወጠለት ዓዲስ ነገር ስለሌለ ትግሉ ይቀጥላል ፡፡ እስሩ ፣ እመቃው ፣ ችግሩ ፣ ስደቱ ፣ እንደቀጠለ ሆኖ ፣ አሁንም አብዛኛውን ክፍል ያገለለ አንባገነናዊ ሥርዓት በሰፈነበት ሁኔታ፣ ከመታገል ሰንፈን ፣ እንዲሆንልን የምንመኘውን ፣ ከላይ እንዲፈቀድልን በተስፋ ደጅ እየጠናን ተጃጅለል ማጃጃሉ አይጠቅመንም ፡፡
ካለፈው እንኳን የቅርብ ታሪካችን ፣ ይህ ሥርዓት ሁሌ ግፊት በሚደርስበት ወቅት ፣ “ለመደራደር “ በሚል ስንት አዛውንቶች ፣ ስልጣን እንቁልልጭ እያላቸው ፣ ሰነድ እያስፈረመ ፣ ከሕዝብ አጋጭቶ ሁኔታውን ፣ በግልባጩ ለራሱ እንደተጠቀመበት መርሳት፣ ትልቅ የፖለቲካ የዋህነት ነው ፡፡ መደራደር የሚባል እንኳን ነገር ቢኖር ፣ ትግልን ሳያቀዘቅዙ ፣ ትጥቅን ሳያላሉ ፣ በስልት ግፊት በማሳደር እንጂ ፣ የገነባነውን የትግል ስሜት እራሳችን ከናድንለት ቦኋላ ፣ተርግጦ መገዛት እንጂ ፣ አገዛዙስ ለምንድነው ለመደራደር የሚፈልገው? ለዛውም እኛው መላ እየመታንላቸውና ፣ እየተረጎምንላቸው እንጂ ፣ ከእነሱ የሰማነው ምንም ተስፋ የለም ፡፡
እንዲያውም አገዛዙ ከሃገራችን አልፎ እጁን አርዝሞ ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በየስርቻው ለአድር ባዮች እየዘራ፣ በጅት መድቦ፣ ያሰማራቸውን የውሸት ተቃዋሚዎች ፣ “በየስብስቡና፣ በየሕብረቱ “ ውስጥ እየጠቀጠቀ አመራሩን በራሱ ሰርጎ ገቦች ሊያሲዝና ፣ መድረኩን ሊያጣብብ ሲሞክር እየታዘብን ነው ፡፡ ይህ ቀድመው መድረኩን ይዘው ሊሰራ ባማይችል መንገድ ጀምረው ካኮላሹት ቦኋላ ፣ ሰዉ ተስፋ ቆርጦ ሁለተኛ የእውነቱንም እንዳይሞክር ፣ ወይም በእውነቱ እና እነሱ በፈጠሩት መሃከል የተምታታ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ነው ፡፡
እነዚህ ሰረገው የሚያስገብዋቸው የሰለጠኑ አደናባሪዎች ፣ መንገድ ለይ እንደተንጠለጠለ የሕዝብ ቴሌፎን ፣ ገንዘብ እያቃሙዋቸው ፣ በቀሚስና ፣ በንዋይ እያባበሉዋቸው የሚያስለፈልፋቸው ፣ አስመሳይ ተቃዋሚዎች አንዱ እግራቸውን ጠላት ሰፈር ፣ ሌላውን ተቃዋሚው ሰፈር ተክለው ፣ እንደ ቱቦ አስተላልፉ የተባሉትን ውዥንብር (disinformation) በመረጃ ስም እየበተኑ ፣ አሁንም የተቃዋሚው ክፍል ተጠናክሮ እንዳይደራጅ የሚችሉትን ሁሉ እንደቀድሞው ለማደናገር ሲሞክሩ የምናየው ነው ፡፡ ተቃዋሚውም ፣ ማን ምን እንደነበር የራሱ (trackrecord) ስለሌለው ፣ ትላንት ከውስጣችን ወጥተው ፣ አስር ጊዜ እየካዱን ሲመለሱ ፣ የሚቀበላቸው በእቅፍ አበባ ነው፡፡
ከአዲሱም ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በትክክል በሚገባን ቋዋንቋ የሰማነው ነገር ቢኖር፣ ሊመልሱ የተዘጋጁት የሕዝባችንን ጥያቄ ሳይሆን ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የጀመሩትን “ራዕይ“ በተጠናከረ መንገድ እውን ማድረግን ነው ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወጥቶ “የሃዘናቸው ተካፋይ መሆኑን“ ለዓለም ሕዝብና ፣ ለእኛ ሊያሳዩን ሲነሱ ፣ ከፍተኛ ድጋፍ አለን ፣ በጀመርነው መንገድ እንቀጥላለን ማለት መሆኑን የማይገባን ከሆነ ፣ አስተርጓሚ ሊያስፈልገን ነው ፡፡ ወይንም አንዳንዶች በሌላ ዘረኛ ስሌት ሊነግሩን እንደሚፈልጉት “ ችግራችን ሥርዓቱ ሳይሆን ፣ የመሪው ማንነትና ፣ የመጣበት ክፍልን ነበር የምንቃወም“ ብለው በግልጽ ይነግሩን እንደሆን እንጂ፣ ተስፋ ማየት ገና ምንም አልጀመርንምና ለገላጋይነት አንጣደፍ ፡፡
ባጠቃላይ ይህን ሁሉ ዘርፈ ብዙ የጋራ ችግራችንን፣ ለማስወገድና አደጋውን ለመከላከል የምንችለው፣ ባልሆነ ተስፋ እራሳችንን በማታለል ፣ ወይም በእልህ እነሱ በሄዱበት የጎጥ መንገድ በግልባጩ ተጉዘን ሳይሆን ፣ ሰከን ብለን ፣ ትግላችንን ሳናቀዘቅዝ ፣ ትጥቃችንን ሳናላላ ፣ ለዋናው ብሔራዊ ደህንነታችን ስንል መለስተኛ ልዩነቶቻችንን በይደር አቆይተን “cease-fire“ ይህች ሓገር እንደ ሃገር እንድትቀጥል የምንፈልግ የአንድነት ሃይሎች ፣ ጋባዥ ሳይጠራን ፣ አስተናጋጅ ሳያስፈልገን፣ ግርግር ፣ ድግስ ፣ አሜሪካ ኦባማ እያልን “መቀላወጥ“ ሳናበዛ ፣ እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ፣ ተፈላልገን ፣ ተጠቃቅሰን ፣ ተሰባስበን ፣ ተደራጅተን፣ ብሔራዊ አጀንዳችንን ቀርጸን በጋራ አምርረን መታገል ስንጀምር ብቻ ነው፡፡በዘር ተዘራዝረን የታሪክ ተጠያቂወች አንሁን !!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ሁሌ በራሱ መንገድ ይጠብቃታል ፡፡
እኛም በቀና የአንድነት መንፈስ እንተባበረው ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
Zekarias Asaye(edenasaye@yahoo.com)

No comments:

Post a Comment