Wednesday, April 24, 2013

የኢትዮዽያ ውስጥ ያለውን ጓንታናሞ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ምርመራ ሊያደርግበት ይገባል!

    
By: Meranu Habibty
ከባራክ ኦባማ ቀደም ብሎ አሜሪካንን ለ8 አመታት የገዛው ጦረኛው ጆርጅ ዊሊያም ቡሽ ከሂትለር የሚሻለው በጥቂቱ ነው፡፡ ሂትለር ኦሺዊትዝ የሚባል ካምፕ ገንብቶ በርካታ ሚሊዮን አይሁዶችን ከነነፍሳቸው እቶን እሳት ውስጥ እያስገባ ሲጨርሳቸው አለም በአንድ ግንባር ተነስቶ የሂትለርን ርእዮትና አስተዳደር ከገምድረ ገፅ ለማጥፋት ግራና ቀኝ ማየት አላስፈለገውም ነበር፡፡ አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ሌላኛው ጦረኛ ጆርጅ ዊሊያም ቡሽ በአፍጋኒስታን “ባግራም” የተባለ ማሰቃያ ካምፕ፣ በኢራቅ “የአቡ ግሬብ”እስር ቤትን ና ሌላኛውን ደግሞ በኩባ ጓታናሞ የተባለውን አሰቃቂ እስር ቤት ገንብቶ በርካታ ሰዎችን በሚዘገንን ሁኔታ ሲያሰቃይ ይህን የሚያውቁ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡ ጆርጅ ቡሽ ከላይ በተለያዩ ሃገራት በገነባው ማሳቃያ እስር ቤቶች ውስጥ እስረኞች በሚጠብቋቸው ወታደሮች ከሚያደርሱባቸው አሰቃቂ ድብደባና ግርፊያ በተጨማሪ በቀጥታ ከጆርጅ ቡሽ አስተዳደር በሚታዘዙ መርማሪዎች አማካኝነት ጥፍር ግሽለጣ፣ ሰውነትን በኤሌክትሪክ ሾክ በማድረግ፣ የሚያናዝዝ መርፌ በመውጋት፣ሰብአዊ ክብርን በመድፈርና(ወታደሮቹ እስርኞቹ ላይ ነውር በሆነ ሁኔታ ወሲብ እንዲፈፀምባቸው በማድረግ፣ በአደገኛና ተናካሽ በሆኑ ውሾቻቸው ማስነከስ ወዘተ ) አይነቶች ማሰቃያ ዘዴዎች በመጠቀም ከሂትለር ቀጥሎ ይቅር የማይባሉ “ወንጀለኞች” የሚያስብላቸውን ድርጊት ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡ ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይሁንና ይህን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስረኞችን አያያዝ በሚመለከት ያወጣውን ህግ በሚጥስ መልኩ የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር በጓንታናሞ፣ በባግራምና በአቡ ግሬብ እስር ቤቶች ሲፈፅሙት የነበረው ህገወጥ ድርጊት በራሳቸው ወታደሮች ሞባይሎች ተቀርፀው በYoutube ፣goole ፣Face book እና Twitter ድረ ገፆች ላይ ለአደባባይ በመብቃታቸው፣ እንዲሁም አለም አቀፍ ሚዲያዎች ነገሩን ተቀባብለው በመዘገባቸው አለም ጆርጅ ቡሽን ስለሰብአዊ መብት አያያዝ የመናገር ምንም አይነት ሞራል እንደሌለውና ቢናገርም አዳማጭ እንደሌለው አስረግጠው ነግረውታል፡፡ ከሁሉም በላይ የአሜሪካንን ክብርና ተሰሚነትም አውርዶት እንደነበር የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበውት ነበር፡፡ በተለይ በጓንታናሞ እስር ቤት የሚፈፀሙት ህገወጥ ምርመራዎችና ሌሎች አሰቃቂ የሰብአዊ ጥሰቶችን የሚያሳዩ በድብቅ የተቀረፁ ቪዲዮዎች በየድረገፁ ይፋ መደረጋቸውና ይህን ተከትሎ አለማቀፍ ጫናዎች በመብዛታቸው አሜሪካ ጓንታናሞ የሚባለውን እስር ቤት ለመዝጋት የወሰነችበትን አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡
ወደሃገራችን ስንመጣም ከሚኒሊክ አደባባይ ወደ ሰሜን ሆቴል በሚወስደው አስፋልት ግማሽ ኪሎ ሜትር የማይሞላ መንገድ እንደተጓዙ በተለምዶ ማእከላዊ የሚባል እስር ቤት ያገኛሉ፡፡ ይህ እስር ቤት ከባባድ ወንጀል የፈፀሙ እስረኞች ግዜያዊ ማረፊያ በሚል የዳቦ ስም ቢሰጠውም በከባድ ወንጀል ስም የሚገቡ እስረኞችን የሚበላና የጓንታናሞ አይነት ማሰቃያ መጋዘኖች ያሉበት የምድር ጀሃነም(ገሃነም) አይነት ነው፡፡ ይህን መንግስት የሚተቹ የሃይማኖት አባቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና ግለሰቦች የትም ሳይሆን እዚህ ቦታ ተወስደው በፊልም ላይ ያዩትን ማሰቃያ ሁላ ያገኙታል፡፡ ሰው መሆን እስኪያስጠላዎት ድረስና በሃገሪቱ ህግ የሌለ እስኪመስልዎት ድረስ ሰውነትዎ ላይ የማያርፍ የማሰቃያ አይነት የለም፡፡ ከኤሌክትሪክ ሾክ ማድረጊያ እስከ ደም የጠማው ድቡልቡል ዱላ ድረስ፡፡ በሽተኛ መሆንዎ ከታወቀማ አበቃ!ህመምተኛ የሆኑበት ቦታ ተፈልጎ ይቀጠቀጣል፡፡ በአፍዎ ውስጥ አሮጌ ቆሻሻ ጨርቅ ይወተፍብዎትና ያለገላጋይ ተገልብጠው ይታሻሉ፡፡ አፍዎ ውስጥ የተወተፈው አሮጌ ጨርቅ 20 አመት ሙሉ በማእከላዊ እስር ቤት የገቡ ሁሉ የተጠቀሙበት ነው፡፡ አንዱ በማእከላዊ እስር ቤት የነበረ እስረኛ ከታሰረ 2 አመት በኋላ ተመልሶ ሲገባ ያንኑ አፍ ውስጥ የሚወትፉትን ማፈኛ መልሰው እንደወተፉበት በአንድ መፅሄት ላይ የፃፈውን ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ሰውየው ከሃገር ስለወጣ ምናልባት ድጋሚ ያ ጨርቅ ለ3ኛ ግዜ የሚወተፍበት አይመስለኝም፡፡ እሱ ውስጥ ተወትፎ የነበረው ቆሻሻ ጨርቅ ግን በሌላው ባለ ተራ አፍ ውስጥ ይወተፍበታል፡፡ ደብዳቢዎቹና እንዲደበድቡ ያዘዛቸው አካል የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስ ምግብ ሳይሆን ኢሰብአዊ ድርጊት ነው የሚመግብዎት፡፡ በጨለማ ክፍል ተዘግቶብዎት ሰውም አይጎበኝዎ፣ ፀሃይም አይሞቁ፡፡ ሌላው ቢቀር ቀኑ ማን እንደሆነና ሰዐቱ ስንት እንድሆነ እንኳ አያውቁትም፡፡ ቀኑ ማን እንደሆነና ሰዐት ስንት እንደሆነ ማወቅ የቅንጦት ያህል ነው፡፡ የሚገርመው ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ለምርመራ መስልዎት ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ሲጀመር የተያዙት ያለ ወንጀል እንደሆነ የያዘዎት አካል ድብን አድርጎ ያውቀዋል፡፡ የሚደበደቡበት ዋናው ጉዳይ የያዘዎት አካል ዝም ብሎ ያዘ እንዳይባል መንግስትን በሃይል ለመገልበጥ ሳሴር ነው የተያዝኩት ብለህ እመን ነው ያ ሁላ ውርጅብኝ፡፡ በማእከላዊ 3 አይነት ደረጃ እንዳለው አንብቤያለሁ፡፡ 1ኛው ደረጃ ሲቀጠቀጡ ያድሩና ሲነጋ ከማንም ጋር የማየገናኙበት ጨለማ ክፍል ያሉባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ እስረኛ ጋር አይገናኙም፡፡ 2ኛው ደረጃ ስቃዩ በከፊል አለ ሆኖም አብረው ሌሎች ተገራፊዎችን በአንድ ክፍል ያገኛሉ፡፡ 3ኛው ደረጃ ደግሞ ደብዳቢዎ አካል ወይ የሚፈልገውን አግኝቶ፣ ወይም ደግሞ በርስዎ ጥንካሬ ተስፋ ቆርጦ ወይም አለማቀፉ ማህበረሰብ ሲጮህበት ፀሃይ የሚሞቁበት፣ ጨለማ ያልሆነ ክፍል፣ከሌሎች እስረኞች ጋር እንድልብ የሚያወሩበት ቦታዎች ናቸው፡፡ በማእከላዊ (ይቅርታ ጓንታናሞው ማለቴ ነው) አንዳንዴ እንኳን ተገርፈው ተገልምጠውም ያላደረጉትን ይለፈልፋሉ፡፡ከዚህ በፊት በ97 ላይ እኔ ነኝ ያለ የተቃዋሚዎቹ ወሬ ነጋሪ የነበረ አንድ ግለሰብ (ፕሮፖጋንዳ ሃላፊ የነበረ ልበለው ይሆን?) በጣም ገልምጠውት ነው መሰለኝ ተልፈስፍሶ ከዱላው በፊት በአንድ ተራ ግልምጫ ብቻ ያላደረገውንና ያላሰበውን ሁሉ አድርጊያለሁ ብሎ በማግስቱ በኢቲቪ አኬልዳማ ፊልም ላይ አጠገቡ ማኪያቶ ቀርቦለት ከደህንነቶችቹ ጋር እየተሳሳቀ በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ጓደኞቹን ሁላ ስም እየጠራ ሲሳደብ አይቼ ትንሽ ገርሞኝ ነበር፡፡ ነገሩ የገባኝ አሁን ነው፡፡ በሱም አልፈርድም፡፡ ማእከላዊ ገቡ ማለት ህግ ሳይሆን የሚያናግርዎት ሌላ ስለሆነ የማያውቁትን ስም እየጠሩ እሱ ልኮኝ፣አዞኝ፣ ቦንብ አፈንድቼ፣ ቦንም ቀምሜ፣ አውሮፕላን ላጋይ ስል፣ በቤተ መንግሱ የኋላ በር ገብቼ ጠቅላይ ሚስትሩን ልጠልፍ ስል፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መስኮት በኩል ገብቼ የህገ መንግስቱን ዋናውን መፅሃፍ ሰርቄ ለዲያስፖራ ልሸጥ ስል ነው የተያዝኩት እያሉ መለፍለፍዎ አይቀርም፡፡
እንግዲህ የኛዎቹ(የኢትዮፕያውያኖቹ ) የእድሜ ልክ ጀግኖች የሆኑት ኮሚቴዎቻችንም በዚህ የነጓንታናሞ ጓደኛ ከሆነው እስር ቤት ገብተው ኢሰብአዊና አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፀምባቸው ከነበሩት ዜጎች መካከል ናቸው፡፡ ለወራት ያህል ሊነገር እንኳ የሚያሰቅቅ ማሰቃያና ግርፊያ ሲደረግባቸው ነበር የቆየው፡፡ በግለሰቦቹ ታላቅ ሰብእናና ጥንካሬ እንዲሁም አላህ ረድቷቸው የያዛቸው አካል ከነሱ የሚፈልገውን ሳያገኝ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ቢዘዋወሩም ድርጊት ግን ዝም የሚያስብል አይደለም፡፡ ኢትዮፕያዊያን በሙሉና አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ማእከላዊ እንዲዘጋ ወይም አያያዙን እንዲያስተካክል፣ እንዲሁም በዚያ ገሃነም እስር ቤት ውስጥ ድብደባ ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ የነበሩት ሁላ ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ማጤን አለባቸው፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮፕያ ህዝብ ስም የሚሰጡትን ብድሮች የራሱን ሃገር ዜጎች የሚያሰቃይበትን ካምፖች መገንቢያና ለአሰቃዮችም ጡንቻ ማፈርጠሚያ ላይ እንደማይውል ማረጋገጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ በዚህ ከቀጠለ ሃገሪቱ ሌላኛዋ በምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ የትርምስ ሃገር እንዳትሆን ያሰጋል፡፡ ሁል ጊዜ ማንም እንደበሬ እየተጎተተ የሚታረድ የለምና፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ለሃገሪቱም ሆነ ስትራቴጂክክ ወዳጅ ለሆኑ ሃገራት የሚፈለግ አይደምና፡፡ አላህ ሀገራችንን ከአምባገነኖች ነፃ ያድርግልን፡፡ ኮሚቴዎቻችንን ጨምሮ ያለ ወንጀል የታሰሩትን ኢትዮፕያውያን ነፃ ያውጣልን፡፡ ድልም ገኛ ጋር ይሁን፡፡ አሚን፡፡

No comments:

Post a Comment