Wednesday, March 6, 2013

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውሳኔ ፖለቲካዊና ዘረኝነት ላይ ያነጣጠረ ነው ተባለ

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረን ግጭት ተከትሎ 10 የኦሮሞ ተወላጆች ከትምህርታቸው እንዲታገዱ መደረጋቸውን የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ሊግ አጥብቆ ያወገዘው ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ውሳኔም ፖለቲካዊና ዘረኝነት ላይ ያነጣጠረ ነው ብሎታል።
የሰብዓዊ መብት ሊጉ ከትምርታቸው የታገዱትን ተማሪዎች ፎቶ አስደግፎ ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታቸው የታገዱት የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተናቸውን አጠናቅቀው የሁለት ሳምንት እረፍት ወስደው ከተመለሱ በሁዋላ ነው ብሏል።
ሊጉ ከውስጥ የደረሱትን መረጃዎች ዋቢ አድርጎ እንደገለጸው ይህ በግልጽ ፖለቲካዊ የሆነውና ዘረኝነት ላይ ያነጣጠረው ውሳኔ የተላለፈው “ዲሲፕሊን ኮሚቴ” ተብሎ በሚጠራው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አካል ሲሆን፤ኮሚቴው ለዚህ ውሳኔ ምክንያት የሆነውም ባለፈው ጥር ወር በኦሮሞና በትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ነው።
በሁለቱ ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል ግጭቱ ሊፈጠር የቻለውም ጥቂት የትግራይ ተወላጆች የኦሮሞ ብሄረሰብን አስመልክቶ ተገቢ ያልሆነና ቆስቋሽ ጽሁፍ ጽፈው በመለጠፋቸው ምክንያት እንደሆነ ማረጋገጡን ሊጉ አውስቷል።
ይህን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በግጭቱ ሳቢያ ከ10 በሚበልጡ ተማሪዎች ላይ የ እስራት፣የግርፋትና የድብደባ እርምጃ መወሰዱን፤ ከታሰሩት መካከል ብዙዎቹ የ ኦሮሞ ተወላጆች እንደሆኑ ይፋ ማድረጉንም ሊጉ አስታውሷል።
በግጭቱ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዲታገዱ የተደረጉት አስሩም ተማሪዎች ኦሮሞዎች መሆናቸውን እና ከመካከላቸው አንዷ ሴት መሆኗን ያመለከተው ሊጉ፤ ሁሉም ለአንድ ወር ያህል ታስረው በዋስ ከተለቀቁ በሁዋላ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው እንደነበር ጠቅሷል።
ከትምህርታቸው የታገዱት የኦሮሞ ተማሪዎች ከወለጋ ነቀምት የመጣው የ 3ኛ ዓመት ተማሪ ታደለ ታረቀኝ፣ ከደቡብ ሸዋ ኦሮሚያ የመጣው የ3ኛ ዓመት ተማሪ አበጀ ቱጂ ጫላ፣ የ4ኛ ዓመቱ ተማሪ ገመቹ ደለቶ ዳፎ፣ የ 4ኛ ዓመት ተማሪ መልካሙ ሙሉጌታ፣ የ 3ኛ ዓመት ተማሪ ፈቃዱ መሰራ፣ የ4ኛ ዓመቷ ሴት ተማሪ አዲስ ጋቴራ ያደሳ፣የ 4ኛ ዓመቱ ተማሪ በቃሉ ስዩም ተሻለ፣ የ3ኛ ዓመቱ ተማሪ ቀጀላ አድማሱ ደሬሳ፣የ 2ኛ ኣመት ተማሪው ኢሳያስ ኢታና እና የ 4ኛ ዓመት ተማሪው አራርሳ ዋቅቶላ ኦልጅራ መሆናቸው ይታወሳል።
ግጭቱን ከቀሰቀሱትም ሆነ በግጭቱ ከተሳተፉት የትግራይ ተወላጆች አንድም ተማሪ ላይ እርምጃ አለመወሰዱ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተብየውን ውሳኔ በግልጽ ፖለቲካዊና ዘር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ያሳያል ሲል የሰብዓዊ መብት ሊጉ አመልክቷል።
ይህ ውሳኔ ከሰብዓዊ መብት ሊጉ ባሻገር ብዙዎችን ያስገረመ እና ጥቂት በማይባሉም ታዛቢዎች ዘንድ፦ “በ እርግጥም ይህች አገር የማናት?” የሚልን ጥያቄ ያጫረ ሆኗል።

No comments:

Post a Comment