March 21, 2013
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴላቪዥን ኢሳት ቀደም ብሎ ከሁለት አመታት በፊት በአዜብ መስፍን የእህት ልጅ አቲኮ ስዩም አምባየ የተመሰረተው ኦርቺድ ቢዝነስ ግሩፕ በጣሊያኑ ሳልኒ ኮንስትራክሽን አማካኝነት በሚገነቡት ግልገል ጊቤ አንድ እና ግልገል ጊቢ ሁለት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ስሚንቶ እና የግንባታ እቃዎችን እንዱሁም ከፍተኛ ማሺነሪዎችን በማቅረብ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ማጋበሱን መዘገቡን አውስቶ ይሄው ኩባንያ ከሳሉኒ ጋር ግልጽነት የጎደለው የቢዝነስ ስምምነት በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ስሚንቶ እንዱሁም ከባድ ማሺኖችን በማቅርብ ላይ እንደሚገኝ አጋልጧል።ኢሳት በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራውን የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት በቅርብ የሚያውቁ ሰዎችን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው ግድቡን እየገነባሁ ነው ከሚለው ሳልኒ በመቀጠል ከፍተኛ የሆነ ትርፍ የሚያገኘው ኦርቺድ፣ ከየትኛውም ድርጅት ጋር ሳይወዳደር በእነ አዜብ መስፍን አማካኝነት የስሜንቶና ማሸንሪዎች አቅራቢ ሆኖ ቀርቧል ብሏል።
ይሄው ኩባንያ ቦዲ ዋይዝ ጂም፣ ካፌ ፓኒኒ፣ ኦርቺድ ጄኔራል ኮንትራክተር፣ ኦርቺድ ትራንስፖርት፣ ኦርቺድ ትራንዚት፣ ኦርቺድ ማሽነሪ ሬንታል፣ ኤስ ኤንድ ኤስ እርሻ፣ ሂላል ቱር ኤን ትራቭል፣ ሜትሮሉክስ ፍላወር፣ ናይል ስፕሪንግ ውሀ፣ ሬንቦው ጊፍት ሾፕ፣ ሪል ሳልን፣ ወንደር ዊሌ ቢዝነስና ሌሎችም በአዲስ አበባና በመላው አገሪቱ ታዋቂ የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በስሩ አቅፎ መያዙን ኢሳት በማያያዝ ዘግቧሌ።
አቲኮ ስዩም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህ ነዉ የሚባሌ ኃብት እንዳልነበራት ታሪኳን ያጠኑ ዘጋቢዎቹ ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢሳት ባለፉት 20 አመታት ግን በልዩ ትዕዛዝ “ኦርቺድ” ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል ድርጅት ተከፍቶላት ሆን ተብሎ አያሌ የግንባታ ጨረታዎችን አንድታሸንፍና በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ቱጃሮች ተርታ ለመመደብ እንደቻለች መግለጹን አውስቷል።
የህወሀት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት በዘመዶቻቸው ስም የሚገነቧቸው የቢዝነስ ተቋማት እየተበራከቱ መምጣቱን በተደጋጋሚ ሲዘግብ እንደነበር ያስታወሰው ኢሳት የባለስልጣናትን የሀብት ምዝገባ ጨርሶ በአጭር ጊዜ ይፋ አድረጋለሁ በማለት ሲፎክር የነበረው ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ቃሉን ለመጠበቅ እንደተሳነውና ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱ በዘመድቻቸው ስም የያዙትን ሀብትና ንብረት ለመመዝገብ ስልጣን እንዳልተሰጠው ገልጿል።
No comments:
Post a Comment