Wednesday, February 5, 2014

ደመቀ መኮንን ልምድ ያለው ውሸታም (ከሁኔ አቢሲኒያዊ)


(የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ በ2004 ዓ.ም የመምህራን ደመወዝ ጭማሪን አስመልከቶ በተነሳው ተቃውሞ መምህራኑን አነሳስተሀል ተብሎ ከመምህርነት ሙያው የተባረረ ነው)

ከሁኔ አቢሲኒያዊ
  • ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3481 መምህራን ከስራቸው ለቀዋል
  • አዲስ አበባ ውሰጥ በበርካት ት/ቤቶች በአንድ ክፍል ውስጥ ከ90 በላይ ተማሪ ይማራል
  • ልጁን በመንግስት ት/ቤት የሚያስተምር አንድም ባለስልጣን የለም
  • በስኳር ቴክኖሎጂ የተማረ የሰው ኃይል የለም ብለዋል አቦይ ስብሀት
  • ለየወረዳው ካድሬዎች እስከ 2500 የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ ተደርጓል
  • በስብሰባ ምክንያት ቅዳሜ ማስተማር ያስቀጣል
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ትምህርት አስተሳሰብን ብሎም ኑሮን ይቀይራል ብለው በማመን ልጆቻቸውን ወደ አሰኳላ በመላክ የማስተማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀርቡት ልጆችን ማስተማር የነገ ህወታቸውን ማስተካከል ነው ብለው ስለሚያምኑ እና ትክክልም ስለነበሩ ነው ነገር ግን ባለፉት 23 ዓመታት የህወሀት ኢህአዴግ ዘመን ከጊዜው እና ካለው የህዝብ ቁጥር አንፃር የተማረ የሰው ኃይል ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም ብዙሀኑ ህዝብ ግን ትምህርትን የሚማረው ነገ ተምሮ ምንም ተስፋ እንደሌለው ተረድቶ ነው፡፡
Ethiopian Minister Demeke Mekonnen
ደመቀ መኮንን
ከሰሞኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትምህርት ለሁሉም በማዳረስ አቻ እንዳልተገኘላት የህወሀት ታማኝ አገልጋይ የሆነው ደመቀ መኮንን በቴሌቪዥን መስኮታችን ብቅ ብሎ ነግሮናል ወይም ዋሽቶናል፡፡
የዚህ ፅሁፍ ፀሀፊ ሀሳብ ኢትዮጵያ እውን ቁጥሩን አሳክታለች አላሳካችም ሳይሆን ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ የትምህርት አሰጣጥን ማሳየት ነው፡፡
በአንድ ወቅት ሁሉንም አውቃለው የሚለው ስብሀት ነጋ በስኳር ቴክኖሎጂ ሀገሪቷ ውስጥ ምንም የተማረ የሰው ኃይል እንደሌለ ሰንደቅ ለተበላው ጋዜጣ ተናግሮ ነበር ነገር ግን ይህ የህዝቡ በስኳር ቴክኖሎጂ ተምሮ ያለመመረቅ ፍላጎት ሳይሆን የመንግስት የተሳሳተ የትምህርት ፖሊሲ በዘልማድ እና ገበያውን እንዲሁም ሀገራችን የሚያስፈልጋትን የተማረ የሰው ኃይል አይነት ካለማወቅ የሚመጣ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዐት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ኬሚስትሪ እና ፊዚክስ ተምረው እቤት ተቀምጠዋል ድህነታቸው ለህወሀት አሽከር ያደረጋቸው ወንድሞቻችን ደግሞ ኮብልስቶን እየሰሩ ይገኛሉ እነዚህ ወጣቶች ቀድሞውኑ የተሻለ የትምህርት ስርዓት እና ፖሊሲ ቢኖር ኖሮ አቦይ ስብሀት እንደሚሉን ምንም የተማረ የሰው ኃይል በሌለበት የስኳር ቴክኖሎጂ ተምረው እራሳቸውንም ሀገራቸውንም በቀየሩ ኖሮ፡፡
ደመቀ መኮንን እንደዛ ያለማፈር አፉን ሞልቶ የተናገረለት የሀገራችን የትምህርት ስርዐትን ለመታዘብ አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የመንግስት ትምህርት ቤት ጎራ ማለት አልያም መምህራኑን ማነጋገር በቂ ነው፡፡
በትምህርት የተሻለ ደረጃ ደርሳለች በምትባለው አዲስ አበባ በርካታ ት/ቤቶች ውስጥ በአንድ ክፍል እስከ 90 የሚደርስ ተማሪ ይማራል ይኸውም ተማሪው በትክክሉ ትምህርት አንዳያገኝ ብሎም መምህሩ እውቀቱን በአግባቡ እንዳያደርስ የሚያደርግ ነው ይህንንም ችግር ስለሚያውቁ ነው ሁሉም ባለስልጣኖች ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት ብሎም ከፍተኛ ክፍያ በሚያስከፍሉ ት/ቤቶች የሚያስተምሩት ነገር ግን ልጆቻቸው እንኳን እንዲማሩ የማይፈቅዱበትን የመንግስት ት/ቤቶች ሀገሪቷ እንደተቀየረች ማሳያ አድርገው ያቀርቡልናል፡፡
መንግስት ማለትም ህወሀት ከትምህርት ይልቅ የፖለቲካው ነገር ያንገበግበዋል ፡፡ በቅርቡ ለሁሉም የህወሀት ኢህአዲግ ተቀጣሪ የየወረዳው የፖቲካ ሹመኞች በሀገሪቱ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ እስከ 2500 ብር የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ አድርጓል ከዚህ ቀደም በኑሮ ውድነቱ ተሰቃየን ሲሉ ከፍተኛ ዛቻ እና ከስራ ማባረር ለፈፀመባው መምህራን እና የመንግስት ሰራተኞች ትኩረት አለመስጠቱ ብሎም ደመወዛቸውን ለመጨመር አለማሰቡ ህወሀት ኢህአዴግ ከዜጎች በላይ ካድሬዎች የሚል ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ት/ቤቶች በአሁኑ ሰዐት እንደበፊቱ ቅዳሜ እና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጫ ከመሆን ይልቅ የካድሬ መሰብሰቢያ ማዕከል ወደመሆን ተሸጋግረዋል ቅዳሜ ቀን ተማሪዎቹን የማጠናከሪያ ትምህርት የሚጠራ ማንኛውም መምህር ስብሰባ እንዳወከ ተቆጥሮ በት/ቤቱ ኃላፊዎች ከፍተኛ ሆነ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርሰዋል ይህንንም ተከትሎ በርካታ መምህራን መምህርነት ሙያን እንደስራ መፈለጊያ ይጠቀሙበታል፡፡ በቅርቡ ከአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ለከተማው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ የቀረበው ማስረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3481 መምህራን ስራቸውን ለቀዋል፡፡
እንግዲህ ይህንን ነው ባለልምዱ ውሸታም ደመቀ መኮንን ለውጥ ብሎ የሚነግረን፡፡

ኢትዮጵያን ከቅርጫ ለማትረፍ


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬEthiopia on the Meles Zenawi’s chopping block

የአሁኑ አስገራሚ ጊዜ ሸክስፒር፣ ጁሊየስ ቄሳር በሚለው ፅሁፉ ላይ ለተናገረው  አነጋገር ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል፣ “ሰዎች የሰሩት ተንኮል ከመቃበራቸው በላይ ሀያው ሆኖ ይኖራል” ብሎ ነበር ሸክስፒር፡፡ በአሁኑ ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ከሰሩት ተንኮሎችና ጭራቃዊነት የሞላው አስቀያሚ ተግባር ውርስ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠን እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የግዛት አካል ተቆርሶ እንደገና ለሽያጭ ለሱዳን ቀርቧል፡፡ ይህንንም ጭራቃዊነት ተንኮል የቀበሮ ባህታውያኑ “የድንበር ማካለል“ ብለው ይጠሩታል፡፡ እኔ ደግሞ ድንበር መቁረስ፣ መቆራረስ፣ መሽረፍ እና መሸራረፍ ብዬ እጠራዋለሁ፡፡ ባጭሩ ኢትዮጵያን  ለቅርጫ ማቅረብ እለዋለሁ… ደግሞ ለሰላሳ ቁርጥራጭ የመዳብ ዲናሮች!
እ.ኤ.አ በ2008 “የኢትዮጵያ ጋሻ“ ተብሎ በሚጠራው የሰሜን አሜሪካ የሲቪል ማህበረሰብ ስብስብ ጉባኤ ላይ በመገኘት የእናት አገር ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅ በሚል ርዕስ ስሜትን የሚቀሰቅስ ንግግር አድርጌ ነበር፡፡
በዛሬዋ ዕለት እዚህ የተሰባሰብንበት ዋናው ምክንያት አቶ መለስ ዜናዊ እናት አገራችንን መቅን አሳጥተው ለመበታተን እንዲመቻቸው በበረሃ ሳሉ ነድፈው ያመጡትን ጭራቃዊ ዕቅድ እና ዕኩይ ምግባር ለማውገዝ እና ለማስቆም ነው፡፡ አቶ መለስ የአሰብን ወደብ አሳልፈው በሰጡበት ወቅት ዝምታን በመምረጣችን ወደብ አልባ የመሆንን ዋጋ ከፍለናል፡፡ እ.ኤ.አ በ1998 ባድመ ተወረረች፣ እናም የ80,000 ኢትዮጵያውያን ህይወትን የበላ መስዋዕትነት ተከፍሎ ጠላቶቻችን ከግዛታችን እንዲወጡ ተደረገ፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ በብርሃን ፍጥነት ተገልብጠው የኢትዮጵያን አንጸባራቂ የጦር ሜዳ ድል ቀልብሰው የዲፕሎማሲያዊ ሽንፈትን በመጋት በእርቅ ሰበብ ስም ባድመን ለወራሪው ኃይል አሳልፈው ለመስጠት ስምምነት አደረጉ… (ዛሬ) በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ወገኖቻችን በግልጽ እንደነገሩን የአያት ቅድመአያቶቻቸውን መሬት እና መኖሪያ ቤታቸውን ሳይቀር አቶ መለስ ለሱዳኑ አምባገነን [በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በወንጀል ለሚፈለጉት እና ከፍትህ ለማምለጥ እራሳቸውን በመደበቅ ተወሽቀው ላሉት] መሪ ኦማር አልባሽር አሳልፈው ለመስጠት በሚስጥር ስምምነት ፈጽመዋል…
ያንን ንግግር ካደረግሁ ከስድስት ዓመታት በኋላ እንኳን በሚያሳዝን ሁኔታ እናት አገራችንን ለመበታተን አቶ መለስ ከበረሃ ውስጥ ነድፈው ያመጡትን ጭራቃዊ ዕቅድ እኩይ ምግባር ለመቀልበስ ባለመቻላችን አዝናለሁ፡፡ አቶ መለስ አሁን በህይወት የሉም፣ ሆኖም ግን እኛን እንዲያጠፋ ጥለውት ከሄዱት ተንኮላቸው ስራቸው ጋር ፊት ለፊት ተጋትረናል፡፡ “መልካም ሰዎች ዝም ስላሉና ምንም ባላማድረ ጋቸው ይሆን ተንኮል የሚበረታው” የሚለው አባባል እውነታነት አለውን? በመጨረሻም ተንኮልና ጭራቃዊነት ድል ተጎናጽፏልን?
ኢትዮጵያ በአቶ መለስ ዜናዊ ቅርጫ መግባት
እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2013 የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ዓሊ ካርቲ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ገዥ አካላቶች “ፋሻጋ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የነበረውን የድንበር አለመግባባት እና በሌሎች አካቢዎችም ያሉትን የድንበር ማካለል ስራዎችንም በሰላማዊ መንገድ ለማጠናቀቅ ስምምነት አድርገናል“ በማለት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ስለሁለቱ አገር መሪዎች አስመልክቶ ካርቲ እንዲህ ብለዋል፣ “የመጨረሻውን የማካለል ስራ ለመተግበር ታሪካዊ ስምምነት አድርገናል፡፡“ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያሉትን “የድንበር ውዝግቦች” በማስመልከት ለሚቀርቡ አስተያየቶች ሁሉ ምንም ዓይነት ሀሳብ እንደማይቀበል ጠቅሶ ሲናገር፣ “በጠረፉ በተወሰኑ የወሰን ድንበር ነጥብ ቦታዎች ላይ“ በጣም ቀላል የሆኑ አለመግባባቶች ከመኖር በስተቀር ሌላ ቸግር እንደሌለ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መምሪያ እንደ ዔሌ አንገቱን ብቅ ጥልቅ እያደረገ በድብቅነት እና ማደናገር በተላበሰ ስልት/strategy “የድንበር ማካለሉን ጉዳይ“ እና “መጠነሰፊ ጠቀሜታ“ አላቸው እያለ ከበሮ የሚደልቅላቸውን “የደህንነት ትብብር ስምምነት፣ የኢኮኖሚ፣ የግብርና፣ የትምህርት እና የባህል“ “የስትራቴጅክ ስምምነት ማዕቀፍ“ በማለት በሚጠራቸው ጉዳዮች ላይ እምነት እንዲያድርብን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን በመሰለቅ ጊዜውን በከንቱ አሳልፏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 “ለድንበር ውዝግቡ” ይሰጡ የነበሩት ምክንያቶች አሁን እየተሰጡ ካሉት ምክንያቶች ፍጹም የተለዩ ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የሱዳን ገዥ አካል እንደገለጸው የድንበር ማካለሉ ስራ አስፈላጊነቱ
“የአልቃዳሪፍን ግዛት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኘው የትግራይ ግዛት ጋር ‘ለማልማት እና ለማቆራኘት‘ የሚል ነበር… ሁለቱ አካባቢዎች በጣም ለም የነበሩ ሲሆኑ፣ ከዚህም በላይ አልቃዳሪፍ ለሱዳን የዳቦ ቅርጫት ተደርጎ የሚቆጠር ነበር… ከአልቃዳሪፍ እስከ መቀሌ ያለው የመኪና መንገድ…እየተጠገነ እና ደረጃው ከፍ እየተደረገ ነው… የትግራይ ግዛት ከዚህ በመነሳት በዚህ በኩል ወደ ቀይ ባህር የሚያሸጋግረው ዕድል ስለሚያገኝ እና አልቃዳሪፍ ደግሞ ከፖርት ሱዳን ጋር የሚያገናኘው ስለሆነ ተቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ፖርት ሱዳን ለመቀሌ በኤርትራ ግዛት ከሚገኘው የአሰብ ወደብ እና በሶማሌ ግዛት ከሚገኘው የበርበራ ወደብ የበለጠ ቅርብ ትሆናለች…“ የሚል ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 አቶ መለስ ዜናዊ ከሱዳን ጋር የተደረገውን “ስምምነት” አስመልክቶ በውሸት ባህር ውስጥ እየተንቦጫረቁ የጭቃ ጅራፋቸውን ማጮህ ጀመሩ፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ሙልጭ አድርጎ በመካድ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ጋት የሚሆን የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገ ሰምምነት የለም የሚል መግለጫ ሰጠ፡፡ ያ መግለጫ በውጭ የሚገኙትን “የዜና አውታሮች” እና “ኃላፊነት የማይሰማቸው” በበሬ ወለደ የፈጠራ ወሬ የተሰማሩ ሽብር እና ፍርሀትን በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነዙ አሸባሪዎች ናቸው በማለት ከሷቸው ነበር፡፡ የሱዳን ባለስልጣኖች ግን ያንን መግለጫ በሚጻረር መልኩ “ከኢትዮጵያ መሬት እንዳገኙ“ በይፋ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ በግንቦት አጋማሽ አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው የመሬት ማደሉን ሚስጥር ደብቀው ማቆየት ባለመቻላቸው ወደ ቀድሞው ታሪካቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡ በድንበር ማካለሉ ወቅት አንዳንድ የቅድመ ስራ እንቅስቃሴዎች ብቻ እንደተከናወኑ፣ እናም የተጠናቀቀ ነገር የለም በማለት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በቀናት ጊዜ ውስጥ አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው ሌላ አዲስ ቅጥፈትን ፈብርከው ብቅ አሉ፡፡ የሆነው “ቀደም ሲል በንጉሱ እና በደርግ ዘመን ከሱዳን ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ አደረግን” ብለው ጭራ ቀረሽ ዉሸት ፈጠሩ፡፡
የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ጉዳዩን በግልጽ ሲያቀርበው እና በተጨባጭ በድንበሩ ባሉ አካባቢዎች ላይ ምን እየተደረገ እንዳለ ይፋ ሲያደርግ እስከ አፍ ጢሙ ተቀብትቶ/ሞልቶ የነበረው የውሸት ጎተራ መፈረካከስ ጀመረ፡፡ በአቶ መለስ ለሱዳን መሬት ዕደላ ፖሊሲ ምክንያት የተጎዱ ዜጎቻችን ለአሜሪካ ድምጽ  የአማርኛው አገልግሎት እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ ተቋማት ቃለመጠይቅ መስጠት ጀመሩ፡፡ በመሬት ዕደላው ምክንያት ቀጥተኛ ተጎጅ የሆኑ ወገኖቻችን አያት ቅደመ አያቶቻቸው ጠብቀው ያቆዩት መሬት በሱዳን ኃይሎች እየተወረረ ይዞታቸው ሲወሰድባቸው እና ከቀያቸው እና እትብቶቻቸው ከተቀበሩባቸው ቦታዎች ሲባረሩ የነበረውን ሁኔታ በመረረ አኳኋን የተሰማቸውን ቅሬታ በሰፊው ማሰማት ጀመሩ፡፡ የእርሻ መሳሪያዎቻቸው እና የመገልገያ ቁሳቁሶች በሱዳን ወራሪ ኃይሎች መወረሱን ገለፁ:: እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያን በሱዳን እስር ቤቶችም ታስረው እንዲማቅቁ አስታወቁ፡፡ በዚያን ጊዜ አቶ መለስ ምንም ምርጫ አልነበራቸውም፣ በግዴታ ሳይወዱ መሬት ለመስጠት ከሱዳን ጋር መፈራረማቸውን  ለማመን ተገደዋል፡፡
እ.ኤ.አ በሜይ 2008 አቶ መለስ ከኦማር አልባሽር ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንዲህ በማለት ይፋ አድርገዋል፣
“እኛ ኢትዮጵያውያን እና የሱዳን መንግስት የድንበር ማካለሉ ስራ በሚሰራበት ወቅት ከሁሉቱም ወገን አንድም ዜጋ እንዳይፈናቀል ለማድረግ ስምምነት ተፈራርመናል… በ1996 የወሰድነውን መሬት መልሰን ለሱዳን ሰጥተናል፣ ይህ መሬት ከ1996 ዓ.ም በፊት የሱዳን ገበሬዎች ይዞታ ነበር፡፡ አንዳንድ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት እንደሚያናፍሱት ሳይሆን በድንበሩ ዙሪያ አካባቢ አንድም የተፈናቀለ ዜጋ የለም፡፡”
እ.ኤ.አ በ2008 በዊክሊስ (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ አመራር ሚስጥር ሰነድ) ሌላ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡ “የቀድሞው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከለዊ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ ‘አቶ መለስ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የድንበር ውዝግብ ውጥረት ለማርገብ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት “ለአማራ ክልል ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ግዙፍ መሬት“ አቶ መለስ ለሱዳን ሰጥተዋል፡፡ እናም የአቶ መለስ አገዛዝ “በድብቅ ይዞ ለማቆየት ሞክሯል” አሉ አቶ ስዬ አብርሃ::
ቀደም ሲል አቶ መለስ፣ አሁን ደግሞ የዕኩይ ምግባር ውርስ አጫፋሪዎቻቸው ያንን ስምምነት “በድብቅ ይዘው ለማቆየት” በመውተርተር እና በመዳከር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2008 አቶ መለስ ከኦማር አልባሽር ጋር ባደረጉት ስምምነት ላይ የሰጡት መግለጫ አንዳንድ ጠቃሚ ምልክቶችን ይሰጣል፡፡ እራሳቸው አቶ መለስ ባመኑት እ.ኤ.አ በግንቦት 2008 በእርሳቸው እና በኦማር አልባሽር መካከል በተደረገው “የመሬት መስጠት ስምምነት” ዝርዝር የስምምነቱን ሁኔታ የሚያመላክት መሆኑ የሚያጣያይቅ አይደለም፡፡ “የስምምነቱን” ሁኔታ ስናጠናው አቶ መለስ በስምምነት መዝገቡ ላይ በርካታ ጠቃሚ ማስረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡ “ስምምነቱ” 1ኛ) መሬቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ሰዎችን ሊያፈናቅል የሚችል ጥያቄ መነሳት እንደሌለበት 2ኛ) ከድንበር ማካለሉ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ከማካለል ስራው ጋር ተያይዞ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሰዎች ጥቅሞች የማስጠበቅ ሁኔታ መኖር እንዳለበት 3ኛ) በኢትጵያውያን ገበሬዎች በህገወጥነት መልክ ተይዞ የነበረ የተባለውን መሬት ለሱዳን ገበሬዎች የባለቤትነት መብትን ማስጠበቅ 4ኛ) በ1996 ዓ.ም በህገወጥ መልክ በኢትዮጵያውያን ተይዞ የነበረውን መሬት ለሱዳናውያን መመለስ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በአቶ መለስ ፈቃድ እና አዛዥነት በእራሳቸው እና በኦማር አልባሽር የተፈረመው መሬት የመስጠት ስምምነት “የ1902 የግዌን መስመር/Gwen Line of 1902” (የ1902 የአንግሊዝ-ኢትዮጵያ ስምምነት)  እየተባለ የሚጠራው “በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን ድንበር” መስመር ማስያዝ ከሚለው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው መገንዘብ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚሁም እ.ኤ.አ ከ1974 በፊት በንጉሱ ዘመን እና በደርግ ዘመን ከ1995 እስከ 1991 ድረስ የተረቀቁ እና የተፈረሙ የድንበር መካለል ወይም ደግሞ መፍትሄ መስጠት ስምምነቶች ካሉ ከዚህ ስምምነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ እ.ኤ.አ ከ1996 መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ አቶ መለስ በእራሳቸው ፈቃድ ከድንበር እና ተመሳሳይ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መልኩ ያደረጉት “ስምምነት” በአቶ መለስ ግላዊ አተያይ የሱዳን መሬት በኢትዮጵያውያን በኃይል የተቀማ ነው በማለት በግላቸው ያደረጉት ህገወጥ እርምጃ እንጅ ሌላ ምንም ዓይነት ማስረጃ የሌለው እርባናቢሰ ስብከት መሆኑ በውል ሊጤን ይገባል፡፡
የኢትዮጵያንግዙፍ መሬቶችበድብቅ እና ለህዝብ ይፋ ሳያደርጉ በሚስጥር ለሱዳን የሚሰጡበትስምምነትምክንያቱ ምንድን ነው”?
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም በአጠቃላይ “በድንበር ስምምነቱ” ዙሪያ እያቀረቡት የነበረው እና ያለው የውሸት ፍብረካ ድሪቶ ሪፖርት እውነታውን ለመደበቅ ከሚሽመደመደው ድሁር አስተሳሰባቸው ያለፈ ፋይዳ አይኖረዎም፡፡ እውነተኛው የድንበር መስጠት ስምምነት እ.ኤ.አ በ2008 ተጠናቁአል፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን አቶ መለስ “ግዙፍ የሆነ መሬት ከአማራ ክልል” ቆርሰው ፈርመው፣ አትመው እና አሽገው ለሱዳን መስጠታቸውና በድብቅ “በድብቅ ተይዞ እንዲቆይ” መጣራቸው የሚያጠያየቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የአቶ መለስን የበከተ ውሸት እንደተለመደው “በሀሰት መጋረጃ ደብቀው” ለዘላለም ለማቆየት በማሰብ ሌላ ዘርዘር ያለ ፖለቲካዊ ድራማ ለመተወን በመውተርተር ላይ ይገኛሉ፡፡
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ጌቶቻቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ሊያታልሉ፣ ሊያጭበረብሩ እና በውሸት ሊደልሉ የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ እነዚህ የዕኩይ ምግባር ባለቤቶች መሬትን ያህል ነገር በድብቅ ሸፍኖ የመስጠት ጨዋታቸውን ኢትዮጵያውያን የማያውቁ እና የማይገነዘቡ ሞኞች አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ እነርሱ ይህን የሞኝነት ጨዋታቸውን እንደፈለጉ መጫወት  ይችላሉ፣ ሆኖም ግን አቶ ኃይለማርያም አንድ ጥያቄ እንዲመልሱልኝ እፈልጋለሁ፣ ይኸውም “ ‘ከአማራ ክልል ግዙፍ መሬቶችን ቆርሰው የሰጡት’ “ድብቅ የሚስጥር ስምምነቶችን የት እንዳስቀመጧቸው ሊያሳዩኝ ይችላሉን? አቶ መለስ እ.ኤ.አ በ2008 እና አሁን ደግሞ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የዕኩይ ምግባር አጋሮችዎ የድብቅ ስምምነቶችን ከህዝብ ፊት ደብቃችሁ ከፊታችሁ ላይ የውሸት መጋረጃ በማድረግ ለመዝለቅ የምትፈልጉት ለምንድን ነው?” ከአገር መሬት ቆርሳችሁ ለባዕድ አገር ስትሰጡ በአገሪቱ ህገመንግስት ስልጣን ለተሰጠው ፓርላማ (ለተወካዮች ምክር ቤት) ተብዬው ለይስሙላ እንኳን ቢሆን መቅረብ የለበትምን“? ህገመንግስቱ የሚለው ሌላ የስርዓቱ ቁንጮዎች የሚያደርጉት ሌላ! አራምባ እና ቆቦ!
ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልሱ ቀላል ነው፣ እ.ኤ.አ 2008 አቶ መለስ የተናገሩለት “የሚስጥር ስምምነት“ እና አሁን ደግሞ አቶ ኃይለማርያም እያነበነቡት እንዳለው አይደለም እውነታው፡፡ ህዝብ ግብር እየከፈለ በሚያስተዳድራቸው መገናኛ ብዙሀን ብቅ እያሉ በእብሪት የሚያሰራጩት ነጭ ውሸት ነው፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ይዋሻሉ ማለት “መለስ ወይስ መቀልበስ” መጠሪያ ስማቸው ነው፡፡ ሁሉም አፍጥጠዉ ይዋሻሉ፡፡ አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከኦማር አልባሽር ጋር በስምምነቶች ላይ ያስቀመጧቸው ቃላት፣ ሀረጎች እና ዓረፍተ ነገሮች ወደ እውነት ተግባርነት የሚሸጋገሩ ከሆነ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? በእውነት እነዚህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በመዳፈር መሬቱን እየቆረሱ ለመስጠት ተፅፈው ተፈረመው የተደበቁ ስምምነቶች የአቶ መለስን እና የአቶ ኃይለማርያምን ቀጣፊነት የሚያስረዱ መረጃዎች ሊሆኑ አይችሉምን?
ድብቅነት በኢትዮጵያ በመግዛት ላይ ላለው ገዥው አካል ዋና መለያ ባህሪው ነው፡፡ ነገሮችን ደብቆ በመያዝ እያንዳንዱን በማሞኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ እና በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሎሌዎቻቸው ደግሞ የቅብብሎሽ ዱላውን ከጌታቸው ራዕይ በመቀበል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያሳዩ ያሉት ንቀት የህዝቡን ምንነት ሳይገመግሙ እና ሳይረዱ በራቁት ገላው ላይ ሱፍ እየጎተቱ መሆኑን በውል ሊያጤኑት ይገባል፡፡ አቶ መለስ እና ጋሻጃግሬዎቻቸው አሰብን እና ባድመን በቤሣ ቁርጥራጮች ካስረከቡ በኋላ ዝምታ ብቻ መልስ ስላገኙ ከዚያ ነገር አንድ ቁም ነገር ተምረዋል፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያን ግዛት የእነርሱ የግል እንደፈለጉ የሚለውጧት፣ የሚሸጧት የህግ ተጠያቂነት የሌለበት የግል ንብረታቸው መሆኗን አረጋገጡ፡፡
በመለስ/ኃይለማርያም ከምዕራብ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መሬት በመቁረስ ለሱዳን ለመስጠት የሚደረግ ማንኛውም “ስምምነት” ህገመንግስታዊ አይደለም፡፡
እ.ኤ.አ. ወደ 2008 መለስ ብለን ስናይ አቶ መለስ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ለሱዳን ወይም ደግሞ ለማንም ቢሆን ለመስጠት ህጋዊ ስልጣን የላቸውም ብዬ ተከራክሬ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ለሱዳን የመስጠት ህጋዊ መብትም ሆነ ስልጣን የላቸውም፡፡ ይህንን ካልኩ ዘንድ አቶ መለስ “ከአማራ ክልል ግዙፍ የሆነ መሬት” ቆርሰው ለሱዳን ለመስጠት “ስምምነት” እንደተፈራረሙ አጠያያቂ ነገር አይደለም፡፡ አቶ ኃይለማርያም እና ጌቶቻቸው ይህን ህገወጥ የመሬት ዕደላ ዕኩይ ተግባራቸውን “የስልታዊ/ስትራቴጂክ ስምምነት ማዕቀፍ” በማለት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመክፈት ጣፋጭ በማስመሰል በማር የተለወሰ መርዛቸውን ሊግቱን ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ምንም ዓይነት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳንም ሆነ ለማንም ሌላ አገር አሳልፎ የመስጠት ህገመንግስታዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ መብትም ስልጣንም የለዉም፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ሊታይ የሚችለው ይህ የተካሄደው የድብቅ ስምምነት የኢትዮጵያን ህገመንግስት አንቀጽ 12 የሚጻረር ስለሆነ የህገመንግስት ጥያቄን ያስነሳል፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ እና እርሳቸውን ተክተው በመስራት ላይ ያሉት የአሁኖቹ ገዥዎቻችን ከኢትዮጵያ ህዝብ እና ከተወካዮች ምክር ቤት በሸፍጥ ደብቀው ከኦማር አልባሽር ጋር ያደረጉትን የሚስጥር “ስምምነት” እየተባለ የሚጠራውን ተግባራዊ ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህግመንግስት አንቀጽ 12 ስር (“የመንግስት የስራ ድርሻ እና ተጠያቂነት“) እንዲህ ይላል፣ “መንግስት ተጣያቂነት እና ለህዝብ ግልጽነት ባለበት ሁኔታ ስራውን ይሰራል… ማንም የህዝብ ባለስልጣን ወይም ተመራጭ በህግ የተሰጠውን ስልጣን በህግ አግባብ ካልተጠቀመ ተጠያቂ ይሆናል፡፡” አቶ መለስ እና ተኪዎቻቸው “የህዝብ ባለስልጣን” እንደመሆናቸው መጠን ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ስራቸውን ለማከናወን ህገመንግስታዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ለህዝብ ሳይቀርብ እና የስምምነቱ ሁኔታም በዝርዝር ምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንዲሁም ህጋዊ ስልጣን የተሰጠው የተወካዮች ምክር ቤት ሳያጸድቀው የአገርን የግዛት አንድነት በመጣስ መሬት ቆርሶ ለሌላ አገር ለመስጠት በእራስ ፈቃድ የሚደረግ የሚስጥር ስምምነት የህገመንግስቱን አንቀጽ 12 ይጻረራል፣ ሙሉ በሙሉም ህገመንግስቱን ይደፈጥጣል፡፡
እዚህ ላይ በአቶ መለስ እና በተኳቸው የዕኩይ ምግባር ተባባሪዎቻቸው ሸፍጥ በተሞላበት ሁኔታ በስውር መሬት ለሱዳን ለመስጠት እየተደረገ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ መልኩ ቁልፍ የሆኑ የህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እነዚህም፣ 1ኛ) አቶ መለስም ሆኑ አቶ ኃይለማርያም በኢትዮጵያ ስም ሆነው ቀያጅ የሆኑ “ስምምነቶችን” ወይም “ውሎችን” በግል ለመፈረም ህገመንግስታዊ ስልጣን አላቸውን? 2ኛ) በአቶ መለስም ሆነ በአቶ ኃይለማርያም ፊርማ የሚደረጉ “ስምምነቶች” ከኢትዮጵያ ህገመንግስት አኳያ ህጋዊ ጠቀሜታ ሊኖራቸው ይችላልን? 3ኛ) በአቶ መለስ እና በአቶ ኃይለማርያም የሚደረግ/ጉ ስምምነት/ቶች በቀጣይነት በኢትዮጵያ ስልጣንን በሚይዙ መንግስታት ተግባራዊ መሆን የሚችል/ሉ መሆን እና አለመሆኑ/ናቸው ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር እንዴት ሊታይ ይችላል? 4ኛ) በአቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም በተፈረመ ስምምነት የተሰጠ የትኛውም በሱዳን የተያዘ የኢትዮጵያ ግዛት በዓለም አቀፋዊ ህግ መሰረት በሌላ አገር እንደተያዘ ሊታይ የሚችል ነው ወይስ አይደለም? 5ኛ) የኢትዮጵያ ህገመንግስት በግልጽ እንዳስቀመጠው “የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን እና ኃላፊነቶች” መካከል “የውጭ ፖሊሲ ማውጣት እና መተግበር፣ ዓለም አቀፍ ውሎችን መዋዋል እና ማጽደቅ“ “የፌዴራል መንግስቱ” አጠቃላይ የውጭ ግንኙነቶች እና ስልጣኖች በስራ አስፈጻሚ ማኔጅመንት ተፈርመው የውጭ ግንኙነት መስኮች እና “የዓለም ዓቀፋዊ ስምምነቶች“ በፓርላማው ይጸድቃሉ/አይጸድቁም፡፡ አንቀጽ 55 (12) በግልጽ እንዳስቀመጠው ዓለም ቀፍ ስምምነቶችን በሚመለከት በስራ አስፈጻሚው ተፈርሞ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በፓርላማው ታይቶ ይጸድቃል፣ የተወካዮች ምክር ቤት ከተሰጡት ዋና ዋና ኃላፊነቶች አንዱ ስራ አስፈጻሚው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ህጎችን ፈርሞ ሲያቀርብለት ፓርላማው መርምሮ ያጸድቃል፡፡”
የአቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም በራሳቸው ፈቃድ መሬት ለመስጠት የሚያደርጓቸው “ስምምነቶች”  የህገመንግስቱን አንቀጽ 55 (12) የሚደፈጥጥ ነው፡፡ አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከሌላ መንግስታት ጋርም ስምምነቶችን ለመደራደር እና ለመፈረምም ይችላሉ፡፡ በህገ መንግስቱ የተሰጣቸው ስልጣን ለመደራደር፣ ለማርቀቅ እና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን በመፈረም ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከሌላ መንግስታት ጋር የሚያደርጓቸው “ስምምነቶች” ፊርማ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንቀጽ 55 (12) በግልጽ እንደተቀመጠው ሁሉ ካልጸደቀ በስተቀር የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ ያህል አያወጣም፡፡
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ሁለቱም መሬት ለመስጠት ከሱዳን ጋር ያደረጓቸውን ስምምነቶች ፓርላማው እንዲያጸድቃቸው ለማቅረብ ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ እንዲሁም በጨዋነት መንፈስ ቢያንስ ፓርላማው እንዲወያይበት እንኳ ስምምነቶች ለመስጠት ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ ስምምነቶችን ፓርላማው እንዲያጸድቃቸው ለማቅረብ አለመቻል ህገመንግስታዊ የስራ ኃላፊነት ድርሻን እና መርሆዎችን የጣሰ ከመሆኑም በላይ ፓርላማው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማጽደቅ ባለው ስልጣን ላይ እየተደረገ ያለ ጣልቃገብነትን የሚያመላክት ነው፡፡
አንቀጽ 86 “የውጭ ግንኙነት መርሆዎችን“፣ የ“ፌዴራል መንግስትን“ (የጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የተወካዮች ምክር ቤትን) ኢትዮዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ይገልጻል፡፡ አንቀጽ 86 ንኡስ አንቀጽ 1 እና 3 የፌዴራል መንግስቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ “በእኩልነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ፣ ዓለም አቀፍ ህጎች እንዲከበሩ የማድረግ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ“ እና ዓለም አቀፍ ህጎች እና ስምምነቶች እንዲከበሩ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ከህዝብ ፍላጎት በተጻራሪ የሚቆሙትን እንደማይቀበል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ከሱዳን ጋር የተፈረመውን ስምምነት ሚስጥር አድርገው የያዙበት ዋናው ምክንያት እነዚህ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በአገጠጠ እና በአፈጠጠ መልኩ የሚጥሱ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ዕኩይ ምግባሮቻቸውን ለመደበቅ ያሰቡት የሸፍጥ ስራ ነው፡፡ እነዚህ የሸፍጥ ሰዎች “ስምምነቶችን” ሚስጥር ማድረግ ይፈልጋሉ ምክንያቱም የኢትዮጵያን ጥቅም አሽቀንጥረው የጣሉ በመሆኑ እውነታው በተጫባጭ ጎልቶ እንደሚታይ እና ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ ከሀዲዎች መሆናቸውን ያውቃሉ እና ነው፡፡ ስምምነቱን ሚስጥር አድርጎ መያዝ ከላይ ከተጠቀሱት የተለዬ ሌላ ምክንያት በፍጹም ሊኖር አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ሚስጥር አድርገው የያዟቸውን ስምምነቶች ግልጽ ያድርጉ እና እኔ እነዚህ ስምምነቶች የተደረጉት እኩልነትን ባዛነፈ መልኩ ነው፣ ኢትዮጵያን ብቸኛ ተጎጅ ያደረገ ነው እያልኩ የምሟገተውን በመርታት ማስተባበል ይችላሉ፡፡
አንቀጽ 9 (“የህጎች ሁሉ የበላይ“) ይህንን አስመልክቶ ህገመንግስቱ የአገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሁሉም ህጎች፣ ወጎች፣ ልማዶች እና በመንግስት አካላት የሚደረጉ ውሳኔዎች ወይም የህዝብ ባለስልጣኖች ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ተጻራሪ ሆነው ከተገኙ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡ ሁሉም ዜጎች፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እና ባለስልጣኖቻቸው ህገመንግስቱን ማክበር ማስከበር እና በህጎቹም መገዛት… ማንኛውም ስልጣንን ለመያዝ የሚፈልግ አካል ሁሉ በህገመንግስቱ ከተደነገገው ውጭ ስልጣንን ለመያዝ ማሰብ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡”
በአቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም የሚደረግ ማናቸውም “ስምምነት” “ውል” “የጋራ ስምምነት” “ድርድር” አንቀጽ 55 (12)፣ አንቀጽ 86 (2) (3) ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ህገመንግስት ተፈጻሚነት የማይኖረው ህግ ወደፊት ስልጣን የሚይዙ ህጋዊነትን የተላበሱ ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት ሊቀበሉት የማይችል ዓለም አቀፍ ህግ በኢትዮጵያ ተፈጻሚነት ሊኖረው ይችላልን?
አንቀጽ 9 (4) የኢትዮጵያ ህገመንግስት እንዲህ ይላል፣ “በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች“ የአገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ናቸው፡፡” ሌሎችስ በኢትዮጰያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያልጸደቁ ዓለም አቀፍ ህጎች ምን ሊባሉ ነው?  ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ማንም ቢሆን የህገመንግስት ልሂቅ መሆንን አይጠይቅም፣ ዓለም አቀፍ ህጎች በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካልጸደቁ ድረስ የተጻፉበትን ወረቀት ያህል ዋጋ አያወጡም፡፡ ማንም ህጋዊነትን ተላብሶ ስልጣን የሚይዝ ቀጣይ የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጸሚነት በማይኖራቸው ህጎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የመፈጸም ግዴታ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ እንደዚህ ያሉትን ስምምነቶች የማውገዝ እና ሱዳኖች ከህግ አግባብ ውጭ በተጽዕኖ ከያዟቸው ይዞታዎች ለኢትዮጵያ አስረክበው በዓለም የህግ አግባብ መሰረት ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጡ ይደረጋል፡፡
የዓለም አቀፋዊው ህግ ስምምነቶች በመንግስታት መካከል መተግበር እንዳለባቸው ግዴታ የሚጥል እንደመሆኑ መጠን (ስምምነቶች መጠበቅ አለባቸው በሚለው መርሆ መሰረት) እንደዚሁም የተወሰኑ የህግ ማዕቀፎች መንግስት ሊያወግዛቸው እና ከመተግበርም ሊቆጠብ የሚችልባቸው (ሊያቋርጣቸው) ወይም ደግሞ በመጀመሪያ ስምምነቶቹ በሚፈረሙበት ጊዜ ስህተት ተሰርቷል ብሎ ካመነ እና ካረጋገጠ ስምምነቶችን ሊሰርዛቸው ወይም ከስምምነቶች እራሱን ሊያገል እንደሚችል ዕድል ይሰጣል፡፡
የቬና ስምምነት በህግ ውል ላይ ውዝግብ በሚነሳበት ጊዜ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል ብዙ ስምምነቶች የህግ መሰረት የሌላቸው ብሎ ውድቅ ሊያደርግ እንደሚችል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አንቀጽ 46 (1)፣ (2) (“ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ውሎች“) ተፈጻሚነት የማይኖራቸውን ስምምነቶች ከአንድ አገር “የውስጥ ህጎች” አንጻር ተፈጻሚነት ሊኖራቸው እንደማይችል ከግንዛቤ በማስገባት እንዲህ ይላል፣
መንግስት ለአንድ ስምምነት ተገዥ ሊሆን የሚችለው በሀገሩ ያለውን ህግ የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ እና ያደረገው ስምምነትም በአገሪቱ ካለው የህግ ማዕቀፍ ጋር የማይቃረን እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡
በተግባር እና በልማድ መተግበር ካለበት ሁኔታ ውጭ በሆነ መልኩ አንድ መንግስት በእራሱ ህግ አውጥቶ ስምምነት ቢገባ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይችልም፡፡
አንቀጽ 49 የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “አንድ መንግስት ከሌላ እምነት ከማይጣልበት መንግስት ጋር ስምምነት ቢዋዋል ይህ ውል ተፈጻሚነት አይኖረውም“ አንቀጽ 50 እንዲህ ይላል፣ “መንግስት ከሌላ መንግስት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የማይገባ ጥቅም በመስጠት ውል የተዋዋለ ከሆነ ያ ውል በአገሪቱ ህግ ተፈጻሚነት አይኖረውም“ መንግስቱን ወይም ደግሞ የመንግስቱን ተወካይ በማስገደድ የተደረገ ስምምነት ካለ ይህ የግዳጅ ስምምነት ስምምነቱን ለማፍረስ መሰረት ይሆናል፡፡
ሊካድ የማይችለው ነገር እነዚህ ተአማኒነት የሌላቸው ስምምነቶች በአቶ መለስ እና በአቶ ኃይለማርያም በሁለቱም ባለስልጣኖች የተፈረሙ ቢሆንም ከላይ በግልጽ ለማመልከት እንደተሞከረው ከኢትዮጵያ ህገመንግስት አንጻር ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡ ሌሎች ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ቢኖሩ የሚከተሉት ናቸው፣ 1ኛ) አንቀጽ 55 (12) ከሚፈልገው የህግ ማዕቀፍ አንጻር ከሱዳን ገዥ አካል ጋር ገና ስምምነቶቹ ሲፈረሙ ግልጽ በሆነ መልክ ጉዳዩ ለሚመለከተው ፓርላማ ቀርቦ እንዲጸድቅ የተደረገ መሆን አለመሆኑ፣ 2ኛ) ስምምነቱ በሚከናወንበት ወቅት “ሙስና” እና “የማጭበርበር ወንጀል” የነበረ ወይም ያልነበረ መሆኑ፣ 3ኛ) ስምምነቱ በሚካሄድበት ጊዜ “አስገዳጅነት” ያላቸው ወይም ለማስገደድ የሚያበቁ ድርጊቶች የነበሩ ወይም ያልነበሩ መሆናቸው፣
በኢትዮጵያ ወገን በኩል ህጉን መርምሮ የማጽደቅ ሂደት ያልተከናወነ ስለነበር ኦማር አልባሽርን በሚጠቅም መልኩ የተፈጸመ እንዲሁም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ እና እንዲጸድቅ ያልተደረገ ስለሆነ የተፈጻሚነት ዕድል እንደማይኖረው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በቬና ስምምነት መሰረት ሱዳን ለኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን የማጽደቅ ዕድል መስጠት እንዳለባት የህግ ግዴታ አለባት፡፡ እራሷን ከጉዳዩ ጋር በማስተሳሰር በተለመደው ልምድ እና እምነት መሰረት ሱዳን ስምምነቱን ለማጸደቅ ስራዎችን ልትሰራ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ መልኩ ሚስጥር ሆኖ መያዙ እና በስምምነቱ ዙሪያም ምንም ዓይነት ፍንጭ እንዳይኖር ድብቅ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት አንጻር ወደፊት ስምምነቱን በጥልቀት እና በዝርዝር በመመርመር የሚገኘው የመረጃ ውጤት ሙስና፣ የማጭበርበር ወንጀል እና የግዳጅ ውል ሆኖ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን የመስጠት ስምምነቶችን ተፈጻሚነት የመሆን ዕድል የሚጻረሩ ሌሎች ህገመንግሰታዊ ጉዳዮች
አቶ መለስ እና አቶ ኃይለማርያም ግዙፍ የሆነ መሬት “ከአማራ የግዛት ክልል” በመቁረስ ለሱዳን በማስረከባቸው የአማራን ህዝብ የጋራ መብቶች ደፍጥጠዋል፡፡ “ስምምነቶቹ” አንቀጽ 39ን (የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት) እንዲሰጥ ስምምነት በተደረገበት መሬት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ ከሉዓላዊ ግዛታቸው በመነጠል ከፍላጎታቸው ውጭ ወደ ሱዳን አሳልፎ የሚሰጥ ስለሆነ ህጉ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ይጻረራል፡፡ አቶ መለስም ሆኑ አቶ ኃይለማርያም መሬት የማስመለስ፣ ብልህነት በጎደለው መልኩ በግዛት ላይ እና በግዛቱ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ድርድር የማድረግ ወይም ደግሞ በእራሳቸው ውሳኔ “የብሄሮችን እና የህዝቦችን” በመሬታቸው ላይ ያላቸውን መብት በመንጠቅ ሳይጠየቁና ምክር እንዲያደርጉ ዕድል ሳያገኙ በሌላ አባባል ሪፈረንደም ሳይሰጥ የመሬት ግዛታቸውን በድብቅ በተሸፈነ ሴራ በመንጠቅ ለሌላ አገር አሳልፎ የመስጠትም ሆነ ስምምነት የማድረግ ህገመንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ በዓለም አቀፋዊ ህግ መሰረት መንግስት የአንድን አገር ሉዓላዊ ግዛት ለሌላ ባዕድ አገር አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ሊሰጥ በታሰበው መሬት ላይ ወይም በዚያ ግዛት ላይ የሚኖሩ ህዝቦችን የማማከር ግዴታ አለበት፡፡ ማማከር ሲባልም የህግ ሂደቱን ለመጠበቅ እንጅ መንግስት ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ እጁን ዘው አድርጎ በማስገባት ምንም ዓይነት ውሳኔ መስጠት እንደማይችል ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ “በአማራ ክልል የሚገኘውን ግዙፍ የመሬት ግዛት” ለሱዳን መንግስት አሳልፎ ለመስጠት ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት በአቶ መለስም ሆነ በአቶ ኃይለማርያም በኩል ህዝቡን ለማማከር የተሞከረ ነገር የለም፡፡
ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ህግመንግስት አንቀጽ 2 የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “በዓለም አቀፍ ህግ ስምምነት እና ኢትዮጵያም ተቀብላ ባጸደቀቸው ህግ መሰረት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አባል ክልላዊ መንግስታት ፌዴሬሽን ድንበሮችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡“ ይኸ ህገመንግስታዊ ቋንቋ የአገር ውስጥ እና የውጭ የወሰን ድንበሮቻቸው ሲካለሉ እና ሲዘጋጁ “የክልል አባል መንግስታት” የሚኖራቸውን ቀጥተኛ ሚና መስተጋብር በግልጽ ያሳያል፡፡ የህገመንግስቱ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ የፌዴራላዊ መንግስት አካል መሬቱን ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት ከመፈረሙ በፊት “በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት” የወሰን ክልል ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ሪፍረንደም/referendum (ጠቅላላ የህዝብ ድምጽ) ማድረግ እንዳለበት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡
ከሱዳን ጋር የተደረገው ህገወጥ ስምምነት ተፈጸሚነት ስለማይኖረው ብዙም አያሳስብም
በአቶ መለስ፣ አቶ ኃይለማርያም እና ጓዶቻቸው የተደረገው ህገወጥ ስምምነት ተፈጻሚነት የማይኖረው ቢሆንም በመጠኑም ቢሆን አሳስቦኛል፣ ሆኖም ግን በግልጽ እና ጥልቀት ባለው መንገድ ሳገናዝበው ብዙ የሚያሳስበኝ አይሆንም፡፡ “ስምምነት” እየተባለ ስለሚጠራው ጉዳይ ብዙ የሚታወቁ ድብቆች አሉ፡፡ ስምምነቶቹን ካባ ደርበው ትልቅ ነገርን እንደፈረሙ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ግን ምን እንደደበቁ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም፡፡ ስምምነቶቹን ከህግ አግባብ ውጭ በሙስና እንዳደረጉ እናውቃለን፣ ሆኖም ግን የሙስናውን ስፋት እና ጥልቀት እስከምን ድረስ እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ስምምነቶቹ ሲፈጸሙ ማታለል እንዳለባቸው እናውቃለን፣ ሆንም ግን የማታለሉ ደረጃ እስከምን ደረጃ እንደሆነ አናውቅም፡፡ ስምምነቶቹ ሲፈጸሙ ማጭበርበር እንዳለባቸው እናውቃለን፣ ሆኖም ግን የማጭበርበሩ ስፋት እና ጥልቀት ደረጃ እስከምን ድረስ እንደሆነ አናውቅም፡፡ የስምምነት ሰነዶች ሲፈረሙ ሁሉንም ዓይነት ያካተቱ ማጭበርበሮች እንዳሉ እናውቃለን፣ ሆኖም ግን የማታለል፣ የማጭበርበር እና የመሰሪነት ዓይነቶችን አናውቅም፡፡ በድብቅ የተፈረሙት ስምምነቶች እና አሁንም ሚስጥር ሆነው የተያዙት ድሁር እና ኮሳሳ ስምምነቶች ወደፊት በጊዜ ሂደት እርቃናቸውን ወጥተው ሚስጥሩ ግልጽ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ”እውነት ለዘላለም ተቀብራ እንደማትኖር ሁሉ ተንኮልም በዙፋን ላይ ለዘላለም ተቀምጣ አትኖርም”፡፡
የኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት አንድነት በምንም ዓይነት መልኩ ለድርድር አይቀርብም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ኃይለማርያም ዳሳለኝ…ሌላም ማንም… ቢሆን በኢንቨስትመንት የማስመሰያ ጨዋታ የኢትየጵያን ለም መሬቶች በቅርጫ ለሱዳን፣ ለሳውዲ ወይም ለህንድ “ባለሀብቶች” ሊሰጥ አይችልም፡፡ እውነታው ግን ጀሴ ጀምስ እና ወሮበላ ጓዶቹ (በአሜሪካ የታውቁ ዘራፊዎች) የዘረፏቸውን ባንኮች ለሌላ የመስጠት መብት እንዳላቸው አድርገው እንዳሰቡት ሁሉ የኢትዮጵያ ቁንጮ አምባገነን መሪዎች ደግሞ የኢትዮጵያን ለም መሬት የመስጠት መብት እንዳላቸው ቆጥረውታል፡፡
ጥንታዊ የሆነች ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች፣ የእኛ እናት ሀገር፡፡ ኢትዮጵያ በክልል መከፋፈል የለባትም፣ “በጎሳ ፌዴራሊዝም” መበጣጠስ የለባትም፣ ወይም ደግሞ በድንበር መካለል ሰበብ “ስምምነት” መሰረት ግዛቷ መሸጥ የለበትም፡፡ ወደ የግዛት ሉዓላዊነት አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያ ስንመጣ ኦሮሞ ኢትዮጵያ የለችም፣ አማራ ኢትዮጵያ የለችም፣ ትግሬ ኢትዮጵያ የለችም፣ ጉራጌ ኢትዮጵያ የለችም… ወይም ደግሞ ጋምቤላ ኢትዮጵያ የለችም፡፡ በቀላሉ አነጋገር የኢትዮጵያ ህዘቦች ኢትዮጵያ ናት ያለችው፡፡ በሉዓላዊነት የግዛት አንድነት ዙሪያ በመሰባሰብ ኢትዮጵያ የማትከፈል እና የማትከፋፈል መሆኗን በማመን መተባበር አለብን፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ጠንቃቃ ሆነን መገኘት አለብን፣ እናም ከመቃብር አፋፍ ላይ ሆነው ለማትረፍ የሚፈልጉ ተንኮለኛ ጭራቆችን እራሳቸው በመቃብር ውስጥ እንዲቀሩ እናድርግ፡፡ አምላክ ሁላችንንም አንድ አድርጎ እንደፈጠረን ሁሉ በፍቅር እና በመከባበር በአንድነት በመኖር ለአምባገነንነት፣ ለጨፍጫፊነት፣ ለመለያየት ቦታ መስጠት የለብንም፡፡ ዛሬም አንዲት ኢትዮጵያ! ነገም አንዲት ኢትዮጵያ! ለዘላለምም አንዲት ኢትዮጵያ!
 ኢትዮጵያ  ለዘላለም  በክብር  ትኑር!
 ጥር 27 ቀን 2006 ዓ.

ወያኔ: የነፃው ፕሬስ ፀር!


በቅዱስ ዩሃንስ
ነፃ- ፕሬስ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዢዎች ፕሬሱ ለአንባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤ ይጠሉታል፤ ያጠፉታል። ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው።
ነፃ ፕሬስ የሀሳብ ነፃነት መብት አልፋና ኦሜጋው ነው ብል ማጋነን አይሆንም። የነፃ ፕሬስ መኖር የሚያረጋግጠው ጋዜጠኞች ያለምንም ጭንቀትና ፍርሃት የሚያስቡትን፡ የሚሰማቸውን፡ የሚሰሙትን እንዲሁም ምርምር አድርገው የደረሱበትን ዜናዎች በነፃ ለመፃፍና ለማሰራጨት ብሎም ሕዝብ እንዲወያይበት ለማድረግ ያላቸው ያልተገደበ መብት ነው። ይህም ጤናማ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ለእድገቶቹም ጉልህ ድርሻ አለው።  ነፃ ፕሬስ የኃሳብ ነፃነት ተግባራዊ ለመሆኑ ዋስትናም መፈተኛም ነው። ኃሳብን ያለምንም ጭንቀትና ፍርሃት በነፃ ለመግለፅ መቻልና መለዋወጥ እንደ ምግብና መጠጥ፤ ሁሉ ሰብአዊ ክቡርነትን የተላበሰ ሕይወት ለመጎናፀፍም አስፈላጊም ናቸው። ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት መኖርና ዋስታናው ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሕግ መረጋገጥ ማለት ዘላቂነት ላለው ዴሞክራሲያዊ እድገት ለማገኘትም ዋና መሰረት ነው።Free the Ethiopian press
የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የነፃ ፕሬስ አስፈላጊነት ትልቅ ቦታ እንዳለው ከልብ ይታመናል፡፡ ያለነፃ ፕሬስ ዴሞክራሲ አለ ብሎ መናገር ማወናበድ እንጅ እውነት ሊሆንም አይችልም፡፡  የነፃ ፕሬስ መኖር በራሱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መኖር መገለጫ ነውና፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖርም ነፃ ፕሬስ ይኖራል፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስመለስ ግን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ወያኔ መንግስት ሆኖ ላለፉት 23 ዓመታት ሃገሪቱን ሲያስተዳድር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በወረቀትና በቃል እንጂ ከዚያ በዘለለ በተግባር ሲፈፅም አላሳየንም፡፡ ለመተግበር የሞከራቸውንም እንደ ቀንዳውጣ ቀንድ መልሶ ሸሽጎታል፡፡ ስለዚህ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማያምን አምባገነን ስርአት ስለሆነ ለነፃው ፕሬስ ፀር በመሆን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በመስጠት ፋንታ አጥፊና ደምጣጭ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።
ዛሬ በዘመነ ወያኔ በኢትዮጵያችን ነፃ ፕሬስ በአሳሪና አስፈሪ የፕሬስ አዋጅ ተጠፍሯል። ጋዜጠኞች ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በየፍርድ ቤቱ እየተጎተቱ ነው። ወደ እስርቤት እየተጣሉ፤ እየተሰደዱም ነው። የጋዜጣ፣ የመጽሔት፣ የመጻሕፍት ማሳተሚያ ዋጋ ሰማይ ጠቅሷል። በሀገሪቱ ሕገመንግሥት ቀርቷል የተባለ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ጓሮ በኩል በእጅ ኣዙር ተመልሶ እንዲመጣ ተደርጔል። ሌሎች በከተማው ያሉ ማተሚያ ቤቶችም ሳንጃ የተከለ ጠመንጃ ወድሮ የሚያስፈራራ ኃይል ያለባቸው ይመስል “የተቃዋሚ ጋዜጣን አናትምም” ብለዋል። በቅርቡ በሰማያዊ ፖርቲ ‘‘ነገረ ኢትዮጵያ’’ ጋዜጣ ላይ የተሰተዋለው ችግር ይሄው ነው። ጋዜጣዋ ተዘጋጅታ ለማተምያ ቤት ብትበቃም ስርአቱ በፈጠረው የማደናቀፍ ተንኮል ለህትመት ሳትበቃ በመቅረቷ በፓርቲው ቀና ትብብር በድህረ ገፃቸው እንድናገኛት ተገደናል። ማተሚያ ቤቶች ሠርቶ የማትረፍና ሀብት የመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን  እንዲሁም ሕዝብን የማገልገል ግዴታቸውን በፍርሀት ጨርቅ ገንዘው በየማተሚያ ቤታቸው ጓሮ ቀብረውታል። የሕዝብ ንብረት የሆኑ፣ በሕዝብ ሀብት የሚተዳደሩ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሃያ አራት ሰዓት በወያኔ በሞኖፖል ተይዘዋል፡ የገዥው ልሳን ብቻ መሆናቸውንም አስመስክረዋል። ሌሎችም የተለያየ ስም እየተሰጣቸው በአየር ላይ አለን የሚሉ ጣቢያዎች ልሳናቸው የበዛ ቢመስልም ከሞላ ጎደል ቋንቋቸው አንድ ነው። ያ ቋንቋ ግን የእውነተኛ ነፃ ፕሬስ ቋንቋ አይደለም። በዚህ ዓይነት የፕሬስ ሁኔታ በሀገራችን ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም።
ይህ ነፃ ፕሬስን ማቀጨጭ ብሎም ለመቃብር ማብቃት ደግም በአለም ላይ በስፋት እንደታየው የአምባገነን መንግስታት መለዬ ካባ ነው። አምባገነኖች የሚገዙትን ህዝብ ለመቆጣጠር ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ቀዳሚው ፕሬስን መቆጣጠር ነው። በጉልበት የሚገዙት ህዝብ እነሱ ከሚሉት ውጭ እንዳይሰማ ለማድረግ ወደ ህዝብ ጆሮ የሚደርሱትን ነገሮች ሁሉ የመቆጣጠር ተግባር ይፈጽማሉ። ከዚህም በተጨማሪ ውሸትን ደጋግሞ  በማውራት እውነት ለማስመሰል ይተጋሉ። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች ሁሉ የጋራ ባህርይ ነው።  ስለዚህ ወያኔም ነፃ ፕሬስን የሚፈራበት ትልቁ ምክንያት በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት አምባገነንነቱንና የጥፋት ተልዕኮ ሚናውን አጋልጠው በሕዝብ እንዲተፋ ማድረጋቸውን በሚገባ ስለሚያውቅ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ነፃ ፕሬሶች ወያኔን ከሥልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በማወቁ ጭምር ነው።
ወያኔ ለሙያቸው ክብር ያላቸው ጋዜጠኞችን በክሶች ብዛት፤ በእስርና እንግልት እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ በሆነ የገንዘብ ቅጣት እንዲሸማቀቁ በማድረግ እውነት ዘጋቢ ስታጣ የኢትዮጵያ የመረጃ አየር በውሸት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል።   ወያኔ በፈለገው መልክ ሊተረጉመው በሚችለው አንቀጽ ጋዜጠኞችን እያስፈራራና እያዋከበ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ነፃነት መብትን ይኸው እስካሁን ድረስ እንዳፈነ ይገኛል። ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ለታሰሩ፥ ለተገደሉ፥ ለስደት ለተዳረጉ በርካታ ጋዜጠኞች ዋና ተጠያቂ ነው። የእስራት ፍርድ ተፈርዶባቸው በመማቀቅ ላይ የሚገኙ አሁንም በርካታ ናቸው። የተወሰኑትም ደግሞ ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርገዋል። በአገር ውስጥ የሚገኙ የመረጃ መረቦችን በማናለብኝነት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፤ ከውጭ አገራት የሚተላለፉ የሬድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶችን በይፋ በማፈን ኢትዮጵያ አገራችን በመረጃ ከዓለም የተነጠለች ደሴት ለማድረግ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ሃብትንም ለዚህ እኩይ ስራው ያባክናል። ነፃ- ፕሬስ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዢዎች ፕሬሱ ለአንባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤ ይጠሉታል፤ ያጠፉታል። ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው።
በመጨረሻም ወያኔ የነፃ ፕሬስ ጠላትነቱን ያረጋገጠው ሥልጣን እንደጨበጠ በመሆኑ ላለፉት 23 አመታት አንድን አፋኝ ሕግ በሌላ አፋኝ ህግ እየተካና እያጠናከረ የነፃ ፕሬስ ፀር መሆኑን ያስመሰከረ በኢትዮጵያ ላይ የመጣ መቅሰፍት ነው። ስለዚህ ለእውነት የቆመ ነፃ ሚዲያ መወለድና ማበብ በአገራችን እንዲኖር ለምንሻው ዲሞክራሲ የመሰረት ድንጋይ መሆኑን በማመን፤ ለእውነት የቆሙ ነፃ ፕሬሶች እንዲፈጠሩ መታገል የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ራሷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ያለ ነፃ ፕሬስ ማሰብ አይቻልምና:: መረጃ የተጠማው የኢትዮጵያ ህዝብም ነፃ የሚዲያ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ እንቅፋት የሆነውን የአንባገነኑን የወያኔ አገዛዝ ከጫንቃው ለማውረድ በጋራ መታገል ይኖርበታል። በተጨማሪም ነፃ ፕሬስ ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በመረዳትና፤ መብትም በትግል እንደሚገኝ በማመን የፕሬስን ነፃነትን ለማምጣት በአንድነት በመነሳት እንቅፋት የሆነውን አገዛዝ በቃህ ልንለው ይገባል።
በመረጃ የዳበረ ህዝብ አንባገነኖችን ቀባሪ ነው!
ለአስተያየትዎ፡ kiduszethiopia@gmail.com አድራሻየ ነው።

በሳንሆዜ፤ ከተማ እና አጎራባች ከተሞች፤ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤ በህብረት የወያኔን ሴራ እናምክን!!


…በሳን ሆዜ ከተማ ውህዳን የወያኔ ጀሌዎች የወያኔን ጭምብል ለብሰው “ልማታዊ” የልመና አኩፋዳቸውን አዘጋጅተው ለፌብሯዋሪ 8፣ በ770 ሞንታጊዩ ኤክስፕሬስ ዌይ ሳን ሆዜ ካሊፎርኒያ (770 Montague Expressway San Jose CA 95134) በህዝባችን እንባ ሊሳከሩ እና በሃዘኑ ሊሳለቁበት ተዘጋጅተዋል።

ሐገራችን ኢትዮጵያ የአንጸባራቂ ታሪክ ባለቤት፤ ለአፍሪካና እንዲሁም በአለም ዙሪያ ለሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች በሙሉ እንደ አጥቢያ ኮከብ የምትታይ መሆኑዋ በወዳጅም በጠላትም የተመሰከረ ሃቅ ነው። ታሪካዊ ጠላቶች፤ የሀገራችንን ሉአላዊነት፤ የህዝባችንን በራስ መተማመን፤ ሀገር ወዳድነት፤ የራሱ የሆነ ባህል፤ ወግ እና እምነት ጠብቆ መቆየት እንቅልፍ ነስቷቸው፤ ሲቻላቸው ከመሃከላችን፤ ለጠላት ያደሩ ከሃዲ ባንዳዎችን በመመልመል፤ ሳይቻል ደግሞ በቀጥታ በመዝመት እኛነታችንን ለማክሰም፤  የነበራቸው ህልም፤ በጀግኖች አባቶቻችን እና ጀግኖች እናቶቻችን ቆራጥ ተጋድሎ የወራሪው ሃይል ህልም መክኖ ቀርቶዋል።
እንዳለመታደል ታዲያ በህዝባችን ጫንቃ ላይ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የስልጣን መንበር ላይ የተፈናጠጠው ጎጠኛውና አምባገነኑ የወያኔው ቡድን ከህዝባችን ፍላጎት በተቃራኒው በመቆም፤ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ባለሙዋልና ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን፤ የሺ አመታት ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ሃገራችንን፤ ህዝቦችዋን እና በውስጡዋ ያዘለችውን አኩሪ ባህል፤ በመናቅ፤ በመካድ፤ ብሎም በዘርና በጎሳ በመከፋፈል፤ በጎጥና በቁዋንቁዋ በመነጣጠል፤ በመንደር እና
በወንዝ በመለያየት፤ የሃይማኖት ልዩነትን ወዳልተፈለገ ጥግ በመግፋት፤ የጋራ የሆኑ ታሪካዊ እሴቶቻችንን፤ እንደ ህዝብ የሚያስተሳስር ሰንደቅ አላማችንን ሳይቀር በመለወጥ፤ ህልውናችንን ከመፈታተን አልፎ፤ ወደ ማጥፋት ግስጋሴ ላይ እንደሆነ የታወቀ ነው። በዚህ ጠባብና ጎጠኛ ቡድን የአገዛዝ ዘመን፤ ታሪካዊ ሃገራችን ወደብ አልባ፤ ትውልድ አልባ፤ እምነት አልባ፤ ጀግና አልባ፤ ብሎም በአጎራባች ሃገሮች ቸርነት ላይ ተስፋዋን የጣለች፤ መጻግኡ ሆናላች ብንል የተጋነነ አይደለም። ጀግኖች ኣባቶቻችን ኣጥንታቸውን ከስክሰው፤ ከባሩድ እና ከጥይት ጋር ተጠራምሰው፤ በመርዝ ጭስ ተጨርሰው፤ እነሱ አልፈው ያቆዩትን ሰነደቅ አላማ፤ ይሄ ዘረኛ ቡድን በበርሃ ስኩዋርና በሶ ሲሸከምበት፤ ከተማ ከገባ በሁዋላም ጨርቅ ነው እያለ ሲራቀቅ እና ሲመጻደቅ የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ
ነው።
በወያኔ አገዛዝ ጋዜጠኞች አሸባረ በመባል ዘብጥያ ወርደዋል፤ የሃይማኖት አባቶች ሞት እና ሰደት እጣ ፈንታቸው ሆኖል፤ ገዳማት ተደፍረዋል፤ዜጎቸ በራሳቸው ሃገር ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ሃብት እና ንብረት የማፍራት መብታቸውን ተነፍገዋል፡ አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ እናቶቸ እና እህቶቸ የሚያመክን መድሃኒት በመስጠት የአማራው ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጉዋል። እስር ቤቶች በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በተለይም በኦሮመኛ ተናጋረ ወገኖቻችን ተጨናንቋል፤ የኑሮ ውድነቱ እማይቀመስ ሆኖል፤ በምርጫ የተሸነፋው ወያኔ በጠራራ ጸሃይ ያልታጠቁ  ህጻናትን  በአደስ አበባ እና በሌሎች ክተሞች በግፍ ፈጅቷል። የእስልምና ጉዳይ አፈላላጊ ወገኖችን በአሸባረነት ከሱዋል፤ በመሃከለኛው ምስራቅ ወጣት ሴት እህቶቻችን ለዘመናዊ ባርነት በመዳረግ በታረካችን ታይቶ እማይታውቅ ውርደት እና የሰነልቦና ጠባሳ ጥሎብናል። በጋምቤላ ዜጎችን በማፈናቀል እና የውጪ ጉቦ ሰጭዎች ለም ቦታ እንዲየዙ አድረጎል፤ በኦጋዴን ግድያው አስገድዶ መድፈሩ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እንደቀጠለ ነው፤ አልፎ ተርፎም የሃገራችን ድንበር ለሱዳን በእጅ መንሻነት ተስጥቷል።
በጣሊያን ወረራ ዘመን ድልድይና ህንጻ በመሰራቱ ወራረው ጦር ይግዛን ያላለውን እና ነጻነቱን ያስቀዳመውን ህዝባችን ዛሬ የወያኔ ደናቁርት ካድሬዎች በህዝብ ጠኔ የትላልቅ ህንጻ ባለቤት እና ባለዘመናዊ ተሽከርካሪ ባለቤት መሆናችው ያደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ፤ ላለፉት ሃያሶስት ያገዛዝ አመታት የህዝባችን ኑሮ ከድጡ ወደማጡ ማምራቱ እየታዎቀ ‘’ልማታዊ’’ የሚል ጭምብል ለብሰው ለማደናገር መሞከር ከጀመሩ ሰንበትበት ብሎል በየሄዱበት ቢከሽፍም። ዛሬ ታድያ በዚህ ብምንኖርበት በሳን ሆዜ ከተማ ውህዳን የወያኔ ጀሌዎች የወያኔን ጭምብል ለብሰው “ልማታዊ” የልመና አኩፋዳቸውን አዘጋጅተው ለፌብሯዋሪ 8፣ በ770 ሞንታጊዩ ኤክስፕሬስ ዌይ ሳን ሆዜ ካሊፎርኒያ (770 Montague Expressway San Jose CA 95134) በህዝባችን እንባ ሊሳከሩ እና በሃዘኑ ሊሳለቁበት ተዘጋጅተዋል። እኒኚህ ከሃዲዎች የወያኔን ሹማምንትም ጋብዘዋል። ከሃዲዎችን ማጋለጥ እና ቅስማቸውን መስበር ኢትዮጲያዊ ግዴታችን በመሆኑ ሁላችንም ኢትዮጲያውያን አንድ ላይ በመሆን በሌሎች ከተሞች እንደተደረገው ሳን ሆዜ ለባንዳዎች አይሆንም ልንላቸው ይገባል። እላይ በተጠቀሰው አድራሻ ክ3፡00PM በመገናኘት ድምጹን ማሰማት ላልቻለው ህዝባችን ድምጽ እንሆነው ዘንድ ጥሪ ቀርቧል።
ከአባይ በፊት ሰብዓዊ መብትን መገደብ ይገደብ !!!!
ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይፈቱ!!!!
ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር!!!
የሳንሆዜ ሀገር ወዳዶች ግብረሃይል