የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ እንደቀልድ እና እንደ እልህ የጀመሩት ”ኤርትራ ኢትዮጵያዊ አይደለችም” ብሎም ”የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” አጀንዳን የሻብያ አጀንዳ እንዲሆን ካስደረጉ በኃላ ከእሳቸው በፊት የነበረው ትውልድ ባይቀበላቸውም የእሳቸውን ትውልድ ”የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” የሚለውን ገለፃ ለመንገር አላንገራገሩም። አቶ ኢሳያስ በአንድ ጎናቸው ተንቤን ትግራይ ቢወለዱም ያነሷት ጉዳይ ግን ኢትዮጵያን ለማዳከም ለዘመናት ከሚያልሙ አንዳንድ የአረብ ሀገራትም ሆነ ጎረቤት ሱዳንን የሚያማልል ብሎም ዳጎስ ያለ ድጎማ የሚያስገኝ የወቅቱ አዋጪ ”የገበያ ማስታወቅያ” መሆኑን የተረዱት ይመስላሉ።
ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ዩንቨርስቲ በነፃ ትምህርት ዕድል ይማሩ የነበሩት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ”የኤርትራ ነፃነት ግንባር” (ELF) ከመቀላቀላቸው በፊት በቻይና የፖለቲካ እና የወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ተጉዘው እንደነበር ተወስቷል። አቶ ኢሳያስ እና ድርጅታቸው ከሰላሳ አመት ውግያ በኃላ ”ሁሉ ነገር ተፈፀመ!” ብለው ተናግረው ሳይጨርሱ ሌላ ጦርነት ”በባድሜ መሬት ሰበብ” እውነታው ግን የምጣኔ ሀብት የበላይነት ለመያዝ ከሕወሓትጋር በነበረ ግፍያ አዲስ ጦርነት ውስጥ ገብተው አስር ሺዎች ሲረግፉ አብረው ከአቶ መለስ ጋር ተዋናይ ሆነው ታዩ። ያ ”የቅኝ ግዛት ጥያቄ” ያሉት ጉዳይ አስመራን ከያዙ በኃላም ጥያቄው ተወሳሰበባቸው።
አቶ ኢሳያስ እና ድርጅታቸው ሻብያ ስልጣን ከያዘ ሃያ ሁለት ዓመታትን አስቆጠረ። በእነኝህ ሃያ ሁለት ዓመታት ውስጥ የኤርትራ ተወላጆችሲነገራቸው የነበረው ”የአፍሪካ ታይዋን ትሆናለች” ትንታኔ ሐሰት መሆኑን ተረዱት። ይልቁን ከአስመራ ዩንቨርስቲ ጀምሮ እስከ ቀድሞ በውሱን አቅም ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶችን የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም ተዳከመ። በአስር ሺዎች በሱዳን፣በኢትዮጵያ፣በየመን አድርገው ተሰደዱ።ኤርትራ ከዲፕሎማሲ እስከ አካባቢ ሃገራት ድረስ እንድትገለል አደረጉ። የአቶ ኢሳያስ ”የዓለም እይታ ፍልስፍና” የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሆነ። እሳቸው አሜሪካንን የሚያዩበት እይታ የግል አስተያየት መሆኑ ቀረና የመንግስት ቃል አቀባይ የሚናገረው ”መዝሙረ-ኤርትራ” ሆኖት አረፈው። አምባገነንነት አስደናቂው እና አዝናኝ ገፅታው ይሄው ነው።መሪው ሲያስነጥሰው ሁሉም ለመሳል ጉሮሮውን ይጠራርጋል።
”የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” የሚለው የአቶ ኢሳያስ ትውልድ ጥያቄ ዛሬም ፈተና ላይ ነው።
አቶ ኢሳያስ እና ትውልዳቸው የወቅቱ ገበያን ስሌት ያደረገው ”የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” አሁን በተነሳው ትውልድ የሚሞገትበት ጊዜ እሩቅ የሚመሰለው ካለ በሃሳቡ የመቀጠል መብቱን አከብራለሁ። ለእኔ ግን ይህ ጥያቄ በእራሱ የሚሞገትበት ጊዜ እንደሚመጣ አስባለሁ። የማኅበራዊ ትምህርት ሳይንስ ለምሳሌ የፖለቲካ ሳይንስ እንደ ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ በቤተ-ሙከራ (ላብራቶሪ) ጥናት ውጤቱን ከወዲሁ ለመወሰን አይቻልም። የሚቻለው ነገር ካለፉት፣አሁን ካለው እና መጪውን ከመተለም አንፃር በምክንያታዊ አቀራረብ ከወዲሁ ሁኔታዎችን መመልከት ነው። ከእዚህ አንፃር የኤርትራ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሶስተኛው ትውልድ ላይ የወደቀ የእዚህ የሶስተኛው ትውልድ ጥያቄም በእርሱ ታሪካዊ ሂደት የሚፈነዳበት ሁኔታ ይኖራል። የሶስቱ በኤርትራ ጉዳይ የተሳተፉ ትውልዶች ጥያቄዎች እንደዘመናቱ ”የፖለቲካ ገበያ አዋጭነት” እንደ አቶ ኢሳያስ ያሉ ተዋናዮች ተጫውተውበታል። ጥያቄው የሶስተኛውንም ትውልድ ጥያቄ አሁንም ”የፖለቲካ ገበያውን” ተመልክተው ጥያቄውን በመሞረድ የአቶ ኢሳያስ ቡድን ሊመራው ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ፈታኝ ነው። መልሱ አይመስልም ነው።
ሶስቱ በኤርትራ ጉዳይ ላይ የነበሩ ትውልዶች
የመጀመርያው ትውልድ
የመጀመርያው ከአቶ ኢሳያስ በፊት የነበሩት የጣልያን እና የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት ግፍ የሚያውቁቱ ሲሆኑ ይህ ትውልድ ከ 1900 ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ የነበረ ትውልድ ነው። በእዚህ ዘመን ውስጥ ኤርትራ መከራ ፍዳ በቅኝ ገዢዎች ማየቷን በአይን የተመለከቱ፣ የምስራቅ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን እንደህልም የሚያልሟት እና የሚወዷት ኢትዮጵያ ክፉ እንዳይነካት እንደ አይን ብሌን የሚሳሱላት ትውልድ ነበሩ። ይህ ትውልድ በግድም ይሁን በውድ በጣልያን የባንዳ ሰራዊት ውስጥ ገብቶ እስከ ሊብያ እና ኢትዮጵያ የዘመተ ቢሆንም ”ኢትዮጵያ ሀገሬን ቅኝ ገዢ አይዛትም” ብሎ እንደ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምን አፍርቶ ግራዝያንን ያቆሰለ ትውልድ ነው። የኢጣልያ ስብከት አላማው እና ግቡን ስለተረዳ ኢትዮጵያ እናት ሀገሬ አይደለችም የሚል አስተሳሰብ ማሰብ በራሱ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን እራስን መካድ መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳ ትውልድ ነው።
ጣልያን ኤርትራን በያዘችበት ጊዜ በአስመራ ከተማ ውስጥ
- ለነጮች የተከለሉ ምግብ ቤቶች እንደ አሸን መብዛታቸውን ፣
- ከምሽቱ 11 ጀምሮ አንድም ኤርትራዊ በአስመራ ጎዳና እንዳይዘዋወር (ጣልያን እና ነጮች ብቻ የተፈቀደ ስለነበር) መታገዱን፣
- በአውቶቡስ ውስጥ ሲሄድ ኤርትራውያን ከነጮች ጋር እንዳይቀላቀሉ በመጋረጃ እንዲከለል ተደርጎ እንደ ዕቃ ይሄድ የነበረ መሆኑን፣
- እስላሙ እና ክርስቲያኑ እንዲጋደል የእስላም ቤት ከውጭ የቀይ ምልክት የክርስቲያን ቤት በነጭ ቀለም እንዲቀለም መድረጉን ወዘተ ያውቃል።