…ዕለቱ የሁለት ሺ ሶስት ዓመተ ምህረት የመስቀል በዓል የተከበረበት ማግስት፤ ሰሜናዊቷ የኤርትራ አዋሳኝ ወልቃይት ገና ከእንቅልፏ ሙሉ ለሙሉ ባለመንቃቷ፣ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ጎፈሪያቸው የተንጨ(ባረረ ፋኖዎች በውስጧ ካሉ ተቋማት ወደ አንዱ እያመሩ ስለመሆኑ የጠረጠረች አትመስልም፤ ከኤርትራ የተነሱት ፋኖዎች መዳረሻ በወረዳዋ ታዋቂ የሆነው አወርቅ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመሆኑ፤ ማንም ልብ ሳይላቸው ልክ እዚያው እንደደረሱ፣ ከፊሎቹ በሰለጠነ ወታደራዊ ስልት ትምህርት ቤቱን ከአጥር ውጪ በመክበብ ድንገተኛ ጥቃት የሚሰነዝር ኃይል ከመጣ ለመከላከል ሲያደፍጡ፤ የተቀሩት ደግሞ ወደ ውስጥ በመግባት በግቢው የሚገኙ መምህራን ሜዳው ላይ እንዲሰበሰቡ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፤ በጥቂት ደቂቃዎችም ውስጥ ሁሉም በተባለበት ቦታ ተሰበሰበ፤ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በዕቅዱ መሰረት መፈፀሙን በጥንቃቄ ሲከታተል የነበረው የቡድኑ መሪ በቅድሚያ ስለራሱና ጓደኞቹ ማንነት እና ስለወከሉት ድርጅት አጭር ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ፣ የትግሉን ዓላማ በስፋት አብራርቶ አስረዳ፤ ሌሎች ጓዶቹም የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ዋና ዋና ርዕሶች የሚገልጹ በአማርኛና ትግርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶችን የማደል ስራቸውን በማጠናቀቃቸው እንደአመጣጣቸው በሽምቅ ተዋጊ ስልት ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡ ይህ በሆነ በአስራ ሁለተኛው ቀን (መስከረም 30) ደግሞ እዛው ወረዳ ወደሚገኝ ሌላ ትምህርት ቤት ለተመሳሳይ ዓላማ ድንገት ተመልሰው መጥተው ነበር፤ ሆኖም መንገድ ላይ ካደፈጡ ፖሊሶችና ታጣቂዎች ጋር ፊት ለፊት ተገጣጥመው በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ከእነርሱ ወገን አንድ ሲሰዋ፤ ከፖሊስ አባላት አንድ ቆስሏል፤ አንድ መምህርም በገዛ ቤቱ በተቀመጠበት በተባራሪ ጥይት ቆስሏል፤ ፋኖዎቹም የዚያ ቀን ዓላማቸው ከሽፎ ወደመጡበት የኤርትራ በርሃ ተመልሰው ለመሄድ ተገድደዋል…
ፊታችሁን ወደ ሰሜን…
ከወዳጆቼ ግርማ ሰይፉና በላይ ፍቃዱ ጋር መቀሌን ለመጎብኘት የነበረን ዕቅድ በተለያዩ ምክንያቶች እየተሰናከለ፤ መልሶ እየተወጠነ ጥቂት ለማይባሉ ወራት ሲጓተት ቆይቶ፣ በግንቦት መጨረሻ ዕለተ-አርብ ምሽት ላይ፣ ህወሓት እነ ለገሰ አስፋውን በኃይል አባርሮ በእጁ ወደአስገባት ሞቃታማዋ የትግራይ ርዕሰ-መስተዳድር መቀመጫ ደረስን፤ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ከባድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተፈጭተው የሚጋገሩባትን፣ የአጼ ዮሀንስ ከተማ ለአራት ቀናት ተቆጣጠርናት ስናበቃ፤ ‹ከእግር እስከ ራሷ…› ለማለት ባያስደፍርም፣ የቻልነውን ያህል በጉብኝት አካለልናት፤ በተናጠልም መነሻዬን ‹ሮሚናት› አደባባይ (መሀል እምብርቷን) አድርጌ በአራቱም አቅጣጫ ለመቃኘት ሞክሬያለሁ፤ በዋናነት ትኩረቴን የሳበው ከሰማዕታቱ ሐውልት በስተሰሜን ተንጣሎ የሚገኘው መንደር ነው፤ መንደሩ በዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተውቦ ሲታይ፣ የደቡብ አፍሪካዋ ጽዱ ከተማ ኬብ-ታዎን ያሉ ቢመስልዎ ስህተቱ የእርስዎ አይሆንም፤ ስለምን ቢሉ? እየተመለከቱ ያሉት ስነ-ሕንፃ ውበት እጅግ በተራቀቁ ዘመን አመጣሽ የግንባታ ቁሳቁሶች የተንቆጠቆጠ መንደር ነውና፡፡ ወደቦታው ይዞኝ የሄደው ጎልማሳ የባጃጅ አሽከርካሪ ‹‹በትግራይ ክልል ባሉ 46ቱም ወረዳዎች በተለያየ ጊዜ በኃላፊነት ከተመደቡ አስተዳዳሪዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ እዚህ መኖሪያ ቤት አላቸው›› ሲለኝ ግን ማመን ቢያዳግተኝም አድናቆቴ ወደ ከፍተኛ ድንጋጤ ተቀይሯል፤ ምክንያቱም ቤቶቹ በመንግስት ደሞዝ ሊሰሩ ቀርቶ፣ ሊታሰቡ እንደማይችሉ በግልፅ ያስታውቃሉና ነው፤ ታዲያ! ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምናልባት የአስተዳዳሪዎቹ ደሞዝ እንደ አክሱማውያን ዘመን በወቂት (በወርቅ ድንጋይ) ይሆን እንዴ?
የሆነው ሆኖ አንጋፋዎቹ ‹የታገለ-ያታገለ፣ በድል አጥቢያ አርበኝነት ያገለገለ፣ በሀገር ሀብት እንዳሻው የመምነሽነሽ መብት አለው› እንዲሉ፣ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ አገሬውም ይህንን እውነታ አብጠርጥሮ በማወቁ አካባቢውን ‹‹ሙስና ሰፈር›› ብሎ እንደሚጠራው ስሰማ፣ ጎልማሳው የነገረኝን ወደማመኑ ጠርዝ ተገፋሁ፡፡ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የተወያየኋቸው በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ በዛ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎችም ባለንብረቶቹ የህወሓት ካድሬዎች እንደሆኑ መስማታቸውን አረጋግጠውልኛል፡፡ በይበልጥ ደግሞ ሁለት ልጆቻቸውን በትግሉ እንዳጡ ያወጉኝ አንድ አዛውንት ምንም እንኳ እተባለው አካባቢ ሄደው ቤቶቹን በአይናቸው አለማየታቸውን ባይሸሽጉኝም፣ በተሰበረ ስሜትና ምሬት በዋጠው ድምፅ ‹‹እነርሱ በእኛ ልጆች ደም ተረማምደው፣ ለድል ከበቁ በኋላ ዓላማቸውን ትተው የሀገርን ሀብት በመዝረፍ ራሳቸውንና ዘመዶቻቸውን ባለፀጋ ማድረግ እንደቻሉ በሰማሁ ቁጥር፣ ልጆቼ የተሰዉት በደርግ ወታደሮች ጥይት ሳይሆን በገዛ የበረሃ ጓዶቻቸው ክህደት እንደሆነ አድርጌ በማሰብ በቁጭት ስለምብሰክሰክ ሀዘኑ እንደ አዲስ ያንገበግበኛል›› ሲሉ መስማት ምንኛ እንደሚያሸማቅቅ ማንም ለመገመት አይከብደውም፡፡
የዚህ አይን ያወጣ ዘረፋ መነሾም ድርጅቱ በተለይም የ1993ቱን ‹ዳግማዊ ህንፍሽፍሽ› ተከትሎ ያጋጠመውን የታማኝ ሰው እጥረት ለማሟላት መስፈርቱ ‹‹ህወሓትን እንደ ግል አዳኝ›› መቀበል ላይ የሚያተኩር እንጂ፤ የስነ-ምግባር ጉድለት ኖረ አልኖረ አሳሳቢው ባለመሆኑ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በዚህ ድምዳሜም የቀድሞ አመራሮቹ ጭምር እንደሚስማሙ አስተውያለሁ፡፡ እውነታውን የሚያውቀው የከተማዋ ነዋሪም ቢሆን፣ ደፍሮ ህወሓትን ‹‹ሌባ!›› ብሎ ባያወግዝም፤ ተቃውሞውን ለመግለፅ መንደሩን ‹‹ሙስና ሰፈር›› በማለት መሰየሙ በራሱ አንድ ማሳያ ነው፡፡ መቼም በመቀሌ እልፍ አእላፍ ሰላዮች ከመሰግሰጋቸውም ባለፈ፣ ከምሁር እስከ ሊስትሮ፣ ከነጋዴ እስከ አርሶ አደር በጠንካራ ጥርነፋዊ መዋቅር የተጠፈሩባት ከመሆኗ አኳያ፣ ግንባታውንም ሆነ ነዋሪው የሰጠውን ስያሜ፤ ትላንት መለስ ዜናዊ፣ ዛሬ ደግሞ እነ አባይ ፀሀዬ ‹አልሰሙ ይሆናል› ብሎ ማሰቡ “ፀሀይ በምዕራብ ትወጣለች” አይነት ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሌላው የከተማዋ ‹‹ጥቁር ሐውልት›› ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ በ2003 ዓ/ም በወርሃ ነሐሴ በታተመችው ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ላይ (በቅርቡ ባሳተመው ‹‹ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ›› በተሰኘ መጽሐፉም አካቶታል) ‹‹ገረቡቡ-የመቀሌው አፓርታይድ መንደር›› በሚል ርዕስ ካስነበበን ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ›› ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ዮናስ በጽሑፉ እንደገለፀው መንደሩ የተመሰረተው በድፍን መቀሌ በምቾቱ የተሻለ በሚባለው መልከዓ-ምድር ላይ ነው፤ ባለቤቶቹ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ጥቂት ባለሀብቶች መሆናቸውንም ሆነ፣ የደቡብ አፍሪካውን የጭቆና ስርዓት የሚያስታውሰው መጠሪያ ስሙ ከመንደሩ አጎራባች ያሉ የኤስ.ኦ.ኤስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዳወጡለት ወዳጃችን ዮናስ ጨምሮ ማስነበቡ አይዘነጋም፡፡ …እነሆም መቀሌ እንዲህ ነች፤ በጉራማይሌ ገፅታ የተገነባች፤ ህወሓታውያኑን በምቾት የምትንከባከብ፤ ሰፊውን ሕዝቧን ደግሞ ምድራዊ ፍዳ የምታስቆጥር፡፡
በነገራችን ላይ ከተማዋ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ መግዘፏን አስተውያለሁ፤ ይህ ግን የፈረደበት ድፍን ትግራዋይን በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ሆኗል እንደማለት አይደለም፤ ዳሩ የዚህ አይነቱን የሕንፃ ጋጋታ ከክልሉ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የአድሎአዊነት ማሳያ አድርገው ሊወስዱት እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡ ጥያቄው ግን ይህ አይደለም፤ ይልቁንም ሰማይ ጠቀሶቹ ፎቆቿም ሆኑ ዘመናዊ ሆቴሎቿ አሊያም ቤተ-መንግስትን የሚያስንቁ መኖሪያ ቤቶቿ ለተርታው ነዋሪ ምን ፈየዱለት? የሚል እንጂ፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለም ይህ ኩነት በዋናነት የሚያመላክተው መቀሌ፣ በህወሓት መካከለኛና ከፍተኛ ካድሬዎች፤ እንዲሁም እነርሱን በተጠጉ ባለሀብቶች ወደ ሀጢአን ቅጥርነት እየተቀየረች መሆኗን ነው፤ ይህን ለማለት ያስደፈረኝ አንድም ብዙዎቹ ግንባታዎች ግለሰባዊ እንጂ መንግስታዊ አለመሆናቸው ሲሆን፤ ሁለትም ሕንፃዎቹ መኖሪያ ቤቶች እና ሆቴሎች በመሆናቸው ነው (እያወራን ያለነው ስለኢንዱስትሪዎች አይደለም)፡፡ እናሳ! ይህ አይነት ግንባታ ለንብረቱ ባለቤቶች ካልሆነ በቀር ለትግራይ ሕዝብ ምኑ ነው? …ርግጥ ነው እነዛ ለ17 ዓመታት ያህል የሰው ልጅ ይቋቋመዋል ተብሎ የማይታሰብ መከራ እየተቀበሉ ተራሮቹን ያንቀጠቀጡ ታጋዮች፤ ከድሉ በኋላ እሳት የላሱ፣ የመርካቶ ነጋዴን በብልጠት የሚያስከነዱ ሆነዋል፡፡
እዚህ ጋ ሳይነሳ የማይታለፈው ሌላው ነጥብ የከተማዋ ነዋሪ በፍፁማዊ ጨዋነት እንግዳ ተቀባይ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ያልኩት በጉዳዩ ላይ ጥናት አካሄጄ ሳይሆን፣ በየሬስቶራንቶች እና መንገዶች ላይ ካጋጠሙኝ በመነሳት በደምሳሳው የታዘብኩትን ተንተርሼ መሆኑን በትህትና እገልፃለሁ፡፡ ጓል መቀሌዎችንም፣ ‹‹የቐንየልና፣ ክብረት ይሃበልና!›› እላለሁ (ይህ ምስጋና ግን የደህንነት ሰራተኞችንም ሆነ፤ ችግር እንዳይፈጠርብን ሊጠብቀን እንደመጣ የገለፀውን የከተማዋ ፖሊስ አዛዥን አይመለከትም፡፡)
የሹክሹክታ ወሬ…
መቀሌ በከፍተኛና መካከለኛ ካድሬዎች የቅንጦት መኖሪያ ቤቶች ከመጥለቅለቋ በተጨማሪ፣ ገዥው-ፓርቲን በተራ ወቀሳም ቢሆን ስሙን ማንሳት ላልተጠበቀ የከፋ አደጋ የሚዳረግባት የአፈና መንደር መሆኗን ለመታዘብ ብዙ ድካም የሚጠይቅ አይደለም፤ በጥቂት ቀናት ቆይታዬም የታዘብኩት እውነታ አረናንና አንድነት ፓርቲን ተቀላቅለው ከሚታገሉ የከተማዋ ወጣቶች በስተቀር፣ በነዋሪው ላይ አስፈሪ ፍርሃት ማርበቡን የሚያስረግጥ ነው፡፡ በተለይም አድራሻና ማንነታቸው የማይታወቅ ‹‹ነጭ ለባሽ›› የሚል ተቀፅላ መጠሪያ ያላቸው ታጣቂዎች ‹በተቃዋሚነት የጠረጠሩትን በሙሉ አፍነው በመውሰድ ያሻቸውን ያደርጉታል› የሚል ወሬ በሹክሹክታ መዛመቱ፣ የፍርሃቱ አንድ መነሾ ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡ ወሬው በሕዝብ ዘንድ ይህን ያህል ስር የሰደደ ፍርሃት ማሳደር የቻለበት ምክንያት፣ ከበረሃው ዘመን ጀምሮ ‹‹ደርግን ይደግፋሉ›› ወይም ‹‹ይሰልላሉ›› ተብለው የተጠረጠሩ ነዋሪዎችን ድርጅቱ ለእንዲህ አይነት ተልዕኮ ባሰለጠናቸው አባላቱ ከመኖሪያ መንደራቸው በውድቅት ሌሊት እያፈነ ከወሰዳቸው በኋላ የደረሱበት አለመታወቁ ነው፤ ይህ ትውልድ ለፍርሃት እጅ መስጠቱም ከዚሁ ጋር እንደሚያያዝ ይነገራል፡፡ ካድሬዎቹም እንዲህ አይነት የበረሃ ወሬዎችን ሆነ ብለው እያጋነኑና እየቀባቡ በሕዝቡ መሀል ማናፈሱን ዛሬም ስለመቀጠላቸው ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች አረጋግጠውልኛል፡፡ በአጠቃላይ በትግራይ፣ በቀድሞው የህወሓት መስራች አቶ አስገደ ገ/ስላሴ አገላለጽ ‹‹ሕዝቡ ሁሉ እስረኛ ነው››፡፡
ከአፈናዊ ማስፈራሪያዎችና ማሸማቀቂያዎች በተጨማሪ በከተማዋ ሥራ-አጥነት አለቅጥ መንሰራፋቱ እና አብዝሃው የበይ ተመልካች መሆኑ፣ የአዲሱን ትውልድ ልብ በህወሓት ላይ ካሸፈተው ውሎ ያደረ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ከወደ ሸገር ተጋንኖ የሚወራውን ያህል ባይሆንም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በመውደድ ብቻ ድርጅቱን የሚደግፉ እንደነበሩ አይካድም፤ ግና፣ ይህም ቢሆን የሰውየውን ህልፈት ተከትሎ ታሪክ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ሌላኛው የተቃዋሚውን ጎራ ያጠናከረው ምክንያት ከቀዳሚዎቹ ሁሉ የከፋ አምባገነን እንደሆነ የሚነገረው የአባይ ወልዱ ካቢኔ፣ በሙስናና መልካም አስተዳደር እጦት የሚቀርብበት ወቀሳ ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ ‹‹ነፃ አውጪ››ውን ህወሓት እና መቀሌን ለሁለት ከፍሎ የማይተዋወቁ ዓለሞች አድርጓቸዋል ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ ይህም ሆኖ ህወሓት በየትኛውም የትግራይ መሬት ተቃዋሚ ፓርቲ የመንቀሳቀስ ዕድል እንዳይኖረው ከጫካው ትግል ጀምሮ፣ በድርጅታዊ ቋንቋ ‹‹የትግራይ መሬት ከአንድ ፓርቲ በላይ መሸከም አይችልም›› የሚለውን ያልተፃፈ ሕግ ለማስፈፀም የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፤ ለአፈናው ቀንበር መክበድም ቀንደኛው መነሾ ይህ ነው የሚለው ጭብጥ የተጋነነ አይደለም፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ስዩም መስፍን እና ፀጋዬ በርሄ፡- መቀሌ፣ አጽብሃ ወአብርሃ፣ ውቅሮ፣ አዲግራት፣ ፈረስ ማይ፣ አድዋ፣ አክሱም፣ ሽሬ እንደስላሴ፣ አላማጣ እና ማይጨው ከተሞች ተገኝተው ከነዋሪዎቹ ጋር ስብሰባ በመቀመጥ፤ እንዲሁም ከነበለት፣ ማይቅነጣል፣ ዕዳጋ ዓርቢ፣ እንዳባጉና እና ሽራሮን ከመሳሰሉ ወረዳዎች ደግሞ የተወሰኑ ግለሰቦችን በተወካይነት ወደ መቀሌ በማስመጣት ‹‹ችግራችሁ ምንድን ነው? አለ የምትሉትን ቅሬታና የጎደለውን ነገር በሙሉ ንገሩን?›› በሚል መንፈስ የተቀኙ ጥያቄዎችን በማቅረብ ውይይት አካሄደው እንደነበር ይታወሳል፤ በዚህ ስብሰባም ሕዝቡ በርካታ ችግሮችን ከመዘርዘሩ ባለፈ፣ በአብዛኛዎቹ መድረኮች ስሜት የፈነቀላቸው አረጋውያን ሳግ እየተናነቃቸው ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ሊጠቃለል የሚችል ተቃውሞ መሰንዘራቸውን ሰምቻለሁ፡-
‹‹እናንተ ክዳችሁናል! ለ17 ዓመታት ልጆቻችንን በጦርነት ማግዳችሁ ስታበቁ፤ ለትግራይ ሕዝብ አንዳችም የጠቀማችሁት ነገር የለም፡፡ እንዲያውም በሌሎች ክልሎች ላይ በሚገኙ ወገኖቻችንን ላይ በምታደርሱት በደል በጠላትነት እንድንመለከት ነው ያደረጋችሁን፡፡ ከዚህ በኋላ በምንም መልኩ አናምናችሁም!!››
የቀድሞዋ የድርጅቱ የአመራር አባል አረጋሽ አዳነም ‹‹እነዚህ ሰዎች (የህወሓት መሪዎች) የምር ኢትዮጵያን ይወዳሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ተብላላብኝ›› ማለቷን ‹‹የትግራይ ሕዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ›› መጽሐፍ ገፅ 81 ላይ መገለፁ የአዛውንቶቹን አባባል ያስረግጣል ብዬ አስባለሁ፡፡
የሆነው ሆኖ እነ አባይ ፀሀዬ ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ቅሬታ ይዘው (በርግጥ መጀመሪያውኑም ችግሩ ስለመኖሩ ሳያውቁ ቀርተው አይደለም)፣ ከክልሉ ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱ ጋር ተወያይተውበት ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት አባይም በድርጅታዊ መዋቅር የቀድሞ አለቆቹ እቢሮው ተገኝተው አንድ በአንድ የዘረዘሩለትን ችግር ካደመጠ በኋላ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- ‹‹እናንተ ያነጋገራችሁት ተቃዋሚ-ተቃዋሚውን ብቻ እየመረጣችሁ ነው፤ የመጣችሁትም ልክ እንደ ተቃዋሚዎች እንከን ፍለጋ ነው››፡፡
መቼም ከዚህ የበለጠ አስገራሚ የፖለቲካ ቀልድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር ሄዶ ሄዶ አንድምታው ‹‹ህወሓት እኛ እንጂ እናንተ አይደላችሁም›› የሚል የልዩነት መልዕክት ይኖረዋልና ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመለስ ህልፈት ማግስት ‹‹የአዲስ አበባው›› እና ‹‹የመቀሌው›› ተብሎ ለሁለት መከፈሉ ሲነገር የነበረው የህወሓት የውስጥ መተጋገል ገና መቋጫ ላለማግኘቱ አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል (በነገራችን ላይ እነ አባይ ፀሀዬ በብዙ ሺህ ቅጂዎች የታተመ መጠይቅ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በትነው የነበረ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ የተሞላው መጠይቅ ተሰብስቦ ወደ አዲስ አበባ መላኩን ሰምቻለሁ፡፡ ይሁንና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን አዲስ ነገር ይኖራል ብዬ ግን አላስብም፤ ምክንያቱም ከአስራ ሶስት ዓመት በፊት በዋነኛ መሪዎቿ አንደበት ‹‹ህወሓት ከአናቷ በስብሳለች›› ተብሎ ከተመሰከረባት ክፉ ህመሟ አለመፈወሷ ዛሬም በገሀድ ይታያልና)
የትግራይ እጣ-ፈንታ
በአስከፊው የትጥቅ ትግል ያለፈው የአካባቢው ነዋሪ፣ በህወሓት ላይ የነበረው ተስፋ መሟጠጡን የሚያስረግጥልን፣ ከላይ ያየነው የመቀሌ ገፅታ እና በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ለጉምቱ የድርጅቱ ታጋዮች ያቀረቡት ብሶት ብቻ አይደለም፤ አርሶ አደሩም በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ በስቃይና በድህነት ኑሮውን የመግፋቱ ጉዳይ ጭምር እንጂ፡፡ በተለይም መሬትና ማዳበሪያ ወሳኝ የፖለቲካ ካርድ ሆነዋል፡፡ ማዳበሪያው በክልሉ በጀት የሚገዛ ቢሆንም፣ በዱቤ የማከፋፈሉን ስራ የሚያሳልጠው ደደቢት ብድርና ቁጠባ ነው፡፡ ብዙሃኑ አርሶ አደርም ከዚህ ተቋም በዱቤ የገዛውን ማዳበሪያ መክፈል ባለመቻሉ በዕዳ የመያዝ ክፉ ዕጣ-ፈንታ ይገጥመዋል፡፡ ስለዚህም ያለው አማራጭ ሁለት ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሚስቱንና ልጆቹን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለልመና አሰማርቶ በሚያገኘው ገንዘብ እንደምንም ዕዳውን ከፍሎ፣ የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት መያዝ የሚችልበትን አጋጣሚ ማመቻቸት፤ ወይም ከህወሓት ጎን በመቆም ዕዳው ተሰርዞለት፣ የሴፍቲኔት ተጠቃሚም ሆኖ በጭቆና አገዛዝ ውስጥ ማዝገም ነው፡፡ ላለፉት ሃያ ሶስት ዓመታትም የሰሜን ኢትዮጵያ መልከዓ-ምድር ይህን በመሰለ ፍርሃትና በአንድ ርዕዮተ-ዓለም ተጠርንፎ ማደሩን ማን ይክደው ይሆን?
የመጪው ጊዜያት የብቻ ፍርሃት…
በዚህ አውድ የማነሳው የትግራውያን ከባድ ፍርሃት፣ ከክፉው የህወሓት አስተዳደር ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በሀገሪቱ በነቢብ ገዥ-ፓርቲ ተደርጎ የሚታሰበው ኢህአዴግ መሆኑ ባይስተባበልም፣ ግንባሩን የፈጠሩት አራቱ ድርጅቶች በፖለቲካዊ ተፅእኖም ሆነ በአንዳንድ መንግስታዊ ቁልፍ ኃላፊነቶች ላይ እኩል ውክልና ያሌላቸው መሆኑ አያከራክርም፤ ይህንን ያፈጠጠ ሀቅ አምኖ አለመቀበሉም መፍትሔውን ሊያርቀው እንደሚችል መዘንጋት የለብንም፡፡ ለማሳያም እንደ ኢህአዴግ ባለ አምባ-ገነን አገዛዝ ውስጥ ከምንም በላይ ወሳኝ የሆኑት የደህንነት እና የመከላከያ ሠራዊቱ አወቃቀር በህወሓት የበላይነት መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊም በመከላከያ ውስጥ ያለውን ፍትሓዊ ያልሆነ ውክልና ከማመኑም በዘለለ፣ በበረሃው ዘመን ታጋዩ በአብላጫው የህወሓት አባል የነበረ መሆኑን እንደ ምክንያት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በአናቱም ድርጅቱ በመሀል ሀገር ያጣውን ድጋፍ ለማካካስ፣ ራሱን የትግራይ ብሔረተኛ አስመስሎ ከማቅረቡም ባለፈ፣ እንዲህ አይነት ከፋፋይ መንፈሶች እንዲናኙ በርትቶ ለመስራቱ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፤ ‹‹እኛ ከሌለን የትግራይ ህዝብ ለአደጋ ይጋለጣል›› ከሚለው አፍራሽ ቅስቀሳው አልፎ፣ በ97ቱ ምርጫ ወቅት የኢንተርሃሞይ ጨዋታን ወደ ክርክሩ መድረክ ያመጣበትን አውድ እና በ2002ቱ ምርጫ አንድነትን ወክሎ በተምቤን ለመወዳደር የቀረበውን አቶ ስዬ አብርሃንም ሆነ አረና ፓርቲን ለማጥላላት የተጠቀመበትን ፖለቲካ መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው፡፡ በቅርቡ የሙስሊሙ መንፈሳዊ መሪዎችም ምርምራ የተደረገባቸውም ሆነ ስቅየት የደረሰባቸው በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ መርማሪዎች መሆኑን ለፍርድ ቤት መናገራቸው ተጨማሪ ማሳያ ነው፤ መቼም የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊዎች፣ ከሌሎች ብሔሮች የተገኙ መርማሪዎችም ሆነ ጨካኝ ገራፊ የፖሊስ አባላት አጥተው አይመስለኝም፤ እንዲህ አይነት አመለካከት በሕዝብ ዘንድ እንዲሰርፅ የሚሹ ፖለቲከኞችን ትዕዛዝ ማስፈፀም እንዲቻል እንጂ፡፡ ይህ እውነታም በአንዳንድ ቦታዎች ድርጅትንና ሕዝብን ቀላቅሎ ለጅምላ ፍረጃ ማጋለጡ አሌ አይባልም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ በክልሉ ላይ ብሔራዊ ሥጋት ፈጥረው ሕዝቡን አማራጭ አልባ አድርገው ድርጅቱን እንደጋሻ እንዲመለከት ቢያስገድዱ አስገራሚ አይሆንም፡፡
ሳልሳዊ ወያኔ
በብላታ ኃይለማርያም ረዳ ፊት-አውራሪነት በ1935 ዓ/ም ትግራይን በአፄው ላይ እንድታምፅ ያነቃቃው የወያኔነት እንቅስቃሴ፤ በያኔዋ የአፄው የክፉ ቀን ወዳጅ ታላቁ ብሪታኒያ ማበር ጭምር ሲቀለበስ፤ በክሽፈቱ ፅንስ ውስጥ ሌላ ትውልድ እንደሚገነግን ግልፅ ነበር፡፡ እናም የእነ ኃይለማርያምን ኢትዮጵያዊነት ጨፍልቀው የተነሱት እነ ስብሐት ነጋ፣ ያን ብርቱ የማህበረሰብ ክፍል ሰቆቃ ጠምዝዘው ከማህበረ-ባህሉ የተጣረሰ መንገድ መርጠው ሸገር ሲደርሱ፤ እነርሱኑ ካፈራ መሬት፣ የተቀለበሰውን ዳግማይ ወያኔ ረግጦ የሚነሳ ትውልድ እንደሚመጣ ዘንግተው ሰንብተዋል፡፡ ይሁንና ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስኩትን የወልቃይቱን ትምህርት ቤት ኩነት በወቅቱ በቦታው የነበረው መምህር ሀጎስ አርዓያ (ስሙ የተቀየረ) እንደተረከልኝ፣ ራሳቸውን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትህዴን/ ብለው በሚጠሩ ነፍጥ-አንጋች ፋኖዎች የተፈፀመ የመሆኑ እውነታ የህወሓትን የተሳሳተ ግምት ያስረግጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ የሳልሳዊ ወያኔ ወኪል እንደሆነ እየታመነ የመጣ የሚመስለው ስብስብ ሁመራ፣ ወልቃይትና ሽሬን በመሳሰሉ ከባቢዎች እንዳሻው የመንቀሳቀስ አቅም መገንባቱ ይነገራል፡፡ ድርጅቱ ከአስራ ሶስት አመት በፊት ወደ ኤርትራ በተሰደደው የህወሓት ሰው ፍሰሀ ኃይለማርያም ተድላ አስተባባሪነት መመስረቱ ይታወሳል፡፡ እንደ ትህዴን እምነት መሪው ፍስሀ ከስድስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ መንግስት ደህንነቶች ነው የተገደለው፤ ከዚያን ጊዜም ወዲህ ሌላኛው የህወሓት አባል የነበረው ፀጋዬ ሞላ አስገዶም ከግማሽ መቶ ሺ አያንስም የሚባለውን ታጣቂ እንቅስቃሴ እየመራ እንደሆነ ንቅናቄውን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ድርጅቱ ለፕሮፓጋንዳ ሥራው የራሱ ቴሌቪዥንና ራዲዮ፤ እንዲሁም ‹‹መጽሔተ ብስራት›› የተሰኘች በአማርኛና ትግርኛ የምትዘጋጅ የህትመት ውጤት እንዳለው ይታወቃል፡፡
ትህዴን የመረጠው የትግል ስልት ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ሙግት ወደጎን ትተን፣ ኢትዮጵያን የሚመለከትበት መንገድ አስደማሚ ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም አጋማሽ በለቀቀው የፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ እንደገለጸው፣ ዓላማው ‹‹አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው››፤ የንቅናቄው ጠንከር ያለ የክልሉን የድጋፍ መሰረት ስናስተውል፣ የአንዲት ኢትዮጵያ መንፈስ የትግራዋይ ዋነኛው መለዮ መሆኑን ያስረግጥልናል፡፡ ‹ትግራይ የኢትዮጵያ መፈጠሪያ መሬት ናት› የሚለው የስብስቡ ድምፅ፣ ‹‹ትላንት የተፈጠረች›› ከሚለን ህወሓት ጋር ያለውን ተፃርሮሽ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ፕ/ር መሳይ ከበደም፣ ከሳምንት በፊት በበተኗት መጣጥፍ ለድርጅቱ ቡራኬያቸውን እንዲሰጡት ያስገደዳቸው፣ ይኸው የአንዲት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነት ምስረታ ናፍቆት ይመስለኛል፡፡ አንቀፅ 39፣ ኢትዮጵያውያን እንዲበታተኑ የሚያደርግ በከፋፍለህ ግዛ የመገንጠል ፖሊሲ የተቀኘ እንደሆነ የሚከራከረው ንቅናቄው፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት የሚያምን ነው›› ሲል ህወሓት የማያውቃትን ትግራይ ይነግረናል፡፡ መሪው ፀጋዬ ሞላም ‹‹የትህዴን አላማ የትግራይ ሕዝብ ጥያቄን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄም ለመመለስ እንደሚታገል›› አበክሮ ይሟገታል፡፡ የሆነው ሆኖ የ17ቱ ዓመታት መራር የትጥቅ ትግል ዋና ገፈት ቀማሽ በሆነች ምድር፣ ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ ‹‹ዱር ቤቴ!›› ማለታቸው ስለህወሓት ክሽፈት ‹‹ግዛቴ›› በሚለው መሬት በግላጭ መታወጅን ይመሰክራል፡፡
በመጨረሻም የለውጡ መንፈስ በመላ ሀገሪቱ እንዲናኝ ከትህዴን የጠቀስኳቸው መሰል መንፈሶች ጋር የሚስማማ አረዳድ ያለው አረና እና በስሩ የተሰባሰቡት ወጣቶችም ሆኑ የብሔሩ ልሂቃን፣ የትግራይን የመከራ መስቀል የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ግፉዓንም እንዲጋሩ የማሳመን ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በርግጥ ይህን መሰል የተንሸዋረረ አረዳድ ለመኖሩ ዋነኛው መነሾን ትህዴን በፖለቲካ ፕሮግራሙ እንዲህ ሲል መግለፁ መዘንጋት የለበትም፡-
‹‹ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ወያኔ (ማሌሊት) ለትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ጠበቃ መስሎ በመቅረብ በሌሎች ሕዝቦች ላይ እየፈፀማቸው ባሉ ግልፅና ስውር ወንጀሎች ሳቢያ የትግራይ ሕዝብ በገዛ አገሩ በአይነ-ቁራኛና በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረጉ ነው፡፡››
ያለፈው አልፏል፤ በመጪው ጊዜያት ይህን ፍርሃት አሸንፎ ትግርኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ የለውጡ አካል ለማድረግ፣ ለሥርዓት ቅየራው የሚካሄደው ትግል ዘርን መሰረት ያደረገ አግላይ የመከራ መስቀልን በጋራ ለመሸከም ዝግጁ መሆንን የሚያካትት ሊሆን ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ጠረጴዛው ላይ ያለው ምርጫ ሁለት ብቻ ነውና፤ ወይ አብሮ መውደቅ፣ አልያም በህብረት መነሳት፡፡ እስከዚያው እነ አባይ ፀሐዬን ከደርግ የሰማይ እሩምታ የከለሉ የትግራይ ተራሮች፣ ለትህዴን ጓዶችም እንደማይጨክኑ በመተማመን እናዘግማለን፡፡
Source Ethiomedia