Friday, January 3, 2014

በናታችሁ ከዚች አገር አውጡኝ!


Alex Abreham (Facebook)
በናታችሁ ከዚች አገር አውጡኝ ! በቃ ሱማሌም ኧረ ምናምን ሱዳንም ይሁን ብቻ ኢትዮጲያ የምትባል አገር የማልሰማበት አገር ውሰዱኝ !
አሁን ቤት አከራየ መጣና የቤት ኪራይ አምስት መቶ ብር ጨምር ሲለኝ ቤት አከራየ ሳይሆን ኢትዮጲያ አስጠላችኝ !! የቤት ኪራዩ ብቻ እንዳይመስላችሁ የግፍ አገር ናት ! ምንም ፍትሃዊ ነገር የላትም ! እንደድመት ወልዳ የምትበላ ጉድ !
እስካሁን የኖርኩበትን እድሜ ቢያንስ ሶስት አራተኛውን አንገቴን ደፍቸ በመማር አሳልፊያለሁ በተማርኩት ሙያም እችን ለዛዋ የተሟጠጠ አገር አገልግያለሁ ! በምሰራው ስራ በመስሪያ ቤቴ የተመሰገንኩ ባለሙያ ነኝ ! ግን አንድ ቀበሌ ለቀበሌ እያውደለደለ በአፉ የሚኖር መሃይም የቤት ባለቤት አፉን ሞልቶ ወይ ልቀቅ ወይ አምስት መቶ ብር ኪራይ ጨምር ይለኛል! የዛሬ አራት ወር ሁለት መቶ ብር አስጨምሮኛል እውነቴን ነው በአገሬ ላይ የማልጠቅም ዜጋ የመሆን ስሜት ነው የተሰማኝ ፡፡
እኔ ማንም ብር እንዲሰጠኝ አልፈልግም ሰርቸ ማግኘት የምችል ጤነኛ የተማርኩ ወጣት በመንግስት ችግር ምክንያት እንደለማኝ መመፅወት አለብኝ እንዴ እንደገና ለፍተው ያሳደጉ ቤተሰቦቸ ለእኔ ብር መደጎም አለባቸው እንዴ እንደህፃን ልጅ ለኔ ልብስ መግዛት አለባቸው እንዴ…. ውለታየን መክፈል ቢያቅተኝ እንኳን እንዳልችል እንዴት በማንም ሆዳም እገፋለሁ መብቴን እቀማለሁ
አንድ የሱማሌ ወይም የኤርትራ ስደተኛ ከእኔ የተሸለ እኔ አገር ላይ ይኖራል ! እንደዜጋ መብራት ውሃ በስርአት አላገኝም ያውም ከፍተኛ የሚባል የስራ ግብር እየከፈልኩ ! እንደዜጋ ትክክለኛ መረጃ አላገኝም ! እንደዜጋ ደፍሬ ስለችግሬ አላወራም ! ላቤን ጠብ አድርጌ የምኖር ዜጋ አባትና እናቴ እድሚያቸውን ሙሉ በፍፁም ታማኝነትና ትጋት ያገለገሏት ኢትዮጲያ ላይ እንደሁለተኛ ዜጋ መንከራተት እጣ ፋንታየ ሁኗል …… ኧረ የምን ሁለተኛ ምንም ደረጃ የሌለኝ ውዳቂ ዜጋ ነኝ እንጅ ! በእውነት ግን እኔ ትላንት ዩኒቨርስቲ ሁኘ ኢትዮጲያን የብርሃን ኩሬ አድርጌ ሳልም የነበርኩት ልጅ ነኝ …..ኦህህህ እውነቴን ነው እንደዛሬ መሮኝ አያውቅም !
ከአቅሜ በላይ እየሰራሁ የለፋሁበት ደመወዝ አምስት ሳንቲም ለመንግስት ግብር በማይከፍል ቤት አከራይ ሲቀማ መንግስት አድገሃል ልማት ምናምን እያለ ይቀባጥራል ! ወጣት ነኝ ጥሩ መልበስ ጥሩ መመገብ አለብኝ ለፍቸ ያገኘሁትን ብር በስርአት ልጠቀምበት መብት አለኝ …. በተዘዋዋሪ የመንግስት ስንፍና እና ሃላፊነቱን አለመወጣት ለማንም ስግብግብ መጫወቻ እያደረገን ነው !
የዛሬ አርባ አመት እች አገር እዛ ትድረስ እዚህ ስሜት አይሰጠኝም ወጣትነቴን እንደቀልድ በባዶ ተስፋ የምትበላ አገር ለኔ ምኔ ናት ጠልቻታለሁ አገሬን !! በውጭ አገር የሚኖሩ እንዴት የታደሉ ናቸው ! እየሸሹ ባህር የበላቸው ከፎቅ የተወረወሩ ምንኛ እድለኛ ናቸው !
ኢትዮጲያ ተስፋችንን የምታኮስስ ተስፋ ቢስ አገር ናት !! እንደዜጋ በደልን ድህነትን ፍርሃትና መሸማቀቅን ብቻ የምታሸክም አገር ናት አገሬ ! ሽ አመት በባርነት መኖር ይሻላል ኢትዮጲያ ውስጥ ከመኖር ! ስንት ጊዜ ችግሯን እንዳላየን በእናትነት ሸፋፍነን አለፍናት ስንት አመት ሙሉ ቻልን በባዶ ተስፋ ተምራችሁ ያልፍላችኋል እያሉን ዶክተር ብትሆን ኢንጅነር ምን በትሆን ምን ወፍ የለም ! ሙሰኛ አጭበርባሪ ውሸታም አስመሳይ ስትሆን ከሰውነት ክብርህ ዝቅ ስትል ብቻ እንደለማኝ ፍርፋሪ ትወረውርልሃለች !
አገሬን ጠልቻታለሁ ! ሰርቸ ለምኖር ለፍቸ ለምኖር ለእኔ ኢትዮጲያ ያደረገችልኝ ነገር ቢኖር የለፋሁበትን ገንዘብ በስግብግብነት መቀማት ብቻ ነው ! እግዚአብሄር እዚች አገር ላይ የፈጠረኝ ለምንድን ነው ? ማንም ሰው ከዚህ አስቀያሚና የግፍ የበደል የአድሎ አገር ቢያስወጣኝ እግሩ ላይ ወድቄ ከመሳም አልመለስም ! አገሬን ጠልቻታላሁ ! መልስ የሚሰጥ የሚጨነቅልኝ መንግስት የለኝም !! አገሬ ዛሬ በውስጤ ሙታለች !

በቅሎና ፈረሰ እኩል ፈሰስ


ታደለ መኩሪያ
አቶ ዳኛቸው ቢያድግልኝ፤ ‘ልጓም የበጠሰው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም የስድብ ፈረስ’ በሚል አርዕስት ፕሮፌሰሩ ባቀረቧችው ሁለት ጹሑፎች ላይ ትችታቸውን አቅርበዋል። እነርሱም አበሻና ልመና፤ አበሻና ሆድ ናቸው።Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
አቶ ዳኛቸው የፕሮፌሰሩን ጽሑፎች መገመገማቻው ወደ ኋላ ተመልሼ አንደንድ የፕሮፌሰሩን ሥራቸው ለመከለስ አስችሎኛል፤ በዚህ አመሰግናቸዋለሁ፤  ከትችት ትምህርት ማግኘትን ግንኙነትንም ለመፍጠር መቻሉን ፕሮፌሰሩ የሚያምኑ መሆናቸውን ከአንዳንድ ጹሑፋቸው ለመረዳት ችያለሁ፤ ስለሥራቸው እንጂ ስለግድላቸው አላትትም፤ የአቶ ዳኛቸው ሐሣብ የራሳቸው መሆኑን እቀበላለሁ፤ ግን የሣቱትን  በማስረጃ ለማሳየተ እሞክራለሁ፤ ጉዳዩ ስለ አቶ ዳኛቸው ወይም ስለፕሮፌሰሩ አይደለም ሁላችንንም ስለሚመለከተን የጋራ ችግር ነው።
እላይ ከቀረቡት  አበሻና ልመና፤ አበሻና ሆድ ከሚሉት ውስጥ ትኩረት የሰጧቸውን ከማቅረቤ በፊተ ለግንዛቤ  አቶ ዳኛቸው ቢያድግልኝ ለትችታቸው መደርደሪያ ያቀረቡት አረፍተነገር እነሆ፤ ‘ይህ ዕውቀትንና ሁኔታን ያላገናዘበ መፍትሄ የመጠቆም ፣ የማስተማር አቅምም የሌለው፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያዋርድ፤ ጅምላስድብን ሽሙጥ በተከታታይ ሲወርድብን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ክብራችንንለማግዶፍናለማዋረድኢትዮጵያችንንለማቋሸሽለሚተጉ ዱላ ማቀበል ይሆናል። ጸሐፊ እዚህ ላይ ሚናቸውን  አለዩም ዱላ እያቀበሉ ያሉት፤ ክብራችንን ለአቋሽሹት ሀገራችንን ለአዋረዱት በሥልጣን ላይ ላሉት ወያኔዎች ወይስ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም? ጅምላስድብ አበሻና ሆድ በሚለው ፡ ‘ሆድ ስላለው ወይም የሚበላው ስላለው አበሻ ነው’ ብለው በግልጽ አስቀምጠውታል፤ በጅምላ አይደለም ለማለት ነው። አእምሮውን ተጠቅሞ ከሆዱ በላይ ነፃነቱን ስለሚጠይቀው ስው ያለመሆኑን የሚጠቁም ነው። ይህን በምን አወከው? እመለሰበታለሁ። አቶ ዳኛቸው ከፕሮፌሰሩ ጹሑፎች ጨምቀው ያወጧቸውን እንይ፤ ‘በዓለም ሕዝቦች መሀከል ውድድር ቢደረግ ያለጥርጥር አበሻ አንደኛ ከሚወጣባቸው ነገሮች አንዱ ልመና ሳይሆን አይቀርም፣ ለአበሻ ልመና የኑሮ ዘዴ ነው’
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ከዚያ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ነው አቶ ዳኛቸውን ያስቆጣቸው የሚመስለው፤ ድምዳሜ ላይ የደረሱትም ከግብተኝነት እንጂ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ ክብራችንን ለማቋሸሽ ሆን ብሎ እንዳቀረቡት ለማመልከት ሞክረዋል።
መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ መስፍን ወልደማሪያም 2005 ዓ ም ከገጽ 194_195 ውስጥ እውነትን የመፈለጊያ ዘዴውን አስቀምጠውልናል። የተረጋገጠ እውነት ሊገኝ የሚችለው በዕውቀት ሲሆን ሌላው እውነት ከእምነት እንደሆነ ነው። ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ሰለሆነች የእኛ እውነት የሚመነጨው ከእምነት ነው ማለት ነው። ለምርምር ለክርክር ክፍት አይደለም። ከዕውቀት የሚነሳው ደግሞ የተረጋገጠ እውነት ነው። ለምርምር ለጥያቄና ለክርክር ክፍት ነው።ፕሮፌሰሩ ያለጥርጥር አበሻው አንደኛ ከሚወጣባቸው ነገሮች አንዱ ልመና ሲሉ፤ ዕውቀቱን  በተረጋገጠ እውነት ላይ መሠረቱን አድርጉ ሀብተ ሰቡን፣ ሀብተ ምድሩን ተጠቅሞ ያለማደጉንና በልመና መኖሩን ለማመላከት ነው። የዕውቀት ጉዳናን እንዳይከተል በሃይማኖት ብቻ በሚገኝ እውነት መሠረት አድርጎ ልመናን የኑሮው ዘዴ ለማድረጉ ምክንያቶችን አቅርበዋል።
‘ብልጦች እግዚአብሔርን የሚለምኑት ሥልጣን፣ ሐብትና ጉልበት ነው።እግዚአብሔር ፍርዱን እስኪሰጥ ድረስ የተለያዩ ስሞችን እየለጠፉ በተዋረድ የለማኞችን ሠራዊት ያደራጃሉ፤ ሕዝብ ሁሉ ከነዚህ የለማኞች ሠራዊት አንዱ ውስጥ ለመግባት በፉክክር ይተላለቃል፤ሠራዊት ውስጥ በመግባት የሚገኘው ጉርሻ ልጆቻቸውን እንኳን ከረሃብ የሚያድን መሆኑን ሳይገነዘቡ መብቻቸውን እያስረገጡ የሌሎችን መብት ለመርገጥ መሣሪያ ይሆናሉ።እነዚህ እንግዲህ ልመናን በማሕበረሰቡ ውስጥ ተክለው እየኮተኮቱ የሚያስፋፉ ናቸው፤ልመናን ባህል የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው።’ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፈን ወልደማሪያም የታወቁ ለማኝ ናቸው፤ 1950 አካባቢ የትግራይ ሕዝብ ተርቦ በግላቸው የሸዋ ገበሬዎችን ለምነው ለተራበው ሕዝብ አድረሰዋል፤ በ1966 ዓ ም ስለረሃብ አስከፊነት ለሕዝብ ሲያሰሙ በመንግሥት ታስረዋል፤ የኢትዮጵያው ዮሴፍ የሚል የቅጽል ስም አሰጥቷቸዋል።
‘አዳም አበሻ ሳይሆን አይቀርም ሁሉንም ነገር ብላ ከተባለው በቀር ብሎ ያስቀመጠው ይመስላል ፤ በላባችሁ ወዝ ብሉ ተብለው አዳምና ሔዋን መረገማቸውን አበሻ ገና አልሰማም አበሻ የተፈጠረው ገነት ውስጥ ቁጭ ብለህ ያለውን ሁሉ ብላ በተባለበት ጊዜ ነው፤እግዚአብሔር አበሻን ሁሉንም ብላ ሲለው ምንአልባት በጆሮው ጭራሽ አታስብ ብሎት ይሆናል።’  ነፃ ተፈጥሮው የፈጣሪውን ትዕዛዝ እንኳን እስከመጣስ  ያደርሰዋል ግን የአበሻው አዳም ይህ ለምን ተሳነው ነው የፕሮፌሰሩ ጥያቄ፤ የሰራው ሁሉ እየተባረከለት ለሚኖርባት ፣ረሃብ፣ችጋርና በሽታ የሚባል ነገር ከማይታወቅባት ገነት ወይም ጄነት ከተባለች ሥፍራ ወደ አደገኛይቱና በውስጧም ያሉ ፍጥረታት ሁሉ በጥረቱ ካላሸነፈቸው በስተቀር ሊጎዱት ወደሚችሉባት ምድር መጣሉን የሃይማኖት ሰባኪዎች ይሰብካሉ፤ ሆኖም ፈጣሪው ሰውን ወደ ምድር ሲወረውረው ከነፃነቱ ጋር መሆኑን አይሰብኩም። አዳም ያላደረገውን እኛ ኢትዮጵያዊያን ነፃነታችን  አስገፍፈን ለሆዳችን ማደራችን ስለአዳም የተነገረው አልገባንም ወይም በተሳሳተ ሁኔታ ወስደነዋል ማለት ነው። አዳም ነፃነቱን ባይሻ ኖሮ በገነት የቀረበለትን አየበላ ሆዱን እየሞላ ይኖር ነበር። ግን የማወቅ ነፃነቱን ፈለገ፣ ከሆድ ነፃነትን መረጠ፤ለዚህም ዋጋ ከፈለ፤ ከገነት ወይም ጄነት ተባረረ፤ በምድር ሰው በሰው ጭቆናን ለመቋቋም ብዙዎች ሕይወታቸውን ሰጥተዋል፤ በሀገራችንም ለነፃነታቸው ብዙዎች በእስር በግድያ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤ ፕሮፌሰሩ በመግቢያቸው እንደጠቀሱት ሆድ ሰላለው ወይም ሰለሚበላው አበሻ ነው ትንታኔ ያቀረቡት በአጭሩ ሕግ አዳምን ጥሶ ለሆዱ ያደረ ማለታቸው ነው። ለነፃነታችን ካልቆምን እኛንም ይጨምራል። በነፃነት፣ በፍትሕ፣ ሕግ አስከብረን እየኖርን ቢሆን ሆዳምነት ስድብ አይሆንም ነበር። አቶ ዳኛቸው ከነጮቹ በላይ ሆነን ነው ወይ የምንሰደበው ብለው በቁጭት ሐሣባቸውን ገልጸዋል፤ አሁን አሳቡ የገባቸው ይመስለኛል።
ከአቶ ዳኛቸው ቢያድግልኝ ጋር አንድ የምጋራቸው ሐሣብ አለኝ፤ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም የሚታወቁት ከንጉሡ ጀምሩ በአስተዳደሩ ላይ ቅዋሜ በማሰማት መፍትሄም በማቅረብ  ነበር።መሪዎቹ አልሰማ ማለታቸውን ተረድተው ይመስላል ድርና ማግ ሆነው በመብት ግፈፋው ላይ ከተሰማሩት ስብስቦች ላይ ጹሑፋቸው ያተኩራል፤ ያም ሁኔታ ከወያኔ ጋር እየዘረፉ እያዘረፉ ገለው እያስገደሉ ከሰላማዊ  ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ወያኔ ወያኔ የሚሉትን ነጥሎ ለማውጣት ያነጣጠረ ይመስላል።
የአቶ ዳኛቸው ቢያድግልኝ ወቀሳ መሰል ትችት ከቃላት አመራረጥ የቸግሩን ምንጭ ለማግኘት ያለመጣር ዳተኛነትን ያጸባርቃል።  ብዕራቸው መልክቱ ላይ ሳይሆን መልክተኛው ላይ ያተኮረ ይመስላል። በኦሮሞኛ አንድ ተረት አለ ‘ኡዳን ኪያ ሚኒን ኪያሚቲ’  አይን ምድሩ የኔ ነው የኮሶ ትሉ የኔ አይደለም፤ ይህን ፓራሣይት የኮሶ ትል መራራውን ኮሶ ጠጥቶ ከማስወገድ ይልቅ ኮሶ ማታ በማለት ማባበሉ የኮሶ ትሉን አያስወግደውም።
ታደለ መኩሪያ
tadele@shaw.ca

አልጋ ወራሹ ማነው?


ባህር ከማል
የአንድ ወጣት እድሜ አስቆጥሯል፤ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ህወሃት/ኢህአዴግ  መግዛት ከጀመረ። በብሄርና  በሃይማኖት  እኩልነት ስም ህብረተሰቡን  በመከፋፈል ለሃያ ሶስት አመታት ስልጣኑ ላይ ከመቆየቱም በላይ፤ ጥቂቶቹ የቡድኑ አባላትና ደጋፊቆቻቸው በጉቦ በዘረፋና  ለም መሬት  በመሽጠት ጭምር ሲከብሩ፤ ብዙሃኑ ሕዝብ ግን ኑሮው ከእለት እለት እያሽቆለቆለበት ሲሄድ፤ አገዛዙ ግን በአሥራ ምናምን ከመቶ አድገሃል እያለ ሕዝቡን ሊያታልለው ይሞክራልል።
በአሳ መበላት፤ በዘራፉዎች መደብደብና  መዘረፍ ከዚያም አልፎ ተገድሎ የሆድ እቃው  መቸብቸብ እንዳለ  እያወቀ ባለሁበት ሁኜ ከሚሞት እድሌን ልሞክር በማለት ክፍት በሆነለት መንገድ ከአጋሪቷ የሚሸሸው ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው ።  ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ ተርፈው   ወደ “ተፈለገበት አገር” የሚደርሱ ወገኖቻችን እዚያም ከደረሱ በኋላ የሚደርስባቸው  ስቃይና እንግልት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ለዚህም በአለም ደቻሳ በሊባኖስ፤ በሸዋዬ ሞላ በሊቢያ፤ እንዲሁም ካሜራና የድምጽ መቅረጫ ያላገኛቸው በሺዎች በሚቆጠሩ፡ ወገኖቻችን የደረሰባቸውና ዛሬም በሳውዲና እንዲሁም በደቡብሱዳ እየደረስባቸው ያለው መከራና ስቃይ በቂ ምስክርነው። በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ እንዲሉ ሊወክላቸው የሚገባው መንግስት ህገወጥ ስደተኖች ናቸው ብሎ ተሳልቆባቸዋል።
ከላይ እንደገለጽኩት የገዢው ቡድን ህብረተሰቡን በመከፋፈልና ያለውን ሃይል በመጠቀም ጭምር እስካሁን ስልጣን ላይ ለመቆየት በቅቶአል፡:
የዛሬው ሁኔታ ባለ መልኩ ለዘላልም ስለማይቆይ ሁሉም ነገር ያልፋልና እነሱ ሲያልፉ (በጡረታም ሆነ በደከመን ወይም በዘረፋው በቃን ሲገለሉ) ልጆቻቸውን ለመተካት ሽርጉዱ ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። መተካካት ይሉታል በነሱ ቋንቋ ።
የመተካካቱ ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያ እርምጃ ተተኪዎችን በአምሳያቸው ማሰልጠን ስለሆነ ለዝህም ለጆቻቸውን በውጭ ሃገር በጥሩ ትምህርት ቤቶች (በአብዛኛው ለዚሁ ጉዳይ) አስተምረዋል እያስተማሩም ነው:: በአንድ ውቅት ይህንኑ የታዘበው ጋዜጠኛ ተመስግን ደሳልኝ እንድህ ብሎ ጽፎ ነበር፡
“በእርግጥ እናንተ ሲደክማችሁ ብላቴና ልጆቻችሁን ለመተካት አስባችሁ ከሆነ የክፍለ ዘመኑ አስቂኝ ቀልድ ነው። ያውም እንዲህ የሚል..ብሶት ከወለዳቸው ወደ ደም  የወለዳቸው የሚደረግ መተካካት…በሰም እና አጥንት ቆጠራ ለስልጣን መብቃት ወይም በአባት እግር ልጅን መተካት። ይህ ከሆነ መቼም በነካ እጃችሁ የመሬት ፖሊሲያችሁንም ወደ … ርስተ ጉልት … ሲስተም መቀየር የሚኖርባችሁ የመስለኛል።”
ገዢው ቡድን እንኳንስ ለሚያስቅ ለሚያስለቅስ ያውም የደም እምባ  ተግባር ግድ የለለው መሆኑን ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ሲያሳየን የሰነበተ በመሆኑ ከተሳካለት ለሳቃችን ብዙም ደንታ የለውም። የመሬት ስሪቱንም በተመለከተ ዛሬም የመሪት ባለቤት ማን ሆኖ ነው።የገዢው ቡድን ነው ገንዘብ ሲያጥረው በእንቨስትመንት ስም መሬቶችን እየቸበቸበ ያለው።ያውም ነዋሪዎችን ከቄዬያቸው በማፈናቅል።
ሃገርን የሚያህል ነገር ለማስተዳደር አነሰም በዛ በተመሳሳይ ሁኔታ በተግባር መፈተንን የግድ ይላል። ይህንን ስል መልካም አስተዳድርን ማለቴ ሳይሆን በስልጣን ላይ እንዳለው  ቡድን ለራስ በሚያመች ሁኔታ መግዛትና ህዝቡን መቆጣጠር መቻል ማለቴ ነው። የህወሃት አባላት ይህንን በረሃ በነበሩበት ወቅት ተለማምድው ነው ቤተ-መንግስቱን የተቆጣጠሩት። ስለዚህም ለተተኪዎቻቸው የሙከራ ሜዳ ማስፈለጉ አልቀረም:: አገር ውስጥ መዋቅሩን እነሱ ስለዘረጉት ተተኪዎቻቸውን (ወራሾቹን) ለማሰልጠን ላያስችግር ይችላል። በዝህ የስለላ መዋቅራቸው (አንድ ለአምስት) ህዝቡን ለግዜውም ቢሆን ጠፍሮ ስለያዙት ስጋታቸው ሌላ ቦታ ነው። ለገዢው ቡድን የራስ ምታት የሆነውና ለወደፊትም ለወራሾቻቸው (ለማውረስ ከበቁ) ጭምር መሆኑ የሚቀጥለው የዳያስፖራው ክፍል ስለሆነ፤ ይህንን ክፍል ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ቀጥሎ፤ ዛሬ ወራሾቻቸው ከሆኑ ዳያስፖራውን መቆጣጠር ከቻሉ የተሳካ ውርስ ሊሆንላቸው ስለሚችል ይህንኑ የተያያዙ ይመስላል። ለዚህም ያለፈው ሰሞን የሳውዲ ተቃውሞ ሰልፍ ሁኔታና የነሱ ቀደም ቀደም ማለት በቂ ምስክር ነው።
ተመስገን ጽሁፉን በመቀጠል
“ከአባት አመራርም ወደ ልጆች አመራር ልታሸጋግሩን መዘጋጀታችሁም ምን አልባት የምትመሩትን ህዝብ አለማወቅ እንዳይመስልባችሁ ብትጠነቀቁ መልካም ነው። ምን አልባት የምትነጥፍው ጥገት ታልባ የተገኘውን ማውረስ እንጂ ሃገርና ህዝብን ለማውረስ መሞከር የመጨረሻ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል ።” ብሎ ነበር
እነርሱ ለምክር የሚሆን ጆሮ ያላቸው አይመስልም። ስልጣናቸውን ተጠቅመው ሀብት አፍርተዋል። የቀራቸው ለስም መጠሪያ የሚያገለግል ዶክቶሬት መሸመት ስለሆነ ይህንኑን ከሰሞኑን የአለም ረከርድ ባሻሻለ ሁኔታ ተያይዘውታል። ስልጣኑን ለልጆቻቸው ካወረሱ በኋላ በጡረተኛ ኑሯቸው ዶክተር እገለ ተባብለው ኑሯቸውን ለመግፋት።
ዳያስፖራው
የተቃዋሚው/የአማራጩ ክፍል ግን ገዚው ቡድን ካጠመደለት የክፍፍል ወጥመድ ብዙም ያመለጠ ሳይመስል 23 አመት አስቆጠረ::
የሃገር ቤቱን የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴን በተመለከተ በዘርም ሆነ በብሄራዊ ደረጃ የተደራጁ ፓርቲዎች እንደ አሸን የፈሉበ ወቅት ከመሆኑ ባሻገር ሀዝቡን በማሳተፍም ሆነ ጫና በመፍጠር ገዢውን ቡድን በህዝባዊ  ምርጫ  ለመለወጥ  አለመቻላቸው እንዳለ ሆኖ ብዙዎቹ በሰላማዊም ሆነ በሌላ አማራጭ ለሥርዓት ለውጥ ትግላቸውን ቀጥለዋል:: ለትግሉ እስካሁን ውጤታማ አለመሆን ምክንያታዊ ሃተታውን ግን ሃገር ቤት ላሉት ገምጋሚዎች ብተው መልካም ነው።
የዳያስፖራው ተሳትፎ ግን ልዩ መልክና ሚና አለው:: በተለያዩ  ምክንያቶች ከነበረበት አገር ለቆ  ወደ ሌላ አገር ለተወሰነም ሆነ ላልተወሰነ ጊዜ እየኖረ ያለ ሰው/ማኅበረሰብ ቀድሞ ለነበረበት አገር ሰዎች ‹ዳያስፖራ› ይባላል (dispersed; Diaspora /የፈለሰ፤ ፈላሻ ፡፡ ባጭሩ ይህ የዳያስፖራ  ትርጉም ሲሆን ይህ የህብረተሰብ ክፍል  ለትውልድ አገሩ (Home land) በፖለቲካው በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ኑሮ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
አፋኝ የሆኑ አምባገነናዊ መንግስታት ባሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሃገሮች ሚዲያ በገዢዎች ቁጥጥር ስር ሆኖ ለነሱ ፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት ብቻ በሚያገልግልበት ዳያስፖራው የራሱን ዘዴ በመጠቀም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ  መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ አቅም  አለው። በተለይም በአሁን የመረጃ ቴክኖሎጂ  ክፍለ-ዘመን፤ ማህበራዊ የመረጃ ልውውጦሽ በተስፋፋበት ስራውን ያቃልለታል። ሀገር ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ በገንዘብ በመደጎም አንጻርም የተሻለ አቅም ያለው ማህበረሰብ ነው።በ እንግድነትም ሆነ በቋሚነት በሚኖርበት ሁለተኛ አገሩ ባሉት መግስታት አማካይነት በትውልድ አገሩ አገዛዝ ላይ ጫና በማስፈጠርም ሚና ይጫወታል። ለዝህም ሃገራችንን በተመለከተ ምርጫ 97ትን አስከትሎ ገዚው ቡድን በህዝብ ስም የሚሰበስበውን እርዳታ በተመለከተና የ2006 የኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ተጠያቂነት ድንጋጌ ህገ-ረቂቅ (H.R.5680 (Bill) known as The Ethiopia Freedom, Democracy and Human Rights Advancement Act of 2006) በምሳሌነት የሚጠቀስነው። ለቅንጅትም ስኬታማነት ዳያስፖራው ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በተሟላ የ97 አይነቱ መንፈስ ጥንካሬ  ባይሆንም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለትግሉ ወደፊት መራምድ ተጽ እኖ ማሳደሩን እንደቀጠለ ነው። በጥቅሉ ዳያስፖራው ለትውልድ ሃገሩ (Home land ) ለሚደረገው ለውጥ የሚጫወተው ሚና የጎላ ቢሆንም፤ ወሳኝነት የለውም፡፡ ወሳኙ ህዝቡ ነው፤ ችግሩንና ብሶቱን እየኖረ ያለው እሱ ነውና።
በአንጻሩም ሁሉም የዳያስፖራው ማህበረ ሰብ አባል  ለትውልድ አገሩ እኩል ይቆረቆራል ወይም ይሳተፋል ማለት አይደልም።ሁሉም  ከህወሃት/ኢህአዴግ ከከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ የጸዳ ነው ማለትም አይደለም። እንዲያም ከሀገር ውስጥ ይልቅ መከፋፈል በጉልህ የሚታይበትና የሚተገበርበት በዳያስፖራው  ሳይሆን አይቀርም። በዘር በሃይማኖት እንዳለ ሆኖ አልፎ አልፎ በተመሣሣይ እምነትና ዘር መንደርን ጨምሮ ክፍፍል ይንጸባረቃል። የክፍፍል ወረርሺኝ ባህር ተሻግሮ እዚህ ካለንበት ሲያተራምሰን ማየቱ እጅግ ያሳዝናል:: ይህም በበኩሉ ከመተማመን መጠራጠርን፡ ከመከባበር መናናቅን፡ ከጋራነት ግለኝነትን ካንድነት መከፋፈልን አስፍኗል። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ይህንን የሚያራምዱ ጥቂት የማይባሉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በበኩሉ ትግሉን ያከብደዋል ያራዝመዋልም።
በርግጥ በግል አነሳሽነት ብዙ መስራት ቢቻልም ለአስትማማኝና ዘላቂ ውጤት ግን በጋራ መስራት አማራጭ የለውም። ለዚህም ነው የድርጅትና የመሪዎች አስፈላጊነትና ወሳኝነት። ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት አብሮ መስራት በማይቻልበት ወቅት ሰዎች የራሳቸውን ድርጅት ለመመስረት ይወስናሉ::
በርግጥ ይህ ለትግሉ ቀጣይነት አማራጭ ከመፈልግ የመነጨ ቢሆንም የድርጅት ጋጋታ ለብቻው መፍትሄ ልሆን አይችልም። ትግላችን የሚለካው ሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ባሉት የድርጅቶች ብዛት ቢሆን ኖሮ ለህዝባችን ያሰብነውን መልካም አስተዳደር እውን ባደረግን ነበር።
የድርጅት መብዛት ውድድሩን ያሰፋና የተወሰኑት ጠንክረው አሸናፊ ሆነው የወጣሉ ብለው የሚከራከሩ አልጠፉም። በሃገራችን የተፈጠሩት ድርጅቶች ግልጽ በሆነ የፖለቲካ ስርአት ላይ ሳይሆን ብሄርን መስረት ያደረጉ በመሆኑ ለፉክክር የማያመቹ ናቸው ያ ከሌለ ፉክክር ደግሞ አንዱ አሸናፊ ሆኖ መውጣቱ አይኖርም ማለት ነው። ስለዝህም መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው በሚያመቸው መልኩ የድርጅቶች አብሮ መስራት የግድ ይላል። የሰው ሃይልና ሃብት/ገንዘብ አንድ ላይ በማምጣት ያሉት ድርጅቶች እንዲጎለብቱና ትግሉን በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ይረዳል።
ብዙዎች የዲያስፖራው ማህበርሰብ አባላት፤ አቶ ሃይለማርያም የገዚው ቡድን መሪ ሆኖ ሲተኩ ከቅን አመለካከት የተነሳ፤ መሰረታዊ ባይሆንም ለውጥ ይኖራል፡ በይቅር መባባል ህዝባችንን ወደ ተሻለ አቅጣጫ መምራት ይቻላልና ጊዜ እንስጣቸው ብለው ነበር ። ያ ሳይሆን ቀረ። አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ ምንም እንኳን የተለወጠ ነገር ባይኖርም የማንዴላን ህልፈት በማስታከክ ለእውነትና ለእርቅ (truth and reconciliation) በድጋሜ ጥሪ እየቀረበ ነው።
የበደልንን ይቅር ብሎ አብሮ ለመስራት መፍትሄ መፈለግ ለሁሉም ይበጃል።  ተበዳዩ ህዝብ ነውና እሱኑ ይቅርታ ጠይቆ እሱኑ ለማገልገል አብሮ መስራት ብልህነት ነው። የቂም ፖለቲካ የትም አያደርስምና። ችግሩ ግን እርቅ የሁሉንም በጎገ ፍቃደኝነት ይጠይቃል። በምኞት ብቻ የሚሆን አይደለም። ከምኞትም አልፎ  አስገዳጅ ሆኔታዎች መፈጠር የግድ ይላል። የደቡብ አፍሪካን ስንመለከትም የአለም አቀፍ መንግስታት ጫና፣ መገለልና አለም አቀፍ ፖለቲካ አሰላለፍ በመለወጡ ጭምር እንጂ ዘረኛው የነጮች መግስት ከምንም ተነስቶ አይደለም ማንዴላንና ፓርቲያቸውን የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስን ነጻ ያደረጋቸው።
ህወሃት/ኢህአዴግ ከጥንስሡ ጀምሮ እያካሄደ ያለው የቂም ፖለቲካ ነው። ብዙ አመታት ወደኋላ ሄዶ እንድህ ነበርን/ነበራችሁ፡ ተደረግን/ተደረጋችሁ እያለ ለስልጣን መቆያ ከመጠቀም ባሻገር እየተጓዘበት ያለው መንገድ የትም እንደማያድርስ አውቆ፤ አንዴም ቆምብሎ አስቦ አብሮ የመድራትን ፍንጭ ያሳየበት ወቅት የለም።
የተቃዋሚው ክፍል ጫና ማሳደር ካልቻለ እርቅ ምኞት ሆኖ የቀራል። በርግጥ  ገዢዎቻችን ቢያውቁበት ኖሮ፤ ፕ/ት ኦባማ እንዳሉት  በፍቃደኝነት ህዝቡን ነጻ ቢያወጡ፤ እነሱ ጭምር ነበር ነጻ የሚወጡት:: ጊዜያቸው ሲደርስ መውደቃቸው ላይቀር። ያኔ ግን ለይቅርታ ጊዜው የመሸ ይሆናል።
ከዳያስፖራውም ክፍል ለሆዱ ያደረና  ከህዝቡ ይልቅ ህገር ቤት የቀለሰ ጎጆ የሚያሳስበው፤ ቤተሰቡን ሰብስቦ ለቀሪው ዘመዱ ላልሆነው የማይጨነቅ “ገለልተኛ ነኝ” ባይ፤ እኔ ፖለቲካ አልወድም ከሚለው አልፎ ፤የመቶ አመት ታሪክ እየጠቀሰ ተበድለን ነበር ፤ በተቃራኒው “ለዘመናት የነበረህን ቦታ ዛሬ ተቀማህ”  እያለ  ጢቂቶችን  የሚያስጨበጭብ….   .ወዘተ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የገዢውን ቡድን እድሜ የሚያራዝም በተቃዋሚው ጎራ  ነኝ ባይ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። የገዚው ቡድን  አንደኛውን “ጠባብ” ሌላኛውን ደግሞ “ነውጠኛው  ዳያስፖራ” ብሎ  የጠራቸዋል። ለትግብርቱ ግን ቀዳሚው እርሱ  ነው። ሁለቱም ቃላት ብዙውን ግዜ ያለቦታቸው ጥቅም ላይ ስለሚውሉ  ባይመቹኝም ከላይ የተጠቀሱትን በተመለከተ ግን ሃቁን ያንጸባርቃሉ።
ጥሩም ሆነ መጥፎው፤ ክፉም ሆነ ደግ ያለፉት የኢትዮጵያ ታሪኮች ወደድንም ጠላን የጋራ ታሪኮቻችን ናቸው። ያለፈወን ታሪካችንን መዝግበን የምናቆየውና የምናስታውሰው መጥፎውን ላለመድገምና ጥሩውን ደግሞ  ያለንበት ዘመን የሚፈቅድ ከሆነ ለማስቀጠል አሊያም በጥሩነቱ ለማስታወስ እንጂ ለቂም በቀል መጠቀሚያነት ለማዋል    አይደለም። እዚህ ላይ በማንኛውም ህብረተብ በአብዛኛው ያለፉት ታሪካዊ  ስህተቶች በስህተትነታቸው የሚታወቁት ከብዙ ጊዜ በኋላ እንጂ በወቅቱ ተጫባጭ ሆኔታ እንደ ስህተት ተደርገው  አይቆጠሩም። ከነዚህ  ስህተቱች ያመለጠና ፍጹም የሆነ የአለም ታሪክም የለም።
ህዝባችን የሚፈልገው የዛሬው ጎስቋላ ኑሮው የሚሻሻልበት፤ ነጻ አየር ተንፍሶ  በመኖር የተሻላች ሃገር ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፍበትን ሁኔታ የሚያመቻችለትን እንጂ ብዙ አመታት ወደኋላ ሄዶ  በታሪክ ያሳለፈውን ኑሮ እንዲኖር ወይም ከዛሬው  መከራና ስቃይ በተጭማሪ ያሳለፈው ችግር እያስታወሱት ለጊዚያዊ የፖሊቲካ አላማቸው መጠቀሚያ የሚያደርጉትን የአዞ እንባ የሚያነቡለትን አይደለም።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ተደራጅቶ እንደታወቁት የአይሁዶች የኩባና የአይርላንድ ዳያስፖራ ድርጅቶች ደረጃ ለመድረስ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፤ ያላቸውን ሃይልና ገንዘብ አንድ ላይ በማምጣት ልዩነትን አቻችሎ፤ ከመጠላልፍ መደጋገፍን፤ ከግትርነት ሰጥቶ መቀበልን በማስቀደም፡ ሁሉንም እኔ አውቃለህና ተከተለኝ እኔ ብቻ ልናገርና አንተ አድምጠኝ፡ ፍጹም ነኝና እኔን ለማረም አትሞክር የመሳሰሉትም ግብዝነትን ትተን፤ በተቃራኒውም የሚሰራ ሰው እንደሚሳሳት በመዘንጋት አሊያም ሆን ተብሎ ትግሉን ለማደናቀፍ የምንሰነዘረውን ቅጥ ያጣ ገንቢ ያልሆነ ትችትን፤ እንደ ጭቃ አንስቶ መለጠፍን አቁመን ለዋና ግባችን (የስርአት ለውጥ) አብረን ከሰራን፤ በየምንኖርበትርበት ሃገር የውጭ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን በማሳደርና ህገር ውስጥ ለሚደረገው ትግል የተሟላ ድጋፍ በመስጠት ገዢው ቡድን ቢያንስ ወደ ክብ ጠረጴዛ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል። ያለ ጫና ከህወሃት/ኢህአዴግ እርቅ መጠበቅ ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነው።
አላህ ኢትዮጵያን ከነ ህዝቦቿ ይባርካት
ባህር ከማል
ለአስተያየት  bahirk@hotmail.com
ዋቢ
  • ይድረስ ለኢህአዴግ አመራር አባላት ልጆቻችሁ ቻይና ምን
እየሰሩ ነው?   ተመስገን ደሳለኝ ከፍትህ ገዜጣ የተወሰደ
  • The Role of Diasporas in Peace, Democracy and Development in  the Horn of Africa   Ulf Johansson Dahre (ed.)
  • Diasporas and democratization in the post communist   World  Maria Koinova

ኢትዮጵያ የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ናት


ገለታው ዘለቀ  
ባለፉት ጥቂት ተከታታይ ጽሁፎች ላይ እንደተወያየነው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ውስጥ መግባት ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ኣማራጭ መፍትሄ ይሆናል። ታዲያ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ላሉብን ውስብስብ ሁለንተናዊ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ይሆናል ማለት ሳይሆን ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊፈቱ የሚገባቸውን ባህላዊ ማህበራዊ ችግሮች መስመር በማስያዝ በሂደት እየተፈቱ እንዲሄዱ ከማድረጉም በላይ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ ኣስተዋጾ ስላለው ነው።   በችግር ኣፈታት ጊዜ ከሚመጡት መፍትሄዎች መካከል የትኛውን ብናስቀድም ነው ሌላውን ችግርም ኣብሮ ሊፈታልን የሚችለው ብለንም እንጠይቃለንና በዚህ ረገድ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ውስጥ መግባት ሌሎች መጋቢና ተለጣጣቂ ችግሮችን ለመፍታት ይጠቅማል ከሚል ነው።
ባለፉት ዘመናችን ያሉብንን ሃገራዊ ችግሮች ሁሉ ስንዘረዝር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ምናምን እያልን ለያይተን እንዘርዝራቸው እንጂ ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ ግን ፖለቲካዊ ይዘት ባለው መንገድ ነው። ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ፖለቲካዊ ይዘት ባለው መንገድ፣ ማህበራዊውን ደግሞ ማህበራዊ በሆነ መንገድ፣ ኢኮኖሚውንና ሌሎቹንም እንደ ተፈጥሯቸው ከመፍታት ይልቅ ለሁሉም ችግር ፖለቲካን የችግር መፍቻ ቁልፍ ኣድርገን መውሰዳችንና የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት በማየሉ ችግሮቻችን መፍትሄ ሳያገኙ እንዲቆዩ ያደረገ ይመስላል። ለማህበራዊ ችግሮቻችን ሁሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ባህላዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩችን ከባህርያቸው ኣንጻር ለመፍታት ብንጥር ችግሮቻችን ኣሁን ያሉትን ያህል ኣይበዙም ነበር። በኣሁኑ ሰዓት ፖለቲካው ማህበራዊውን ህይወታችንን የነካበት ምክንያት የማያገባው ውስጥ ገብቶ በመገኘቱ ነው።
በዛሬው ውይይታችን የምናነሳው ጉዳይ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ስንል ኣንድ ቁልፍ ቃል በዚህ የመወያያ ርእስ ውስጥ ይሰመርበታል። ይህም  ስምምነት የሚለው ነው። ስምምነት ስንል ወይም እንዴት ኣድርገን ነው ወደ ስምምነት የምንመጣው ስንል  በዚህ ኣገባብ ሶስት ጉዳዩችን ይዳስሳል።
1. ያለፈውን ታሪካችንን እንዴት ኣድርገን ነው ወደ ስምምነት የምንመጣው? ታሪካዊ ግድፈቶችን እንዴት እንፍታቸው? እንዴትስ እንያቸው? በሚለው ዙሪያ ያጠነጥናል::
 2. ችግሮቻችን ታሪካዊ ብቻ ሳይሆኑ ኣሁን ድረስ ስላሉ እነዚህን ችግሮች እንዴት እንያቸው?  እንዴትስ እንዳይቀጥሉ ማድረግ እንችላለን? የሚለውን ይይዛል
3. ሁላችን የምንፈልጋትን የወደፊት ኢትዮጵያን እንዴት ኣድርገን ነው በጋራ ጥሩ መሰረት ጥለን መጻኢ እድሏን የምናበጀው? የሚለውንም ይይዛል።
እንግዲህ በነዚህ ከፍ ብለን በዘረዘርናቸው ኣሳቦች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ስንል በምን መንገድ ነው የምንወያየውና የምንስማማው? የትና በማን ኣማካኝነት ይፈጸማል? የሚሉ በጣም ተግባር የናፈቃቸው ጥያቄዎች መነሳታቸው ኣይቀርም። ምክንያቱም ሃገራችን ውስጥ ላሉት ችግሮች የመፍትሄ ኣሳብ ኣይደለም የጠፋው:: በየጊዜው በቡድንም በግልም ጠቃሚና የሃገርን ችግር ሊያቃልል የሚችል ኣሳብ ይመጣል:: ነገር ግን እነዚህን የመፍትሄ ኣሳቦች የሚያደራጅና መልክ የሚያስይዝ ባለመኖሩ እንዲሁ ኣንዱን እያነሳን ኣንዱን እየጣልን እንኖራለን።
በዛሬው ውይይታችን ስምምነት የሚለውን ኣሳብ እንዴት ልናመጣው እንደምንችል ተግባራዊ ሃሳቦችን እናነሳለን። እንግዲህ ወደ ነጥባችን እንውረድና ስምምነትን ልናመጣበት ከምንችልባቸው ዘዴዎች ኣንዱ የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽንን ኣቋቁሞ በመስራት ነው። ይህ ኮሚሽን ኣሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ቢደግፈውና ኣብሮ ቢሳተፍ እሰየው ካልሆነም ግን ከመንግስት እውቅና ውጭ መቋቋም ይችላል። መንግስት ደገፈው ኣልደገፈው የሚያመጣው ችግር ኣይኖርም። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሁዋላ እንወያያለን። ለኣሁኑ ስለ ብሄራዊ እርቅ መሰረታዊ ጉዳዮችን ኣንስተን እንወያይ።
ስለ ብሄራዊ እርቅ ምንነትና ይዘት እንዲሁም ኣፈጻጸም ስንወያይ ብሄራዊ እርቅን የምናየው  ባለፈው በተወያየንበት በስምምነት ላይ በተመሰረተ የባህል ውህደት ጽንሰ ሃሳብ ማእቀፍ (framework) ውስጥ ነው።
የብሄራዊእርቅምንነት ይዘትና ኣፈጻጸም
ከሁሉ ኣስቀድመን ብሄራዊ እርቅ የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ማለት እንደሆነ ልንበይነው ይገባል። ብሄራዊ እርቅ በኣለማችን ታሪክ ውስጥ በብዙ ኣገሮች የተፈጸመ ሲሆን የእርቁ ትርጓሜና ኣፈጻጸም እንዲሁም ግቦች ሁሉ ሊለያዩ ይችላሉ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ወደ ብሄራዊ እርቅ ለመግባት መጀመሪያ ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ሁኔታ (context) ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ካልተረዳን ብሄራዊ እርቁ ግቡን ላይመታ ይችላል። በመሆኑም ብሄራዊ እርቅ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጉዳይ ኣንስተን በሚገባ እንወያይ። ሃሳባችንን ለማፋፋት ብሄራዊ እርቅን ከኣንዳንድ ሃገሮች ታሪክ ኣንጻር በመጀመሪያ እንመልከት። ለምሳሌ  ያህል በኣውስትራሊያ ውስጥ የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ ተነስቷል። እንደሚታወቀው ከታላቋ ብሪታኒያ የኣስራ ስምንተኛው ክፍለዘመን ሰፈራ ፕሮግራም በፊት ኣውስትራሊያ በነባር(indiginious) ህዝቦች የተያዘች ኣገር እንደነበረች ይታወቃል። በሰፈራው ጊዜ በነባሮቹ ህዝቦች ላይ የመፈናቀል፣ የማንገላታት ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ዛሬ የኣውስትራሊያ መንግስት ያን የተፈጸመ ታሪካዊ  ስህተት ኣመርቅዞ እንዳይቆይ የወሰደው ርምጃ ብሄራዊ እርቅ ማድረግ ሲሆን ከ 1998 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት የብሄራዊ እርቅ ወይም (National sorry day) ኣውጆ በየዓመቱ እየታሰበ ይገኛል። የዚህ የይቅርታ ቀን ኣዋጅ የሚያሳየው ነገር ላለፉት ስህተቶች ሃላፊነት የሚወስድ ኣካል መገኘቱንና የነበረውን ግፍ እውቅና መስጠት መቻላቸውን ለወደፊቱም እንደዚያ ኣይነት ግፍ እንዳይፈጸም ዋስትና መስጠታቸውን ነው። የኣውስትራሊያ ችግር እንደኛ በሶስት መንገድ ላይታይ ይችላል። ይቅርታው ግን ለስንት ኣመት እንደሚደረግ ኣይታወቅም። ዋናው ግን በነባሩ ህዝብ ዘንድ የነፍስ ጽዳት ለማምጣት የታሰበ በመሆኑ ብሄራዊ እርቁ ለኣውስትራሊያውያን ከፍተኛ ጠቀሜታ ኣለው። የነበረውን ታሪካዊ ችግር እውቅና ሰጥቶ ይቅርታ ማወጁ የኣውስትራሊያን ህዝብና መንግስት ልበሰፊነትና ኣርቆ ኣሳቢነት ያሳያል። ነባር ህዝቦችም በዚህ የሚረኩ ይመስለኛል። ከዛ ውጭ ኣፈታሪክ እንደሚናገረው ራሳቸው ነባር ህዝቦችም ከሌላ ክፍለ ዓለም መጥተው የሰፈሩ ናቸው። ዋናው ጥያቄያቸው በሰፈራው ወቅት የነበረው ግፍና በደል ሲሆን እነሆ ዛሬ ተባብረው ዴሞክራሲያዊ መንግስት  በመመስረታቸው ታሪክን ወደ ሁዋላ ኣይቶ ለችግሮች እውቅና ለመስጠት ችለዋል።
ደቡብ ኣፍሪካን ደግሞ እንይ። በደቡብ ኣፍሪካም እንደዚሁ ታሪካዊ የሆነ ብሄራዊ እርቅ የተካሄደባት ኣገር ስትሆን ከኣፓርታይድ ኣገዛዝ ለመላቀቅም ሆነ ከተላቀቀች በሁዋላ ደቡብ ኣፍሪካን በከፍተኛ የመንፈስ ልእልና ሲመራ የነበረው የብሄራዊ እርቅ ስሜት ነው። በደቡብ ኣፍሪካ ብሄራዊ እርቅ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት መካከል Nelson Mandela ኣውራ ናቸው። በኔልሰን ማንዴላ የተመራው ደቡብ ኣፍሪካን እንደገና የማነጽ ስራ ሲጀመር ኣገሪቱ ያለፈችበትን መራራ ችግር ለመፍታት የተጠቀመችው ዘዴ በሪስቶሬቲቭ  ጀስቲስ (Restorative justice) እና ቀስ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ ቁስልን ማከምና የወደፊቷን የሁሉም የምትሆንን ደቡብ ኣፍሪካን መገንባት ይመስላል።
ደቡብ ኣፍሪካ ከኣፓርታይድ እንደተላቀቀች ወደ ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ (Retributive juctice) ኣተኩራ ቢሆን ምናልባትም ውጤታማ ኣትሆንም ነበር። ዋናው ጉዳይ ግን ደቡብ ኣፍሪካ ውስጥ የኣፓርታይድ ገዢዎች ለነበረው ችግር ሃላፊነት የመውሰድና ብሄራዊ እርቅን በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስና በዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው የጥፋትና የሞት መላእክን ከደቡብ ኣፍሪካ ሊያባርሩት ችለዋል። ታላቁ የብሄራዊ እርቅ መሪ ኔልሰን ማንዴላም በዚህ ረገድ የተጫወቱት ሚና ታሪክ ሁሌ ሲዘክረው ይኖራል።
የሩዋንዳን ጉዳይም እናንሳ። ሩዋንዳ በዚህኛው ክፍለ ዘመን የዓለምን ህዝብ ያስደነገጠ ወንጀልን ካስተናገደች በሁዋላ ወንጀሉ ጋብ ሲል የወደፊት ኣቅጣጫዋ ግራ ያጋባት ኣገር ነበረች። ለኣንድ መቶ ቀናት በየቀኑ ስምንት ሺህ ሰዎች፣ በየሰዓቱ ከሶስ መቶ ሰላሳ ሰዎች በላይ ያለቁባት ሃገር የወደፊት እጣ ፈንታዋን ለማሰብ በርግጥም እጅግ ከባድ ስራ ነበር።  በርግጥ ሩዋንዳ ያ ወንጀል ጋብ ሲል ለወደፊት እጣፈንታዋ ወዲያው ኣዋጭ መስመር መስሎ የታያት ብሄራዊ እርቅ ማውረድ ቢሆንም ብሄራዊ እርቁ በሩዋንዳ ሁኔታ ምን መልክ ይያዝ? በምን መልኩ ይፈጸም? የሚሉት ጥያቄዎች ግን በጣም ሊከብዷት የሚችሉ ጉዳዩች ነበሩ። በኣንዳንዶች ዘንድ ኣጥብቆ ይቀነቀን የነበረው ጉዳይ ብሄራዊ እርቁ በሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ኣማካኝነት ሊፈጸም ይገባዋል የሚል ነበር። ሁላችን እንደምናውቀው ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ማለት ለወንጀለኛው ተገቢውን ቅጣት በመስጠት የተበዳይን ነፍስ ማጽዳት ወይም ማርካት ማለት ሲሆን ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ደግሞ የሚያተኩረው ወንጀለኛውን በመቅጣት ላይ ሳይሆን ተበዳዩን በመካስ ላይ ያተኮረ የፍትህና የእርቅ ማውረጃ ዘዴ ነው። ታዲያ ኣንዳንድ  ሩዋንዳዊያን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ነው ፈውስ የሚያመጣልን ሲሉ በርግጥ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ኣልቀሩም። ምክንያቱም ወንጀሉ የተፈጸመው በኣጭር ጊዜ በመሆኑ፣ ወንጀሉ ግድያ በመሆኑ፣ ገዳይና የሟች ቤተሰብ ጎረቤት በመሆናቸው፣ ኣሰቃቂ ወንጀል በመሆኑ ሪትሪቢዮቲቭ ጀስቲስ ተገቢነው እንዲሉ የገፋፋቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ በኣንድ መቶ ቀናት ላለቀው ስምንት መቶ ሺህ ህዝብ ገዳዩችና ለገዳዩቹ ተባባሪዎች ፍርድ ለመስጠት ሩዋንዳ ኣቅም ኣልነበራትም። ሩዋንዳ በዚያን ወቅት ላለቁት ስምንት መቶ ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኞች ወደ ኣንድ መቶ ሺህ ወንጀለኞችን ለፍርድ ኣቅርባ መቅጣት ከፈለገች ኣጠቃላይ የፍርዱ ሂደት ወደ  ኣንድ መቶ ኣመት ይፈጅባት ነበር የሚሉ ወገኖች ኣሉ።  ሪስቶረቲቭ ጀስቲስን ተጠቅማ ችግሯን ለመፍታት ብትሞክር ደግሞ ገዳይና ሟች ጎረቤታም በመሆናቸው፣ የሟች ደም ገና ስላልደረቀ በርግጥ የሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሌላ ችግር ውስጥ መውደቁ ሌላ ኣሳብን ያመጣባት ትመስላለች። ሩዋንዳ የነበረችበት መስቀለኛ መንገድ ኣስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የጣላት በመሆኑ ሁለቱንም የፍትህ ኣሰጣጥ ዘዴዎች ኣደባልቃ እንድትሄድ ሳያስገድዳት ኣልቀረም። በመሆኑም ባህላዊ የጋካካ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የተወሰነውን ችግር በዚህ በሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ የተወሰነውን ደግሞ ዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲና በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ይፈታል እያለች እየደለለች ማርገብ ችላለች። ከሁሉ በላይ ግን ሩዋንዳ ወደ ዘጠና በመቶ የሚሆነው ህዝብ ክርስቲያን በመሆኑና ኣብያተ ክርስቲያናት የሚሰብኩት የይቅርታና የምህረት ትምህርት የሩዋንዳን ችግር በሪስቶሬቲቭ ፍትህ ለመፍታት ከፍተኛ ኣስተዋጾ ሳያደርግ ኣልቀረም። በኣጠቃላይ የሩዋንዳ ችግር ውስብስብና ኣስቸጋሪ በመሆኑ ሁለቱም የፍትህ ኣሰጣጥ ዘዴዎች ተግባር ላይ የዋሉ ይመስላሉ።
ለኣብነት በየሃገሩ የተፈጸመውን ወንጀል እያነሳን የተወያየነው ችግር በየቤቱ ኣለ፣ ይሁን እንጂ ሁሉም ሃገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ኣገር የቆመው ለማለት ነው። ወደኛው ኣገር እንመለስና ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን የብሄራዊ እርቅ ይዘት ለማየት መጀመሪያ ስለ ኣለፈው ታሪካዊ ግድፈቶች ማንሳት ተገቢ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው በኣውስትራሊያ ውስጥ ለነበረው ግፍ ሃላፊነት የሚወስድ እውቅና የሚሰጥ ኣካል ተገኝቱዋል። ወደኛ ሃገር ስንመጣ ላለፉት በደሎች እውቅና ለመስጠትም ሆነ ኣንድ ኣካል ለጥፋቱ ሃላፊነት ለመውሰድ የምንችልበት ሁኔታ ጠፍቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁሉም የባህል ቡድን በየፊናው ባለፉት ስርዓቶች ተጎድቻለሁ ባይ በመሆኑ ነው።
በኣጼ ምኒልክ ጊዜ የጠፉ ጥፋቶች ካሉ ለነዚያ ጥፋቶች የኣማራውን ህዝብ ሃላፊነት ውሰድና ይቅርታ በል የሚል ኣካል ቢነሳ ኣማራው ለራሱ ተበድያለሁ ባይ ነው። በፊውዳሉ ስርዓት በጭሰኝነት፣ በባርነት መከራየን ኣይቻለሁ:: በወቅቱ የተጠቀሙት ጥቂት ፊውዳሎች ናቸው:: ተውኝ እባካችሁ ይላል። በኣጼ ሃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን የወሎ ርሃብ ሲመጣ ሃይለስላሴ ዓለም እንዳይሰማ ኣድርገው በዚያ ደረጃ ጨክነው ኣስጨርሰውኝ የለም ወይ? ደርግ ኣማራ ነው ካላችሁ ደግሞ የጎንደርንና የወሎን ወላድ እምባ ኣታዩም ወይ? ወዘተ. እያለ እያነባ ባለፉት ስርዓቶች የተጎዳውን ይቆጥራል። ኦሮሞው በበኩሉ በዚህኛውም ባለፈውም መንግስት ተነጥየ ተጎዳሁ፣ ባህሌ፣  ማንነቴ ተጎዳ ብሎ እያነባ ይናገራል፣ ትግሬው በበኩሉ ባለፈውም ሆነ ኣሁን የተመቸኝ ነገር የለም፣ የውስጥ ችግሬን እኔ ነኝ የማውቀው ተለይቼ ተበድያለሁ እያለ ያነባል፣ የደቡብ ህዝቡ ተበድያለሁ የኔን መከራ ማን ባየው እያለ እያነባ ይናገራል፣ ሱማሌው የኔ መከራ መቼ ነው የሚያቆመው? መከራየን እያየሁ ነው እያለ ያነባል። ጋምቤላው፣ ኣፋሩ ሁሉም በተናጠልም በቡድንም ተጎድቻለሁ እያለ ያነባል። ታዲያ እንዲህ በሆነባት ኣገር ብሄራዊ እርቅ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለው ጥያቄ ላይ ነው መወያየት ያለብን።
በመጀመሪያ ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፉ ታሪካዊ ችግሮች ኣጥንተን መፍትሄ ለመስጠት የታሪክ ተዓማኒነትም ችግር ኣለብን። በተለይ በኣሁነ ወቅት ፖለቲካው ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴን የሚጠቀም በመሆኑ ኣንዳንድ በፈጠራ የሚጻፉ ታሪኮች ያለፈውን ታሪካችንን በሚገባ ኣይተን ብሄራዊ እርቅ ለማምጣት እንቅፋት ነው። የሆነ ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፈውም ሆነ ኣሁን ላለው ግፍና በደል ኣንድ ቡድን እንደ ቡድን ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ የሚልበት ሁኔታ የለም። በደቡብ ኣፍሪካም ሆነ በኣውስትራሊያ ወይም በሌሎች ኣገሮች እንደተፈጠረው ኣይነት ሃላፊነት ወስዶ የቡድኖችን እንባ የሚያብስ ጠፋ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ምሁራን በዚህ ኣስቸጋሪ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ እርቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነና ሁላችንን የሚፈውስ ኣሳብ በግድ ኣምጠው ሊወልዱ ይገባል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው ቡድኖች እንደቡድንም በጅምላም ባለፈው ጊዜ ለደረሰባቸው በደል ሁሉ ያለፈውንና ኣሁን ያለውን ስርዓት የታሪክ ተጠያቂ ማድረጉ ኣንዱ የስምምነቱ ኣሳብ ወለል ቢሆን መልካም ነው። ይሁን እንጂ ላለፉት ችግሮቻችን ቡድኖች እንደ ቡድን ተጎዳሁ የሚሉት ካለ ለዚያ ቡድን ጉዳት እውቅና መስጠት ኣንዱ የስምምነቱ ኣካል ሊሆን ይገባል። ኣንድ ቡድን ተጎዳሁ ተጎድቼ ነበር ሲል የለም ያንተ ጉዳት ትንሽ ነው የኔ ይበልጣል ማለቱ ብሄራዊ ፈውስን ኣያመጣም።ሰው ህመሙን የሚያውቀው ራሱ ነው። በመሆኑም ቡድኖች  የተጎዳነው ኣለ ሲሉ ማዳመጥና ሃዘንን መጋራት ለችግር እውቅና መስጠት ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ መሰረቱ።  ኦሮሞው ኣጼ ምኒሊክ ጎድተውኛል ካለ ሌላው ብሄር ልክ ኣይደለም ኣልጎዱህም ማለቱ ለብሄራዊ እርቁ ኣይጠቅመንም። ኣንዱ ዜጋ ኣጼ ምኒሊክ  ካጠፉት ጥፋት ይልቅ የሰሩት ጀብዱ በተለይም ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ለመመከት ያደረጉት ተጋድሎ ከበለጠበት ቢወዳቸው ቢፎክርላቸው ሌላው ኢትዮጵያዊ መበሳጨትና ጥል ውስጥ መግባት የለበትም። ኣንድ መሪ ለኣንዱ ኢትዮጵያዊ ተወዶ ለሌላው የሚጠላ ቢሆንም ከዚህ ልዩነታችን ጋር ኣብረን መኖር እንችላለን። ኢትዮጵያዊ ለመሆን ሁሉ ሰው ኣጼ ምኒሊክን መውደድ ኣለበት ማለት ኣይደላም።ፕሬዚደንት ኦባማንና ፕሬዚደንት ቡሽን የሚወድም የሚጠላም በሰላም እንደሚኖረው እኛም ከልዩነት ጋር መኖርን መልመድ ያስፈልገናል።
ኣሁን እኛ ጋር ያለው የኮሙኒኬሽን ችግር ይመስላል። የኮሙኒኬሽን ችግሮች ምንጫቸው የእውነት መዛነፍ (distortion of truth) እንዲሁም የማንነት ፖለቲካ ውጤቶች ስለሆኑ ለነዚህ ችግሮች ራስን ሰለባ ኣለማድረግ ነው።በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ዋናው መሰረት እርስ በርስ መረዳዳት(understanding eachother) ነው ማለት ነው። ያለፈውን ህመማችንን በመደማመጥ ነው ልንፈታው የምንችለው። ችግራችንን ስንገልጥ የለም ያንተ ቁስል ትንሽ ነው የኔ ነው ትልቁና ኣንተ ስለ ብሶትህ ኣታንሳ ኣይባልም። ቢሆን ቢሆን ራስን ከውጭ ወደ ውስጥ ከውስጥ ወደ ውጭ የማየት ልብ ቢኖረን እሱ ነው ያለፈውንና ኣሁን ድረስ የቀጠለውን ችግራችንን የሚፈታው። በኣሁኑ ሰዓት እኔ ኦሮሞ መሆኔ ቀርቶ ትግራይ ሆኘ ብፈጠር ምን ይሰማኝ ነበር? ምን እሆን ነበር? ብሎ ቢያስብ በኣንጻሩ የትግራይ ህዝብ ኦሮሞው ኣማራው ተለይቼ ተጎዳሁ ሲል  በኣሁኑ ሰዓት እኔ ኦሮሞ ሆኘ ተፈጥሬ ቢሆን ምን ይሰማኝ ነበር? የሚል ከፍ ያለ መረዳት (understanding eachother’s pain and understanding each other’s feelings) በተለይ በሌሂቁ በኩል ቢታይ ነው የብሄራዊ እርቁ መሰረቱ የሚጠብቀው። ኣንድ ሰው ጉዳቴ ከፍተኛ ነው ሲል የለም ያንተ ትንሽ ነው የኔ ነው ትልቁ ጉዳት ወደ ማለት ማዘንበላችን የኮሙኒኬሽን ችግር ያመጣብናል። እውነቱን እንነጋግር ከተባለ እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፈውን ችግር  በብሄራዊ ይቅርታ ለመዝጋት የገጠመን ችግር ይሄው የኮሙኒኬሽን ችግር ነው። ያለመደማመጥና ህመምን ለመካፈል መድረክ ማጣት ትልቅ ችግሮች ሆነዋል። ሌላው ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ያለፈውን ችግራችንን በብሄራዊ እርቅ ለመፍታት የነበሩትን በደሎች ወደ መድረክ ኣምጥቶ እውነትን ለመግለጥ ኣሁን ያለው መንግስት ታሪክን ስላቆራፈደውና ብርታትንም ሆነ ድካምን ከቡድን ማንነት ጋር እንድናያይዝ የሚገፋ ነገር በመኖሩ በከፍተኛ ሁኔታ እውነትን የማግኘትና የመዋጥ ችግር ይገጥመናል። በተጨማሪም  ኢትዮጵያዊያን ኣዳዲስ በሚወለዱ ታሪኮች ሳንደነብር ከስሜት በላይ ሆነን እርስ በርስ በመረዳዳትና ኣለ ለተባለው ችግር እውቅና በመስጠት ነገሩን ማርገብ ይጠበቅብናል።ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያ ያለፈውን ችግር ልታይበት የምትችልበት ኣንድ ሌላ ትልቅ ነገር የዛሬው ይዞታዋ ነው። በፊት የነበሩ ማህበራዊና ፓለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ኣሁን ድረስ እየተንከባለሉ መጥተው ስለሚገኙ ኣሁን ያለውን በቡድኖች መካከል ያለውን ክፍተት በሪስቶሬቲቭ ፍትህ ልትፈታው ይገባታል።  በትምህርት፣ በፖለቲካ ተሳትፎ በባህልና በቋንቋ ኣካባቢ ያለውን ችግር ኢትዩጵያ ለመፍታት ስምምነት ውስጥ መግባት ኣለባት። ይህ ስምምነት ነው ኣንዱ የብሄራዊ እርቁ ይዘት።  ሪስቶሬቲቭ  ፍትህ ስንል በማህበራዊ ተቋማት ግንባታ ይሁን ከፍ ሲል በገለጽናቸው ሁኔታዎች የተጎዱ ኣካባቢዎችን በኣፌርማቲቭ ኣክሽን ዘዴዎች ለመፍታት ስምምነት ላይ መጀመሪያ መድረስ ኣለብን። ይህ የብሄራዊ እርቁ ሰነድ የሚይዘው ኣንዱ ጉዳይ መሆን ኣለበት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በስምምነቱዋ ወቅት የምታካትታቸው ጉዳዩች በግልጽ መጀመሪያ መቀመጥ ኣለባቸው። ቡድኖች እንደ ቡድን ሁሉም ተበድለዋልና ብሄራዊ እርቁ  ሁሉንም ሊክስ የሚችልና ኮሙኒኬሽንን የሚያዳብር መሆን ኣለበት። በዓለማችን የሚነሱ ጦርነቶች ኣብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ምክንያታዊነት ያላቸው ኣይደሉም ኣብዛኛዎቹ ከኮሙኒኬሽን ችግር ጋር የተያያዙ ናቸው። ኣንዳንዴ ቡድኖች የተጣሉበትን ሁኔታ በውል ሳያውቁት ብዙ ይዋጉና ብዙ ሰው ካለቀ በሁዋላ ይታረቃሉ። የሚገርመው ሲታረቁና ስሜታቸው ሲረጋ የከፈሉት ዋጋ እንዲሁ ሜዳ ላይ ሆኖ የሚያገኙበት ጊዜ ይኖራል። በመሆኑም ብሄራዊ እርቁ በቡድኖች መካከል ያለን ኮሙኒኬሽን ለማስተካከል መላ ሊወልድ ይገባዋል።
ከፍ ሲል እንዳልነው ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ የሚኖረው መልክ ሁሉንም በመካስ ላይ ሁሉንም ችግሮች እውቅና በመስጠት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል። በተለይ ያለፈውን ችግራችንን ለመፍታት ችግሩ ከኮሙኒኬሽንና ከስሜት ሃያልነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በረጋና በሰከነ መንፈስ ዜጎች ያለፈውን ችጋራቸውን በጋራ እውቅና ሰጥተው ሲንከባለል ለመጣው ችግር ደግሞ ኣፈርማቲቭ ኣክሽንስና ሌሎች የርስበርስ የመካካሻ ዘዴ ተጠቅመው  ፈውስን ማውረድ ኣለባቸው። እንዲህ ስናደርግ ብሄራዊ እርቁ ሁለቱን ርምጃዎች የሚራመድ ሲሆን ሌላ ሶስተኛ ጉዳይ ደግሞ በውስጡ ሊያቅፍ ይገባዋል :: ይህ ሌላው የእርቁ ፓኬጅ የሚይዘው ደግሞ ኣዲሲቷን  ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ እንዴት ኣብረን እንውጣ? እንዴት የጋራ ቤታችንን ኣብረን እናጥብቅ የሚለውን ያካትታል:: በመሰረቱ ይሄ ጉዳይ ቀላልም ከባድም ነው። ቀላል የሆነበት መንገድ በኣብዛኛው ፖለቲከኛና ሌሂቅ ዘንድ ቅንነቱ ካለ መፍትሄው ቀላል ስለሆነ ሲሆን ጠማምነቱ ካለ ደግሞ   ፈተና ነው።
በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ብሄራዊ እርቅን በኢትዮጵያ የሚያየው እንደዚህ ነው። በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ብሄራዊ እርቁ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስን መሰረት ያደረገና  በሚያድግ ዴሞክራሲ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ስምምነት ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ቦታ የለውም ማለት ኣይደለም። በኣሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሙስናና ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ይህንን ኣሳባችንን እያዩ እንደ ጅልነት ኣይተው ከስልጣን እስኪወርዱ በግፋቸው እንዲቀጥሉ በር ኣይከፍትም።
የብሄራዊ እርቅ ሰነዱ እንደነዚህ ኣይነት ሰዎችን በቡድን እያየ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ወደ ፍርድ ሊያመጣቸው መቻሉ ኣያጠያይቅም። እንደ ቡድን እንደ ሃገር ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን ዝግ እያለ ሊሰራጭ በሚችል የሪዲስትሪቢዩሽን ዘዴ ተመጣጣኝ እድገት ለማምጣት መስማማት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ከባህላዊ ውህደት ስምምነት ኣንጻር ኣይቶ ከብሄር ፖለቲካ ኣውጥቶ በኣንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ለመገንባት መስማማት፣ ዋና የሃገሪቱን ቋንቋዎችን ቁጥር  መጨመር ኣጠቃላይ ፈውስን ለማምጣት ይጠቅማል።
ኢትዮጵያ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ላይ እንድታተኩር የሚያደርጋት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ኣንድነት የሚረዳት ሲሆን ይህ የፍትህ  ኣሰጣጥ ዘዴ በኢትዮጵያ ቡድኖች ዘንድ የተባረከና የሚበረታታ ነው። የኦሮሞ ስርዓትን ብናይ ለሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ትልቅ ቦታ ኣለው። ይቅር ማለትን፣ በዳዩን ከመቅጣት ይልቅ ተበዳዩን መካስን ያበረታታል። ኣማራው ኣካባቢ ያለውን የሽምግልና ስርዓት ስናይ በኣብዛኛው ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ የሚበረታታበት ሁኔታ ኣለ። በደቡብ፣ በምስራቅ በተለይም በሶማሌ ክልል ይህ የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ ተጽእኖ ኣለው።
የሃይማኖት ዳራችንም ቢሆን ወደ መቶ ፐርሰንት የሚጠጋው ህዝብ ሃይማኖተኛ በሆነበት ኣገርም ይህ የፍትህ ስርዓት ሊሸከመው የሚችል በተፈጥሮው የተደራጀ ተቋም በመኖሩ ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል።
ሌላው ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ባለፈው ጊዜ በግድ በሆነ ኣሲምሌሽን ጠፉ የሚባሉ ባህሎች ካሉ እነሱን የማስመለስ (Restoration and revival) ስራ ለመስራት መስማማቱ ነው ኣንዱ የእርቁ ሰንድ የሚይዘው ጉዳይ። የጠፉና በመጥፋት ላይ ያሉ ጠቃሚ ባህሎች ካሉና ቡድኖች የሚቆጩባቸው ከሆነ የማስመለስ ፖሊሲ ኣውጥቶ ቡድኖችን ሁሉ ተባብሮ ለመካስ ኪዳን መግባት። ቡድኖች ኣጣናቸው የሚሉዋቸውን በሙሉ ለማስመለስ ባይቻልም ኣብዛኛውን በመመለስ የቡድኖችን ልብ ማሳረፍ ይቻላል።
ሌላው የብሄራዊ እርቁ ሰነድ ሊይዘው የሚገባው ጉዳይ ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የሚሆን ኣስተዳደራዊ ባህልን የመገንባት ስምምነት ሲሆን ይህም ዴሞክራሲ ነው። ቡድኖች በመጀመሪያ ዴሞክራሲ ከኣሁን በሁዋላ ያስተዳድረን  መንግስታት ቢቀያየሩም ዴሞክራሲ ግን የጋራ ባህላችን ይሁን የሚል ስምምነት ውስጥ ሊገቡ ይገባል። ይህ ኣስተዳደራዊ ባህል የጋራ የሁላቸው በመሆኑ ወደፊት ለህይወታቸው መሪ ይሆናል ማለት ነው።
ሌላው መሰመር ያለበትና የስምምነቱ ኣንዱ ኣካል ሊሆን የሚገባው ለመልካም ታሪኮቻችንም እውቅና መስጠት ነው። ኢትዮጵያን የመከራ ቤት ብቻ ኣድርጎ ከማየት የኣፍሪካ መቀመጫ ያደረጋትን የነጻነት ታጋይነቱዋን ማስታወስና ለነዚህ ታሪኮቻችን ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ኣስተዋጾ በማድረጋቸው እውቅና ሊሰጡት ይገባል። ይህ ኣይነቱ ስሜት ሚዛናዊ የሆነ ስሜትን ከመፍጠሩም በላይ ኣገር ኣለን ስንል የምንመካባቸው ብዙ ኣኩሪ ታሪኮች እንዳሉንም ስለሚያደርግ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የስምምነታቸን ሰነድ ኣንዱ ሊይዘው የሚገባው ነገር የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሳለፍ ነው። መንግስት መጥቶ መንግስት ሲሄድ ቋሚ ዶግማ የሆነ ስምምነት ሆኖ ሊቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው። የወደፊቷን ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት ይሄው ነው።
ማጠቃለያ
በቅርቡ ከኔልሰን ማንዴላ ሞት ጋር በተያያዘ ዓለም ያሳየችውን ስሜት ስናይ ያስደንቃል።በኔልሰን ማንዴላ ሞት ምክንያት የዛሬይቱ ዓለማችን በሚያስደንቅ መልኩ መነቃነቋ፣ ያ ሁሉ መሪ ወደ ደቡብ ኣፍሪካ መጉረፉ የሚያሳየው የሃያ ኣንደኛዋ ክፍለ ዘመን ዓለም ለብሄራዊ እርቅና ይቅርታ የሰጠችውን ታላቅ ክብርና ቦታ ነው።ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ የምንማረው ኣለ:: ኢትዮጵያ ብህዙ በመሆኑዋ ይህ ተፈጥሮዋ በስምምነት ላይ የተመሰረተች  ኣገር እንድትሆን ያስገድዳታል:: በመሆኑም በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ያስፈልገናል የምንለው ኣንዱ መነሻ ይሄ ነው። እንዴት ወደ ስምምነት እንገባለን? በምን መንገድ ነው ወደዚያ መስመር የምንገባው? ተግባራዊ ሂደቱ ምንድነው? ካልን ኣንዱ መንገድ ብሄራዊ እርቅ ማምጣት ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው ብሄራዊ እርቅ ማለት በኢትዮጵያ ኣንዱ በዳይ ሌላው ካሳ የሚሰጥ ሳይሆን ርስበርስ የሚረዳዱበትና ሁሉም የሚካሱበት የእርቅ ኣሳብ ነው። በዋናነት ብሄራዊ እርቁ ያለፈውን ችግር መፍታት ኣሁን የዘለቀውን ችግር ማቆም ሆኖ ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ የስምምነት ነጥቦችን ኣውጥቶ በነዚያ ስምምነቶች ዙሪያ መስማማት ነው። እነዚህ የስምምነት ኣጀንዳዎች የሃገሪቱ ዶግማዎች ይሆኑና ዘላለማዊ ኪዳን ይሆናሉ። ይህ ኪዳን ከህገ መንግስቷም በላይ ሆኖ የሚኖር ይሆናል።። ህገ መንግስት የሚያረቁ መንግስታትም ከነዚህ ዶግማዎች ኣንጻር ህጎችን ሊያወጡ ይገባል። ይህ የእርቅ ሰነድ በሃይማኖት መሪዎች፣ በባህል መሪዎች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሲቪክ ማህበራት ዘንድ ሁሉ የሚቀመጥ የሚከበር ትልቅ ኪዳን መሆን ኣለበት።ኢትዮጵያ በእንደዚህ ኣይነት ለየት ባለ ቅርጽ ብትተዳደርስ? ከህገ-መንግስቷም በላይ ሌላ ዶግማ የሆነ ኣዲስ ኪዳን ቢኖራት ጥሩ ኣይሆንም?
መቼም ይሄ ተግባር የናፈቀው ህሊናችን ጥያቄ ማንሳቱ ኣይቀርም። ይህ ብሄራዊ እርቅ የሚባለው ነገር መቼ ነው መካሄድ ያለበት? ተዋንያኑስ እነማን ይሆናሉ? የሚል ተግባራዊ ጉዳዮች ይመጣሉ። በኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ማለት የተጣሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መታረቅ፣ ወይም ውህደት ማድረግ ማለት ኣይደለም። በርግጥ የነዚህ ፓርቲዎች ውህደትና ስምምነት ለብሄራዊ እርቁ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣለው። ኣሁን የምናወራውን ሰፊ ኪዳን ለመፈጸም ነው። ዓለምን የሚያስደምም ስምምነት ተስማምተን ኢትዮጵያን እንደገና ልናቆም ነው። ተዋንያን የሚሆኑት የተለያዩ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ቡድኖች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ባህላዊ ቡድኖች ዜጎች ሁሉ ናቸው። ከኣለማቀፉ ማህበረሰብም ታዛቢ ኣስገብታ ይህንን ስምምነቱዋን ለኣለም ማሳየት ኣለባት። ከዚያ በሁዋላ ኢትዮጵያ ታላቅ ድግስ ደግሳ ያን የተስማማችበትን ቀን ዘወትር የምታከብረው የኢትዮጵያ ዳግም ምስረታ (Foundation day) ቀን ብላ ያን ቀን ዘወትር በየዓመቱ ታከብረዋለች።ይሄ መሆን የሚችል ነው።
ኢትዮጵያ ይህን የእርቅ ኪዳን የምትገባው ኣሁን ያለው መንግስት ወደ እርቅ ከመጣ ብቻ ኣይደለም። ይህ መንግስት ለዚህ እርቅ ሁኔታዎችን ቢያመቻችና ኣብሮ ቢሳተፍ ታሪክ ያመሰግነዋል። ነገር ግን በነውጥም ሆነ በጠመንጃ ይህ መንግስት ከወደቀ በሁዋላም ኢትዮጵያ የግድ ወደዚህ ኪዳን ውስጥ መግባት ስላለባት ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ባለፈው ታሪካችን የጠፋው ይሄ ነው። ለውጦች ሲመጡ ብሄራዊ እርቅ ሳይደረግ ኣሸናፊው ተሽናፊውን እየረገመ የተሻልኩ ነኝ እያለ ስለመጣን ብሄራዊ ችግሮቻችን እየባሱ መጥተዋል። ኣሁን ግን በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን ኢትዮጵያ በዚህ የእርቅ ኣሳብ ውስጥ ማለፍ ኣለባት። ይሄ የግድ ነው።የብሄራዊ እርቁን የሚመራውና የእርቅ ኣሳቦችን የሚያመጣውን ኮሚሽን ኣገር ወዳድ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ሚዲያዎችና ኮሚኒቲዎች ከፊታቸው ያለውን የልዩነት ተራራ በጎን በኩል ዞረው ኣልፈው ይህን ሰነድ የሚያዘጋጁና መላ የሚፈጥሩ ኣካላትን ሊፈጥሩ ይገባል።ይሄ ሰው የሚሰራው ኢትዮጵያዊያን ልንሸከመው የምችለው ሃላፊነት ነው። ኣሁን ባለው የፖለቲካ ኣሰላለፍ ኢትዮጵያ የጎደላት ይሄ ነው። ኣልፎ ኣልፎ የተለያዩ ፓርቲዎችን ኣገናኝቶ በማነጋገር የእርቅ ኣሳብን ለማዳበር የሚሰራ የለም ማለት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው የሚመጡ ለችግራችን የሚሆኑ የመፍትሄ  ኣሳቦችን የሚያጠናና የሚያደራጅ ባለመኖሩ ወርቅ የሆኑ ኣሳቦች ሁሉ ባከኑ። ለዚህም ኣንድ ጠርናፊ እውነትን የሚያፈላልግ የእርቅ ኣሳቦችን የሚያዳብር ተቋም ያስፈልገናልና በዚህ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትኩረት ሰጥቶ መላ ሊለው መስሎኝ ነው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ቸር እንሰንብት
geletawzeleke@gmail.com

South Sudan rebels set eyes on capital

South Sudan rebels set eyes on Capital
(AP) – Rebels in South Sudan are forcibly recruiting civilians to march on the capital, the military said, even as representatives of the warring factions gathered in neighboring Ethiopia on Thursday for the start of peace talks.
South Sudan has been plagued by ethnic tensionThe fighting underscored the challenge facing African mediators as they try to nudge two rivals _President Salva Kiir and ousted Vice President Riek Machar _toward the negotiating table after more than two weeks of bloody violence in the world’s newest country.
South Sudan has been plagued by ethnic tension and a power struggle within the ruling party that escalated after Kiir dismissed Machar as his vice president in July, with the violence boiling over in mid-December. The rebels back Machar, who is now a fugitive sought by the military.
Rebels currently hold Bor, the capital of the key oil-producing state of Jonglei that is seeing some of the fiercest fighting of the conflict. Military spokesman Col. Philip Aguer said the central government had sent in reinforcements from Juba, the capital.
He said rebels were arming reluctant civilians as they focus on their next target: Juba.
“Juba, that is their intention,” he said. “They are trying to march to Juba. The (South Sudanese military) will return them to where they came from.”
It was not possible to independently verify Aguer’s account.
The fighting has overshadowed efforts in neighboring Ethiopia, which is playing a leading role in trying to extract a cease-fire deal from both sides.
In Addis Ababa, the Ethiopian capital, African mediators under the banner of a regional bloc met representatives for both sides, briefing them separately ahead of the official start of direct talks. Face-to-face meetings between the two groups were not expected to start until later in the week. One delegate from Machar’s side said he believed the first direct meetings would happen on Saturday.
The United Nations and the African Union have said they support the efforts by East African leaders to broker peace in South Sudan.
Kiir on Wednesday declared a state of emergency in the states of Jonglei and Unity, where rebels also control the capital.
The fighting has exposed ethnic rivalry between the country’s two largest ethnic groups, the Dinka of Kiir and the Nuer of Machar. The U.N. says there is mounting evidence that people were targeted for their ethnicity.
More than 1,000 people have been killed and nearly 200,000 displaced by violence.
Kiir insists the fighting was sparked by a coup attempt mounted by soldiers loyal to Machar on Dec. 15 in Juba.
But that account has been disputed by some officials of the ruling party, who say the violence began when presidential guards tried to disarm their Nuer colleagues. From there, violence spread across the country, with forces loyal to Machar defecting and seizing territory from loyalist forces.
South Sudan’s government said in Twitter updates Thursday that the military had formed committees to “investigate those involved in killing people,” as well as the fight among presidential guards. It also said “criminals” accused of looting from civilians had been arrested.
Machar has criticized Kiir as a dictator and says he will contest the 2015 presidential election.
South Sudan peacefully broke away from Sudan in 2011 following a 2005 peace deal. Before that, the south fought decades of war with Sudan.
In New York, U.N. humanitarian chief Valerie Amos said that some 194,000 South Sudanese have been driven from their homes by the violence, and more than 57,000 are under protection at U.N. peacekeeping bases.
She said the United Nations has provided 107,000 with U.N. assistance, and the world body aims to reach over 600,000 South Sudanese with humanitarian aid in the next three months.