መስከረም 15 ቀን 2007 ዓም፣ የዩ. ኤስ. አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማና ባልደረቦቻቸው በአንድ በኩል ኃይለማርያም ደሣለኝና አለቆቹ በሌላ በኩል ሆነው የሁለትዮሽ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ኦባማ ያደረጉት ንግግር የዲፕሎማሲ ጨዋነት ከሚጠይቀው ርቀት በላይ ተጉዘው ሸሪኮቻቸው ባልሠሯቸው ጀብዶች ማሞገሳቸው አሳዝኖናል። ፕሬዚዳንት ኦባማ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ያደረጉት ንግግር ላይ በርካታ ስህተቶች፣ ህፀፆችና ግድፈቶች የያዘ ከመሆኑም በላይ አንዳንዱ አስተያየት የኢትዮጵያዊያንን ክብር የሚነካ ሆኖ አግኝተነዋል።
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን የጀመሩት “ኢትዮጵያ በዓለም ከሁሉም በላይ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለች አገር ነች“ በሚል ዓረፍተ ነገር ነበር። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ጽ/ቤት የፈጠራ ቀመሮች በዓለም ባንክ በኩል ዞረው በሚስ ሱዛን ራይስ ተቀነባብረው በባራክ ኦባማ አንደበት መስማት የሚያሳፍር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦባማ የተናገሩትን ዓረፍተ ነገር ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥና ራድዮ ደጋግሞ ሰምቶ ሰልችቶታል። ኦባማ፣ ይህ የተሰለቸ ዓረፍተ ነገር በእሳቸው አንደበት ሲነገር ስለሚሰጠው ትርጉም ጥቂት ቢያስቡ ኖሮ ለእሳቸውም ለአሜሪካም የተሻለ ነበር ብለን እናምናለን። “በአንድ ወቅት ራሷን መመገብ ያቅታት የነበረችው አገር ዛሬ ከፍተኛ እድገት የሚታይባት ሆናለች፤ አሁን የግብርና ብቻ ሳይሆን [የኤሌክትሪክ] ኃይልንም በመሸጥ በቀጠናው ቀዳሚነት ይዛለች” ሲሉ ያሞካሿት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊያን የማያውቋት መሆኑን፤ እሳቸው የሚያወድሷት ኢትዮጵያ በህወሓት ፕሮፖጋንዳ እንጂ በመሬት ላይ የሌለች መሆኑን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ማወቅ ነበረባቸው። በአንፃሩ የእውነተኛዋ ኢትዮጵያ 70% ሕዝብ በድህነት ወለል በታች በሆነ ኑሮ ሕይወቱን እየገፋ እንደሆነ፤ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያዊያን የእለት ጉርስ ምንጭ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች እርዳታ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኦባማ አያውቁም ማለት ይከብዳል። ፕሬዚዳንት ኦባማ የተናገሩለት የመብራት ኃይልም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተስፋ ተረት መሆኑን፤ ዛሬም የኢትዮጵያዊው የምሽት ኑሮ የሚገፋው በባትሪ፣ በሻማና በኩራዝ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኦባማ አያውቁም ማለት ያስቸግራል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ ከተናገሩት ውስጥ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ቢኖር ስለ “ሰላም ማስከበር” የተናገሩት ነው። የህወሓት አገዛዝ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ገንዘብ ባለበት እና አሜሪካ ወደ ፈለገችው ቦታ ሁሉ የሚልክ መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም የጦሩ የሰላም ማስከበር ሥራ ማሞካሸታቸው የሚጠበቅ ነው። እንዲያውም የፕሬዚዳንቱ ሙሉ ንግግር የተቃኘው ከዚህ አቅጣጫ ይመስላል። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ የራሳቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያወጣውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርትን ውድቅ የሚያደርግ ነገር ባልተናገሩም ነበር። አንዳችም ነፃ ተቋማት በሌሉበት አገር ውስጥ ፍትሃዊ ምርጫ የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል አውቀው ቀዳሚው ጥያቄዓቸው የሰብዓዊ መብቶች መከበር እና የነፃ ተቋማት ግንባታ ጉዳይ ባደረጉት ነበር። ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለኢትዮጵያ ተጨንቀው ቢሆን ኖሮ የራሳቸው ስቴት ዲፓርትመን የዘንድሮውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፓርት ያስታውሱ ነበር። ሪፓርቱን በማስታወሳቸው ብቻ በግፍ እየታሰሩ ስላሉት ዜጎች፣ በኦጋዴን፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር እና በአማራ እየተጨፈጨፉ ስላሉ ዜጎች፣ ስለ መሬትና የሀብት ዘረፋ፣ ስለፍትህ እጦት፣ ስለ ተቋማዊ ዘረኝነት እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች እንዳነሱ ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ያ ሪፓርት የያዘው ይህንን ሁሉ ነው። ፕሬዚዳንት ኦባማ ግን የንግግራቸው ግብ ዘማች ወታደር ማግኘት በመሆኑ የራሳቸውን የስቴት ዲፓርትመንት ሪፓርት ትተው የወያኔን ሪፓርት ይዘው የቀረቡ አስመስሎባቸዋል። ይህ አካሄድ አሜሪካ ወደማትፈልገው የጦር አረንቋ የሚላኩ የሠራዊት አባላት ሊያስገኝ ቢችልም የሚያስከትላቸው ጉዳቶችም መታየት ነበረባቸው። የንግግራቸው ፈጣን አሉታዊ ውጤት ለማየት ቀናትም አልፈጀም፤ እነሆ በኦባማ አይዞህ ባይነት የተነቃቁት የህወሓት ገዳዮች ከኢትዮጵያ አልፈው በአሜሪካ ምድርም በኢትዮጵያዊያን ላይ መተኮስ ጀምረዋል።
የኦባማ ንግግር ትኩረት የፀጥታ ጉዳዮች ሆኖ ኢኮኖሚ የግኑኝነት ማሳለጫ ሆኖ ቀርቧል፤ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅና የዲሞክራሲ ጉዳዮች ደግሞ ፈጽመው ተገፍተው ወጥተዋል። ይህ ንግግር አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፓሊሲ አመላካች ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በፀጥታ ጉዳይም ቢሆን አሜሪካ የያዘችው አቋም በረዥም ጊዜ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካን ጥቅም የሚጎዳ ነው ብሎ ያምናል። ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ከወታደር ምንጭነት በላይ የምታገለግል አገር ናት። ኢትዮጵያ ውስጥ ከራሱ ሕዝብ ጋር የታረቀ መንግሥት መኖር ለቀጠናው ሰላም እና ብልጽግና ወሳኝ ከመሆኑም በላይ የቀጠናው ሰላምና ብልጽግና የአሜሪካም ስትራቴጂያዊ ጥቅም ነው ብለን እናምናለን። የአጫጭር ጊዜ ጊዜዓዊ ጥቅሞችን ብቻ በመመልከት አምባገነኖችን መደገፍ አሜሪካን ምን ያህል ውድ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ በዓይኖቻችን እያየነው ያለ ሀቅ ነው። አሜሪካ አምባገነኖችን መደገፏን ከቀጠለች ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የምታገኘው እስካሁን ስታገኝ የነበረውን ውግዘትና የጽንፈኞች መጠናከር ነው። አሜሪካ የተሳሳተ ፓሊሲ በያዘችባቸው አገሮች ሁሉ ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ለዘብተኞችና ዲሞክራቶች ሲሆኑ እየተጠናከሩ የሚመጡት ደግሞ ጽንፈኖች ናቸው። አሁንም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን ፓሊሲ የአገሪቱን የዲሞክራሲ ኃይሎችን የሚያዳክም እና ጽንፈኛ ኃይሎችን የሚያበረታታ እንደሆነ ከወዲሁ ሊጠን ይገባዋል።
ዩ. ኤስ አሜሪካ የምትመራባቸው የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትህ እሴቶች የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እሴቶችም ናቸው። ኢትዮጵያዊያን እንደ አሜሪካ ዜጎች ሁሉ ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና ዲሞክራሲን ይሻሉ፤ እነዚህ መሻት ደግሞ መብታቸው ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል። አሜሪካ ይህን ትግል ማገዝ ይገባታል። በተግባር የምናየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። አሜሪካ ለአጫጭር ጊዜ ጥቅም ስትል ከአምባገነን ኃይሎች ጋር ማበሯ የዓላማ ተጋሪዎቿን እያዳከመ መሆኑ የወቅቱ የዓለም ሁኔታ የሚመሰክረው ሀቅ ነው። በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለችው ያለው ፓሊሲው ተመሳሳይ የረዥም ጊዜ መዘዝ እንዳያመጣ ያሰጋል። ይህ እንዳይሆን እርምት የሚገባው አሁን ነው።
ስለሆነም፣ ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ዩ. ኤስ. አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን ፓሊስ እንደገና እንድትመረምር እና ዘረኛና አምባገነኑን የህወሓት አገዛዝን መርዳት እንድታቆም አበክሮ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!