አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ 28 አንቀፆችን ሊያሻሽል ነው።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባው አዋጅ ቁጥር 809/2006 ላይ ያሉ 28 አንቀጾች እንዲሻሻሉ የመከረው በአገሪቷ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ሰራዊቱ አገራዊ ግዴታውን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑም ተገልጿል።
የአገራዊ ደህንነት ስጋቶችና የጦርነት አይነቶች፣ ባህሪያትና ውስብስብነትንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ደግሞ የሪፎርሙ አንድ አካል ነው።
በዚህ መሰረት ከተሻሻሉት አንቀጾች ውስጥ የሰራዊቱ አደረጃጀት ቀደም ሲል ከነበረው በተጨማሪ በባህር ሃይል፣ በስፔስና በሳይበር ሃይሎችም እንደሚደራጅ በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል።
የሰራዊቱ ምልመላ፣ ቅጥር፣ ወታደራዊ ስልጠና፣ የአባላት ግዴታ፣ ማበረታቻ፣ የውትድርና አገልግሎት የሚቋረጥበት ሁኔታ፣ የአገልግሎት ካሳና ጡረታም በአዋጁ ከሚሻሻሉ አንቀፆች ወስጥ ይጠቀሳሉ።
የምክር ቤቱ አባላትም በሚሻሻሉ አንቀፆች ላይ ያላቸውን አስተያየት ከሰጡ በኋላ አዋጁ በዝርዝር እንዲታይ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው የህዝብና ቤት ቆጠራ አባላትን ለመመደብ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
አዲስ የተመረጡት የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን 20 አባላት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በመንግስትና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለልማት ፖሊሲ ፋይናንስ ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅንም መርምሮ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።