Friday, March 15, 2013

ትግላችን ይቀጥላል

            ድምፃችን ይሰማ
             አንዋር መስጊድ ነገ ጭር ይላል!
ትግላችን ይቀጥላልየድምጻችን ይሰማ ሕዝባዊ መነሳሳትና ተቃውሞ በግፍ ለእስር በተዳረጉት መሪዎቹ ቃል ኪዳን ታስሮ የስኬት ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ትግላችን ድንበሮችን አቋርጦ ክልሎችን ከክልሎች፣ ከተሞችን ከከተሞች እንዲሁም ሕዝቦችን ከሕዝቦች ከምንም በላይ ልቦችን ከልቦች ጋር አስተሳስሮ እየነጎደ ነው፡፡ አልሀምዱሊላህ! ይህን ክብር እና ስኬት ያሳየን አላህ (ሱ.ወ) ምስጋና ይገባው፡፡ በዚህ ሳምንት በሚደረጉ ሁሉን አይነት ተቃውሞዎች የምናንጸባርቀዉ ዋነኛ ሀሳብም ትግላችን እያደገ፣ መስዋእትነታችንም እያየለ ግን ደግሞ ጥንካሬያችንና ስኬታችን በአስተማማኝ መሰረት ላይ እየተገነባ መሆኑን ማሳየት እና ትግላችንም እንደሚቀጥል ማስገንዘብ ነው፡፡
በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ የሚኖረው ተቃውሞ ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ ባለመሄድና መስጊዱን ጭር በማድረግ የሚገለጽ ነው፡፡ ዘወትር ለተቃውሞም ሆነ ለጁምአ ሰላት የምንሄድ ሁሉ የነገውን የጁምአ ሰላት በሌሎች አማራጭ መስጊዶች በመስገድ ብቻ የሚገለጽ ይሆናል፡፡
ተቃውሞአችን በድምጽ በሚደረግባቸው ከተሞች የሚኖረው ጠንከር ያለ ተቃውሞ ዝርዝር የአፈጻጸም መርሐ ግብሩ ይህን ይመስላል፡፡
ኢማሙ የጁመዓ ሰላት ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ በአንድ ከፍ ያለ ድምፅ:-
• የአላህን ታላቅነት ለማሳየት ለሦስት ደቂቃ ‹‹አላሁ አክበር!››
• የተቃውሞችንን መሪ ቃል እና የተቃውሞችንን መንፈስ ለመግለጽ ለሦስት ደቂቃ ‹‹ድምፃችን… ይሰማ!››
• መንግስተ የመብት ጥያቄ ሂደታችንን ከሽብር ተግባር ጋር በማያያዝ ሕዝቡን አሸባሪ ለማለት ደፍሯል እኛ ግን ሰላም መርሁ የሆነው የኢስላም ተከታዮች መሆናችንን ለማስገንዘብ ለሦስት ደቂቃ ‹‹ኢስላም… ሠላም!››
• መሪዎቻችንን ጨምሮ ያለጥፋታቸው ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ታስረው በመላዋ አገሪቱ ወህኒ ቤት የሚገኙ ሁሉ እንዲፈቱ ለሦስት ደቂቃ ‹‹የታሰሩት….ይፈቱ!››
• ብሄራዊ ውሸታቸውን በየእለቱ እየጋቱን ላሉት መንግስት ብዙሀን መገነኛዎች ከሀሰተኛ ዘገባዎች እንዲቆጠቡ ለመንገር ለሦስት ደቂቃ ‹‹ውሸት …. በቃን!››
• ጥያቄዎቻችን በማያዳግም መልኩ እስካልተመለሱ ድረስ ትግላችን እንደማይቋረጥ እና ሕዝባዊ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ለማመልከት ለሦስት ደቂቃ ‹‹ትግላችን….ይቀጥላል!››
• በመጨረሻም ሁላችንም ባለንበት ለሦስት ደቂቃ ወደ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የመጣብንን በላእ እንዲያነሳልን ዱዓ በማድረግ የዕለቱ ተቃውሞ ይጠናቀቃል-ኢንሻ አላህ፡፡
ይህን በቁጥር በርካታ በሆኑ ከተሞች የሚደረገው ተቃውሞ ላይ ሁሉም በተጠቀሱት ከተሞች ላይ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ሁሉ በነቂስ ወጥቶ እንደሚሳተፍበት ጥርጥር የለንም፡፡ ይህ እለት ዳግም አንድነታችንን፣ ጥንካሬያችንና ለመሪዎቻችን ያለንን ታማኝነት የምናሳይበት ነው፡፡
አላሁ አክበር!

“ከምድር በታች ጨለማ ቤት ውስጥ የታሰሩትን በቀን ለ10 ደቂቃ እናያቸዋልን። ልብ የሚነካ ነው። የብርሃን ማነስ አይናቸውን እንደጎዳቸው ያስታውቃሉ …

“ከምድር በታች ጨለማ ቤት ውስጥ የታሰሩትን በቀን ለ10 ደቂቃ እናያቸዋልን። ልብ የሚነካ ነው። የብርሃን ማነስ አይናቸውን እንደጎዳቸው ያስታውቃሉ … ሴቶችን በተገኘው ሰበብ ያስሯቸዋል። ምክንያት ፈልገው እስር ቤት ይከቷቸዋል። ከዚያም ይደፍሯቸዋል። በርካታ የተደፈሩ እህቶች አሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና መንግሥት ያሰማራቸው ሚሊሻዎች ይህንን አሳዛኝ ድርጊት እንደፈጸሙ ተነግሮናል” ይህ ማዕከላዊ እስር ቤት ታስሮ፣ ችግሩ ባለበት ቦታ ተገኝቶ የነበረው ስዊድናዊ የፍሪላንሰር ጋዜጠኛ ማርቲን ካርል ሻቢዬ ቃል ነው።
ስለ ማዕከላዊ እስር ቤት መስማት ይጨንቃል። ሰዎች በሲቃ የሚያሰሙት የጣር ድምጽ ለጆሮ የተለመደ ነው። ከመሬት በታች የጨለማ ክፍል አለ። በዚህ መታጎሪያ ውስጥ ሆነው ስቃይ የሚፈራረቅባቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ማዕከላዊ ብዙ ጉድ ያለበት ሲኦል ነው። የሰው ልጆች በግፍ ማቅቀውበታል። እየማቀቁበትም ነው። ለውጥ እስከሌለ ድረስ የሚቆም አይመስልም። በመሃላ የሚነገርለት ውርስና ይቀጥላል የሚባለው የመለስ ራዕይ አንዱ ክፍል ይህ ነው።
መጋቢት 3፤2005 (3/12/2013) በኖርዌይ ኦስሎ የሥነጽሁፍ ቤት (ሊትሬቸር ሀውስ) በተዘጋጀ የመወያያ መድረክ ላይ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ተገኝተው ነበር። መድረኩን ያዘጋጀው ደግሞ NOAS በሚል ስያሜ የሚታወቀው የስደተኞች ተሟጋች ድርጅት ነው። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አን-ማግሬት ኦስቴና ሁለቱን እንግዶች ካስተዋወቁ በኋላ መድረኩን እየመሩ ውይይቱ ተካሄደ። በዚህ ውይይት ላይ ሁለቱ ጋዜጠኞች እየተፈራረቁ የደረሰባቸውንና በትክክል ያዩትን አስታወቁ።
ማርቲን ካርል ሻቢዬና ባልደረባው የፎቶ ጋዜጠኛ ጆሃን ካርል አበክረው የሚናገሩት ስለ ሙያቸው ነው። “ጋዜጠኛ ለመጻፍ ማየትና ማነጋገር አለበት። በተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች ችግር ባለባቸው ቦታዎች ገብተው ለመዘገብ ድንበር ያቋርጣሉ። አሁን በሶሪያ፣ ቀደም ሲል በሊቢያ የሆነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ግን ሽብርተኛ ያሰኛል” ሲሉ ግርምታቸውን ይጀምራሉ።
የ19 ዓመት ወጣት ነው። ስራዉ ሹፍርና ሲሆን “ኦነግ ነህ” ተብሎ ነው የታሰረው። መርማሪዎች ባዶ ወረቀት እየሰጡ ስለ ኦነግ ጻፍ ይሉታል። ምንም የሚያውቀው ነገር ስላልነበር መጻፍ አልቻለም። በመጨረሻ ራሳቸው ጽፈው አዘጋጅተው በራስህ እጅ ጽሁፍ ገልብጥ አሉት። እናም የተባለውን ፈጸመ። ጋዜጠኞቹ ብዙ መረጃ አላቸው። እነሱንም ያልሆኑትንና ያላደረጉትን አድርገናል እንዲሉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። “በሶማሊያ አምስት ዓመት ተቀምጫለሁ እንድል አስገድደው አሳመኑኝ” በማለት ጆሃን ካርል ገለጸ።

ወ/ሮ ዙፋን አማረ
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ ሊቀመንበር ወ/ሮ ዙፋን አማረ እንደሚሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች ኖርዌይ እንዲመጡ ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር ከመነጋገር ጀምሮ ማህበራቸው የበኩሉን ስለማድረጉ ይናገራሉ። ይህ እንዲሆን የታሰበው ደግሞ ጋዜጠኞቹ በትክክል ያዩትንና የደረሰባቸውን ለኖርዌይ ባለስልጣናት በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲያስተካክሉ የሚደረገውን የቅንጅት ትግል ለማጠናከር እንደሆነ ወ/ሮ ዙፋን ያስረዳሉ።
ሁለቱ ጋዜጠኞችም ያሰመሩበት ጉዳይ ይህንኑ ነው። ኖርዌይ የመጡበት ዋናው ምክንያት ከተለያዩ ፖለቲከኞች፣ አግባብ ካላቸው መስሪያ ቤቶችና ከዋናው ፓርላማ በመገኘት ስለ ኢትዮጵያ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል። በርግጠኛነት ባለስልጣናቱ ያገኙትን መረጃ ለመልካም ይጠቀሙበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሙሉዓለም
ኢትዮጵያዊያን ባሉበትና የስደተኞች ጉዳይ በሚነሳበት ሁሉ የማይጠፉት ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም የኢትዮጵያ መንግስት ስለሚፈጽመው በደልና ግፍ ለማስረዳት ብዙ መደከሙን፣ እነሱም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት ምን አይነት መንግስት እንደሆነ እንደሚያውቁ፣ መንግስትም ራሱን ሊሰውር ቢል የሚፈጽመው ተግባሩ ከግብሩ ሊሰወር እንደማያስችለው በሚያስረዳ መልኩ አስተያየት ከሰጡ በኋላ “”እነዚህን ሰዎች እኮ አቁሙ የሚላቸው የለም። የምታውቁትን ያስረዳችኋቸው ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ምን ምላሽ ሰጡ?” የሚል ሁሉንም የሚወክል ጥያቄ አቀረቡ።
በተደራራቢ ስብሰባና በውይይት መዳከማቸውን የገለጹት ሁለቱ ጋዜጠኞች “የኖርዌይ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ያገኙትን መረጃ ለበጎ ይጠቀሙበታል የሚል እምነት አለን” በማለት መልስ ሰጥተዋል። ስለ አውሮፓና አሜሪካ ዝምታ ለተጠየቁት የመለሱት አሸባሪነትን በመዋጋት ስም ከፍተኛ ገንዝብ እንደሚገኝ በመግለጽ ነው። በምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካው መልክ የተወሳሰበ በመሆኑ ኢህአዴግም ይህንኑ እንደሚጠቀምበት አመላክተዋል። አሜሪካንና እንግሊዝን ኮንነዋል።
ስለ ኢህአዴግ የስለላ መረብና በስደት ላይ በሚገኙ ወገኖች ላይ ስላሰማራቸው ጆሮ ጠቢዎች አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አገር ቤት ያስተዋሉትንና ያላቸውን መረጃ በማጣቀስ አድማጮችን አስፈግገዋል። በካፌና ተራ መዝናኛ ቦታዎች ጆሮ ጠቢዎች እንደሚሰማሩ፣ ሰዎች ሻይ እየጠጡ የሚያወሩትን እንደሚለቅሙ፣ በመገረም ተናግረዋል። ስደተኞችን መሰለልና መቆጣጠር አደገኛ ወንጀል እንደሆነ በሃዘን ስሜት አስረድተዋል።
እስር ቤት “ግምገማ አለ” በማለት ግምገማ የምትለዋን የአማርኛ ቃል ተጠቅመው ማብራሪያ ሰጥተዋል። እስር ቤት ውስጥ ባለው ግምገማ 100 ነጥብ የሚያገኙ ይቅርታ እንደሚያገኙ፣ 10 ወይም ከዚያ በታች የሚያገኙ ደግሞ ተቃራኒው እንደሚተገበርባቸው እየሳቁ የኢህአዴግን የቆሸሸ አካሄድ ተናግረዋል።
የኖርዌይ PEN (ፔን) ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሊሳቤጥ ኤዲ “በሽርክና ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ” ሲሉ የጠሩትን የአገራቸውንና የኢትዮጵያን ግንኙነት የገለጹት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ እንደሚመላለሱ መግለጽ ነው። እርሳቸውን ተከትሎ አቶ ዳዊት መሰረታዊ ጉዳዮችን አንስተው ጥያቄ የሰነዘሩ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት ውስጥ መርማሪዎቹ እርስ በርስ የሚነጋገሩበት ቋንቋ በኢትዮጵያ ከሚነገሩት ቋንቋዎች የትኛው እንደሆነ እንዲያስረዱ ያቀረቡት ጥያቄ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውና አፈናውን የሚያካሂዱትን ቡድኖች የሚያጋልጥ በመሆኑ ከስብሰባው በኋላ መነጋገሪያም ነበር። የጎልጉል ዘጋቢ ያነጋገራቸው አንድ የኖርዌይ ተወላጅ በጥያቄው መነሳት መገረማቸውን አስረድተዋል። ጥያቄው የቀረበላቸው ጋዜጠኞች ግን በተለይ ቡድን ለይተው አልመለሱም። ይሁንና በቅርቡ በሚያሳትሙት መጽሃፍ ብዙ ጉዳዮች እንደሚነሱ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌዲዮን ደሳለኝ ስለ እስክንድር ነጋ አንስተው ነበር። የማህበሩ ጸሐፊ አቶ ቢኒያም በውይይቱ ላይ ከተገኙት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ ሊቀመንበሯ ወ/ሮ ዙፋን በማህበራቸው ስም ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ ከሰብአዊ መብት መጣስ ጋር በተያያዘ ጥያቄ አንስተው ነበር።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አስቀድሞ በመታሰሩ የመገናኘት እድል እንዳላገኙ ያስረዱት ሁለቱ ጋዜጠኞች፣ ርዕዮት ዓለሙን እንዳገኙዋት፣ መነጋገር ስለማይቻል በምልክት ለመግባባት ይሞክሩ እንደነበር አስታውሰዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም “እነዚህ ጋዜጠኞች የታሰሩት በመጻፋቸው ነው። የተከሰሱት ስለጻፉ ነው። ጋዜጠኞቹ ሲጽፉ ይህ እንደሚደርስባቸው ያውቁ ነበር። ሃላፊነቱን ራሳቸው ወስደው ጻፉ። አገራቸውን ስለሚወዱ፣ ሙያቸውን ስለሚያከብሩ፣ ህዝባቸውን ስለሚያፈቅሩ አደረጉት። ለነሱ ልዩ ክብር አለን” ብለዋል፡፡
“እስር ቤት እያለን አንድ ስጋት ነበረን” አሉ የስዊድን ጋዜጠኞች “ፍርሃታችን የስዊድን ጋዜጦች ስለኛ መጻፍ እንዳያቆሙ ነበር። የስዊድን ሚዲያዎች ስለኛ መጻፍ ካቆሙ እንረሳለን። መወያያ አጀንዳ የምንሆነው ካልተረሳን ብቻ ነው … ” በማለት የሚዲያን የመቀስቀስ ኃይል አጉልተው አሳይተዋል። አሁን በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞች “ከመቃብር በታች ናቸው” በማለት ሁሉም ሚዲያዎች ሊረሷቸው እንደማይገባ የሚያስገነዝብ ውድ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ነጻ ፕሬስ ከሌለ ለአገር አደጋ ነው። ነጻ ፕሬስ የሌለበት አገር አስተማማኝ መረጋጋት አይኖርም” ሲሉ የነጻ ሚዲያን አስፈላጊነት አስምረውበታል።
ጋዜጠኞቹ መጽሃፋቸውን በቅርቡ ጽፈው ለህትመት አስኪያበቁ ድረስ ዝርዝር ጉዳዮች በሚዲያ ላለመስጠት መወሰናቸው አስቀድሞ በስብሰባው አዘጋጆች በመነገሩ የሪፖርቱ አቅራቢ በዚህ ሊገደብ ችሏል። ስለሃብት ስርጭትና ሞኖፖሊ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበውን ጥያቄ ጨምሮ ሰፊ ጉዳዮች በስብሰባው ላይ ተነስተው ነበር።
ተጋባዦቹ ጋዜጠኞች ፊትለፊት አውጥተው ባይናገሩም እስር ቤት ሆነውና፣ ኦጋዴን በአካል የታዘቡትን፣ እንዲሁም በግል ባሰባሰቡት መረጃ መሰረት በቅርቡ የሚያሳትሙት መጽሃፍ ታላቅ ዋጋ ያላቸው መረጃዎች የተካተቱበት እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው። መጽሃፉ የሚታተምበት ትክክለኛ ጊዜ ባይታወቅም መጽሃፉ ከመረጃ ሰጪነቱና ኢህአዴግን ከማጋለጡ በተጨማሪ መንታ አላማ ማንገቡ የተገለጸው ሰዎቹ ከእስር እንደተፈቱ ነበር።
“በርግጥ ከእስር በመለቀቃችን እድለኞች ነን። ሆኖም ግን አዕምሯችን እረፍት አላገኘም። ምክንያቱም ብዙ ባልደረቦቻችን አሁንም እዚያው እስር ቤት ናቸው። የእስር ቤት ባልደረቦቻችን ባብዛኛው በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳሉ ራሴን እጠይቃለሁ። እስር ቤቱ ጥሩ ስፍራ አይደለም። እንዲህ ባለ እስር ቤት ውስጥ መሞት ቀላል ነው። እኛ ከመንግስታችን ባገኘነዉ ትልቅ ድጋፍ ነጻ ወጥተናል። በርካቶች ግን አልታደሉም። ባልደረቦቻችን እዚያው ናቸው። አሁንም እዚያው ናቸው” ይህ ቃል ከእስር በተፈቱ ማግስት የተናገሩት ነው። ይህ ብቻም አይደለም በስማቸው የርዳታ ድርጅት በማቋቋም የህግ፣ የመድሃኒት፣ የእስረኞቹን ቤተሰቦች በገንዘብ ለመርዳት ቃልም ገብተው ነበር።
አትረሱ! ሚዲያ አይርሳችሁ! በሚዲያ መረሳት ሞት ነው! ነጻ ሚዲያ የሌለበት አገር አደጋ ውስጥ ነው! ነጻ ክርክርና ነጻ ሚዲያ የሌለበት አገር ሰላምና መረጋጋቱ አስተማማኝ አይደለም። ነጻ ሃሳብና ነጻ ህዝብ መፈጠር አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩም ሆነ በማንነቱ ለነጻነት አዲስ አይደለም። በእስር ለሚማቅቁ መጮህና ደጋግሞ ያለመሰልቸት መከራከር የሚዲያዎች ሁሉ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። እስረኞች ሲባሉ ደግሞ ሁሉንም ነው። በሚዲያ አትረሱ! ሚዲያ ያልደረሰላቸው ወገኖች የሚዲያ ያለህ የሚሉ ወገኖች አንደበትና ጠበቃ ከመሆን በላይ ታላቅ ስራ የለም። ብዙ የተረሱ አሉ።

 

ሦስት ቀናት የፈጀው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል።


  ሦስት ቀናት የፈጀው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል። ለጉባኤው የሚሆን ኣጀንዳ ለመለየትና ልዩነታቸው ለማጥበብ ሲነታረኩ ቆይተው ቀጣዩ 11ኛ የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ በሰላም ለማጠናቀቅ የተስማሙ ይመስላሉ።
የስብሰባው ተስታፊዎች በሁለት ተከፍለው ዘለፋና የጠብ መንፈስ የተሞላበት ጭቅጭቅ ከተካሄደ በኋላ ሌላ ሦስተኛ ቡድን ተፈጥሮ “ህወሓትን እናስቀደም፣ ልዩነታችን ወደ ጎን ትተን የጋራ ጠላቶቻችንን እንታገል፣ ሁለታቹ (ቡድኖቹ) የህዝብ ድጋፍ የላችሁም፤ ስለዚ በሁለት ከተከፈልን ህወሓት ህልውናው ያበቃል።” ሲል ተማፅነዋል።
በዶክተር ቴድሮስ ኣድሓኖም የተመራ የሽምግልና ጥረት ታድያ ሁለቱም ቡድኖች ልዩነታቸው ኣጥብበው ኣብረው በጉባኤው እንዲሳተፉና በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸው እንዲተባበሩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ልዩነታቸው ግን የከረረ ጠብ እንደወለደና እስካሁን ‘ የእግዚሄር ሰላምታ’ እንኳ እንደማይለዋወጡ ተነግረዋል። ኣሁን ባይለያዩም የመከፋፈሉ ኣደጋ ግን እንዳለ ነው። የቸገራቸው ነገር ኣንዳቸው ሌላኛው ቡድን ቢያሸንፍ እንኳ ለብቻው ህወሓትን ለማስቀጠል የሚያስችል የህዝብና ካድሬ ድጋፍ እንደማያገኝ ተረድተዋል።
የሚቀጥለው የህወሓት 11 ኛ ድርጅታዊ (ዉድባዊ) ጉባኤ “ጉባኤ መለስ” (የመለስ ጉባኤ) ተብሎ ተሰይመዋል። መለስ የሁለቱም (የሁሉም) ቡድኖች የጋራ ነጥባቸው ነው።
ከጉባኤው በኋላ “ጠላቶች” ያሉዋቸውን ኣካላት እንደሚመቱ (እንደሚጨፈልቁ) ዝተዋል። ‘ ፀላእትና ክንከራታትሞም ኢና!’ የሚል መግለጫ ኣውጥተዋል።
እስቲ እናያለን።

የኢንተርኔት ስለላ:ኢትዮጵያ

                                                                                                                                      March 15,2013

ኢትዮጵያ

የኢንተርኔት ስለላና ቅኝት

ዘመኑ የኢንተርኔት ብሎም የመረጃ ተብሎ ቢነገርለትም በኢንተርኔት የተሰራጩ መረጃዎችን ለማገድ እርምጃ የሚወስዱ አካላት መበራከታቸዉ ይታያል። በኢንተርኔት ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ስለላ የሚያካሂዱ ሀገሮችን ዝርዝር ይፋ ያደረገዉ ዘገባ ቁጥጥር የሚያደርጉ መንግስታትን ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ቴክኒዎሎጂዉን የሚያቀርቡ ኩባንያዎችንም ማንነት አጋልጧል።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት RSF በያዝነዉ ሳምንት ባወጣዉ የኢንተርኔት ቁጥጥርን የሚመለከት ዘገባ አምስት ሀገሮችን የኢንተርኔት ጠላት ሲል ፈርጇል። የሶርያ፤ ቻይና፤ ኢራን፤ ባህሬን እንዲሁም የቬትናም መንግስታት የኢንተርኔት መረጃዎችን ለመቆጣጠር ከሚሰነዝሩት የድረገፅ ጥቃት በተጨማሪ ዜጎችን ለመሰለል የግለሰቦችን የኢሜል መረጃ የሚያጠምዱ ፕሮግራሞችን በመጠቀም ግንባር ቀደም ተብለዋል። ከበርካታ ሀገሮች እነዚህ አምስቱ የተመረጡትም ለኢንተርኔት ቁጥጥሩ የሚጠቀሙበት ቴክኒዎሊጂ መራቀቅና በዚህ ስለላ መሠረትም ጋዜጠኞችና ዜጎቻቸዉን በማሰራቸዉ እንደሆነ የRSF የዘመናዊ መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ተመራማሪ ግሬግዋ ፑዤ ገልፀዋል።
በተለይም ቻይና የኤሌክትሮኒክ መከላከያዋ ከዓለም ምናልባትም የረቀቀ ተብሎ ሲገመት ይህንኑ ቁጥጥሯን ለማጠናከር የግል ኢንተርኔት ኩባንያዎች ዜጎቿን ለመሰለል የሚረዱ ስልቶችን እንዲያቀርቡላት ማድረጓም ተገልጿል። ኢራን በበኩሏ የራሷን «ሃላል ኢንተርኔት» በሚል አቋቁማ የኢንተርኔት መረጃ ቁጥጥሯን አጠናክራለች። RSF የተራቀቀ ቴክኒዎሎጂን ሳይኖራቸዉ አምባገነን መንግስታት ዜጎቻቸዉን ለመሰለል እንደማይችሉ በማመልከት ለመጀመሪያ ጊዜ ተባባሪ የኢንተርኔት ጠላቶች ሲል የመሰለያ ፕሮግራሞችን የሚሰሩና ለሀገራቱ የሚያቀርቡ ድርጅቶችንም ስም አጋልጧል።
ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት ዜጎቻቸዉን በኢንተርኔት መረጃ ልዉዉጥ ሳይቀር እንዲቆጣጠሩና እንዲሰልሉ ስልቱን እያስተካከሉ የሚያቀርቡትን አምስት የግል ኩባንያዎችም የዘመኑ «ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች» ሲል RSF ወቅሷል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በርከት ያሉ ድረ ገፆች መነበብ እንደማይችሉ ተደጋግሞ የተገለፀ ጉዳይ ነዉ፤ መንግስት በበኩሉ ወቀሳዉን ቢያስተባብልም። የጥናቱ ተባባሪ ፀሐፊ ግሬግዋ ፑዤ ከአምስቱ ሀገሮች ተርታ በዘገባዉ ኢትዮጵያ ያልተጠቀሰችዉ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንደአምስቱ ሀገሮች የተስፋፋ ባለመሆኑ እንደሆነ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ያ ማለት ግን ድርጅታቸዉ ክትትል አላደረገም ማለት አይደለም፤
«ባለፈዉ ዓመት ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን እንደተደረገ እየተካተልን ቆይተናል። ማለትም TOR የተሰኘዉ ስልት ተዘግቷል፤ የሰዎች ኢሜይል ልዉዉጥ እየሰበረ የሚበረብረዉ DPI የተሰኘዉ ፕሮግራምም ስራ ላይ መዋሉን እናዉቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ሲቲዝን ላብ የተሰኘዉ ተቋም ከቶሮንቶ አንድ ዘገባ አዉጥቷል፤ ያም ኢትዮጵያ ዉስጥም አንድ የግለሰቦችን የኮምፕዩተር መረጃ የሚያጠምድ ፕሮግራም መጠቀም መጀመሩን ይገልፃል። ተቋሙ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢንተርኔት ላይ የሚካሄደዉን ቁጥጥር የሚያረጋግጥ መረጃ አካቷል።»
ግሬግዋ ፑዤ የጠቀሱት ሲቲዝን ላብ የተሰኘዉ ተቋም ይፋ ያደረገዉ ዘገባ የግለሰቦችን መረጃ የሚያጠምደዉ የኢንተርኔት ፕሮግራም ፊን ፊሸርስ እንደሚባል ይገልፃል።

እንደዘገባዉም ኢትዮጵያ በተለይም ከተቃዉሞ ፖለቲካ ቡድኖች ጋ ግንኙነት ያላቸዉ ግለሰቦችን ለመከታተል ትጠቀምበታለች። ኩባንያዉ ይህን የግለሰቦችን የኢንተርኔት መረጃ የሚያጠምድ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ያዘጋጀዉ የግንቦት ሰባት አባላትን ፎቶዎች በመጠቀም እንደሆነም ዘገባዉ በመዘርዘር ምስሎቹን ያሳያል። ግሬግዋ ፑዤ፤
«ባለፈዉ የበጋ ወቅት ሲቲዚን ላብ ፊን ፊሸር የተሰኘዉ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ዉስጥ ሥራ ላይ መዋሉን ደረሰበት። የግንቦት ሰባትን «ስሙን በትክክል ብየዉ እንደሁ አላዉቅም» ምስል የያዘዉ ይህ ህገወጥ ፕሮግራም በርካታ የተቃዉሞ ፓርቲ አባላት በኢሜል አድራሻቸዉ እንዲደርሳቸዉ ተደረገ። እናም ይህ ምስል ትክክለኛ መልዕክት የያዘ ሳይሆን ያ መረጃ የሚያጠምደዉ ፕሮግራም ነዉ። ይህን ፕሮግራም አንዴ ኮምፕዩተርሽ ዉስጥ ከገባ ወደማዘዣዉ ኮምፕዩተር መረጃዎችን በሙሉ እየቀዳ ይልካል። ይህ ነገር ኮምፕዩተርሽ ዉስጥ ካለ እያንዳንዷ የምትፅፊያት ነገር ፕሮግራሙን ወደላከዉ አካል ይሸጋገራል።» እሳቸዉ እንደሚሉትም ሲቲዚን ላብ ባደረገዉ ክትትል የግለሰቦችን መረጃ እየቀዳ የሚልከዉ ህገወጥ ፕሮግራም ትዕዛዝ አስተላላፊ የኮምፕዩተር መረጃ ማከማቻ የሚገኘዉ እዚያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሆኑን ደርሶበታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በኢንተርኔት ላይ የሚከናወነዉን ጥብቅ ቁጥጥር እና ስለላ አስመልክቶም ሲቲዚን ላብ ይፋ ያደረገዉን አዲስ መረጃ በማካተት ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዘገባ ይፋ እንደሚያደርግም ከወዲሁ ጠቁመዋል።

የመለስ ዜናዊ የመጨረሻ ስብሰባ ሰነድ ይፋ ወጣ!


ኢ.ኤም.ኤፍ) የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በአዲስ አበባ አድርገውት የነበረው የመጨረሻ ለሊት ስብሰባ፤ እንዲሁም የስብሰባውን ቃለ ጉባዔ ሙሉ ቃል እነሆ ይፋ አድርገናል። ስብሰባው የተደረገው ጠቅላይ ሚንስትሩ በአሜሪካ ቆይታቸው ወቅት አበበ ገላው በተቃውሞ ካስደነገጣቸው አስራ አምስት ቀናት በኋላ፤ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 15 ቀን፣ 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ነው። የመነጋገሪያ አጀንዳው በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ የተነሳውን ተቃውሞ አስመልክቶ ሲሆን፤ በዝርዝሩ ውስጥ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰጠውን ማብራሪያ ተካቷል። ስብሰባው ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ ሲጠናቀቅ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአስቸኳይ ህክምና ወደ ውጭ አገር እንደሚሄዱ እና ከህክምናቸው በኋላ ውሳኔውን ለመተግበር እንደሚሰሩ ቀጠሮ ተይዞ ነበር። ነገር ግን የታሰበው ሳይሳካ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደወጡ ቀሩ፤ በዚያው ሞቱ።