Thursday, March 21, 2013

የኦህዴድ ምርጫ ውጤት ተራዘመ

tplf meeting


ህወሃት አባረረ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ባሉበት ቀጠሉ

ድሮ “ላዩ ካኪ ውስጡ ውስኪ” እየተባለ በኢሰፓ አባላት ዩኒፎርም ይቀለድ ነበር። ዛሬ ደግሞ ኢህአዴግ ተመሳሳይ ልብስ አልብሶ በየክልሉ የሰየማቸውን ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውን የተመለከቱ “ስቱኮ” እያሉ እንደሚቀልዱባቸው ተሰምቷል።
“ስቱኮ” ግልብጥና ግጭት የበዛበት መኪና ተቀጥቅጦ አልስተካከል ሲል፣ የተገጣጠበና አልመሳሰል ያለ ግድግዳ “በግድ” ለማመሳሰል የሚያገለግል ቶሎ የሚፈረካከስ ጭቃ መሰል የቀለም አይነት ማጣበቂያ ነው።
“ኮሚኒስቶች በችግርና በቅራኔ ውስጥ ሆነው በግድ ለመመሳሰል አንድ ዓይነት መለያ መልበስ ይወዳሉ። ኢህአዴግም በተመሳሳይ በችግር ውስጥ ተዘፍቆ ሳለ፣ ለተመልካችና ለካሜራ ተመሳሳይ ልብስ ለብሶ በግድ አንድ ነኝ ሲል ማየቱ ብዙም የሚገርም አይደለም” የሚለው አስተያየት በስፋት እየተሰጠ ነው። “በግድ አንድ” ሆነው በየክልሉ ስብሰባ የሚያካሂዱት እህት ፓርቲዎች የለበሱትን መለያ የሚያመርተው ደግሞ የህወሃት የንግድ ድርጅት አልሜዳ ጨርቃጨርቅ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ባህር ዳር ላይ ለሚያካሂደው ጉባኤ በዝግጅት ላይ ያሉት “እህት” ፓርቲዎች በየክልላቸው በስብሰባና በምርጫ ተጠምደው ሰንብተዋል። ውሉ ያልታወቀውና ምስጢር የተደረገው የኦህዴድ ጉባኤ የምርጫውን ውጤት ማጠናቀቅ አልቻለም። ህወሃት በመተካካት ስም ነባሮቹን አራት አመራሮች ሲያሰናብት፣ አቶ በረከትና አዲሱ ለገሰ የኢህአዴግ የመተካካቱ ስልታዊ በትር ሳይነካቸው ማለፉ ተደምጧል። ደኢህዴን በነበረበት እንደሚቀጥል ይፋ ሆኗል።
ኦህዴድን ለመምራትና ሰባት አመራር በሚሰየምበት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን አባ ዱላ ገመዳ፣ ግርማ ብሩ፣ ድሪባ ኩማ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አለማየሁ አቶምሳ፣ አስቴር ማሞና ደግፌ ቡላ ከተጠቆሙት መካከል ይገኙበታል። የህወሃት የንግድ ተቋምና አንደበት የሆነው ሬዲዮ ፋና “የተጠቆሙትን አመራሮች ለማሳወቅ የድምጽ ቆጠራው ጊዜ ስለሚወስድ ለነገ ተላልፏል” የሚል ዘገባ አሰራጭቷል።
ፋና ይህን ይበል እንጂ የጎልጉል ምንጮች ከስፍራው እንዳሉት የኦህዴድ ስብሰባ ከፍተኛ ንትርክ የተስተናገደበት ሆኗል። ምንጮቹ እንዳሉት የበታች አመራሮች፣ የቀበሌና ወረዳ የስር መዋቅሮች በድፍረት የድርጅቱን አመራሮች ነቅፈዋል። በራሳቸው ውሳኔና መንገድ የማይመሩበት ምክንያት መነሻና ይህ አካሄድ መቼ ሊያቆም እንደሚችል ሊገባቸው እንዳልቻለ የተናገሩ አሉ።
“ውርስና ቅርስ” እየተባሉ የሚወደሱት አቶ መለስ በህይወት እያሉ ህወሃት ድምጽ ነፍጎ ሲያባርራቸው “መለስ ይሁን” በማለት የተሰጣቸውን የህወሃት ሊቀመንበርነት ስልጣን ላለመቀበል ያፈገፈጉት አቶ አርከበ እቁባይ በመተካከት ስም ከህወሓት መሰናበታቸው ይፋ ሆኗል። ዊኪሊክስ ይፋ ባደረገው መረጃ ህወሃትን እንዲመሩ ተመርጠው የነበሩት አቶ አርከበ አዲስ አበባ ፎቶግራፋቸው ከተለጠፈበት ጊዜ ጀምሮ “የድስትና ማማሰያ” ምሳሌ በመሆን ጥግ ተደርገው ከተረሱ በኋላ በመጨረሻ አማካሪ ተብለው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተዛውረው ነበር።
አቶ በረከትን ተከትሎ አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ ዘርአይ አስገዶምና አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ህወሃትን በይፋ መሰናበታቸው ታውቋል። ፋና “በክብር ከማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰናብተዋል” ሲል አሞካሽቶ መርዶ አብስሯል። ፋና በነካ እጁ የዋናውን የሚዲያ ፊት አውራሪ አቶ በረከትን ዜና ይፋ አደርጓል።
መለስ ያዘጋጁት “የማጽጃ በትር” የሚባለው መተካካት ብአዴን ውስጥ ተግባራዊ አልሆነም። ታማኞቹ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ቡድን የሆኑት አቶ በረከት፣ ሰሞኑን በተዘጋጀ ዶክመንታሪ ፊልም በትግርኛ ተረት ሲያወርዱ የታዩት አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ጉዱ ካሳና ፓርላማ ውስጥ የስነስርዓት ጥያቄ ሲቀርብላቸው “ታዝዤ ነው፣ ከታዘዝኩት ውጪ የማደርገው የለም” በማለታቸው የሚታወቁት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በአዲሱ ምርጫ ተካተዋል።
ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ደኢህዴንን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ምክትል ሆነው እንዲቀጥሉ ተሰይመዋል። በደቡብ ክልል ሃዋሳ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት የሞባይል ስልክ ማነጋገር አስቸጋሪ እንደነበር የጎልጉል መረጃ አቀባይ ከስፍራው አስታውቋል። አቶ ሃይለማርያም የአገሪቱ መሪ ከሆኑ በኋላ ሃዋሳ ሲገኙ ለደህንነት በሚል የስልክ መስመሮች ላይ ማዕቀብ መደረጉን ተገልጋዮች በቅሬታ ሲገልጹ ተሰምቷል።
ከሁሉም ጉባኤዎች ጎልቶ የወጣው የህወሃት ጉባኤ ሲሆን የትግራይ ክልል ሃብትና እድገት በታላቅ ትዕይንት ከጉባኤው በፊት ለህዝብ እንዲተላለፍ መደረጉ የተለያየ አስተያየት እየተሰነዘረበት ነው። መቀሌ በትዕይንት አቅራቢ ህዝብ ተጨናንቃ ሲጨፈርና ከበሮ ሲደበደብ ያሳየው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዳለው ትዕይንቱ የተዘጋጀው መለስን ለመዘከር ነው። ዜናው በተመሳሳይ ሌሎች ክልሎች የደረሱበትን የልማትና የዕድገት ደረጃ የሚያሳይ ትዕይንት እንመራዋለን ለሚሉት ህዝብ በይፋ ያላሳዩበትን ምክንያት ግን አልገለጸም።
ጋዜጠኛ ተመስገን “ሽክ” ብሎ ፊቱ ላይ ርካታ እየተነበበት ያነጋገረው ጋዜጠኛ መቀሌ ባየው ነገር መገረሙን ደጋግሞ አመልክቷል። በተሽከርካሪ ላይ በተዘጋጁ ሞዴል ማቀናበሪያና ምስሎች ትግራይ የደረሰችበትን ደረጃ የተመለከቱ “ልማት ያስደስታል። ከሰባ ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚያለቅስበት ልማት መሆኑንን ስናስብ ያሳዝነናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
አርቲስት መሐሙድ አህመድ “ትግራይ ልትሰምጥ ነው የሚባለው ውሸት ነው” በማለት የተናገረውን ያስታወሱ አስተያየት ሰጪ፣ “ብሶት ሁሉም ቦታ፣ በየትኛውም ጊዜና ወቅት የሚከፋቸውንና በቃን የሚሉ ዜጎችን ይፈጥራል። የትግራይ ህዝብም ብሶት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ ትግራይ ብቻዋን ስትለማና ስታድግ ሌላው እየተረገጠ መሆኑንን በመገንዘብ ከመጨፈር ይልቅ በማስተዋል በስማቸው የሚፈጸመውን ግፍ እንዲቆም የመጠየቅ ሃላፊነት አለባቸው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

No comments:

Post a Comment