“ከእንግዲህ የቀድሞው መንገድ አይሰራም”
ላለፉት አርባ ዓመታት ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ሲታገል የቆየው ኦነግ አመራሮቹ ሲጣሉና ሲታረቁ መስማት የተለመደ ነው። የግለሰብ ጸብ የሚመስለው የድርጅት በሽታ ሲንጠው የቆየው ኦነግ በውል ባይታወቅም ተሰነጣጥቆ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ድርጅት ከሆነም ዓመታት ተቆጥረዋል። ስህተትን ገምግሞ የትግል አቅጣጫና ፕሮግራም ከመቀየር ይልቅ ጊዜው ባለፈበት አስተሳሰብ ባለበት ሲረግጥ እድሜውን የፈጀ ድርጅት እንደሆነ ተደርጎም ይወሰዳል።
ስለ ኦነግ ሲነሳ አብዛኞች በመገረም የሚናገሩትና ሚዛን የሚደፋው አስተያየት የሚሰነዘረው በድርጅቱ መከፋፈልና መበጣጠስ ሳይሆን ተለያይተውም አስመራን የሙጥኝ ያሉበት ምክንያት ነው። ኢህአዴግ ህጻን እያለ ሻዕቢያ እንዳሻው ይነዳው እንደነበር የሚያስታውሱ አስተያየት ሰጪዎች ከሽግግር መንግስት ምስረታ በኋላ ኦነግ አገር ለቆ እንዲወጣ መንገዱን የጠረገው ሻዕቢያ መሆኑንን በቁጭት ይናገራሉ።
ኢህአዴግ ለስልጣን አዲስ በሆነበት የጨቅላነት ዘመኑ፣ ኦነግ በታሪኩ ያልነበረውን ሰራዊት በመገንባት አስጨንቆት እንደነበር በመጠቆም በወቅቱ አስተያየት የሰጡ ኢህአዴግ በተለይም መለስ በሻዕቢያ በኩል ኦነግን ለመታረቅ አቅርበውት የነበረውን የሽምግልና ጥያቄ ኦነግ እንዳይቀበል ሰሚ ባያገኙም በአጽዕኖት ምክራቸውን ሰጥተው ነበር።
በኦነግ ታጣቂ ሃይሎችና በኢህአዴግ ሰራዊት መካከል እኩል ሊባል በሚችል ደረጃ የጡንቻ መፈታተን ነበር። ደርግ ሲበታተን ኦነግን የተቀላቀሉ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አካላት ወያኔን የማዳፋት አቅሙ ነበራቸው። በወቅቱ የንስር ያህል ጉልበትና ሃይል ቢኖራቸውም ራሳቸውን ጫጩት አድርገው ተመለከቱ። አዲስ አበባ ሲገቡ የነበራቸውን የህዝብ ድጋፍ አራግፈው ጣሉት። በስሜት እየተነዱ ከሚወዷቸው ሁሉ ተቀያየሙ። ህወሃት አጋጣሚውን ለቅስቀሳና ለስም ማቆሸሻ ሰራበት። በስተመጨረሻ ኦነግ ሃይሉንና አቅሙን ዘንግቶ በአመራር ችግርና በአቋም ሸውራራነት ሃይሉን በሙሉ ወደ ካምፕ በማስገባት የኢህአዴግን የእርቅ ጥያቄ ተቀበለ። ሰራዊቱን እየነዳ በፈቃደኛት አሳሰራቸው።
በሻዕቢያ አደራዳሪነት ሁርሶ፣ ደዴሳና መስኖ የገባው ሰራዊት “በደባ” ተከቦ ትጥቁን እንዲፈታ ተደረገ። አብጦ የነበረው የኦነግ ጡንቻ በቅጽበት ከሰመ፤ ሰለለ። ኦነግ ሲቆጣጠራቸው የነበሩትን ቦታዎች ለማስተዳደርና በኦህዴድ ለመተካት ኢህአዴግ እንደ እባብ ተሹለክልኮ ዓላማውን አሳካ። ሻዕቢያም በዚሁ ውለታው ኢትዮጵያንና ኢኮኖሚዋን ብሎም የኢትዮጵያን ስነልቦና እንዳሻው እንዲጋልብ ተፈቀደለት። ብዙ አሻጥር ተፈጠረ፤ ተፈጸመም። ደንዳና ቆዳ ያላት ኢትዮጵያና ህዝቧ ተቦጠቦጡ። ተዘረፉ። አንድ እግር የቡና ተክል የሌላት ኤርትራ ቡና ላኪ ከሚባሉት ቀዳሚ አገራት ዝርዝር ውስጥ ተሰለፈች። አፈርን።
“አገሬን ከወራሪ አጸዳሁ” በማለት ከበሮ እየመታ ጦርነት አልቋል ብለው እጅ የሰጡ የወገን ወታደሮችን የረሸነው ሻዕቢያ ኢትዮጵያንም ያስተዳድር ጀመር። ዛሬ የሚማልባቸውና “ውርሳቸውን ሳናዛባ እናስጠብቃለን” የሚባልላቸው አቶ መለስ እንደ ባዕድ መሪ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለሻዕቢያ አሳልፈው ሰጡ። የሻዕቢያ ታጣቂዎችና ኢትዮጵያ አብልታ ያሳደገቻቸው ጎረቤቶቻችን ሳይቀሩ ናጠጡብን። በየደጃቸው መሳሪያ ወደላይ እየተኮሱ በደስታ ውለታ ባስቀመጠችላቸው አገር ላይ ተሳለቁ። ምስኪኖችን ቤት እያስለቀቁ ወረሱ። የሌላቸውን ሃብትና ንብረት ሰበሰቡ። በኤርትራ ምድር በግፍ ለተረሸኑ የኢትዮጵያ ልጆች ተከራካሪ ጠፋና የሞት ሞት ሞቱ። አገራችን የግፈኞች መፈንጫ እንድትሆን መለስ በበረገዱት በር የገባው ሻዕቢያ ከርሱ ሲጎድል፣ “ልክህን እወቅ” የሚሉ ሲነሱ፣ ስርዓት ያዝ ሲባል ደሙ ተንተከተከና የሃይደር ህጻናትን በጠራራ ጸሃይ በላቸው። ትግራይን ወረረ። ሲሰርቁ ኅብረት የነበራቸው ሲከፋፈሉ ተጣሉና አገር ውርደት ገባው።
ይህንኑ ተከትሎ አገር አልበቃ ብሏቸው የነበሩና ወያኔን ሲያገለግሉ የነበሩ ቅጥረኞች የሰበሰቡትን ሳይበሉ ወደ “ከባርነት ናፅነት” ብለው ድምጻቸውን ወደሰጡላት “እናት አገራቸው ኤርትራ” ተጋዙ። ንብረታቸውን በትነው አገር ለቀው ወጡ። ከነጻነት በኋላ “ታይላንድ ትሆናለች፣ ሲንጋፖር ትሆናለች፤ ሆንግኮንግ ትሆናለች” በተባለላት አገራቸው ለመኖር ተገደዱ። ዳቦ ተሰልፈው ለመግዛት ታደሉ። ኬክ በለመደው፣ ቁርጥ በቆርጠው፣ “ሹካ ባስለመደው” እጃቸው ይድሁበት ገቡ። ወታደር ሆኑ። የሰገዱለትና ቅጥረኛ ሆነው ያገለገሉት ህወሃት መልሶ በረሃ በተናቸው። የሚያሳዝነው ግን ኤርትራዊያን ከየመንደሩ ተለቅመው ወደ አገራቸው ሲሄዱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አውቶቡስ ከብበው ደረት እየመቱ ያለቅሱላቸው ነበር። ደብቀው ያስቀሩዋቸውም አሉ። ጨርቃቸውን ጥለው አውቶቡስ እንዳይነሳ በፍቅር አምላክ የተንፈራፈሩ ነበሩ። ሁኔታውን የሚያስታውሱ ድርጊቱን “የሞኝ” ተግባር አድርገው ሲወሰዱት ሌሎች ደግሞ “ክፉ ላደረገብህ ክፉ አትመልስ” የሚለው ግብረገብነት የገባቸው የፈጸሙት የጀግንነት ተግባር ነው በማለት የአዲስአበባ ነዋሪዎችን የመንፈስ ልዕልና ያደንቃሉ፡፡
ይህ ከመሆኑ በፊት ጀምሮ ኦነግ ሻዕቢያን ሲለማመነውና እግሩን ሲልሰው የኖረ ድርጅት ዛሬ ድረስ ተበጣጥሶም እዛው አስመራ አምልኮ ደጅ ይገኛል። ከአመት ዓመት ያለ ለውጥ እዛው ይንፏቀቃል። እንደሚሰማው ከሆነ ወታደሮቹ የሻዕቢያ አግልጋዮች ሆነዋል። አመራሮቹም ቢሆኑ አስመራን ለቀው የመውጣትና እንዳሻቸው የመንቀሳቀስ መብት የላቸውም። በዚህም ይሁን በሌላ መነሻ ኤርትራ በከተሙት የተለያዩ የኦነግ ሃይሎች ላይ ከያቅጣጫው ስሞታ መቅረብ ከጀመረ ሰንብቷል። ኤርትራን ለቀው መውጣት አለባቸው የሚለው የኦሮሞ ልጆች ድምጽም በርክቷል። ጥያቄው አያሌ ፖለቲካዊ ማብራሪያ የሚጠይቅና አማራጭ መፍትሄ የሚያሻው ቢሆንም ኤርትራ ውስጥ አሉ በሚባሉ ታጣቂ ተቃዋሚዎች ያልተማረሩና ያልተሰላቹ ቢኖሩ አፍቃሪ ሻዕቢያዎች ወይም ራሳቸው የሻዕቢያ ሰዎች ወይም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሻዕቢያን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ብቻ ናቸው።