Saturday, May 2, 2015

ኢትዮጵያ እየተነቃቃች ከሆነ ወጣቶቿ ለምን ይሰደዳሉ?

 

የሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርግ ይችላል፤ ነገር ግን በሃገሪቱ ተመዘገበ በተባለው ተአምራዊ ኢኮኖሚ ላይ ግን ጥርጣሬን ያጭራል?”    ረዳት ፕሮፌሰር ሃሰን ሁሴን
በአንድ ሳምንት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተደራራቢ የሞት መርዶን አስተናግደዋል፡፡ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም በሊቢያ የሚንቀሳቀሰው የእስላማዊ መንግስት አቀንቃኙ አይኤስ፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን መግደሉን አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በአይኤስ እጅ የወደቁት ደግሞ የተሻለ ህይወት ፍለጋ በሊቢያ አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ባደረጉት ጥረት መሃል ነው፡፡
ይህ አስከፊ አጋጣሚ የተፈጠረውም በዚያው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በስደት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ባለበትና 3 ኢትዮጵያውያን የመገደላቸው መርዶ በተነገረበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ ለኢትዮጵያውያን መራር ያደርገዋል፡፡
በሌላ በኩል አልጀዚራም ሆነ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ በየመን እንዲሁ በተመሳሳይ ስደት ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጦርነት መሃል ለሰቆቃ ተዳርገዋል፡፡ በዚያው አስከፊ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ሮቤ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ወላጆች፣ ሚያዚያ 11 ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ከ900 በላይ ስደተኞች ጭና ስትገጓዝ የነበረችው ጀልባ መስጠሟን ሰምተው መሪር ሃዘንን አስተናግደዋል፡፡
በአንድ ሳምንት ውስጥ የተፈጠሩት እነዚህ ሁሉ አሳዛኝ ክስተቶች፣ለጊዜው ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረጉ ቢመስልም በዚያው ልክ ኢትዮጵያውያኑን ከአስፈሪ ሞት ጋር ለመጋፈጥ ለምን ስደትን የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደርጋሉ የሚለው በሁሉም ህሊና ውስጥ የሚመላለስ ጥያቄ ሆኗል፡፡
ቀውሱ የተፈጠረው የኤስያ ነብሮች የተባሉ ሃገራት በ1970ዎቹ ያስመዘገቡት አይነት ተአምራዊ ኢኮኖሚ ሃገሪቱ አስመዝግለች በሚባልበትና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ መሆኑ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊነትን እየተላበሰች ነው በተባለባት ሀገር መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ በተደጋጋሚም ሃገሪቱ ከአፍሪካ ሃገሮች ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ነው ከተባለ ለምንድነው በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቿና ሴት ልጆቿ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሃገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት? መቼስ ነው ይሄ ፍልሰት የሚያበቃው?
እንደሚታወቀው አስደንጋጩ ዜና ከተሰማ በኋላ የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ “ክስተቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ላሰቡ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ነው” ብለዋል፤ ግን የሃገሪቱ ወጣቶች እንደ ማስጠንቀቂያ አላዩትም፡፡ በአገራቸው የተሻለ ህይወት የመኖር ህልም ያላቸው አይመስልም፡፡ በሃገሪቱ ከፍተኛ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መበራከት፣የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እድል—-ከፖለቲካ ጋር መያያዙና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የፓርቲ አባልነት መስፈርት ማስፈለጉ፣ ከፍልሰቱ ጀርባ እንዳለ በርካታ እማኞች ይገልጻሉ፡፡
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው አለማቀፉ የእድገት ማዕከል፤ በ2012 እ.ኤ.አ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በከተማ የሥራ አጥነቱ በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣
ማስማ በገጠርም ወጣቱ መሬት አልባ መሆኑን ጠቃሚ የስራ እድሎ እንደሌሉት ጠቁሟል፡፡ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፤በሃገሪቱ በሚታይ ደረጃ የትምህርት አቅርቦት ቢጨምርም ተምሮ ለሚወጣው ዜጋ በተማረበት የሙያ መስክ በቂ የስራ እድል አለመኖሩን አስቀምጧል፡፡
በአይኤስ ከተገደሉት መካከልም በዲግሪ የተመረቁ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ከ100ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ባስወጣችበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱም የአይኤስ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እንዲሁ በሃገሪቱ ካሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በጥሩ ደመወዝ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ወጣትም አለበት፡፡
ይሄ ሁሉ የሚያመለክተን ብዙ የሚወራለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ የሃገሪቱን ወጣትና የህዝብ ቁጥር ምጣኔን ለማስተናገድ አለመብቃቱን ነው፡፡ የሀገሪቱን ወጣቶች ለስደት የሚዳርገው የኢኮኖሚ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ወጣቶች አማራጭ የመረጃ ምንጭ መከልከላቸውና የነፃነት ስሜት እንዳይሰማቸው መደረጉ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በየአገሩ የሚገኝ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂ ነው፡፡ በየመን 75ሺህ ያህል የተመዘገቡ ስደተኞች መኖራቸውን የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን በኬንያ ከ20 ሺህ በላይ፣ በግብፅና በሶማሊያ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በስደተኝነት ተመዝግበዋል፡፡
አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች በግንቦት ወር ምርጫ ይደረጋል፡፡ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄድ ምርጫ ቢሆንም ላለፉት 10 ዓመታት ገዥው ፓርቲ፣ የፀረ ሽብር ህግና የሲቪል ማህበራት ህግ በማውጣት እንዲሁም ተቃዋሚዎችን በተለያዩ መንገዶች በማዳከም፣የምርጫ መወዳደሪያ ሜዳውን መዝጋቱም በገሃድ የሚታይ ሆኗል፡፡
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በማፈን ደግሞ አገሪቱ ከአለም በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰርም ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃንን በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ ጥቂት ተቃዋሚዎች በቀጣዩ ምርጫ ፓርላማ ሊገቡ ይችሉ ይሆናል፤ ወጣቶች ግን አሁንም የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግሮች ባሻገር ኢትዮጵያ በአካባቢው ከሚገኙት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ አንፃር የተረጋጋች ሃገር ነች ማለት ይቻላል፡፡ የአገሪቱ መንግስት በሽብርተኝነት ላይ ጦርነት አውጃለሁ ማለቱ ደግሞ የአሜሪካን ቀልብ ገዝቷል፡፡ ይሄም አሜሪካን የመሳሰሉ ለጋሽ ሃገራት ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ግፊት ከማድረግ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል፡፡ በሃገሪቱ ያለው የጎሳና የሃይማኖት ግጭት፣ የፖለቲካ ነፃነት እጦት በሃያላኑ ሃገራት እምብዛም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ ዜጎቿን በስደት እያጣች ያለችው ሃገር፣ ይበልጥ በአካባቢው በሽብርተኝነትና ደህንነት ላይ ብቻ አተኩራ የምትቀጥል ከሆነ፣የዜጎች ፍልሰትና የማህበራዊ አለመረጋጋቱም በዚያው መጠን ይቀጥላል፡፡ ከዚያ ይልቅ የቅርብ ጊዜውን አሳዛኝ ክስተት መነሻ በማድረግ መንግስት የመፍትሄ ሃሳቦችን መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም የታለፈባቸውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ቁጭ ብሎ በመመርመር፣ሁነኛ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ካልተቀመጡ አሁንም ስደቱ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም አሳዛኝና አስደንጋጭ መርዶዎችን መስማታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ረዳት ፕ/ር ሀሰን ሁሴን፤ በአሜሪካ ሚኒሶታ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡
ፅሁፉ ሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም በአልጀዚራ ድረ-ገፅ ላይ ታትሞ ለዓለም የተሰራጨ ነው፡፡
*ከላይ በቀረበው ጽሁፍ ውስጥ የተካተቱት ሃሳቦች በሙሉ የጸሃፊው ብቻ ነው፡
Source: addisadmass

No comments:

Post a Comment