Saturday, May 2, 2015

"ለመሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች በአገሩ የለንም?"



ሴቶችን በወንዶች ፊት፣ ወንዶችን በሴቶች ፊት ልብስ እያስወለቁ የአካላቸውን ክፍሎች ሁሉ ለማየት የሚያስችል እንቅስቃሴ አንዲሠሩ ማስገደድ በሽተኞችን ያስደስታል፤ የምርመራ ዘዴ ግን አይደለም፤ ውርደት እንዲሰማቸው ከሆነ በወራዶች ሰዎች ፊት የምን መዋረድ አለ? ወራዶች እነሱ ደረጃ ላይ ከእነሱ ጋር ያስተካክላሉ አንጂ አያዋርዱም፤ በሌላ አነጋገር ወራዶች አያዋርዱም፤ ወራዶቹ ደንቆሮዎችም ሆነው ነው እንጂ ልብስ የሚያስወልቁ እነሱ ብቻ አይደሉም፤ ሀኪሞችም ልብስ አስወልቀው፣ አጋድመው በጣታቸውም ሆነ በመሣሪያ የፈለጉትን የአካል ክፍል አንደፈለጉ ያደርጉታል፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ከሚያደርጉት የሀኪሞቹ የሚለየው ሀኪሞቹ ሰዎችን ለማዳን ሲሉ ነው፤ ወራዶቹና ደንቆሮዎቹ ግን የራሳቸውን ሱስ ለማርካት፣ የራሳቸውን ህመም ለማስታገስ ነው፤ ወራዶቹንና ደንቆሮዎቹን ከመለዮአቸው አራቁቻቸዋለሁ!

ከነውር በቃላት ወደነውር በተግባር፣ ያውም በመሥሪያ ቤት!

ዱሮ ዱሮ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ፊት ለፊት የአንድ ኢጣልያዊ ቡና ቤት ነበር፤ እዚያ ውጭ ተቀምጠን ቡና ስንጠጣ አንዲት ውብ ሴት ወደጸጉር መሥሪያው ቤት ስትመጣ የሁላችንም ዓይኖች እየዘለሉ እስዋ ላይ ዐረፉ፤ ከሦስታችን አንዱ ስለሴትዮዋ የወሲብ ችሎታ በዝርዝር መናገር ሲጀምር ሁለታችን ተያየንና አፈርን፤ ጨዋታው የጣመለት መስሎት ሲቀጥል የሕግ ባለሙያ የሆነ ጓደኛዬ አቋረጠውና ‹‹ስማ! ይህን ጊዜ እናትህ በአንድ ቦታ ስታልፍ አንዱ እንዳንተ ያለ ስለእርስዋ ችሎታ ያወራ ይሆናል!›› አለው፤ ሊጠጣ ወደአፉ ያስጠጋውን ስኒ ቁጭ አደረገና ተነሥቶ ሄደ፡፡

ሥልጣን ተሰጥቷቸው ሴቶችን ልብስ እያስወለቁ ምርመራ ነው የሚሉ በእናቶቻቸውና በእኅቶቻቸው ላይ ሊደርስ እንደሚችል አይገነዘቡም ይሆናል፤ ደንቆሮ የሚያደርጋቸውም ይኸው ነው፤ የአንዱ እናት አንድ ቦታ ላይ ራቁትዋን ቆማ በሽተኞች ተሰብስበው ሲስቁባት፣ በሌላ ቦታ ደግሞ ጓደኛው የእሱን እናት ወይም እኅት ያንኑ እያደረገ ያስቅባት ይሆናል፤ አንተ በእኔ እናትና በእኔ እኅት አስቅባቸው፤ እኔ ደግሞ በአንተ እናትና በአንተ እኅት አስቅባቸዋለሁ፤ ይህንን እየሠራን ኑሮአችንን እናቃናለን፤ እቤታቸው ሲገቡና ከእናቶቻቸውና ከእኅቶቻቸው ጋር ሲቀመጡና ሲበሉ (?!) ሰው ይመስላሉ፤ እነዚያም ግፉ የተፈጸመባቸው እናቶችና እኅቶች ‹ነውራቸውን› ምሥጢር አድርገው ለሰው ስለማይናገሩ ግፈኞችና የግፍ ሰለባዎች አብረው ይበላሉ!

አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የደረሰባቸውን ተናገሩ፤ አሁን ያፍራሉ የተባሉት እውነቱን ራቁቱን አወጡትና ከእፍረት ነጻ ወጡ! እውነቱ ሲወጣ የሚያፍረው ማን ነው? ደካማዎቹና የግፍ ሰለባ የነበሩት በጭራሽ አያፍሩም፤ የሚያፍሩት ግፈኞቹ ናቸው፤ የሚያፍሩት የሕዝብን አደራ በማቆሸሻቸው፣ በሥልጣን በመባለጋቸው፣ የሕዝብንና የአገርን ክብር በማዋረዳቸው ያፍራሉ፤ ኅሊናቸው በየቀኑ ነፍሳቸውን አርባ ሲገርፋት እየሳሳች እንቅልፍ ትነሳቸዋለች፡፡


ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

No comments:

Post a Comment