- ያደረውን የሕገ ቤተ ክርስቲያን አጀንዳ በፈቃዳቸው ትተው ሌላ ርእሰ ጉዳይ አንሥተዋል
- የተቃወሟቸውን አባቶች በአሳፋሪ ንግግሮች በመዝለፍ ለማሸማቀቅ ሙከራ አድርገዋል
- የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አጀንዳ ቀጣይነት በድምፅ ሊወሰንበት እንደሚችል ተመልክቷል
- እንደ ሕጉ ስብሰባውን በአግባቡ ካልመሩ ምልአተ ጉባኤው ሌላ ሰብሳቢ መርጦ ይቀጥላል
* * *
- ‹‹ተጠሪነትዎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ሕግ ቢመሩ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን ቢያከብሩ ይሻልዎታል፤ ሕግ አይገዛኝም ካሉ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንሔዳለን፡፡›› /ቅዱስ ሲኖዶሱ/
- በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነው በተፃራሪ ማኅበሩ ለልዩ ጽ/ቤታቸው ሳያሳውቅ አንዳችም መርሐ ግብር እንዳያከናውንና ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ የሚወስዷቸውን ሕገ ወጥ ርምጃዎች መከላከልን በተመለከተ መመሪያ እንዲሰጥ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው እና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠይቀዋል፡፡
- ‹‹ማኅበራት ገንዘባቸውን ወደ ማእከላዊ ካዝና ያስገቡ ይላሉ፤ የማኅበራት ዓላማ ገንዘብ ማሰባሰብ አይደለም፤ ገንዘብ አሰባሳቢ አይደሉም፤ ለተቋቋሙበት ዓላማ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ግን እንዴት ሥራ ላይ እንዳዋሉት መቆጣጠር ይገባል፡፡››
- ‹‹ዓላማዎ ማኅበሩን መዝጋት ነው፤ አይደለም? አይዘጋም!››
/የምልአተ ጉባኤው አባላት/
* * *
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አክራሪና አሸባሪ ሊባል የሚችልና የሚገባው አካል እንደሌለ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላት ገለጹ፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም በማንኛውም መድረክ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለን አካል/ተቋም አክራሪና አሸባሪ ከማለት እንዲቆጠቡ ምልአተ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፡፡
‹‹በቤታችን ውስጥ አክራሪና አሸባሪ የሚባል አንድም አካል የለንም፤›› ያሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ፓትርያርኩ ሌሎች በሌላ መድረክ እንደሚሉት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለን አካል አክራሪና አሸባሪ የሚሉ ከኾነ ‹‹ተወጋግዘን እንለያያለን›› ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋቸዋል፡፡
ፓትርያርኩ በትላንቱ የስብሰባ ውሎ፣ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ የተሰጣቸውን እየጠቀሱ ማኅበራትን ከአክራሪነትና አሸባሪነት ጋራ እያቆራኙ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ በምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸውም ቤተ ክርስቲያን በአክራሪነት የምትፈረጀው፣ ‹‹ማኅበራት በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት ስለሚሰበስቡ ነው፤›› በማለት ‹‹በሕግ ማስተካከል አለብን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚኽም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ‹‹ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሔ አስቀምጣለኹ›› በሚል ለውይይት በቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ÷ ማኅበራት ገንዘባቸውን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድና ተጠሪነታቸውም ለቅዱስ ሲኖዶሱ መኾኑ ቀርቶ ለፓትርያርኩ እንዲኾን የሚደነግግ አንቀጽ ካልገባ በሚል የምልአተ ጉባኤውን ሒደት ለተከታታይ ኹለተኛ ቀን እግዳት ውስጥ ከተውት ውለዋል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የማሻሻያ ረቂቅ፣ የማኅበራትን ጉዳይ ጨምሮ በፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ጎልተው የወጡ ሦስት ዐበይት ነጥቦችን ባስቀመጠው ልዩነት ትላንት የተጀመረው ፍጥጫ የተሞላበት ውይይት በዛሬ፣ ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የቀትር በኋላ ውሎው ወደለየለት መካረር አምርቶ ብዙም ሳይቆይ ለስብሰባው በድንገት መቋረጥ ምክንያት ኾኗል፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፣ ጠዋት ስብሰባው እንደተጀመረ ርእሰ መንበሩ ከትላንት ለዛሬ ስላደረው አጀንዳ ምንም ሳያሳውቁ በቀጥታ በደቡብ አፍሪቃ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ስላለው አለመግባባት ወደተመለከተው አጀንዳ አለፉ፡፡ በአንዳንድ የስብሰባው ምንጮች መረጃ፣ ፓትርያርኩ ለአኹኑ እንተወውበሚል ወደ ግንቦት እንዲሸጋገር ጠይቀው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ኹኔታው ለጊዜው በዝምታ ቢታለፍም በሻይ ዕረፍት ሰዓት ብፁዓን አባቶች በጉዳዩ ላይ ተነጋግረውበት ከዕረፍት መልስ የአርቃቂው ኮሚቴ አባል በኾኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥያቄ ተነሥቷል፡፡
‹‹ለምን ወደ ሌላ አጀንዳ ይገባል፤ ጉዳዩ በዚኽ መልክ መታለፉ አግባብ አይደለም፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው የልዩነት አቋም የተያዘባቸው የአጀንዳው ነጥቦች በውይይት እልባት እንዲያገኙ አልያም ምልአተ ጉባኤው በሕጉ መሠረት ድምፅ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡
ፓትርያርኩም የትላንቱን አቋማቸውን እየመላለሱ ‹‹ገንዘባቸውን ገቢ ያደርጋሉ፤ ገቢ ካላደረጉ በተኣምር አናየውም፤ እርሱ ይቆይና ወደ ሌላው እንግባ፤››ይላሉ፡፡ ስለማኅበረ ቅዱሳን እያወሩ ከኾነ ያለአጀንዳው እንዳያነሡት በግልጽ ቢጠየቁም ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጡ ‹‹ብቻ ገንዘባቸውን ገቢ ያደርጉ›› ይላሉ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ‹‹ማኅበራት በበጎ ፈቃድ ለተነሡበት አንድ ዓላማ የቆሙ እንጂ ገንዘብ አሰባሳቢ አይደሉም፤ ለተቋቋሙበት ዓላማ ለመሥራት ያሰባሰቡትን ገንዘብ ግን እንዴትና ምን እንደሠሩበት መቆጣጠር ይገባል፤›› በሚል አቋማቸው ያለበትን ግድፈት እየነቀሱ የቀናውን ለማመላከት ይሞክራሉ፡፡ በትላንት ውሏቸው እንዳደረጉትም ፓትርያርኩ ‹‹ማኅበራት›› ሲሉ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን እንደተናገሩ በመውሰድ የማኅበሩ አጀንዳ በወቅቱና በቅደም ተከተሉ እንዲታይ ያማፅኗቸዋል፡፡
ነገሩ ስልቻ ቀልቀሎ… እየኾነ ቢያስቸግር ታዲያ÷ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃምና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ‹‹ዓላማዎ ማኅበሩን መዝጋት ነው፤ አይደለም? ማኅበሩ በሕጉ ይሔዳል እንጂ አይዘጋም፤›› ብለዋቸዋል፡፡ ሌሎችም ብፁዓን አባቶች ቃላችኁ ቃላችን ነው ሲሉ አስረግጠዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ እስኪጠናቀቅ ማኅበሩ በዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ሥር ኾኖ አመራር እየተቀበለ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያሳለፈውን ውሳኔና መመሪያ ያስታወሱት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷ ፓትርያርኩ ውሳኔውን በመጣስ ማኅበሩ ለልዩ ጽ/ቤታቸው ሳያሳውቅ ‹‹ስብሰባም ኾነ ከፊል ጉባኤ እንዳያደርግ›› ማስታወቃቸውንና የማኅበሩን መርሐ ግብሮች እያስተጓጎሉ መኾኑን ተናግረዋል፤ በዚኽ ተፃራሪ መመሪያና ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ሊወስዷቸው የሚችሉ መዋቅሩን ያልጠበቁ ሕገ ወጥ ርምጃዎችን መከላከልን የተመለከተ አቅጣጫ እንዲሰጥ ምልአተ ጉባኤውን ጠይቀዋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው አንድ ቃል መኾኑን የተመለከቱት አቡነ ማትያስም ግትርነቱ እንዳላዋጣ አይተው ‹‹እሺ፣ ለነገ አሳድሩልኝ›› ማለት ይጀምራሉ፡፡ መግባባት ባለመቻሉና የምሳው ዕረፍት በመድረሱ ‹‹ለምሳ እንውጣና በኋላ እንገናኝ›› ሲባሉ ‹‹ቅድም በልተናልኮ፤ አኹንማ መሸ›› ማለታቸው ግርታም ፈገግታም አጭሯል፡፡
ይኹንና ከምሳ መልስም ‹‹ለነገ ይቀጠርልኝና አኹን ወደ ሌላው እንግባ›› ቢሉም ከዛሬ ለነገ ማስተላለፉ ከአማሳኝ መለካውያን ጋራ ለመዶለት ካልኾነ ትርጉም የሌለው ቢኾንም ጉዳዩ ለነገ የሚያድር ከኾነም ኹሉም ነገር አድሮ እርሱው አስቀድሞ ሳይቋጭ ወደ ሌላ አጀንዳ እንደማይገባ ቁርጡን ያሳውቃቸዋል፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት÷ ከዚኽ በኋላ የተሰማው የአቡነ ማትያስ አነጋገር፣ ሐሳባቸውን በሚሰጡ በእያንዳንዳቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ በግል ያነጣጠረ፣ በርካሽና ተራ ቃላት ሌሎች አባቶች እንዳይናገሩ ለማሸማቀቅ የሞከሩበት፣ ከአባትነታቸውና ከሓላፊነታቸው አኳያም የማይጠበቅና ቂመኝነታቸውን ያሳየ ነበር፡፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ‹‹አንተኮ ጥንትም ጠላቴ ነኽ››፤ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልንና ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን ‹‹አንተኮ እኔን አልመረጥከኝም፤ ድምፅኽን ለሌላ ነው የሰጠኸው››፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን ‹‹የማኅበሩ ጸሐፊና ሥራ አመራር አባል ነኽ›› ብለዋቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ‹‹ፓትርያርክ ቢኾኑም ለካ ቂመኛ ነዎት›› በማለት የቀድሞው አለመግባባት በይቅርታ የተፈታ መኾኑን ቢያስታውሷቸውም አቡነ ማትያስ ግን አልተገሠጹም፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ‹‹ሲኖዶሱን መስለው ከሲኖዶሱ ተግባብተው ይሒዱ፤ የያዙት አካሔድ ትክክል አይደለም›› ሲሉ ከቀድሞው ልምዳቸው እየተነሡ ቢመክሯቸውም አቡነ ማትያስ አልተገሠጹም፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ‹‹እኔ በምልአተ ጉባኤው እንደተሰጠኝ ሓላፊነት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ነኝ፤ የማወራውም ስለ ሕግ ነው፤ ቅዱስነትዎም ሕጉን ተመርኩዘው ቢናገሩ ይበጅዎታል፤›› ብለው ቢያሳስቧቸውም አቡነ ማትያስ አልተገሠጹም፡፡
ስለኾነም ምልአተ ጉባኤው ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥነ ሥርዐት በሚደነግገው መሠረት÷ ፓትርያርኩ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶሱ በመኾኑ ቅዱስ ሲኖዶሱን እንዲያከብሩ፣ እንደ ሕጉም ስብሰባውን በአግባቡ እንዲመሩ፣ ሕግ አይገዛኝም ካሉም ‹‹ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንሔዳለን›› ሲል ወደማሳሰብ ገብቷል፡፡ የአጀንዳውን ቀጣይነት በተመለከተ የተጀመረውን ርእሰ ጉዳይ በድምፅ አሰጣጥ ማሳለፍ እንደሚቻልተጠቅሶላቸዋል፤ ስብሰባውን በአግባቡ ካልመሩ ደግሞ ዋና ጸሐፊውን ሰብሳቢ በማድረግ መደበኛ ስብሰባውን ለመቀጠል እንደሚገደዱ በግልጽ አስጠንቅቀዋቸዋል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የተጀመረው ውይይት በኾነው መንገድ እልባት ካላገኘ ፓትርያርኩ እንደሚሉት ወደ ሌላ ርእሰ ጉዳይ ላለመግባት የወሰነው ምልአተ ጉባኤውም ያለወትሮው ከቀኑ 9፡00 ላይ የዕለቱን ውሎውን ከሰዓቱ በፊት አቋርጦ ተነሥቷል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥርዐት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የሚመራው በፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት ነው፡፡ ፓትርያርኩ በልዩ ልዩ ምክንያት ስብሰባውን መምራት ባይችል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በተመረጠ የሹመት ቅድምና በአለው አንድ አባት ስብሰባው ሊካሔድ ይችላል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚባለው ከአቅም በላይ የኾነ እክል ካላጋጠመ በቀር መላው አባላት የተገኙበት ጉባኤ ሲኾን ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ÷ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ከኾነ በሙሉ ድምፅ ያልፋል፡፡ አንድን ጉዳይ ለመወሰን የአባላቱ ድምፅ እኩል በእኩል ከኾነ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያለበት ያልፋል፡፡ አስተዳደርን በሚመለከት ጉዳይ ከኾነ ከተገኙት አባላት መካከል ከግማሽ በላይ በኾነ ድምፅ የተደገፈው ሐሳብ ያልፋል፡፡
ምንጭ፡ ሃራ ተዋህዶ
No comments:
Post a Comment