Thursday, October 30, 2014

ባነሰ ወጪ ድልን መቀዳጃ አመቺ ጊዜ ላይ ነን – እንጠቀምበት!


በአለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በምንም የማይገናኙ እና የተመሰቃቀሉ የሚመስሉ፤ በጥልቀት ላያቸው ግን የተያያዙና የተደጋገፉ ከመሆናቸው አልፎ እንደከዋክብት ፈለግ አቅጣጫን የሚያመላክቱ በርካታ ክስተቶች ተስተውለዋል። የጊዜ ቅደም ተከተላቸውን ሳንጠብቅ አንዳንዱን ለአብነት ያህል እናንሳ።
በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የዘነበው የዘለፋና የዛቻ ውርጅብኝ ህወሓት በቀጥታ በማይቆጣጠራቸው ማኅበራት ላይ ሁሉ ሲደርስ የቆየው ነፃ ማኅበራትን የማፍረስ ዘመቻ አካል መሆኑን መገንዘብ ቀላል ነው። ህወሓት የእስልምና እምነት ተከታዮችን ነፃ ማኅበርን በቁጥጥሩ ውስጥ ካስገባ በኋላ ፊቱን ወደ ክርስትና በተለይም ወደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማዞሩ የተረጋገጠ ነገር ሆኗል። ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ማንም ከጥቃት እንደማያመልጥ፤ ለምንም ጉዳይ ይቋቋም ወያኔ የማይቆጣጠረው ማኅበር እንዲኖር የማይፈልግ መሆኑ ከዚህ በፊት የሚታወቅ ቢሆን በድጋሚ ማረጋገጫ የሰጠበት አጋጣሚ ሆኗል።
በመዠንግር ከአስራ አምስት በላይ የሥርዓቱ ታጣቂዎች ከነመሣሪያዎቻቸው አገዛዙን ክደው ጠፍተዋል። የጠፉትን ለማደን የመጡ ወታደሮች ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በፈጠሩት ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ ግጭት ብቻ ከ40 በላይ ወታደሮች መገደላቸው ይነገራል። በጋምቤላ እና በቤንሻንጉልና ጉሙዝ ወረዳዎች ውጥረት ሰፍኗል። ከመሃል አገር ሄደው ኑሮዓቸውን እዚያው ያደረጉ ዜጎች ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደርስባቸው አፈናና እንግልት ጨምሯል። ግድብ እየተሠራበት ነው በሚባለው አካባቢም ከአሁኑ የፀጥታ ችግር እየደረሰ መሆኑ መረጃዎች ይጠቅማሉ። ወያኔ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን ውስጥ የገባበት ዓይነት ማጥ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያም እየመጣ መሆኑ አመላካች ነው። የመከላከያ ሠራዊት አባላት መፍለስና የነፃነት ታጋዮችን መቀላቀል የእለት ለእለት ትዕይንት እየሆነ ነው። ወያኔ በመሃል አገር በሙስሊም እና በክርስቲያን ወገኖቻችን የእምነት ማኅበራት ላይ በከፈተው ግንባር “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ሲል ዳር ዳሩን ሠራዊቱና ሕዝቡ ለማይቀረው ፍልሚያ እየተዘጋጁ ነው።
በርካታ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች ለስደት ከተዳረጉ ጥቂት ሣምታት በኋላ “የሚመጣውን ሁሉ አገሬ ውስጥ ሆኜ እቀበላለሁ” ያለውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ አሳዛኝም አስቂኝም በሆኑ ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ ወደ ወህኒ ተግዟል። በጋዜጠኞች ሕይወትና ሞት ወያኔ የፓለቲካ ቁማር መጫወቱ አጠናክሮ ቀጥሏል። በአንፃሩ ደግሞ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያን አምርረዋል። የወያኔ ሹማምንት በአሜሪካ እና አውሮፓ የሚዘዋወሩት በሰቀቀን ሆኗል፤ በየደረሱበት ውግዘትና ውርደት ይጠብቋቸዋል። የወያኔ ሹማምንት በኢትዮጵያዊያን የተጠሉና የረከሱ ተደርገዋል።
የዩ.ኤስ. አሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከኢትዮጵያ ቴሌቬዥን ባላነሰ ወያኔን በልማት አምጭነት አሞካሽተዋል። የአውሮፓ መንግሥታት በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ወያኔን እየተቹም ቢሆን ወያኔ በሚሰጣቸው ቁጥር እየማለሉ “እውነትም ልማት እየተፋጠነ ነው” በሚል ተስፋ ማበረታቻ እየሰጡት ነው። በዚህ ደስታ አቅሉን ያጣው ኃይለማርያም ደሣለኝ የውሸት ቁጥሮችን የመፈብረክ ሥራ ከስታትስቲክስ ጽ/ቤት ነጥቆ የራሱ የሥራ ድርሻ አድርጎታል። በዚህ አዲሱ ሥራውም ውጤት እያስመዘገበ ነው። ሁለት መቶ አምሳ (250) ሚሊዮን ኩንታል ሰብል አመረትን ባለ በሶስት ወሩ ሶስት መቶ (300) ሚሊዮን ኩንታል አመረትን በማለት በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ የ20 በመቶ የግብርና ምርቶች የውሸት እድገት ፈጥሯል።
የውሸት ቁጥሮች ፈጠራ እንዲህ ቢፋፋምም፤ ቁጥሮቹን የሰሙ ኦባማ፣ የአውሮፓ መንግሥታት ሆነ ዓለም ባንክ ቢያወድሱትም አገር ውስጥ ያለው ሀቅ አልቀየረም። ስኳር፣ ዘይት፣ እንቁላልና ሌሎች የምግብ ግብዓቶች የደረሱት የሚያውቅ ጠፍቷል። ውሃ የለም፤ መብራት የለም፤ ኔት ዎርክ የለም። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመቸውም በባሰ መጠን በነዳያን እና በቤት አልባ በረንዳ አዳሪ ዜጎች ተጥለቅልቀዋል። ድህነት ከጎጆዎች ወጥቶ ጎዳናዎች ላይ ፈሷል። የገንዘብ ዋጋ ወርዶ ወርዶ ብር ቁራጭ ወረቀትን ማከል አቅቶታል። በጥቂት በዝርፊያ በደለቡ የህወሓት ሹሞችና በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ማነፃፀር እንኳን እንዳይቻል ሆኖ ተራርቋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በኑሮም በዘረኝነትም እየተማረሩ ነው፤ አለቆቻቸው ግን አሁንም በዝምድና እየተፈላለጉ እየተሿሿሙ ነው። አሁንም በዝምድና እየተፈላለጉ እርስ በራሳቸው እየተሿሿሙ ጄኔራሎች ሁሉ ዘመዳሞች ሆኑ፤ በሥራቸው ያለውን ኢትዮጵያዊውን ወታደር ግን እንደ ግል አሽከራቸው እንኳን ማየት ተጠይፈዋል። በጄኔራሎችና በሠራዊቱ መካከል ያለው ግኑኝነት ከጌታና ሎሌም የባሰም ሆኗል።
እነዚህ ምስቅልቅል ያሉ ሁኔታዎች ምንን ያመለክታሉ?
እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ምስቅልቅል ያሉ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ የተነተነ ሰው በምስቅልቅነታቸው ፋንታ ሥርዓት የያዙ ፈለጎችን ያገኛል። ከእነዚህ ፈለጎች አንዱ የሚያመላክተው መጪዎቹ ጥቂት ወራት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜያት እንደሚሆኑ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ምስቅልቅል ውስጥ ያለው ወያኔ ነው። ወያኔ፣ በድንገት አዕምሮዉን እንደሳተ ሰው ይይዘው ይጨብጠው ጠፍቶታል። በዚህ ምስቅልቅል ወቅት ውስጥ በቢሊዮን የሚገመት የሕዝብ ሀብት አውጥቶ፤ የማይረቡ ድርሳናትን ጽፎ የአገሪቱን ዜጋ በሙሉ ካላሰለጠንኩ ሞቼ እገኛለሁ ማለቱ ራሱ የውስጡን መመሰቃቀል ማሳያ ነው። ስልጠናውን ሰልጣኞች ብቻ ሳይሆን አሰልጣኞችም ጭምር የጠሉት ቢሆንም ፋታ የሚሰጠው መስሎት ገፍቶበታል። የነፃነት ኃይሎች በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ኃይላችንን አሰባስበን ከገጠምነው ባነሰ ወጪ ድልን መቀዳጃ አመቺ ጊዜ ይሆናል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያለንበት ወቅት ወሳኝነት በመገንዘብ ከመሰል ድርጅቶች ጋር ውህደት በመፍጠር፤ ከሌሎቹ ጋር በጥምረት ትግሉን ለማፋጠን ቆርጦ ተነስቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የወቅቱን ልዩ ባህሪ በመገንዘብ በአንድ ልብ ለትግል እንዲነሳ ግንቦት 7 ጥሪ ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment