Wednesday, April 30, 2014

ሴቶችን አብዝቶ የሚፈራው መንግሥት


ቹቸቤJailed Ethiopian female bloggers, activists and journalists መነሻቸው ግልብ ጎጠኛነት መድረሻቸው መንደረተኛነት በመሆኑ በዘረፋ እየከበሩ በመለስ ራዕይ እያጨናበሩ ከመኖር ያለፈ ከእውነት ጋር ፊት ለፊት ተያይተው መኖር ያልቻሉት የትግራይ ጉጅሌዎች በወጣቶች ላይ የሚፈጽሙት ሰቆቃ አሳፋሪ ነው። በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚበረቱ የማስተዋል ድርቅ የመታቸው፣ የእውቀት ረሀብ ያደነዛቸው ፍርሃት እንቅልፍ የነሳቸው ናቸውና ድፍረት ያላቸው ህጻናት ያስፈሯቸዋል እውነት የያዙ ሴቶች ያስደነግጧቸዋል። ለዚህ ነው የወጣቶችን ግንባር በምንደኛ ጦር ሲነድሉ ወጣት ሴቶችን ሲደፍሩ ሲያስደፍሩና ሲያዋርዱ ደስታን የሚያገኙት።
አብዛኞቹ በዚህ ጎጠኛ ቡድን የሚንገላቱት ወጣቶች ወያኔ በገባበት ዘመን የተወለዱ ወይም ገና ድክድክ የሚሉ ህጻናት ነበሩ። ሲነገራቸው የኖረውና ህይወታቸውን ሙሉ የተመለከቱት ኢትዮጵያ ስትዋረድ የሀገሪቱ ጀግኖች ሲሰደቡና ዘር በዘር ላይ ሀይማኖት በሀይማኖት ላይ የሚያነሳሳ ታሪክ ሲማሩ ነበር ያደጉት። ሬድዮ፣ ቴሌቭዥን ጋዜጣና መጽሄቱ ሁሉ የሰሩት የወያኔን ፕሮፓጋንዳ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነት ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ እየገነነ፣ ለነፃነት የሚደረገው ትግል እየጠነከረ መምጣቱ ይልቁንም አፍራሹ ፕሮፓጋንዳና ድርጊት ጠንካራ ወጣት ወንዶችና ወይዛዝርቶችን ቁርጠኛ ታጋይ እንዲሆኑ አደረገ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ሲሞት አላየንም።
ከዚህ መማርና መለወጥ የሚቻል ቢሆንም ኢትዮጵያዊነትን ያሟጠጠ አእምሮው በጥላቻ የሰከረን መመለስ እንደማይቻል መመልከት አሳዛኝ ነው። “የሚያድግ ልጅ አይጥላህ” የሚባለው ተረት የሚያስተምር ቢሆን በወጣቶች ላይ የሚሰራውን ግፍ ቀነስ ማድረግ በተቻለ ነበር። እኒህ ወጣቶች ይቅር ባይ እንጂ ቂመኛ እንዳይሆኑ ግን ምኞቴ ነው።
እነዚህ ክፉዎች በየቀኑ የሚተክሉት የጥላቻ ችግኝና የእልቂት ድግስ የመቶ አመቱን በደል አስታውሶ ከሚያጫርሰው በላይ ዛሬ የሚደርሰውን ግፍና በደል አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ የታች አምናውን ሳይሆን የትናንቱን የወያኔን ሕዝብ ከመኖርያ ማፈናቀል፣ ገበሬዎችን መበተን፣ የሀገር ድንበር መቁረስን፣ በአማራና ኦሮሞ ላይ እየተኪያሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት እያስታወሰ የሕዝብ ሃይል መልሶ ጠራርጎ እንደሚያጠፋቸው አለማወቅ የግብዝነትና የድንቁርና ምልክቱ ነው። በዘመነ ደርግና በንጉሳውያኑ ዘመን ከሆነው ሁሉ የበለጠ ግፍና በደል የተፈጸመው በነዚህ ጎጠኞችና የሀገር ጠላቶች እንደሆነ ለመናገር እዚያው ትግራይ ያለውን ተቃውሞ ምሳሌ ማድረግ ይበቃል። ጎጠኞቹ ልብ ያላሉት የታቀፉት የእባብ እንቁላል እነሱኑ ቀድሞ እንደሚነድፍ ነው። ይህ እንደሚሆን ለማወቅ በሀገሪቱ ከተበተኑት ሰላዮች መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን እውነት እንዲናገሩ ብቻ ቢፈቅዱላቸው እንኳ ያንዣበባቸውን አደጋ ባወቁት ነበር።
ርዕዮት አለሙ ጽንፈኛና አሸባሪ ልትባል የምትችልበት ምንም መረጃ የለም። ወያኔዎችን ያስፈራው እውነትን መያዝዋና ድፈረቷ ብቻ ነው። ርዕዮትን ማሸማቀቅ ሌሎችን ለማስፈራራት የተወሰደ እርምጃ ነበር ግን ውጤቱ በተቃራኒው ሆነ። እናም አነሆ ወይዛዝርቶቹ ተነሱ! ስለወያኔ ክፋት ሳይሆን ስለሕዝባችን ብርታትና መነሳሳት የምናወጋውም በኩራት የሚሆነው ለዚህ ነው።
ሴቶች ትግሉን አልተቀላቀሉም፣ ብዙዎቹ ወደሁዋላ ይላሉ እንላለን ጥቂት ግን በጣም ጥቂቶቹ ደፍረው ሲወጡ ከጎናቸው ልንቆምና በየአቅጣጫው ልንታገልላቸው ይገባል። ርዕዮት እድሜዋ ገና ሰላሳዎቹ ውስጥ ያለች ወጣት ትዳር ያልመሰረተችና ልጅ የሌላት ብዕረኛ ናት። ትዳሩ ይቅር ልጅም አይኑራት ነገር ግን ለህይወትዋ አስጊ በሆነ የጤና ችግር ላይ መሆንዋ እየታወቀ ህክምና እንዳታገኝ ማድረጉ አሰቃይቶ የመግደል እኩሌታ ነው። ይህ የግፍ ጽዋ ሞልቷል። ወጣቱ ቆርጦ ተነስቷል።
ምስላቸው ከዚህ ጽሁፍ ጋር የሚታየው ወጣቶች የእስርቤት ሰለባ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ በጣም ያሳዝናል። ይሁን እንጂ ሁላቸንንም የሚያበረታቱ የጣይቱ የዘር ግንድ የጀግኖች የዜግነት ውርስ በዚህ ትውልድ ደም ውስጥ መፍሰሱን ስለሚያመለክቱ ተስፋ ይሰጡናል ብርታትም ይሆኑናል። እኒህ ወጣቶች ከታሰረው ከሰፊው ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ለነጻነት ለሚደረገው ትግል አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ተባብረን እንነሳ! ከትንሹ እስር ቤት ወደ ትልቁ ይመጡ ዘንድ ድምጻችንን እናሰማ። አብረንም ሆነን የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልስ። ኢትዮጵያችንንም ነፃ እናውጣ!
ኦህ ኢትዮጵያ ባንቺ ተሰፋ አይቆረጥም… ልጆችሽ የነጻነት ዐየርን ይተነፍሱ ዘንድ በጀግንነት እንታገላለን… ሁሌም የመከራ ገፈት የሚቀምሱትና የበደል ጫና አንገት ያስደፋቸው የሀገራችን ሴቶች በሀገራቸው ኮርተው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ የድርሻችንን ሁሉ እናበርክታለን።

No comments:

Post a Comment