ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ሰማያዊ ፓርቲን እንደፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ ለምን እንደምደግፈው፣
እ.ኤ.አ ዴሴምበር 15/2013 ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብላ በምትገኘው አርሊንግተን ከተማ የስብሰባ አዳራሽ
በተዘጋጀው የሰማያዊ ፓርቲ የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ንግግር እስካደረግሁባት ዕለት ድረስ በበርካታ ጥያቄዎች
እወጠር ነበር፡፡ አንደኛው ተደጋግሞ የሚጠየቀው ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት ገለልተኛ ሆኘ እና ከማንኛውም የፖለቲካ
ፓርቲ ወይም ቡድን ጋር ሳልወግን ከቆየሁ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ለሰማያዊ ፓርቲ ለምን ያልተቋረጠ ድጋፍ በመስጠት ላይ
እንደምገኝ በሚቀርብ ጥያቄ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
በኢትዮቱብ ድረገጽ/ethiotube.com በሰጠሁት ቃለ ምልልስ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት ለሰማያዊ ፓርቲ
ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የምሰጥበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያ ትኩስ ወጣት ኃይል የሀገሩን መጻኢ ዕድል የመወሰን እና
በሰላማዊ የትግል ሂደት በመሳተፍ ለውጥ ለማምጣት ዝግጁ ነው የሚል ሙሉ እምነት ያለኝ በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ
ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ከ35 ዓመት የዕድሜ ክልል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል 70 በመቶ ይሸፍናል፡፡
እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ሰለባ ሆኖ የሚገኘው ወጣቱ የህብረተሰብ
ክፍል ነው፡፡ አብዛኛው የወጣት ህብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ የማጎሪያ እስር ቤቶች የፖለቲካ ጭቆና እና ማስፈራራት፣
ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር የመዋል እና እስራት፣ የስቃይ፣ የመብት እረገጣ እና ከህግ አግባብ ውጭ
የእስር ቤት አያያዝ ሰለባ ዒላማ ሆኖ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስር በሰደደ የስራ አጥነት ወጥመድ
ተጠፍረው እና ጥራት ያለው የትምህርት ዕድል እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መብታቸውን ተነፍገው በሀገራቸው ላይ የበይ
ተመልካች ሆነው ይገኛሉ፡፡ እዚህ ላይ የእኔን “አስረጅ” ምሰክርነት ለማስመዝገብ እንዲሁም ለሰማያዊ ፓርቲ
‘ምስክርነት’ ለመስጠት ያህል በማያወላውል መልኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች የቆሸሸውን የጎሳ ፖለቲካ፣ አስፈሪውን
የኃይማኖት ጥላቻ እና በውሸት ድር እና ማግ የተደወረውን የቅጥፈት ተምኔታዊ ፖለቲካ በጣጥሰው በመጣል “ፍቅር የነገሰበት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ” የሚባል
አንጸባራቂ ከተማ ከተራራው አናት ላይ እንደሚገነቡ ያለኝን የማይታጠፍ እምነት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ይህ የተቀደሰ
ተግባር የዛሬው ወጣት ትውልድ ቋሚ ታሪካዊ ዕጣ ፈንታ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
የእኔ “አስረጅ” ሆኖ መቅረብ የእራሴን ሀሳብ እና አስተያየት ከመግለጽ ባለፈ በምንም ዓይነት መልኩ የሰማያዊ
ፓርቲን፣ የአመራሩን ወይም የአባላቱን ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን ድርጅታዊ እና ድርጅታዊ ያልሆነ አቋም
አይወክልም፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ ላይ ምንም ዓይነት ሚና የለኝም፡፡ ያለኝ ብቸኛ ሚና ቢኖር “የሰማያዊ ፓርቲ ቁጥር 1
አድናቂ” መሆኔን በኩራት መግለጼ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ የእኔ ለሰማያዊ ፓርቲ ‘በአስረጅነት’ በጽናት መቆም
ቅንድቦችን ከፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ጠንካራ ደጋፊ በመሆኔ ከአንዳንድ ወገኖች ህብረተሰቡን በእድሜ
እየለያየ የሚል ትችት ሲሰነዘር ሰምቻለሁ፡፡ እኔ በእድሜ በመከፋፈል መረጃ የመስጠት ጨዋታ ተጫወትኩ እንጅ በስልጣን
ላይ ያለው ገዥው አካል እንደሚያደርገው ሁሉ በዘር ወገኔን በመከፋፈል የቁማር ጨዋታ አልተጫወትኩም፡፡ በዚህ ጉዳይ
ላይ ወጣቱ ኃይል ብይን እንዲሰጥበት በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ጆርጅ ኦርዌል እንዳሉት ‘ዓለም አቀፋዊ ማጭበርበር
ተንሰራፍቶ በሚገኝበት በዚህ ዘመን ስለእውነት መናገር አብዮታዊ ድርጊት ነው‘፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ
አጭበርባሪነት፣ የሞራል ዝቅጠት እና አታላይነት ተንሰራፍቶ በሚገኝበት ሁኔታ እኔ ስለሰማያዊ ፓርቲ እየሰጠሁት ያለው
‘አስረጅነት’ እንደ ‘አብዮታዊ ድርጊት’ ይቆጠራል የሚል ዘርፈ ብዙ አመለካከት አለኝ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ቁጥር: 1ኛ አድናቂ ለምን ሆንኩ?
በመጀመሪያ ደረጃ ሰማያዊ ፓርቲን የምደግፍበት ምክንያት ከወጣቶች፣ በወጣቶች፣ ለወጣቶች፣ የተቋቋመ የፖለቲካ
ፓርቲ ስለሆነ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የአብዛኛውን የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ፍላጎት እና ጥቅም ሊወክል የሚችል ፓርቲ
ስለሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ35 ዓመት የዕድሜ ክልል በታች ያለው የህብረተሰብ ክፍል 70
በመቶውን ይሸፍናል የሚለውን ሀቅ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡ (የሚቀርበውን መረጃ ታሳቢ በማድረግ በአሁኑ ጊዜ
በኢትዮጵያ አማካይ የህይወት እድሜ ከ49 – 59 ዓመት ነው፡፡)
የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ) ብዙሀኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ለመወከል የሚያስችል የራሱን
የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ይፈልጋል፡፡ የአቦሸማኔው ትውልድ ለራሱ/ሷ መናገር፣ ለራሱ/ሷ መቆም፣ ለሴቶች፣ ለወንዶች
መቆምን ይፈልጋሉ፡፡ የእራሳቸውን እና የአገራቸውን ዕጣ ፈንታ ሊወስኑ የሚችሉት እራሳቸው ወጣቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
የጉማሬዎቹ ትውልድ (የእኔ ትውልድ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉማሬዎቹ፣ ለጉማሬዎቹ የተቀመሩ እና በእነርሱ
የአስተሳሰብ ንፍቀ ክበብ ውስጥ የታጠሩ ፍልስፍናዎች ስለሆኑ ከእረፍትየለሾቹ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች (የወጣቱ
ትውልድ) ህልሞች፣ ውስጣዊ ፍላጎቶች፣ ዓላማዎች እና የጋሉ ስሜቶች የስምምነት እምነቶች ንፍቀ ክበብ ውጭ ናቸው፡፡
እኛ የኢትዮጵያ የጉማሬዎች ትውልድ (የእኔ ትውልድ) የአቦሸማኔዎችን ትውልድ (የወጣቱን ትውልድ) ፍልስፍናአና
አስተያየት አንረዳውም፡፡ ይህም በመሆኑ ብዙዎቻችን በጎሳ እና በክልል (“ባንቱስታን” ወይም “ክልላዊ”) የፖለቲካ
ጭቃ፣ በሚያጣብቅ የጎሰኝነት ዝቃጭ ቆሻሻ፣ እና በታሪካዊ ምክንያተቢስ ጥላቻ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ተዘፍቀን
ስንዋኝ የቆዬን ስለሆነ ለስኬታማነት የማንበቃ የተሽመደመድን የህበረተሰብ ክፍል ነን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ
የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልዶች (የወጣቶች ትውልድ) የጥንቱ ወይም የኋላቀር ፋሽን የጎሳ ማንነት ፖለቲካ እስረኛ
መሆን አይፈልጉም፣ እንዲሁም ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከእራሳቸው ጋር በጥብቅ ተቆራኝቶ በታሰረ የታሪክ ክስተት መንገድ
ላይ ለመራመድ አይፈልጉም፡፡ እንዲሁም ነጻነታቸውን በማወጅ እና የእራሳቸውን ዕጣ ፈንታ ለመምረጥ በመወሰን
የእራሳቸው የሆነቸውን ኢትዮጵያ መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡
“የኢትዮጵያ የጉማሬ ቡድን” ታማኝ አባል እንዳለመሆኔ መጠን የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ ከኢትዮጵያ የጉማሬ
ትውልድ በጣም ልዩነት አለው የሚለውን እውነታ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ለእኔ እና ለእኔው የጉማሬ ትውልድ የዱላ
ቅብብሎሹን ለአቦሸማኔው ትውልድ በማቀበል ከጎን ሆነን የአቦሸማኔውን ትውልድ በትህትና የምናግዝበት የመጨረሻው ጊዜ
እየደረሰ መሆኑን ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ለዚህም ነው እራሴን ከጉማሬ ትውልድ ወደ “አቦ -ጉማሬ” ትውልድ
ያሸጋገርኩት፡፡ ይህንን ሽግግር “የአቦ – ጉማሬ ትውልድ መነሳሳት” በሚለው ትችቴ ላይ መዝግቤ ማስቀመጤ የሚታወስ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የወደፊቱ የኢትዮጵያ ወጣት ዕጣ ፈንታ በጥልቅ ያሳስበኛል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለማስታወስ
እንደሞከርኩት ሁሉ “ደስታ የራቀው እና በመጥፎ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣት በጊዜ ቀመር ተሞልቶ
ለመፈንዳት በመጠባበቅ ላይ የሚገኝ የሰው ቦምብ የመሁኑን ሀቅ ያመለክታል፡፡ የወጣቱ ተስፋ መቁረጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ
ደስታ እየራቀው መሄድ፣ በቅዠት ህይወት ውስጥ መኖር እና ለብዙ ጊዜ በሚቆይ የኢኮኖሚ ቀውስ በመደቆስ ጥንካሬን
ማጣት፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እና ተጠቃሚነትን ያለማግኘት እና የፖለቲካ ጭቆና በገፍ ተንሰራፍቶ መገኘት ሊፋቅ
የማይችል አስተማማኝ መረጃ ነው፡፡ ወጣቱ ለነጻነት ያለው ጥልቅ ፍላጎት እና የለውጥ ፈላጊነት ስሜት በእራሱ
ማረጋገጫ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ብቸኛ ጥያቄ የሀገሪቱ ወጣቶች ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉት እየጨመረ
በመጣው ወይም በሌላ በሰላማዊ የለውጥ አማራጮች…የሚለው ነው፡፡” ሰማያዊ ፓርቲ ተስፋ ያጣውን የወጣት ኃይል ወደ
ሰላማዊ ሽግግር በማምጣት በኢትዮጵያ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሦስተኛ በወጣት ኃይል አድራጊ እና ፈጣሪነት ላይ በሙሉ ልቤ እተማመናለሁ፡፡ የወጣት ሀሳብ እና ጥልቅ የለውጥ
ፈላጊነት ስሜት ልብን፣ አዕምሮን እና ሀገርን የመለወጥ ኃይል አለው፡፡ የወጣት ኃይል በዓለም ላይ ከሚገኙ
ጠብመንጃዎች፣ ታንኮች እና የጦር አውሮፕላኖች በላይ የበለጠ ኃይል አለው፡፡ የአሜሪካ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ
የተካሄደው በወጣቶች ኃይል በተከፈለ የጉልበት መስዕዋትነት አማካይነት ነው፡፡ አብዛኞቹ በአመራር ቦታ ላይ የነበሩት
እና የመብት ተሟጋቾች ወጣቶቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በቢርሚንግሀም አላባማ
የተካሄደውን የሲቪል መብቶች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲመሩ የ26 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ ጆን ሌዊስ የ23
ዓመት ወጣት የነበሩ ሲሆን 24 ጊዚያት ታስረዋል፣ እንዲሁም ድርጊቱን ሊያስታውሱት በማይችሉት መልኩ በብዙ
አጋጣሚዎች ሰውነታቸው ድቅቅ እስከሚል ድረስ ተደብድበዋል፡፡ እ.ኤ.አ በሜይ 6/1963 በበርሚንግሃም ከ2000
በላይ የሚሆኑ አፍሪካ አሜሪካውያን የሁለተኛ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች የዘር
መድልኦን በመቃወም ሰልፍ በመውጣታቸው ብቻ ለአሰቃቂው እስር ተዳርገዋል፡፡
ወጣት አሜሪካውያን በቬትናም ላይ በእብሪት በመነሳሳት የተካሄደውን ጦርነት እንዲቆም አድርገዋል፡፡ በካሊፎርኒያ
የዩኒቨርስቲ የተጀመረው የመናገር ነጻነት እንቅስቃሴ በአሜሪካ የመናገር ነጻነትን እና የዩኒቨርስቲ አካዳሚ
ነጻነትን አጎናጽፏል፡፡ ያለወጣቱ ድምጽ መስጠት ባራክ አቦማ ለፕሬዚዳንትነት መመረጥ አይችሉም ነበር፡፡ ኮሚኒስታዊ
ገዥዎችን እና በቅርቡም በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለመለወጥ አስቸጋሪ ናቸው ተብለው ይታሰቡ
የነበሩትን ርህራሄየለሽ አምባገነኖች በሰላማዊ ትግል አንኮታኩቶ በመጣሉ እረገድ ወጣቱ ኃይል ወሳኝ የሆነ ሚና
ተጫውቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተፈናጥጠው የሚገኙት ገዥዎች የንጉሳዊውን አገዛዝ እና
አምባገነናዊውን የወታደራዊ መንግስት በትጥቅ ትግል ለማንበርከክ ሲፋለሙ የነበሩ ወጣት “አብዮተኞች” ነበሩ፡፡
በእርጅና የእድሜ ጊዚያቸው ግን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር ለማስወገድ ሲፋለሙት የነበረውን ጭራቅ
ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ለመመስረት ለበርካታ ዘመናት መስዕዋትነትን
በመክፈል የእራሳቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ ባሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ኃይል ላይ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ እ.ኤ.አ
በ2005 አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ገዥ አካል ታጣቂዎች እንደ አበደ ውሻ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ
በመክለፍለፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በጥይት ጨፍጭፈዋል ገድለዋል፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለእስራት
ዳርገዋል፡፡ (በዚያን ጊዜ በሰው ልጅ ህይወት ላይ በጣም አስደንጋጭ እና አስፈሪ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀል
በማየቴ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት አንደቀላቀል ተገድጃለሁ፡፡) በአሁኑ ጊዜም እንኳ የኢትዮጵያ ወጣቶች
ለዴሞክራሲ፣ ለህግ ልዕልና፣ ለነጻነት እና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ሲባል የደም፣ የላብ እና የእንባ መስዕዋትነት
በመክፈል ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጡ እና ብሩህ አዕምሮ ያለው ወጣት እየተቀጣ፣ ፍርደገምድል ፍርድ
እየተበየነበት፣ እየታሰረ፣ እና ጸጥ እረጭ ብሎ እንዲገዛ እየተደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ የወጣት ዝርዝር የመጀመሪያው
እረድፍ ላይ የሚገኙት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡበካር
አህመድ፣ ውብሸት ታዬ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣ አህመዲን ጀቤል፣ አህመድ ሙስጣፋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ በቅርቡ ከህይወት
የተለየው የኔሰው ገብሬ እና ሌሎች ለቁጥር የሚያታክቱ ትንታግ የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው፡፡
በመጨረሻ ሆኖም ግን አስተዋጽኦው ቀላል ካልሆነው ከሰማያዊ ፓርቲ ፕሮግራም ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በደንብ አስቦበት እና የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባራዊ ፕሮግራም ነድፎ
የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው፡፡ ከእኔ ልዩ አተያይ እና ስጋት አንጻር በፍትሀዊ አስተዳደር፣ በሰብአዊ መብቶች እና በህግ
የበላይነት አተገባበር ላይ ትኩረት በማድረግ የፓርቲውን ፕሮግራም ስገመግመው በጠንካራ መሰረት ላይ የተዋቀረ ልዩ
ፓርቲ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ፓርቲው ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ እንዲሁም ከፖለቲካ ተጽዕኖ እና ጣልቃገብነት ፍጹም ነጻ
የሆነ እና ብቃት ያለው የፍትህ ስርዓት በሀገሪቱ እንዲመሰረት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ዳኞች ሲያጠፉ መከሰስ ያለባቸው
መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሙያቸው በቋሚነት ጡረታ እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ ተቀጥረው እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ፓርቲው
ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ከነሙሉ ስልጣኑ ጋር እንዲቋቋም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ፈርማ ባጸደቀቻቸው ዓለም
አቀፍ ውሎች እና ስምምነቶች ለመገዛት እና ለተግባራዊነታቸውም ዕውን መሆን ፓርቲው ጠንክሮ እንደሚሰራ ቃል
ገብቷል፡፡ የግለሰብ መብቶችን ጥበቃ የመናገር እና የእምነት ነጻነቶችን ጨምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ፓርቲው ቃል
ገብቷል፡፡ መንግስት እና ኃይማኖት በግልጽ መለያየት እንዳለባቸው ፓርቲው በጽኑ ያምናል፡፡ ፓርቲው ማንኛውንም
በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚደረግን ቅድመ ምርመራ አጥብቆ ይቃወማል፣ እንዲሁም ከህግ አግባብ ውጭ የሲቪክ
ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ማህበራት እንዳይዘጉ ያደርጋል፡፡ የሀገሪቱ የጦር እና የደህንነት ኃይል ታማኝነቱ ለሀገሪቱ
ህገመንግስት መሆን እንዳለበት እና በምንም ዓይነት መልኩ ለፖለቲካ ፓርቲ፣ ለጎሳ ቡድን፣ ለክልል ወይም ለሌላ
አካል ታማኝ መሆን እንደሌለበት ፓርቲው በፕሮግራሙ ላይ አጽንኦ በመስጠት አስፍሮታል፡፡ የፓርቲው የኢኮኖሚ፣
የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የባህል ጉዳዮችም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ ትኩረትን በጣም የሚስቡ ናቸው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን እንደ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ የአቦሸማኔዎች (ወጣቶች) ትውልድን እውነተኛ ድምጽ ለምን እንደምደግፍ፣
እንደ እራሴ ሀሳብ ሰማያዊ ፓርቲ እንደማንኛውም ተወዳድሮ ስልጣን በመያዝ ወደ ስልጣን ቢሮ ከሚገባ የፖለቲካ
ድርጅት የበለጠ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንደፖለቲካ ድርጅት እራሱን ቢያዘጋጅ እና በተለመደው መልክ ምርጫ ቢያሸንፍ
እና የፓርላማ ወንበር ቢይዝ ምንም አዲስ የማገኘው ነገር የለም፡፡ ከ80 በላይ “የተመዘገቡ ፓርቲዎች” ባሉባት
ሀገር (በጣም አብዛኞቹ ለይስሙላ የተቋቋሙ የጎሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች) እና ገዥው “ፓርቲ” በ99.6 በመቶ
በሚያሸንፍበት ሁኔታ ከግማሽ ነጥብ በመቶ ያነሰ ድምጽ ለማግኘት እንደሰማያዊ ፓርቲ ሁሉ ሌላ ፓርቲ ተመዝግቦ ለዚህች
በጣም በጣም ትንሽ ለሆነችው ድምጽ ለመወዳደር የመሞከሩን አስፈላጊነት ትርጉምየለሽ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ነው
ሰማያዊ ፓርቲን በኢትዮጵያ ከወጣቶች፣ ለወጣቶች፣ በወጣቶች የተቋቋመ የወጣቶች ንቅናቄ ነው የሚል እምነት ያለኝ፡፡
“የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄን” የኢትዮጵያ ወጣቶች ለእራሳቸው እና ለወደፊቱ ትውልድ የሚተላለፍ
ህልማቸውን እና ሀሳቦቻቸውን የሚተገብር ድርጅታዊ ተቋም አድርጌ እወስወደዋለሁ፡፡ እንደ ንቅናቄ ሰማያዊ ፓርቲ በብዙ
የአቅም ደረጃዎች ላይ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያን ወጣቶች ስለብዙው የሀገራቸው ታሪክ፣ ልማዶች እና
ባህሎች እንዲያውቁ የሚያደርግ “የትምህርት” ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች የማትከፋፈል የአንዲት ኢትዮጵያ፣
ኃያል ወራሪውን የአውሮፓ ኃይል አሸንፋ እና አሳፍራ የመለሰች የኩሩ አርበኞች ዘር የትውልድ ሀረግ መሆናቸውን
ያስተምራል፡፡ እንደ አሁኑ ሳይሆን በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም እና በአፍሪካ ለሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች የኩራት
ፈርጥ ነበረች፡፡ የአሁኑ የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ የቀደመውን ኩራታችንን እንደገና መልሶ ለኢትዮጵያውያን ህዝቦች
የማጎናጸፍ ዓላማን ሰንቆ ተነስቷል፡፡
“የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄን” ዋና ዋና ዕሴቶች እጋራለሁ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ገዥዎችን እና ኢፍትሀዊነትን በሰላማዊ
የትግል ስልት መንገዶች የማስወገድ እምነት አለው፡፡ በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ገዥዎችን እና ኢፍትሀዊነትን
በሰላማዊ የትግል ስልቶች በመጠቀም ለማስወገድ እሰብካለሁ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ ወጣቶች የሽግግር ኃይል ላይ
እምነት አለው፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ “እና በአፍሪካ” ላይ ወጣቶች የጻፍኳቸውን የሰኞ ዕለታዊ ትችቶች
በሙሉ መልክ በማስያዝ በጥራዝ ቢዘጋጁ የኢትዮጵያ ወጣቶችን የሽግግር ኃይል በተጨባጭ የሚያመላክት ማስረጃ
ይሆናልሉ፡፡ የእኔ መፈክርአሁንም በፊትም ወደፊትም ፣ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ተባበሩ፣ በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ፣ ኃይል
ለኢትዮጵያ ወጣቶች!” ነው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ አንድ ግብ ብቻ አለው፣ “ፍቅር የነገሰበትን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ” መፍጠር፣ ልክ
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በረዥሙ የትግል ጉዟቸው በአሜሪካ የሰብአዊ እና የሲቪል መብቶችን በማለም “ፍቅር
የነገሰበት ማህበረሰብን” ለመመስረት እንዳደረጉት ተጋድሎ ሁሉ፡፡ ዶ/ር ኪንግ እንዲህ ብለው አስተማሩ፣ “የሰላማዊ
ትግል ማህበራዊ ለውጥ መጨረሻው ዕርቅ ነው፣ መጨረሻው ኃጢያትን ተናዝዞ ንስሀ መግባት ነው፣ መጨረሻው ፍቅር
የነገሰበትን ማህበረሰብ መመስረት ነው፣ እንግዲህ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እና ፍቅር ነው በባላንጣነት የሚተያዩትን
ወገኖች ወደ ጓደኝነት የሚያመጣው፡፡” “ፍቅር የነገሰበት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ“ ከክልላዊነት (ባንቱስታን)
አመድነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚወጣ እምነቴ የጸና ነው፡፡
“ፍቅር የነገሰበት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ” የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ መሰረቱ አንድነት፣ ሰላም እና ተስፋ ነው፡፡
“ፍቅር የነገሰበት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ” ሰው በመሆኑ ብቻ አንድ ይሆናል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከከፋፋይ
የጎሰኝነት እና ከአፍቅሮ የጎሰኝነት ስሜት ነጻ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ማህበረሰብ እኩልነት፣ ፍትሀዊነት እና
ተጠያቂነት ያለው ህብረተሰብ ለመመስረት ጥረት ያደርጋል፡፡ “ፍቅር የነገሰበት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ“ ከእራሱ እና
ከጎረቤቱ ጋር ሰላም ፈጥሮ የሚኖር ህብረተሰብ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከጎሳ አለመቻቻል እና ጥላቻ ነጻ የሆነ
እንዲሁም ከፍርሃት፣ ጥልቅ ጥላቻ እና ከገዥዎች እና ከጨቋኞች ነጻ የሆነ ማህበረሰብ ይፈጥራል የሚል እምነት
አለኝ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ደኃ እና ሀብታም፣ ወጣት እና ሽማግሌ፣ ወንድ እና ሴት፣ ክርስቲያን እና
ሙስሊም… ለማለም ነጻ፣ ለማሰብ ነጻ፣ ለመናገር፣ ለመስማት እና ለመጻፍ ነጻ፣ ከጣልቃገብነት ነጻ ሆኖ ለማምለክ፣
ለመፍጠር ነጻ፣ ለመስራት ነጻ እና ነጻ ለመሆን ነጻ የሆነ ዓላማ ይዞ ነው የተነሳው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ
ሰላምን በአግባቡ በመጠቀም ጥላቻን፣ የጥላቻ መንፈስን፣ ለመጣላት መቸኮልን፣ ወደ ጓደኝነት፣ መተሳሰብ እና መከባበር
በማሻጋገር ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምን ያመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ንቅናቄው ከመራራ ትችት በውይይት፣ ከመቃረን
በስምምነት፣ ከጥላቻ በፍቅር፣ እና ጭካኔን፣ ወንጀለኝነትን እና ታጋሽየለሽነትን ለማሸነፍ የሰው ልጅን ክብር ከፍ
የሚያደርጉትን መርሆዎች እንደሚከተል እምነቴ የጸና ነው፡፡ “ፍቅር የነገሰበት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ“ “የተስፋ እና
የህልሞች መሬት” ነው፡፡ ይህ ማህበረሰብ ወጣቶች ለእኩል ዕድሎች፣ ለእኩል መብት እና ፍትህ እንዲያስቡ የሚያደርግ
ነው፡፡ ይህ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ወጣቶች ነጻ ሆነው ተስፋዎቻቸውን እና ህልሞቻቸውን በጋራ መካፈል እንዲችሉ
የሚያበቃ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ወጣቶች የማይገታ ተስፋ አንዳላቸው ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
ለሰማያዊ ፓርቲ ምን ማድረግ እንዳለብን እንጠይቅ፣
ሁሉም ኢትዮጵዊ በተለይም የእኔ የጉማሬው ትውልድ ከሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ጎን እንድንቆም አበረታታለሁ፣
እማጸናለሁም፡፡ አውቃለሁ፣ ብዙዎቻችሁ ቀደም ሲል ድጋፋችሁን ለመስጠት በሞከራችሁበት ጊዜ በተፈጠረው ያልተሳካ
የትግል ውጤት ምክንያት ተገቢነት ያላቸው ጥያቄዎች፣ ብዥታዎች፣ እና ጥርጣሬዎች ሊኖሯቹህ እንደሚችሉ እገነዘባለሁ፡፡
“እነዚህ ወጣት እና የአመራር ልምድ የሌላቸው ሰዎች ትክክለኛውን ነገር የሚሰሩ ለመሆናቸው ምን ማስተማመኛ
አለን?“ በማለት ተጠይቂያሁ፡፡ እኔም እንዲህ የሚል መልስ ሰጠሁ፣ “ልምድ ያለን እና እምነት የሚጣልብን የጉማሬው
ትውልድ አመራሮች የሆንነው ከዚህ ቀደም እንዴት ሰራን?“ አፍሪካ በማያቋርጥ አምባገነናዊ የአገዛዝ መዳፍ ስር ወድቃ
ስለምትገኝ የወጣቱን የህብረተሰብ ትኩረት የሚስቡ በርካታ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ
አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ስብዕናዎቻቸው ከምን ከምን ነገሮች እንደተዋቀሩ አሳይተውናል፡፡ የተዋቀሩባቸው
የመሰረት ድንጋዮች በዝርዝር ሲታዩ የሚከተሉትን ያካትታል፡ ድፍረት፣ የሞራል ጽናት፣ ስነስርዓት፣ ብስለት፣
ጀግንነት፣ ክብር፣ የመንፈስ ጽናት፣ ፈጣሪነት፣ ትህትና፣ ሀሳብ አፍላቂነት እና እራስን ለመስዋዕትነት ማዘጋጀት
ናቸው፡፡ ስብዕናዎቻቸውን በማክበር ላለመንበርከክ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል፣ ታስረዋል፣ እንዲሁም ተደብድበዋል፡፡
ሰላማዊ ትግሎቻቸውን አላቋረጡም፡፡ እኛን በማሳመን ሙሉ ድጋፋችንን ከማግኘታቸው በፊት ሌላ ምን ተጨማሪ መስዕዋትነት
መክፈል ይኖርባቸዋል? ወጣቶች እና አዲስ ነገር ለማምጣት ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው ናቸው፣ በሰላማዊ ትግል ለውጥ
ለማምጣት ተገቢው ልምድ ያላቸው ሲሆን ይህንኑ ልምዳቸውን እስከመጨረሻው ይቀጥሉበታል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ሰማያዊ ፓርቲ ለገዥው አካል ወይም ለሌላ ድብቅ ዓላማ ላላቸው ኃይሎች ተቀጣሪዎች ላለመሆናቸው
ምን ማረጋገጫ አለ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የምለው ነገር ቢኖር የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች፣
አባላት እና ደጋፊዎች የገዥው አካል ታማኝ ሎሌዎች ናቸው ብለን የምናስብ ከሆነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣
ፕሮፌሰር ያዕቆብ ኃይለማርያም እና ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያምም ሊጠቀሱ የሚችሉ ታማኝ ሎሌዎች ናቸው ማለት
ነው፡፡ ገዥው አካል ብልህ ከሆነ ሰማያዊ ፓርቲ ስለየህግ የበላይነት እና ስለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ያሉትን
ፕሮግራሞች በመገናኛ ብዙሀን ለማስተላለፍ እንዲችል መፍቀድ ይኖርበታል፣ ይህን ካደረገ እኔ ለዚህ ደጋፊ ነኝ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ገዥው አካል ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች (በሚስጥር እስር ቤቶች የሚገኙትን ጨምሮ) የሚለቅ ከሆነ፣
ጨቋኝ ህጎችን የሚሰርዝ ከሆነ፣ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎችን እና ምርጫ ማጭበርበርን የሚያቋም ከሆነ ከመንገድ
በመውጣት የመጀመሪያ በመሆን እነሱን በማሞገስ የምዘምር እሆናለሁ፡፡ ጉዳዩ በስልጣን ላይ ስላሉት ሰዎች አይደለም፣
ሆኖም ግን ጉዳዩ በስልጣን ላይ ስላሉት ጭራቃዊ ድርጊት ስለሚፈጽሙት ሰዎች እንጅ፡፡
ባለፉት አስርት ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ተመስርተው በመንቀሳቀስ ላይ የነበሩት እና በመንቀሳቀስ ላይ
የሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ስኬታማ ሳይሆኑ እንደቀሩ አንዳንድ ሰዎች ይነግሩኛል፡፡
እንዲህ በማለትም ይጠይቁኛል፣ “ሰማያዊ ፓርቲም ስኬታማ ሳይሆን የሚወድቅ ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለህ?“ ሰማያዊ
ፓርቲ ላለመውደቁ ምንም ዓይነት ዋስትናዎች የሉም፡፡ ስኬታማ ሳይሆን የሚወድቅ ከሆነ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እና
አባላት ጽናት እና እራስን ለስነስርዓት ያለማስገዛት፣ የዓላማ ጽናት እና እራስን መስዕዋት ለማድረግ ያለመቻል
ጉድለት ሊሆን አይችልም፡፡ በዋናነት ለውድቀቱ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ድጋፍ ያለማግኘት፣ ቅን መንፈስ ያለመኖር፣
በእራስ የመተማመን ጉድለት፣ የለጋሽነት እጥረት እና በአገር ውስጥ ካለው ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖች እና ከዲያስፖራው
ማህበረሰብ የማቴሪያል እና የሞራል ድጋፍ ለማግኘት ያለመቻል ነው፡፡ ፓርቲው ስኬታማ ባይሆን እና ለውድቀት ቢዳረግ
በእብሪትነት ተነሳስተን፣ የሌባ ጣታችንን ወደ ፓርቲው በመቀሰር፣ “ተናግሬ አልነበረም!“ ስንል ሦስቱ ጣቶቻችን
ደግሞ ቀስ ብለው ወደ እኛ እያመለከቱ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እንዲህ ሲሉ ተማጽነዋል፣
“እኔን በማስመዘግባቸው ስኬቶች አትገምግሙኝ፣ይልቁንም ምን ያህል ጊዜ እንደወደቅሁ እና ከውድቀቶች ተመልሸ
እንደተነሳሁ እንጅ” ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰማያዊ ፓርቲ ወደፊት ምን ያህል ጊዜ አዳልጦት ይወድቃል ብለን
ከመገምገም ይልቅ ፓርቲው በእኛ እገዛ እና ድጋፍ ከውድቀቱ እንደገና ለመነሳት ምን ያህል ጊዜ ጥረት ያደርጋል
የሚለውን ነው መገምገም የሚኖርብን፡፡
ባለፉት በርካታ ጊዚያት እንደታየው የሚያዋጡት የገንዘብ ድጋፍ አላግባብ ሊባክን ይችላል የሚል ስጋታቸውን
አንዳንድ ሰዎች ገልጸውልኛል፡፡ ጠንካራ የሆኑ የተጠያቂነት እና ግልጸኝነት ዋስትናዎችን ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ
ብለውም ይጠይቁኛል፣ “ባለፉት ጊዚያት ሌሎች እንዳደረጉት ሁሉ ሰማያዊ ፓርቲም በእርሱ ላይ ያለንን እምነት
ላለመሸርሸሩ በምን ሁኔታ ማረጋገጥ እንችላለን?”
በሰሜን አሜሪካ ያለው የሰማያዊ ፓርቲ የድጋፍ ስብስብ በጣም ጠንካራ እና በስነስርዓት የታነጸ የኢትዮጵያ ወጣት
ኃይል ስለሆነ ከዚህ ስብስብ ጋር መተዋወቄ እና አብሬም መስራቴ ታላቅ ክብር እና ደስታ ይሰጠኛል፡፡ እነዚህ ወጣት
ኢትዮጵያውያን/ት የኢትዮጵያን ወጣቶች ትግል ለመደገፍ ከኪሳቸው በርካታ ገንዘብ በማውጣት በስራ ላይ እንዲውል
በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሙያ ስብጥራቸውን ስንመለከት ወጣት ፕሮፌሽናሎች፣ በንግድ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ወንዶች
እና ሴቶች እንዲሁም የኢትዮጵያን የጎሳ፣ የጾታ እና የባህል ህብረ ብሄር የሚወክሉ ናቸው፡፡ የተያቂነትን እና
ግልጸኝነትን ዋጋ በሚገባ የተገነዘቡ ናቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው በመተማመን እና ለእሴቶቻቸው ተገዥ በመሆን
ድጋፋቸውን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ለወጣቶቹ ዕድሎችን በመስጠት መሞከር እና ለምሰጠው የድጋፍ ገንዘብ ችግር የለብኝም፣
ምክንያቱም ወጣቶቹ የዚህ አይነት ዉርደት ላይ መውደቅ አንደማይሹ ተገንዝበአለሁ፡፡ መርህን በሚያከብሩት የኢትዮጵያ
ወጣቶች እና ህዝቦች ታላቅ እምነት አለኝ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ትክክለኛውን ነገር ይሰራሉ የሚል እምነት የእኔ
ዋስትና ነው፡፡
እ.ኤ.አ ዴሴምበር 15/2013 በኣርሊንግቶን ከተማ አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጠራው የሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባ
ላይ በመገኘት ባደረግሁት ንግግር የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት እርዳታ ለመሰብሰብ እና ለኑስ አምስት
ሳንቲም ልመና ወደ አሜሪካ አልመጣም በማለት ለተሰበሰበው ታዳሚ ተናግሬ ነበር፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከእኛ በሰሜን
አሜሪካ ከምንኖር ኢትዮጵያውያን/ት እርዳታ ወይም የገንዘብ ልገሳ አይፈልግም፡፡ ይልቁንም ይልቃል ወደ አሜሪካ
የመጣው ገዥው አካል በሰማያዊ ፓርቲ ላይ እያደረሰ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ፣ የህግ ስርዓት ሂደቱን፣ በአባላቱ ላይ
የሚደርሱባቸውን ችግሮች፣ ጨካኝ አምባገነናዊ ስርዓት ባለበት ሁኔታ ፓርቲው ዓላማዎቹን ለማሳካት እንዴት እየሰራ
እንዳለ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ነጻ እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ትግል ላይ ያሏቸውን
ህልሞች እና ተስፋዎች ለእኛ ለወገኖቹ ለማካፈል ነው፡፡
በአሜሪካ ከተሞች ለሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባዎች በተያዙ ፕሮግራሞች ሁሉ በመገኘት በኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ
ለውጥ እንዲመጣ ለሚታገሉት ባለራዕይ ወጣቶች ለይልቃል፣ ለሰማያዊ ፓርቲ አባላት እና ለንቅናቄው ድጋፍ ሰጭ ጀግኖች
ወጣቶች አቀባበል ማድረግ እንዳለብን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በከተማው የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄዱትን ስብሰባዎች ወጣት
መሪዎች እንደእነ ይልቃል፣ እስክንድር፣ አንዷለም፣ ርዕዮት እና ሌሎች ብዙዎቹ በግል ያደረጓቸውን የጀግንነት
ስራዎች በማወደስ ብቻ የምናልፈው ሳይሆን በአዳራሹ ማክበር ያለብን ሌሎችም ወጣት ጀግኖች በአደባባይ በመንገዶች
በመውጣት ተቃውሟቸውን እንዲህ እያሉ ላሰሙት ጭምር ነው፣ “አንለያይም! አንለያይም!“ (እንደተባበርን እንኖራለን!)
ወይም ኢትዮጵያ፣ አገራችን! ኢትዮጵያ፣ አገራችን! (ኢትዮጵያ፣ የእኛ አገር!)፡፡ (አንለያይም! አገራችን፣
ኢትዮጵያ! በማለት ወጣቶቹ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲጮኹ ስሰማ ሁልጊዜ ይነሽጠኛል፡፡)
የሰማያዊ ፓርቲ መሪ ይልቃል እዚህ በመካከላችን መገኘቱ ለእኔ እ.ኤ.አ በ2005 በተደረገው ምርጫ
የተጭበረበረውን ድምጽ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው በአምባገነኑ መሪ ትዕዛዝ በታጣቂዎች በግፍ ያለቁት ወጣቶች
እንዳልሞቱ የሚያደርግ ኩራትን በመፍጠር እለቱን እንድናስታውሰው ያደርገናል፡፡ ይህ ዕለት የህግ የበላይነት ምንም
ይሁን ምን መቀጠል እንዳለበት እና ለነጻ እና ለፍትሀዊ ምርጫ ዕውን መሆን በሰላማዊ ትግል ሲፋለሙ ለነበሩት እና
በግፍ ለተገደሉት ወጣቶች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የይልቃል በመካከላችን መገኘት ሕያው ምስክር ነው፡፡
ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ምን ማድረግ እንችላለን? የተሸለ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው ለወጣት ጀግኖቻችን፣ ሲፋለሙ
ህይወታቸውን ላጡት፣ በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት፣ የግርፋት ስቃይ እየተፈጸመባቸው ላሉት፣ በየዕለቱ
ማስፈራራት ለሚፈጸምባቸው፣ ስቃይ እና ውርደት ለሚፈጸምባቸው ምስጋናችንን፣ ክብር መስጠታችንን እና አድናቆታችንን
እንዴት ነው መግለጽ የምንችለው? የሚል ይሆናል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ማግኘት የሚችለውን ማንኛውንም ድጋፍ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ የሞራል ድጋፋችንን ይፈልጋሉ፡፡ የእኛን
ማበረታታት ይፈልጋሉ፣ እኛ በእነርሱ ላይ እምነት ያለን መሆኑን ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ወጣቶችን በሙሉ
ለመድረስ እንዲችሉ፣ ለትምህርት እና ለግንዛቤ መፍጠሪያ ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ሊውሉ የሚችሉ ከእኛ የማቴሪያል ድጋፍ
ይፈልጋሉ፡፡ ድርጅታዊ ህልውናቸውን ለማጠናከር እና በመላ አገሪቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ መንቀሳቀስ እንዲችሉ
የእኛን የማቴሪያል ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ጠንካራ የህግ መከላከያ ገንዘብ ለማግኘት የእኛን ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ በአፍሪካ
አህጉር አላግባብ በበለጸጉ፣ ሙስናን በሚያራምዱ እና ምህረትየለሽ አምባገነኖች ላይ ትግል ለማድረግ የማቴሪያል
ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡
ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ የምናደርገው የገንዘብ ድጋፍ በሰላማዊ ትግል ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲ እና
ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅ የሚያደርጉትን በቅርብ በመደገፍ ምስጋናቸንን በማቅረብ ከጎናቸው መሆናችንን ለመግለጽ
ነው፡፡ ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ያለን ስጦታ ሰላሟ በእራሷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለማየት ሀብትን ማፍሰስ ነው፡፡
እንሰጣለን፣ እንለግሳለን፣ በዚህም መሰረት ቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ በእኛ ስህተት እና ድንቁርና በተፈጠረው ሁኔታ
ሳይቸገር በአዲሲቱ ኢትዮጵያ በሰላም ይኖራል፡፡ የእኛን ወጣት ትውልድ መደገፍ የእያንዳንዳችን እና እንደሀገርም
የማህበረሰባችን ኃላፊነት ነው፡፡ እኛ ልጆቻችንን፣ ሁሉንም በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶችን ካልረዳን… ማን እንዲረዳ
ይፈለጋል?
ሰማያዊ ፓርቲ ለእኛ ምን እንደሚያደርግልን እንጠይቅ፣
እ.ኤ.አ በኦገስት 2012 በአንድ ትችቴ ላይ “የአቦሸማኔው ትውልድ፣ የጉማሬው ትውልድ” በሚል ርዕስ እንዲህ
ስል ጠየቅሁ፣ “ኢትዮጵያን ሊጠብቅ ሊያድን የሚችል ማን ነው?“ በሰላማዊ መንገድ በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት መከተል
ያለብን መንገድ አገራዊ ውይይት ማድረግ እንደሆነ የኢትዮጵን ወጣቶች ተማጽኛለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቤቱታዬን
ለበርካታ ጊዚያት በተደጋጋሚ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄን በመጀመሪያ በተጠናከረ መልኩ በእራሳቸው
በፓርቲው አባላት ላይ በቀጣይም በመላው የኢትዮጵያ ወጣት ማህበረሰብ ላይ የዕርቅ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ
ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የዕርቅ ውይይት በኢትዮጵያ የወጣቱ ህብረተሰብ ውይይት መጀመር ቀጥሎ
የሚፈጸም ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ እራሳቸውን ማጠናከር አለባቸው፣ የእራሳቸውን የፖለቲካ እና የማህበራዊ ቦታ
መፍጠር አለባቸው፡፡ አገራቸው ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ሽግግር ማድረግ እንድትችል
የእራሳቸውን አጀንዳ በመቅረጽ ወጣቶቹ ዘርፈ ብዙ ውይይቶችን መጀመር አለባቸው፡፡ የቋንቋ፣ የኃይማኖት፣ የጎሳ፣
የጾታ፣ የክልል እና ወዘተ ገደብ ሳይኖር ወጣቶች የእራሳቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የዘመቻ እቅድ ማዘጋጀት እና በወጣቱ
ማህበረሰብ ዘንድ ንግግሮችን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ውይይቶቻቸው ግልጽ በሆኑ መርሆዎች፣ በእውነት፣
በዴሞክራሲያዊ ተግባሮች እና በነጻነት እና በሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው፡፡ ከፍርሃት
እና ከጭፍን ጥላቻ ነጻ ሆነው መወያየት አለባቸው፡፡ ሆኖም ግን በመከባበር እና በሰለጠነ መንገድ መከናወን
ይኖርበታል፡፡ ከሁሉም በላይ የአቦሸማኔው ትውልድ የውይይት ሂደቱን “የእራሱ” ማድረግ አለበት፡፡ የአቦሸማኔው
ትውልድ በሚሰበሰብበት ጊዜ የጉማሬው ትውልድም ይገኛል፣ ነገር ግን በዝምታ ማዳመጥ ነው ያለባቸው:: ወጣቱን
የህብረተሰብ ክፍል በቀላሉ ለማታለል የሚችሉ መሰሪ የጉማሬው ትውልድ አበጋዞች ስለሚኖሩ ምንጊዜም ቢሆን የአቦሸማኔው
ትውልድ ነቅቶ ባይነ ቁራኛ ሊጠብቃቸው ይገባል፡፡ በአረብ የለውጥ አመጾች/Arab Spring እንደታየው ሁሉ
ወጣቶች በወጥመድ ተይዘው የታዩባቸው ሁኔታዎች ስለነበሩ የኢትዮጵያ ወጣቶችም በወጥመዶች እንዳይጠለፉ ጥንቃቄ ማድረግ
አለባቸው፡፡ በመጨረሻም በማታለል የተካኑት የጉማሬው ትውልድ አባላት ወጣቶችን ከጨዋታ ውጭ እንዲሆኑ፣
እንዲጭበረበሩ፣ እንዲደለሉ ያደርጓቸዋል፡፡ መጠንቀቅ ተገቢ ነው::
የዕርቅ ወይይቶች በድንገት እና ተራ በሆነ መልኩ በወጣት የመብት ተሟጋቾች መካከል መጀመር እንዳለባቸው
አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ እንደዚህ ያሉ ውይይቶች በሚግባቡ እና ተመሳሳይነት አስተሳሰብ ባላቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች
ወጣቶች መካከል በመንደር ወይም በጎረቤት ደረጃ መካሄድ ይችላሉ፡፡ ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ወጣቶች
አቅማቸውን፣ ያላቸውን እምቅ ኃይል፣ ዕድሎችን እና ችግሮችን ለይተው በማውጣት ዕቅድ ነድፈው ትናንሽ ህብረተሰብ
አቀፍ የዕርቅ ውይይቶችን ማካሄድ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያሉትን ድርጅቶች፣ ተቋሞች፣ ማህበራትን እና መድረኮችን
በመጠቀም ወጣት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዕርቅ ውይይቶችን በማካሄድ የወጣቶችን ግንዛቤ ማሳደግ ይችላሉ፡፡
የዕርቅ ወይይት መነጋገርን ብቻ አይደለም የሚያካትተው ነገር ግን እርስ በእርስ በንቃት መደማመጥን ጭምር
እንጅ፡፡ ወጣቶች ከኢትዮጵያ ብሄረሰቦች እርስ በእርስ በመማማር የእራሳቸውን ብዙሀንነት ማጠናከር ይችላሉ፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ ከጉማሬው ትውልድ ስህተቶች እና ከሌሎች አገሮች ወጣቶች ልምዶችም ለመማር
ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አቦሸመኔ ትውልድ የሚያደርጓቸው የዕርቅ ውይይቶች በመርህ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ አጥብቄ
እማጸናለሁ፡፡ ወጣቶች ደስተኛ ባልሆኑባቸው ነገሮች ላይ መቃወም መቻል አለባቸው፡፡ በነገሮች ላይ አለመስማማት ማለት
የዕድሜ ልክ ጠላት መሆን ማለት አይደለም፡፡ የሰለጠነ ውይይት ማድረግ ለጉማሬው ትውልድ ከባድ ቢሆንም ለአቦሸማኔው
ትውልድ ግን በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ምነው ዝምታ?
“ዓለም አቀፍ ማጭበርበር በተንሰራፋባት ምድር ላይ“ ዝምታ ከቃላት እና ከስዕል የበለጠ ይናገራል፡፡ ማርቲን
ሉተር ኪንግ እንዲህ አሉ፣ “በመጨረሻ የምናስታውሰው የጠላቶቻችንን ቃላት አይደለም፣ ነገር ግን የጓደኞቻችንን ዝምታ
እንጅ“፡፡ ይህንን ትችት ካጠናቀቅሁ በኋላ “ስለጓደኞቻችን” “ዝምታ” መናገር አለብኝ፣ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ
ዝምታ ከመናገር የበለጠ የመግለጽ ችሎታ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፓርቲ መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ
በመጡበት ጊዜ እና እስከ አሁን ድረስ ለበርካታ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች
በተገኙበት ስብሰባ ላይ የወጣቶቹ መሪ ንግግር በሚያሰሙበት ጊዜ ትኩረትን በሚስብ መልኩ የአሜሪካ ድምጽ ወኪል
ጋዜጠኛ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ድርጊቱን ለመዘገብ አንድም ጋዜጠኛ ሳይልክ ቀርቷል፡፡ የአሜሪካ ድምጽ
ዜናውን ለመዘገብ ለምን እንዳልተገኘ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባ ግን ከተለያዩ የኢትዮጵያ
ስፖርቶች፣ ባህላዊ፣ አካዳሚያዊ እና የማህበረሰብ ስብሰባዎች እንዲሁም የመጽሀፍት ርክክብ ፊርማ ስነስርዓት ሲኖር
የአሜሪካ ድምጽ በሳምንቱ መጀመራያ እና በሳምንቱ ማጠቃለያ በዋሽንግተን ዙሪያ አካባቢ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ከሚዘግበው
የሚያንስ አለመሆኑን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ምናልባትም ሰማያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ለአሜሪካ
ድምጽ ምንም ያልሆኑ ቀላል ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ለወጣቶቹ ግድ ላይኖረው ይችላል፣ የኢትዮጵያ
ወጣቶችም ለአሜሪካ ድምጽ ጉዳያቸው አይደለም፡፡
የአሜሪካ ድምጽ እንዲገነዘበው የምፈልገው ነገር ግን በሟቹ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዝናዊ “ኢትዮጵያ
ላይ ዘር ማጥፋት” ፕሮፓጋንዳ አካሂደዋል የሚል ክስ በይፋ ባስታወቀበት ጊዜና ሌላም ጊዜ ወንጭፋቸውን
ሲያነጣጥሩባቸው እና ቀስቶቻቸውን ሲቀስሩባቸው በነበረበት ወቅት ከእነርሱ ጎን ቆሜ ነበር፡፡ በዚያ ውንጀላ ጊዜ
የአሜሪካ ድምጽ በጽናት ለመርህ የቆሙ መሆናቸውን፣ ለሙያው ክብር ሰጥተው ይዘግቡ እንደነበር፣ ያለአድልኦ እንደሚሰሩ
ጊዜን አክብረው ደግመው እና ደጋግመው እንደሚዘግቡ ሽንጤን ገትሬ ተከራክሪያለሁ፡፡ የአሜሪካ ድምጽ በሰማያዊ ፓርቲ
ጉባኤ ላይ በመገኘት እንደ ድሮው ሁሉ በጽናት ለመርህ ቆመው፣ ለሙያው ክብር ሰጥተው እና ያለአድልኦ የጉባኤውን
ሂደት እንደሚዘግቡ እጠብቅ ነበር፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ ድምጽ የሚለውን ስያሜ የዝምታ
ድምጽ ተብሎ መጠራት ጀመረ ወይ ብለው እየጠየቁ ይሆናል፡፡ የዝምታ ድምጹን ለመስማት እንቀጥላለን፣ ሆኖም ግን
በዝምታ አይደለም የምንሰማው፡፡
ከዚህ በኋላ ዝምታ መኖር የለበትም፣ ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንጩህ እና ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ድጋፋችንን
እናሳይ፣ ዝምታን ከዚህ በኋላ እናቁም፡፡ ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ድጋፋችንን በይፋ እናውጅ፡፡ ቀጥ ብለን እንቁም
እና በእነርሱ እንኩራ፡፡ ለሚያካሂዱት ሰላማዊ እና ግጭት አልባ የስርዓት ለውጥ ትግል አድናቆታችንን በመግለጽ
ድጋፋችንን እንስጥ፡፡ ወደ ነጻነት የሚወስደው መንገድ የቱንም ያህል ረዥም ጉዞ ቢፈጅ ከእነርሱ ጋር መሆናችንን
እናረጋግጥላቸው፡፡ ወጣቶቹ በመጨረሻም ድልአድራጊዎች ይሆናሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ አባላትን እንደምንወዳቸው
በተግባር እናረጋግጥላቸው!
የኢትዮጵያ ወጣቶች ተባበሩ፣ በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ፡፡ ኃይል ለኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶች!
ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment