የዓረና መድረክ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እንዳሳወቀው፤ ከሽሬ ህዝብ ጋር በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ለእሁድ
ታህሳስ 20, 2006 ዓም በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ መጥራቱን ገልጿል። የዓረና አመራር አባላት
በሽሬ እንዳስላሴ ከተማና አከባቢው ቅስቀሳ ጀምረዋል። ስብሰባው ከጠዋቱ ሦስት የሚጀምር ሲሆን በከተማ ልማት አዳራሽ
ይደረጋል።
የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው እንደገለጸው፤ የሽሬ ህዝብ ፅኑ ሲሆን በትጥቅ ትግሉ ዋነኛ ተካፋይ ነበር። በህወሓት
ትግል ወቅት ከፍተኛ መስዋእት ከከፈሉ የትግራይ አከባቢዎች በቀዳምነት የሚጠቀስ ሲሆን በልማታዊ ተጠቃሚነት ግን
የመጨረሻ ደረጃ ከሚይዙ አከባቢዎች ይሰለፋል።
ሽሬዎች ህወሓትን ተንከባክበው አሳደጓት። ህወሓት ስልጣን ከያዘች በኋላ ግን ተመልሳ ሽሬዎችን ጎዳች። ህወሓት ለሽሬ ከተማ የውኃ አገልግሎት ለማቅረብ ሃያ ሦስት ዓመት ፈጀበት። አሁንም ችግሩ አልተፈታም።
መቼም የሽሬን ሰው ማስፈራራት አይቻልም። የህወሓት ካድሬዎች እንደለመዱት ህዝቡ በስብሰባ እንዳይሳተፍ ለመከልከል ምን ያደርጉ ይሆን? አብረን እናያለን።
“እሁድ ጠዋት በሽሬ ከተማ እንገናኝ።” በማለት መልእክቱን አስተላልፏል – የዓረና መድረክ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣ አቶ አብርሃ ደስታ።
No comments:
Post a Comment