March 12, 2013
ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጽማቸዉን ግፎች በሰፊዉ የዳሰሰና አያሌ የመፍትሄ ሀሳቦችን ያካተተ ህዝባዊ ስብሰባ አሜረሪካን ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የዲሲ፤ የቨርጀንያና የሜሪላንድ ነዋሪ ኢትዮጵያዉያን በተገኙበት ባለፈዉ እሁድ መካሄዱን እዚያዉ ዋሽንግተን ዉስጥ የሚገኙ የግንቦት ሰባት ዘጋቢዎች በላኩልን ዜና ገለጹ። በዚህ የእስልምናና የክርስትና እምነት አባቶች፤ ምሁራን፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና የሰብዓዊ መብት ታጋዮች በተሳተፉበት ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተዉ ንግግር ካደረጉ ታዋቂ ኢትዮጵያዉያን ዉስጥ ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ፤ ዝነኛዉ ጋዜጠኛ ሳድቅ አህመድ፤ ከእልምና እምነት አመራር አካባቢ ሼክ ከሊድና አቶ ነጂብ መሐመድ፤ ከምሁራን ዶ/ር አክሎግ ቢራራና አቶ ፈቃደ ሸዋቀና የሚገኙበት ሲሆኑ ስብሰባዉን የመሩት ደግሞ ወ/ት ሂሩት ልብስወርቅ ናቸዉ።በዚህ ስምንት የተለያዩ ተናጋሪዎች ንግግር ባደረጉበት ስብሰባ ላይ ከአንድ አመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረዉ የኢትዮጰያዉያን ሙስሊሞች ትግል በሽብረተኝነት የመፈረጁ ጉዳይ፤ የታሪካዊዉ የዋልድባ ገዳም ጉዳይና ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርሲቲያን ለሁለት የመከፈሏ ጉዳይ የስብሰባዉን ተሳታፊዎች በብዛት ያወዬዩ ዋና ዋና አርዕስቶች ነበሩ። ይህንን ስብሰባ ከብዙ ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ከተደረጉት ስብሰባዎች ልዩ የሚያደርገዉ የአገራችን ሁለቱ ትልልቅ ሐይማኖት መሪዎች መድረክ ላይ ጎን ለጎን ተቀምጠዉ ይህ የምናደርገዉ ትግል የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብትና ለነጻነት የሚያደርገዉ ትግል ስለሆነ እስላምና ክርስቲያን ብለን ሳንከፋፈል በጋራ እንታገል የሚል ጥሪ ማስታለፋቸዉ ነዉ። አቡነ ፊሊጶስ ወያኔ ክርስቲያንና እስላም እያለ ለመከፋፈል የሚያደርገዉን ጥረት ማክሸፍ ብቻ ሳይሆን የወንድሞቻችንን ትግል በሽብርተኝት መፈረጁን ነግበኔ ነዉና አጥብቀን ልንቃወመዉና ልንዋጋዉ ይገባል ሲሉ ሼክ ከሊል ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደ ህዝብ የምንገዘዉም ነጻ የምንወጠዉም አንድ ላይ ነዉ፤ ሙሰሊሙ ነጻ ሳይወጣ ክርስቲያኑ ነጻ መሆን አይችልም ወይም ያሻንን ያክል ብንታገል ክርስቲያን ወንድሞቻችን እየተገዙ እኛ ሙስሊሞች ብቻችንን ነጻ ነን ማለት አንችልም ብለዋል።
በስብሰባዉ ላይ የተገኙ ቁጥራቸዉ በርካታ የሆነ ኢትዮጵያዉያን በስብሳዉ እጅግ የረኩ መሆናቸዉን ጥያቄ በመጠየቅና አስተያት በመስጠት ያሳዩ ሲሆን በስብሰባዉ ላይ በርካታ ሴቶች እህቶቻችን ተገኝተዋል። አብዛኛዉ ተሰብሳቢና ተናጋሪዎች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን ከአንድ አመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረዉን የሙስሊም ወንድሞቻችን “ድምጻችን ይሰማ” የሚል ትግል እንዲቀላቀልና አገሩን ኢትዮጵያን ከወያኔ ዘረኝነት ማዳን እንዲችል ተዳጅቶ መታገል እንዳለበት አበክረዉ አስጠንቅቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የስብሰባዉ ተሳታፊዎች እንደዚህ አይነት ህዝብን የሚያሳትፍና የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር ስብሰባ በየግዜዉ እንዲደረግና የስብሰባ ተሳታፊዎችም በአድማጭነት ብቻ ሳይሆን በታጋይነትም እንዲሳተፉ ጥሪ አድርጓል።
No comments:
Post a Comment