Saturday, April 12, 2014

አሸባሪው ኢህአዴግና ነፃው ፕሬስ


ከሚልክያስ መንግስቱ
በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ ስልጣን ከያዘ 23ዓመት አስቆጠረ። ይህን ያህል አመት በስልጣን ቆይቶ ህዝቡን በሰላም መምራት አልቻለም። ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ አውጥቻለሁ፣ ሀገሪቱንም እያሳደኩ ነው..ቢልም ህዝቡ ግን፥ ኑሮ ተወደደ፣ ሀገራችን ተከፋፈለች፣ ዲሞክራሲ የለም፣ ሰብአዊ የመብት ረገጣ እየተፈጸመ ነው በማለት ማማረሩን ቀጥሎዋል። ከብዙ ኢትዮጵያውያኖች ጋር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ገብቶዋል።
ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ጥያቄና ቅራኔ በማሳወቅ ዙሪያ ነፃው ፕሬስ ታሪካዊና አገራዊ ግዴታውን በጀግንነት እየተወጣ ነው። በዚህም ምክንያት የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የአንባገነኑ ኢህአዴግ መንግስት ሰለባ ሆነዋል። እንደ አምንስቲ መግለጫ መሰረት ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ከ1984ዓ.ም ጀምሮ ከ200 በላይ ጋዜጠኞች ተሰደዋል። ከ1992 እስከ 2005 ብቻ 38 ጋዜጠኞች እንደታሰሩ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲ.ፒ.ጄ ገልጾዋል። ሲ.ፒ.ጄ ባወጣው መግለጫ ባለፉት 10 አመታት ከ79 በላይ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ ከ75 በላይ የሚሆኑ አሳታሚ ድርጅቶች እንደተዘጉ ገልጾዋል። መንግስትን በድፍረት በመተቸታቸውና እውነትን ለህዝብ በማሳወቃቸው ምክንያት በዋነኛነት ከሚታወቁት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙና ውብሸት ታዬ እስከአሁን በእስር ይሰቃያሉ።
የኢህአዴግ መንግስት ከፈፀማቸው ፋሺስታዊ ድርጊቶች መካከል ታሪክ ይቅር ከማይላቸው የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። አንጋፋውና እውቁ ጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌ አራት ጊዜ በማሰር 16 ክስ መስርተውበታል። ይህም አልበቃ ብሎ የወያኔ ደህንነቶች በመኪና ገጭተው አደጋ አድርሰውበታል። ቢሮውን አቃጥለውበታል። እዚህ አሜሪካ ሀገር ከመጣ በኋላ ፓስፖርቱን ለማሳደስ ሲጠይቅ ፖስፖርቱን እንዲቀማ አድርገዋል። የተለያዩ ጋዜጦች አሳታሚ የነበረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በማእከላዊ ተደብድቦዋል። ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እስር ቤት ወልዳለች። አሸባሪው ወያኔ/ኢህአዴግ በእስክንድር ላይ በፈጠራ ክስ 18 አመት ፈርዶበታል። የነፃው ፕሬስ አባል የነበረው ጋዜጠኛ መኮንን በወያኔ ደህንነቶች በተፈፀመብት እስርና እንግልት ምክንያት የገዛ ህይወቱን አጥፍቶዋል። የሕወሐት/ኢህአዴግን ምስጢር በድፍረት ሲያጋልጥ የነበረውና ኢየሩሳሌም አርአያ በሚል ብእር ስም የሚታወቀው ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም በሰባት ፌዴራል ፖሊሶች ተደብድቦ ስድስት ሜትር ድልድይ ውስጥ ተወርውሮዋል፤ አካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአሜሪካ ድምፅ ባልደረባ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ ሰሎሞን ክፍሌ የሚወዳት ባለቤቱን በሞት ማጣቱን ተከትሎ አስክሬንዋን ይዞ አገር ቤት መሄድና አፈር ማልበስ አልቻለም። አገር ወዳድና ለእውነት የቆመ ጋዜጠኛ በመሆኑ በወያኔ/ኢህአዴግ የውሸት ክስ ስለተለጠፈበት ብቻ የ30 አመት ባለቤቱ የቀብር ስነስርአት ላይ መገኘት አልቻለም። አሸባሪው ኢህአዴግ ዛሬም በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፅመው አፈናና እስር ቀጥሎዋል።
Free Ethiopian journalists poster

ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ (ነገረ ኢትዮጵያ)


አዲስ አበባ፡- ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የተነጠቁ መብቶችን እናስመልስ!›› በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከአሁን ቀደም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያልተሰጣቸው ከመሆኑም ባሻገር ጭራሹን እየተባባሱ በመምጣታቸውና ህዝብም እየተማረረ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉን መጥራት እንዳስፈለገ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡Ethiopia's blue party called for rally in Addis Ababa
ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 2005 ዓ.ም ያደረገውን ጨምሮ በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ባደረገበት ወቅት የኑሮ ውድነት፣ የእምነት ጣልቃ ገብነት፣ ሉዓላዊነት፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀልና ሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንስቶ የነበረ ቢሆንም ጥያቄዎቹ ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ የህዝብ ግንኙነቱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በእስልምና እና ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስና አሁንም ድረስ ተባብሰው መቀጠላቸው ሰላማዊ ሰልፉን በመጥራት ህዝቡ እነዚህን የተነጠቁ መብቶች እንዲያስመለስ ማስተባበርና ማታገል የግድ በማለቱ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ለገዥው ፓርቲ ስልጣን እንጅ ለህዝብ አገልግሎት የማይጨነቁት ተቋማት ስራቸውን በሚገባ ባለመስራትቸው ህዝብ ለከፈለው ክፍያ የሚገባውን አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑም ሌላኛው ሰላማዊ የሰልፉ ምክንያት መሆኑን ተገልጹዋል፡፡ በተለይ የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮሚኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ህዝብን እያማረሩ መቀጠላቸው መፍትሄ ስለሚያስፈልገው የሰላማዊ ሰልፉን አስፈላጊነት እንዲሚያጎላው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳ ‹‹የህዝብ መብት መነጠቅና የአግልግሎቶች እጦት ሰላማዊ ሰልፉን ወቅታዊ ቢያደርገውም የሰማያዊ ፓርቲ በአመት ውስጥ ከያዛቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ህዝብ የተቀማቸውን መብቶች ማስመለስ መሆኑንና ይህም በተደጋጋሚ በተለያዩ ሚዲያዎች መገለጹን›› አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ገልጸዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ እሁድ ሚያዚያ 19 ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ካሳንቺስ ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት እስከ ጃን ሜዳ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን ጃን ሜዳ የተመረጠበት ምክንያትም መብቱን የተነጠቀውና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በሚገባ ማግኘት ያልቻለው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ጥያቄዎቹን እንዲያነሳ ሰፊ ቦታ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየ ክፍለ ከተማው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው ‹‹በሀይል የተቀሙትን መብቶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያውና እያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ በማድረግ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Source: – ነገረ ኢትዮጵያ