Saturday, April 12, 2014

አሸባሪው ኢህአዴግና ነፃው ፕሬስ


ከሚልክያስ መንግስቱ
በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ ስልጣን ከያዘ 23ዓመት አስቆጠረ። ይህን ያህል አመት በስልጣን ቆይቶ ህዝቡን በሰላም መምራት አልቻለም። ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ አውጥቻለሁ፣ ሀገሪቱንም እያሳደኩ ነው..ቢልም ህዝቡ ግን፥ ኑሮ ተወደደ፣ ሀገራችን ተከፋፈለች፣ ዲሞክራሲ የለም፣ ሰብአዊ የመብት ረገጣ እየተፈጸመ ነው በማለት ማማረሩን ቀጥሎዋል። ከብዙ ኢትዮጵያውያኖች ጋር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ገብቶዋል።
ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ጥያቄና ቅራኔ በማሳወቅ ዙሪያ ነፃው ፕሬስ ታሪካዊና አገራዊ ግዴታውን በጀግንነት እየተወጣ ነው። በዚህም ምክንያት የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የአንባገነኑ ኢህአዴግ መንግስት ሰለባ ሆነዋል። እንደ አምንስቲ መግለጫ መሰረት ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ከ1984ዓ.ም ጀምሮ ከ200 በላይ ጋዜጠኞች ተሰደዋል። ከ1992 እስከ 2005 ብቻ 38 ጋዜጠኞች እንደታሰሩ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲ.ፒ.ጄ ገልጾዋል። ሲ.ፒ.ጄ ባወጣው መግለጫ ባለፉት 10 አመታት ከ79 በላይ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ ከ75 በላይ የሚሆኑ አሳታሚ ድርጅቶች እንደተዘጉ ገልጾዋል። መንግስትን በድፍረት በመተቸታቸውና እውነትን ለህዝብ በማሳወቃቸው ምክንያት በዋነኛነት ከሚታወቁት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙና ውብሸት ታዬ እስከአሁን በእስር ይሰቃያሉ።
የኢህአዴግ መንግስት ከፈፀማቸው ፋሺስታዊ ድርጊቶች መካከል ታሪክ ይቅር ከማይላቸው የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። አንጋፋውና እውቁ ጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌ አራት ጊዜ በማሰር 16 ክስ መስርተውበታል። ይህም አልበቃ ብሎ የወያኔ ደህንነቶች በመኪና ገጭተው አደጋ አድርሰውበታል። ቢሮውን አቃጥለውበታል። እዚህ አሜሪካ ሀገር ከመጣ በኋላ ፓስፖርቱን ለማሳደስ ሲጠይቅ ፖስፖርቱን እንዲቀማ አድርገዋል። የተለያዩ ጋዜጦች አሳታሚ የነበረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በማእከላዊ ተደብድቦዋል። ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እስር ቤት ወልዳለች። አሸባሪው ወያኔ/ኢህአዴግ በእስክንድር ላይ በፈጠራ ክስ 18 አመት ፈርዶበታል። የነፃው ፕሬስ አባል የነበረው ጋዜጠኛ መኮንን በወያኔ ደህንነቶች በተፈፀመብት እስርና እንግልት ምክንያት የገዛ ህይወቱን አጥፍቶዋል። የሕወሐት/ኢህአዴግን ምስጢር በድፍረት ሲያጋልጥ የነበረውና ኢየሩሳሌም አርአያ በሚል ብእር ስም የሚታወቀው ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም በሰባት ፌዴራል ፖሊሶች ተደብድቦ ስድስት ሜትር ድልድይ ውስጥ ተወርውሮዋል፤ አካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአሜሪካ ድምፅ ባልደረባ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ ሰሎሞን ክፍሌ የሚወዳት ባለቤቱን በሞት ማጣቱን ተከትሎ አስክሬንዋን ይዞ አገር ቤት መሄድና አፈር ማልበስ አልቻለም። አገር ወዳድና ለእውነት የቆመ ጋዜጠኛ በመሆኑ በወያኔ/ኢህአዴግ የውሸት ክስ ስለተለጠፈበት ብቻ የ30 አመት ባለቤቱ የቀብር ስነስርአት ላይ መገኘት አልቻለም። አሸባሪው ኢህአዴግ ዛሬም በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፅመው አፈናና እስር ቀጥሎዋል።
Free Ethiopian journalists poster

No comments:

Post a Comment