Wednesday, January 28, 2015

ኢትዮጵያ የማን ነች?


“ኢትዮጵያ የማን አገር ነች” የሚል ጥያቄ ከዚህም ከዚያም እየተሰማ ነው። ህወሃቶች ከፈጠሯቸው ቀውሶች መካከል አንዱ ይሄው ነው። ዜጎች የአገር አልባነት ስሜት ውስጥ ገብተው የገዛ አገራቸውን “የማን ነች” ብለው እንዲጠይቁ መገደዳቸው።
ለኢትዮጵያዊያኑ ኢትዮጵያ አገራቸው እየሆነችላቸው አይደለም። ኢትዮጵያዊ መሆን ወንጀል እስኪመስል ድረስ በዜጎች ላይ ግፍ እየተፈፀመ ነው። የሚፈፀመው የግፍ ዓይነት ወሰን የለውም። ግማሹ በጠራራ ፀሃይ ደሙ እንዲፈስ ይደረጋል። ሌላው ለቁም ስቃይ ወደ ወይኒ ይጋዛል። ቀሪውም እትብቱ የተቀበረበትን አገር ትቶ ለመሰደድ ይገደዳል። በአገሪቷ ውስጥ የሚፈፀመውን ወሰን አልባ በደል የተመለከቱ ኢትዮጵያን ከውዳቂ መንግስታት ተራ መድበዋታል። በኢትዮጵያችን የዜጎችን መብት አስከብሮ ለመምራት ብቃት ያለው መንግስት ባለመኖሩ እጣ ፈንታችን እንዲህ ከውዳቂ አገራት ተርታ መግባት ሁኗል።
ኢትዮጵያን ለመምራት ብቃት ያለው መንግስት ቢኖር ኑሮ ለረዥም ዘመን በሰላም ተጎራብተው ይኖሩ በነበሩ ህዝቦች መካከል ግጭት ተፈጠረ መባልን ባልሰማን ነበር።ህወሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ሆን ተብሎ በሚፈጠር ግጭት ብዙ ደም ፈሷል። አማራው ከኦሮሞው፤ ትግሬው ከአማራው እና ከአፋሩ፤ ሶማሌው ከኦሮሞ፤ኦሮሞው ከጉጂው፤ ኑዌር ከአኙዋክ፤ ዲዚ ከሱርማ፤ ሌሎችም ብዙ ግጭቶች በየቀየው ተፈጥረው አይተናል። የብዙ ዜጎችም ህይወት ተቀጥፏል። ይሄ ሁሉ ደም መፋሰስ የሚከሰተው ህወሃት ከህዝብ ፈቃድ ያልሆነ እና ከህዝቡ የተለየ በመሆኑ ነው።
ህወሃቶች ከህዝብ የተለዩ ብቻ ሳይሆኑ የህዝብ ጠላት መሆንን የመረጡ ብድኖች ስለመሆናቸው ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ህወሃቶች “አማራና ተፈጥሮ” የትግራይ ህዝብ ጠላቶች ናቸው ብለው መፃፋቸው እና ማስተማራቸው የህዝብ ጠላት መሆንን ስለመምረጣቸው ቋሚ ምስክር ነው። ህወሃቶች በስልጣን የሚያቆየን በህዝቦች መካከል የሚፈጠረው አለመተማመንና የጠላትነት ስሜት ብቻ ነው ብለው ከልባቸው ያምናሉ። በህዝቦች መካከል የሚፈጠረው አብሮነት፤ አብሮነቱን ለማዘመን የሚረዳ መተማመን፤ ይሄም የሚወልደው አንድነትና ህብረት በህወሃት ዘንድ የሚወደድ ነገር አይደለም። በህወሃት ዘንድ የሚወደደው በህዝብ መካከል የሚፈጠረው የአለመተማመን ስሜት ይህም አለመተማመን የሚወልደው ግጭት ነው። ግጭት ተፈጥሮ የንፁህ ደም ሲፈስ በህወሃቶች መንደር ደስታ ይሆናል።በዜጎቹ ግጭት እና ደም መፋሰስ ተደስቶ የሚኖር ቡድን እንደ ህወሃት ዓይነት በየትም አገር ታይቶ አይታወቅም።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል ነዋሪዎችና በትግራይ ክልል ነዋሪዎች መካከል ግጭት ተከሰተ መባልን ሰምተናል። ይሄ በጣም አሳፋሪና አሳዛኝ ነገር ነው። ህወሃት ከመፈጠሩ በፊት በሠላም ተጎራብቶ የሚኖር ህዝብ ዛሬ ደም መፋሰስ ደረጃ ወደ ሚያደርሰው ግጭት ተሻግሮ መስማታችን አሳፋሪ ነው። ህወሃቶች ከመቸውም ግዜ በላይ የኢትዮጵያ አንድነት ተጠናክሯል እያሉ ሳይታክቱ በሚያወሩበት በዚህ ግዜ አብሮ ለብዙ ዘመን የኖር ህዝብ ወደ ግጭት የመግባቱ ነገር የህወሃቶች ትሩፋት ሁኖ እናገኘዋለን። ህወሃቶች በዘመናቸው ካተረፉልን ቀውሶች መካከል ሳይጠቀስ የማይታለፈው በህዝቦች መካከል የሚፈጥሩት ግጭት ነው። በህዝቦች መካከል በሚፈጠረው ግጭት ብቻ እድሜያችን ይረዝማል ብለው ማመናቸው ህወሃቶች የገበቡት የክፋት አዘቀት ምን ያክል ጥልቅ እንደሆነ ያሰየናል።
ጥላቻ ለህወሃቶች የመኖሪያቸው ድንኳን ሁኖ አቆይቷቸዋል። ከእነርሱ ያልሆኑት በሙሉ ከጠላትነት በታች ስፍራ የላቸውም። ሁሉንም ጠላት አድርጎ ማየት ደግሞ ከፍርሃት እና በራስ ላይ ዕምነት ከማጣት የሚመነጭ መሆኑ ይታወቃል። አሁን አሁን እነዚህ ቡድኖች ፍራቻቸው ፈሩን ለቆ የራሳቸውን ጥላ የመፍራት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የራሱን ጥላ መፍራት የጀመረ ቡድን ራዕይ ኖሮት በሰከነ መንፈስ አገርን የመሰለ ትልቅ ነገር ለመምራት ብቃት አይኖረውም። ህወሃቶች አስቀድሞ በነበርው የአቅም ማነስ ተግዳሮታቸው ላይ ፍርሃት ታክሎበት አገሪቷን ወደ ከፋ ሁኔታ ሊወስዷት እየሞከሩ ነው።
ለህወሃቶች አገር ማጥፋት ጀግንነት ሁኖ እንደሚቆጠር ድርሳናቶቻቸው ይመሰክራሉ። ለምስሌ “እኛ ከሌለን አገሪቷን እንበትናታለን” የሚለው ሟርት በእያንዳንዱ የጥፋት ቡድኑ አባል ልብ ውስጥ የተፃፈ ሃሳብ ነው። ከዚህ በላይ አገር የሚያጠፋ ሃሳብ የለም።” እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚሉ ቡድኖች በአገሪቷ ጫንቃ ላይ ተቀምጠው ስለ ሰላምና እድገት ማውራት ፈፅሞ አይቻልም። ሠላም ማለት የጦርነት አለመኖር ማለት አይደለም፤ ልማትም ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ማቆም ማለት አይደለም። ሠላምም ሆነ ልማት ህወሃቶች ከሚያወሩት የተለየ የአስተሳሰብ ደርዝ ያለው ትልቅ ፅንሰ ሃሳብ ነው። ህወሃቶች ይህን ትልቅ ትርጉም ያለውን ቁም ነገር ለመረዳት አዕምሮአቸው የተከፈተ አይደለም። በክፉ አስተሳሰባቸው ተተብትበተው፤ ከቂምና በቀል ራሳቸውን መለየት አቅቷቸው ራሳቸው ለራሳቸው የገነቧቸውን ህንፃዎች እየቆጠሩ ኢትዮጵያ በልማት እየገሰገሰች ነች ይሉናል። ዕለት ዕለት የንፁህ ሰው ደም እያፈሰሱ ከመቸውም ግዜ በላይ ሠላማችን ተጠብቋል ሲሉም ፈፅሞ አያፍሩም። ይህን ወሬያቸውን እውነት ነው ብለን እንድንቀበል የሚያደርገን አንዳችም እውነት የለም። ህወሃቶች የሃሰት ልጆች በመሆናቸው መዋሸት በእነርሱ ዘንድ የፖለቲካ ጥበብ ነውና በትልቁም በትንሹም ይዋሻሉ።
ለእነዚህ የጥፋት ቡድኖች የልማትንና የሠላምን ምንነት ለማስተማር መሞከር በጭንጫ መሬት ላይ መልካም ዘርን እንደመዝራት ይሆንብናል።የህወሃቶች አዕምሮ በጎ ነገር የማይዘልቅበት ፍፁም ጭንጫ ሁኗል። እነዚህ ቡድኖች ከህዝቡ ሁሉ በላይ ጠቢብ የሆኑ ይመስላቸዋል። እንደ ፈጣሪ ቃል እነርሱ ያሉት ካልሆነ ህዝቡ ሁሉ ቢጠፋ ግድ እስከማይኖራቸው ድረስ በትዕቢት ታውረዋል። ትዕቢተኛ ቡድን አገርንና ህዝብን ያጠፋል እንጂ አያለማም። ደም መፋሰስን ያበዛል እንጂ ሠላምን አያመጣም።የህወሃቶች የስንፍናቸው ብዛት የወለደው ግጭት አብሮ በኖረው ወደፊትም አብሮ መኖር በሚችለው ህዝብ መካከል ደም እያፋሰሰ ነው።በቅርቡ በአማራ እና በትግራይ ክልል ድንበር አካባቢ ተነስቶ የሰው ህይወት ያለፈበትን ግጭት ምሳሌ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል።
በአጠቃላይ ህወሃቶች በአገሪቷ ጫንቃ ላይ እስካሉ ድረስ ሠላምም ሆነ ልማት ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነገር በኢትዮጵያችን አይኖርም። እነዚህን የጥፋት ልጆች ከቅዥታቸው ነቅተው ከሰው መሃል ሁነው እንደ ሰው ልጅ ያስባሉ ብሎ መጠበቅም ከንቱ ምኞት ነው። ለብዙ ዘመን ከዛሬ ነገ ከቅዥታቸው ነቅተው ሰው ይሆናሉ ብለን ስንመኝ ነበር። የቻሉትን ያክል ዘርፈው በቃኝ ይሉ ይሆናል የሚልም ተስፋ ነበረ። ምኞታችንና ተስፋችን ግን እንዲሁ በከንቱ ውሃ በልቶት ቀርቷል። በጎ ምኞታችንን የሚገዳደሩን ኃይሎች በወንበሩ ተቀምጠው ፈራጅ ሆነው ሳለ፤ ተስፋችንን በሚያመክኑ ቡድኖች እግር ተወርች ታስረን እያየን ዝም ብለን እንኖር ዘንድ ሰው መሆናችን ሊከለክለን ይገባል።አዎን ሰው መሆናችን ብቻ ህወሃቶች የሚፈፅሙትን እኩይ ተግባር ለማስቆም እንድንነሳ ያደርገናልና ሁላችንም አብረን ተነስተን በፍርድ ወንበር የተቀመጡ ክፉዎችን አደብ እናስገዛለን።
ህወሃቶች አገር አጥፊ ኃይሎች እንደሆኑ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚስማማበት እውነት ሁኗል። ከዚህ እውነት ለጥቆ የሚያሳስበን ብርቱ ነገር በዚያች አገር እጅግ በጣም ብዙ አደር ባዮች የመፈጠራቸው ነገር ነው።”እኛ ምን እናድርግ ታዘን ነው እንዲህና እንዲያ የምናደርገው “የሚሉ የሂሊና ሙግት የሌለባቸው ዜጎች በዚያች አገር የመብዛታቸው ነገር አሳሳቢ ነው። ሰው ለቁሳቁስ፤ ለሚበላና ለሚጠጣ ኃላፊ ነገር ብሎ የወንድሙን ደም ማፍሰስ ሲጀምር ያን ግዜ አገር መፍረስ ትጀምራለች። በተለይም እንዲህ ዓይነቱ ነውር ድርጊት በህግ አስከባሪው አካል መፈፀም ሲጀምር አንድ አገር እንደ አገር የመቀጠሏ ሁኔታ አደጋ ላይ ይወድቃል። ዛሬ በኢትዮያችን የፍርድ ቤት ወንበሮች በምናምንቴዎች ተይዘዋል፤ የፍትህ መዶሻዎችም በጨካኞችና በሃሰተኛ ልጆች እጅ ወድቀዋል። አገርንና ህዝብን ለመጠበቅ የተሰለፉ ኃይሎች የህዝባቸውን ደም በከንቱ የሚያፈሱ ሁነዋል። የፖሊስ ኃይሉም የዘራፊዎችንና የነፍሰ ገዳዩን ቡድን የሚጠብቅ እንጂ የዜጎችን ሠላም የሚጠብቅ ሊሆን አልቻለም። እነዚህ ኃይሎች ከሂሊናቸው በላይ ለሥጋቸው እንዲገዙ የሚያደርጋቸው ምን እንደሆነ ባናውቅም አደር ባይነታቸው አገርንና ህዝብን በብርቱ እየጎዳ እንደሆነ መካድ አይቻልም።
ታዝዤ የገዛ ወገኔን ገደልኩ የሚል የመከላከያ ኃይል አባል፤ ታዝዤ በሃሰት ማስረጃ ክስ መሰረትኩ የሚል ፖሊስ እና አቃቤ ህግ ፤ታዝዤ በሃሰት ማስረጃ ፈረድኩ የሚል ዳኛ ነገ የሚያስጠይቅ ዘመን ሲመጣ ማምለጫ ምክንያት እንደማይኖረው ሊገነዘበው ይገባል። ታዞ ወንጀል መፈፀም ከወንጀሉ ነፃ አያደርግም። በተለይም በህግ አስከባሪውና አስፈፃሚው አካል ይህን መሰሉ ነውር ሲፈፀም ማየት ለኢትዮጵያችን ትልቅ ውድቀት መሆኑን እነዚሁ አካላት እንዲያውቁት ያስፈልጋል።ታዞ ደግሞ ደጋግሞ ወንጀል መፈፀም ከአደር ባይነት በላይ የሆነ ራሱን የቻለ ወንጀል ነው። በንፁሃን ላይ ወንጀል ሲፈፀም አይቶ እንዳላዩ መሆን፤ ሰምቶም እንዳልሰሙ መምሰል አደር ባይነት ሊባል ይችላል ታዞ የገዛ ወገንን መግደል ግን ወንጀል መሆኑን ማወቅ ይገባል። ኢትዮጵያችን ከገጠሟት ቀውሶች መካከል አንዱ ነፍሰ ገዳዮችን እያዩ ዝም የሚሉ አደር ባዮች የመበራከት ነገር ነው። ከትላልቅ የኃይማኖት መሪዎች አንስቶ እስከ ተራው ምዕመን ድረስ ያለው ኃይል በዚህ እርግማን የተያዘ እስኪመስል ድረስ በዝምታ ተውጧል።ይህ ዝምታ የሚሰበርበት ግዜ እሩቅ አለመሆኑን ስንናገር በህወሃቶች ዘንድ ድንጋጤ እንደሚሆን እናውቃለን። እናም ዝምታው ይሰበራል።ዜጎችም ለፍትህ፤ለእኩልነት እና ለነፃነት የሚያደርጉትን ትግል አፋፍመው ይቀጥላሉ። እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል የተዘጋጁ ወጣቶች ሰይፋቸውን ከሰገባው መዘዋል።
ግንቦት ሰባት ንቅናቄም የጥፋት ኃይል መሆንን ምርጫቸው ያደረጉ ህወሃቶች የገነቡትን የጥፋት መረብ እንበጣጥሰዋለን። በወገኖች መካከል የሚፈጠረው ግጭት የመኖሪያቸው ድንኳን የሆናቸው የጥፋት ኃይሎችን አደብ ለማስገዛት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል እየሰራን ነው። ህወሃቶች ሆይ በዜጎች ደም እየቀለዳችሁ አትቀጥሉም። በተገኘው አጋጣሚ በተገኛችሁበት አምባ ሁሉ እንታገላችኋለን። በሚገባችሁ ቋንቋም እናናግራችኋለን። ደግሞም እውነት ከእኛ ዘንድ ስላለ አለ ምንም ጥርጥር እናሸንፋችኋለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

No comments:

Post a Comment