Monday, November 3, 2014

የወያኔ ግፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ


ዘረኛዉ ወያኔና ባለሟሎቹ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላና በሸኮ መዠንገር አካባቢ የሚያካሄዱትን የማንአለብኝነት የመሬት ዝርፍያና ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያደርጉት አራዊታዊ ሩጫ የተነሳ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝብ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የማይችል እልቂት እየተፈጸመበት ነዉ። የመዠንገር ህዝብ የሞትና የህይወትን ያክል የማይወጣዉ ምርጫ ስለቀረበለት ተወልዶ ያደገበትን የአባቶቹንና የአያቶቹን አካባቢ ለቅቆ በመዉጣት እራሱን ለመከላከል ባደረገዉ እንቅስቃሴ የብዙ ንጹሃን ዜጎችና ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ምስኪን ወታደሮችም ህይወት ማለፉ በይፋ እየተሰማ ነዉ። ይህንን ተከትሎ ግፈኞቹ የወያኔ መሪዎች በአካባቢዉ ብዙ ዘመን በቆዩ ብሄሰቦች መካክል ሆን ብለዉ ግጭት እንዲነሳ እያደረጉ በህዝብ መካክል ግጭትትና ዕልቂት የተነሳ በማስመሰል በአካባቢዉ ከፍተኛ ሰቆቃ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ።
በዚህ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰ ላለዉ መጠነ ሰፊ ግጭትና ዕልቂት ተጠያቂዉ በአካባቢዉ ለዘመናት አብሮ በመደጋገፍ የኖረዉ ህዝብ ሳይሆን የዚህ አሰቃቂ ዕልቂት ባለቤትና ጠንሳሽ ህወሓትና ዘረኛ መሪዎቹ መሆናቸዉን ለአንድም ደቂቃ ሊዘነጋ አይገባም። ይህ ግጭት ሊነሳ የቻለዉ ህወሓት የአካባቢዉን ደሃ ገበሬ ከትዉልድ መሬቱ ላይ እያፈናቀለ መሬቱን ለከፍተኛ የጦር መኮንኖቹና የኔ ለሚላቸዉ ባለሟሎቹ በማከፋፈሉ መሆኑን ይህንን ግፍ የሚሰማ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልብ ሊለዉ ይገባል። ህወሃት የአማራን ተወላጆች አካባቢዉ የእናንተ አይደለምና ዉጡ እያለና እያፈናቀለ በሌላ በኩል ግን በየክልሉ የአካባቢዉን ነዋሪ እያፈናቀለ የራሱን ሰዎች የመሬት ባለቤት ማድረጉ አዲስ የጀመረዉ ክስተት ሳይሆን ቆየት ያለና ስር የሰደደ የወያኔ አሰራር ነዉ።
ይህ ዛሬ በጋምቤላና በአካባቢዋ እየደረሰ ያለዉ ግፍና መከራ ለአካባቢዉ ህዝብ ብቻ የሚተዉ ነጠላ ችግር ሳይሆን በአጠቃላይ ወያኔ በአገራችን ላይ ሆን ብሎ በማድረስ ላይ ያለዉ ችግርና መከራ አካል ነዉ። በጋምቤላ ዉስጥ የፈሰሰዉና እየፈሰሰ ያለዉ የሴቶች፤ የወጣቶች፤ የአረጋዉያንና የህጸናት ደም ለሁላችንም የነጻነት ጥሪ እያቀረበልን ነዉ። ይህ የነጻነት ጥሪ ሰምተን የምናልፈዉ ወይም ነገ እንደርሳለን በለን በቀጠሮ የምናልፈዉ ጥሪ አይደለም። ጥያቄዉ የአገርና የዜጎች ህልዉና ጥያቄ ነዉና ነገ ዛሬ ሳንል አሁኑኑ ይህንን የነጸነት ጥሪ ሰምተን ምላሽ ልንሰጠዉ ይገባል።
ይህ ወያኔ በደቡብ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በንጹሃን ዜጎቻችን ህይወት ላይ እየፈጸመ ያለዉ ግፍ በአገራችን ህዝብ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያዉ አይደለም፤ ካላቆምነዉ በቀር የመጨረሻዉ እንደማይሆንም አካሄዱ በግልጽ እያሳየን ነዉ። ወያኔ ጋምቤላ ዉስጥ ለምለም መሬት እየፈለገና ነዋሪዉን እያፈናቀለ መሬቱን ለባለሟሎቹ ማደሉን ሳይታቀብ በማንለብኝነት እንደቀጠለበት ነዉ። መሬቱን የተቀማዉ ደሃዉ የጋምቤላ ገበሬም ጫካ እየገባ ከወያኔ ጋር መተናነቁን ቀጥሏል። ትናንት በኦሮሚያ፤ በጉራፈርዳና በቤንሻንጉል አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰዉ ግፍና መከራ ዛሬ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ብሄረሰቦች ላይ እየደረሰ ነዉ።
ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ ይህ ለከቱን የለቀቀ የህወሓት ዕብሪት እንዲተነፍስና በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰዉ ግፍና ሰቆቃ እንዲቆም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነግ በኔ እያለ የነጻነት ትግሉን እንደቀላቀል የትግል ጥሪ ያደርጋል። ወያኔ እያደረሰ ያለዉ እስራት፤ ድብደባ፤ ግድያና ስደት የሁላችንንም ቤት እያንኳኳ ነዉና ሁላችንም እንደ አንድ ሰዉ ቆመን ወያኔንና ወያኔ የፈጠረዉን ዘረኛ ስርዐት በትግላችን መደምሰስ አለብን። በጋምቤላና በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የፈሰሰዉ የንጹሃን ወገኖቻችን ደም ደመከልብ ሆኖ የማይቀረዉ ለመብታችንና ለነጻነታችን ቆመን ወያኔን ካስወገድን ብቻ ነዉ።
በህብረት እንነሳ!!!!

No comments:

Post a Comment