Saturday, November 1, 2014

መንግስት በ10 ፖለቲከኞችና ላይ ክስ መሰረተ


ጥቅምት (ሃያቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የፌደራል አቃቢ ህግ በ10 ተከሳሾች ላይ የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን አብዛኞቹ ተከሳሾች ከግንቦት7 እና ከደሚት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለዋል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት  ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም  ሲሰየም ተከሳሾች በመቶዎች የሚቆጠሩ ገጾች ያሉዋቸው ክሶች ደርሷቸዋል። የግንቦት7 አመራር ነው የተባለው ዘላለም ውርቅአገኘሁ፣ አንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የፓርቲው ምክትል የድርጅት ሃላፊ
አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አረና ፓርቲና መምህርና ጸሃፊ አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሽዋስ አሰፋ፣ በግልና በመንግስት ተቋማት ውስጥ ሰርተዋል የተባሉ ዮናታን ወልዴ፣ አብርሃም ሰሎሞን፣ ግርማ ባህሩና ተስፋየ ተፈሪ በተከሳሽነት ቀርበዋል።
አቃቤ ህግ ሁሉም ተከሳሾች  የግንቦት 7 ድርጅት አባል በመሆን ህግ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለማፈራረስ መንቀሳቀሳቸውንና በመንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ማሰባቸውን ገልጿል። አቃቢ ህግ ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ ዋስትና
እንዳይሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። የተከሳሾችን የዋስትና ጉዳይ ለማየት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለረቡእ ጥቅምት 26 ቀጠሮ ሰጥቷል።
እስረኞቹ በማእከላዊ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ ሲፈጸምባቸው ቆይታል። መንግስት ለፖለቲካ ስልጣኔ ያሰጉኛል የሚላቸውን ሁሉ በሽብርተኝነት እየከሰሰ ማሰቃየቱን አለማቀፍ ተቋማት እያወገዙት ነው።
በተመሳሳይ ዜና የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን መታሰር ኮንኖ፣ ኢትዮጵያ ያሰረቻቸውን ጋዜጠኞች እንደትፈታና በልማት በኩል ያሳያቸውን ተሳትፎ የ ሲቪል መብቶችንም በማክበር እንድታሳይ ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment