(ከኤፍሬም እሸቴ/ PDF)
ገና ሃይ ስኩል ተማሪ ነኝ። የትምህርት ጥማቴ ገና ያልወጣልኝ። ተስፋዬን በደብተሬ ቅጠሎች መካከል አቅፌ የምዞር። ሰው ለመሆን የምማር። ተስፋዬን ከመናገሻ ተራራ ጀርባ የተሰቀሉ ይመስለኝ ነበር። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ፣ ከተራራው ገመገም ጀርባ የምትወጣው ፀሐይ ተስፋዬ በካዝና ከተቀመጠበት አገር የምትመጣ እንደሆነ ሁሉ ሙቀቷ ብርዴን፣ ጨረሯ ችግሬን ያስረሱኝ ነበር።
ገና ወፎች ጭውጭው ሲሉ የገነት ጦር ት/ቤት ሰልጣኝ ካዴቶች በዋናው አስፓልት ላይ የዕለቱን ስፖርት ለመከወን በሰልፍ ሲሮጡ፣ ከስከስ ጫማቸው ከአስፓልቱ ጋር ሲገናኝ የሚፈጥረው ድምጽ ሰፈራችንን ከእንቅልፍ ድብርቱ ያባንነዋል። ወደ ላይ እየሮጡ ሲሔዱ ሰምተናቸው ከ30 ደቂቃ በኋላ እየሮጡ ይመለሳሉ። ዋናውን ስፖርት ለመሥራት እየተሟሟቁ መሆን አለበት። ዋናውማ ካምፓቸው ውስጥ ነው። ከሰኞ እስከ አርብ ሁሌም ሲሮጡ ይሰማል። ወጣት የአገሬ ልጆች። ቆይተው “ተመረቁ” ይባልና ሰሜን ጦር ግንባር … ኤርትራ …. ትግራይ ….። ከዚያ መርዶ …።
አንዱ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የካዴቶቹ ከስክስ ጫማና ሩጫው አይደለም። ከዘራውን ተመርኩዞ የሚያዘግም ጠይም መልከ መልካም ሽማግሌ እንጂ። ደብዘዝ ወዳለችው ቤት ሲገባ ብርሃን በቅጡ የምታገኝበት መስኮት ላልነበራት ክፍል የእርሱ ፈገግታ ቤቱን ሲሞላው ይታወቀኛል።
እንደ ሁሎቹም የእናቴ ዘመዶች መልከ መልካም ፊቱ፣ በእርግና ያልደከመ ገጹ፣ ፈገግታ ያልተለየው ዓይኑ፣ ሰልካካ አፍንጫው …. ከዕድሜው አብዛኛውን በስደትና በእስር ያሳለፈ አይመስልም። እናቴ “ጋሽ ኢጀታ” … ብላ ስማው … እኛም የማናውቀውን … በዝና ብቻ ስለርሱ የጠገብነውን አረጋዊ ሰላምታ ሰጥተን … “ቁጭ በል ቁጭ በል” ብላው አረፍ አለ። ለመቀመጥ ወገቡን ካጠፈበት እስከተቀመጠበት ባለችው ቅጽበት አረጋዊው ጋሽ ኢጀታ ከእርጅናው በላይ በሽታ ውስጡን እንዳደከመው ያስታውቃል።
በዚያች በምታምር ከዘራው መሬቱን እየቆረቆረ ከእናቴ ጋር ብዙ ብዙ ተጫወቱ። ዓይኑን ግን ከእኛ ከወጣቶቹ ላይ አልነቀለም። አንዴም በአማርኛ አንዴም በኦሮምኛ ሲያወራ እናቴ ግማሹ አማርኛ ግማሹ ኦሮምኛ በሆነ ኦሮአማርኛ ስትመልስለት እየሳቀም ራሱን እየነቀነቀም ያዳምጣታል።
የሸዋ ሰው ሁሉ ነገሩ ቅይጥ ነው። አባቱ አማራ፣ እናቱ ኦሮሞ፤ ዘመዶቹ ጉራጌዎች፣ ጎረቤቶቹ የኤርትራ ልጆች፣ ገበያ ሽንኩርት የሚገዛው ከወላይታዎች፣ ወታደሮቹ የትግራይ ሰዎች፣ አስተማሪዎቹ የሲዳሞ ልጆች …. ሆለታ እንዲህ ቅይጥይጥ ያለች ከአዲስ አበባ ውጪ ያለች መርካቶ ናት። የሸዋ ኦሮምኛው እንደዚያው ቅይጥይጥ ያለ ነውና ጋሽ ኢጀታ እየሳቀ የሚሰማት ለምን እንደሆነ የገባኝ ኋላ ነው።
“ሸገር ባኔ፤ ሸገር ወጥተን
ጠጂ ጠጣኔ፤ ጠጅ ጠጥተን
ዱላ’ዻን ተደባደብኔ፤ በዱላ ተደባድበን” እያለ ይቀልዳል አንድ ወዳጄ። ከዚህ ንግግር ውስጥ “ባኔ፤ ሸገር፣ ‘ዻን” የሚሉት ቅንጣቶች ካልሆኑ በሙሉ ኦሮምኛ አይደለም።
“ደህና ነኝ፤ ይቺ ሪኽ አስቸገረችኝ እንጂ። አሁን እግሬንም እንደልብ ማዘዝ እያቃተኝ ነው። ያመኛል ሲነሳብኝ” ብሎ መለሰላት፤ “ጤናህ እንዴት ነው ጋሽ ኢጀታ?” ላለችው ለእናቴ ጥያቄ።
እኔ ደግሞ ዝም ብዬ አስባለሁ። ከእስር የወጣ ሰው እንዲህ ፈገግታ በፈገግታ ይሆናል? እያልኩ። ስለበሽታው እያወራ እንዴት ግንባሩ ላይ የስቃይ ምልክት ሳይሳልበት ቀረ? እያልኩ።
ጋሽ ኢጀታ ከእናቴ ጋር ከተጫወተበት ጊዜ ይልቅ ከእኛ ከልጆቹ ጋር ያወራበት ይበልጣል። ምናልባት በዚህች ምድር ላይ የሚቆይባቸውን የመጨረሻ ወራት የራሱን ልጅነት እያስታወሰ፣ ደግሞም የወደፊት የአገሩን ተስፋ በእኛ ውስጥ እያየ ይሆናል። ሰው ከአገሩ ሲወጣ ወይም በእርግናው ወራት ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ የተወለደበት መንደር በሙሉ እጅጉን ይናፍቁት ይሆናል።
ለምን እንደታሰረ፣ ለምን በስደት ሱዳን አገር እንደኖረ በቀጥታ ባይነግረንም ቤት ውስጥ ሲወራ ከሰማነው ጋር ከእርሱም የቀራረምናትን ይዘን መጠነኛ ግንዛቤ አለን። በሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር ምክንያት በንጉሱ ዘመን አገሩን ጥሎ ሱዳን ገባ። አብዮት አብዮት ሲባል ተመለሰ። እንደገና እነ ንጉሥ መንግሥቱ ኃ/ማርያም አሰሩት። ከእስር ከወጣ ብዙም ሳይቆይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ይህንን ሁሉ የመከራ ቀንበር የተሸከመ ሰው በዘመኑ መጨረሻ ሳገኘው ፊቱ ላይ ፈገግታውን እንጂ ምሬቱን አላየሁም። “ከኦሮምኛ ውጪ አልናገርም” የሚል የቂመኝነት እና አንድን ወገን የመጥላት ነገር አላየሁበትም። “መሞቴ ካልቀረ እስቲ በደሌን ልናገር” ብሎ ለእናቴም ሆነ ገና በማደግ ላይ ለነበርነው ለእኛም በልባችን ቂም የሚያስቋጥር መልእክት አልተናገረም። የእርሱ ዘመድ በመሆናቸው በሌሉበት መከራ የተቀበሉ ዘመዶቹንም እያነሣ “ግፋ በለው፤ ሒድ በለው” አላለም።
“ምክንያቱም ኦሮሞ ስለሆንኩ/ Because I am Oromo” የሚለው የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ሲወጣና በኦሮሞዎች ላይ በሕወሐት አስተዳደር እየደረሰ ያለውን ነገር ስመለከት ወደ ውስጡ ገብቼ በጥልቅ ሳላየው ይህ አጭር ሐረግ ኅሊናዬን ሰቅዞ ያዘው። ስምህ ወይም የምትናገረው ቋንቋ ለዚህ ሁሉ መከራ ይዳርግሃል ማለት ነው። አሁንማ መታወቂያህ ላይ ሳይቀር በግድ የምትለጥፈው የብሔረሰብ ስም ሊያስገድልህ ወይም ሊያስሾምህ ይችላል። በዚህ ዘመን ጋሽ ኢጀታ ቢኖር ኖሮ ይህንን መከራ ድጋሚ እንደሚቀበል አሰብኩ። ኢጀታ ስለሆነ ብቻ።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብሔረሰቡ ምክንያት፣ አማር በመሆኑ ብቻ የተፈናቀለውን ወገን አስቤ “አይቴ ብሔሩ ለአማራ፤ የአማራአገሩ የት ነው? ኢትዮጵያ አይደለምን?” ብዬ የጻፍኩትን ተጠየቃዊ ጽሑፍ አስታወስኩ። እዚያው ላይ “አይቴ ብሔሩ ለኦሮሞ” ብዬ መጨመር አለብኝ።
ኢትዮጵያ አሳዘነችኝ። የአገር ዋርካ ኦሮሞ፣ ትልቁ ኦሮሞ፣ ኦሮሞ ሰፊው፣ ኦሮሞ ሆደ ሰፊው ሲያለቅስ … እናም የሚመጣው ሲታሰበኝ … ኢትዮጵያ አሳዘነችኝ።
ኢትዮጵያ አሳዘነችኝ!!!!! ልጆቿ በየስማቸውና በየቋንቋቸው በየተራ መከራ ሲቀበሉ። ሳይረዳዱ … እየተያዩ በየተራ ሲያልቁ። የሰላሌው አያቴ ከአባይ ማዶ ሚስት አገባና አባቴን አስገኙ። ከመንዝ የመጡት ቅድመ አያቴ እምዬ የሜታውን ወጣት አገቡና እናቴንና ዘመዶቿን አስገኙ። ዛሬ ግን የእምዬ ወገኖች ከዚያ ማዶ፣ የአባይ ማዶዋ አያቴ ወገኖች ከዚያ ማዶ … የሜታና የሰላሌ ዘመዶቼ ወገኖች ከዚያ ማዶ … እኛ ከእነርሱ የተፈጠርነው ከተሜዎች ከዚህ ማዶ … የተለያየን ሆንን ማለት ነው? መታወቂያችን የሚያሳየው አንድ መሆናችንን ሳይሆን የተለያየን መሆናችንን ነው።
++
(ማስታወሻ፦ በዘር እና ወንዝ በሽታ ልትከሰኝ የምትፈልግ ካለህ ጊዜህን አታጥፋ። የሚሆነውን ነገር ለማየት ዓይንህን ጨፍነህ ቃላት ለመሰንጠቅ አትድከም። ከምታለቅሰው እናት፣ ከሚሞተው ወጣት፣ ያለ ወላጅ ከሚቀረው ሕጻን ልጅ ይልቅ፣ ተደላድለህ የተኛህበት ሕይወትህ፣ ምንም ነገር መስማት የማይፈልገው ዕዝነ ልቡናህ እንዳይረበሽ “አትጩኹብኝ፣ አትረብሹኝ እስቲ” የምትለውን … አልሰማህም።
No comments:
Post a Comment