Tuesday, September 23, 2014

ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (አፈንዲ ሙተቂ)


ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (እውነተኛ ታሪክ)
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
—–
ዛሬ የማወጋችሁ ታሪክ ከመጽሐፍ የተገኘ አይደለም፡፡ በሬድዮ ጣቢያም አልተላለፈም፡፡ በቴሌቪዥን ፕሮግራምም አልቀረበም፡፡ በኢትኖግራፊ ጥናት (ethnographic research) ሰበብ በየከተማውና በየመንደሩ እየዞርኩ ከሰበሰብኩት ዳታ የተወሰደም አይደለም፡፡ በዐይኔ ያየሁትንና በራሴ ላይ የደረሰውን ነው እንደወረደ የማጫውታችሁ፡፡
ይህንን ታሪክ የማወጋበት በርካታ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ በመጀመሪያ በህይወቴ ያየሁትና ሳላዉቀው በውስጡ ራሴን ያገኘሁበት ብቸኛው ውጊያ ይህ አሁን የማወጋችሁ ውጊያ ስለሆነ ነው፡፡ ሁለተኛ “ኦነግ” የሚባለው ድርጅት ከዘመኑ የሽግግር መንግሥት ከወጣ በኋላ ከኢህአዴግ ጋር የተፋለመበት የመጀመሪያ ጦርነት በመሆኑ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በሁለቱ ድርጅቶች አለመግባባት ዙሪያ ሰፊ ተመክሮና መረጃ ያላቸው ሰዎች ታሪኩን እንዲያጋሩን የምሻ በመሆኔ ነው፡፡ ሌላም ሌላም……
===ቅድመ-ታሪክ==
የደርግ መንግሥት ከስልጣን ሲባረር በሀረርጌ ክፍለ ሀገር ደጋማው ክፍል ያሉት አውራጃዎችና ወረዳዎች በአብዛኛው በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እጅ ነው የወደቁት፡፡ በአምስት አውራጃዎች የተከፈለውን ቆላማውን የኦጋዴን ክልልን ጨምሮ ድሬ ዳዋ፣ ሀረር፣ ጭሮ (ዐሰበ ተፈሪ)፣ ሂርና፣ ቁልቢ፣ ባቢሌ፣ ጅጅጋ የመሳሰሉትን ትልልቅ ከተሞችን የተቆጣጠረው ደግሞ ኢህአዴግ ነው፡፡
በዚያን ጊዜ በኦነግ ቁጥጥር ስር ከዋሉት አውራጃዎች አንዱ የሀብሮ አውራጃ ይባላል፡፡ ይህ አውራጃ በውስጡ ስድስት ወረዳዎች የነበሩት ሲሆን ዋና ከተማው ገለምሶ ናት፡፡ የኢህአዴግ ጦር ከሀብሮ አውራጃ ጋር የሚዋሰነውን የአርሲ ክፍለ ሀገር ሙሉ በሙሉ (ከጎሎልቻ ወረዳ በስተቀር)፤ እንዲሁም ከሀብሮ በስተሰሜንና በስተምዕራብ ያሉትን የጨርጨር አውራጃ (በሀረርጌ የሚገኝ) በከፊል እና የየረርና ከረዩ አውራጃን በሙሌ (በሸዋ ክፍለ ሀገር የሚገኝ) ተቆጣጥሯል፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ይዞታቸውን እንደጠበቁ እስከ መጋቢት ወር 1984 ድረስ በጉርብትና ቆይተዋል፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ ሁለቱ ሀይሎች በጋራ የሽግግር መንግሥት መስርተው ሀገሪቷን ለመምራት ሞክረው ነበር፡፡ ቢሆንም በብዙ ነገሮች ላይ አልተግባቡም፡፡ በየጊዜው በፕሮፓጋንዳ መቆራቆሳቸው የወቅቱ ትዕይንት ነበር፡፡ ኦነግ “ኢህአዴግ የሽግግር መንግሥቱን በሞኖፖሊ ተቆጣጥሯል” እያለ ሲከሰው ኢህአዴግ ደግሞ “ኦነግ በተቆጣጠራቸው ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽማል” በማለት ይከሰው ነበር፡፡ ከመስከረም 1984 ጀምሮ በመሀላቸው አልፎ አልፎ ግጭቶች ይከሰቱ ነበር፡፡ ቢሆንም በማዕከል ደረጃ ባዋቀሩት የጋራ ኮሚቴ አማካኝነት በቶሎ ይታረቃሉ፡፡
ከመጋቢት 1984 በኋላ ግን በሁለቱ ሀይሎች መካከል የሚደረገው ግጭት መልኩን መቀየር ጀመረ፡፡ ኦነግ ኢህአዴግን ከይዞታው ለማስለቀቅ፣ ኢህአዴግም ኦነግን ከያዛቸው መሬቶች ለማባረር እንደሚዋጉ ግልጽ ሆኖ ታየ፡፡ በተለይም ሁለቱ ሀይሎች በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚያካሄዱት ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሳ ሄደ፡፡ ይህ ሁኔታ ያሰጋቸው የጊዜው የአሜሪካ አምባሳደር እና የወቅቱ የኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት በሚያዚያ 1984 ሁለቱን ሀይሎች የማሸማገል ጥረታቸውን ጀመሩ፡፡ ሽምግልናው ተሳክቶም በተደረሰበት ውጤት መሰረት የኦነግ ጦር የያዛቸውን አውራጃዎች ለቆ ወደ ካምፕ እንዲገባ ተወሰነ፡፡ የኢህአዴግ ጦር ኦነግ በለቀቃቸው ከተሞች አቅራቢያ ሰፍሮ የሀገሪቱን ሰላም ያስጠብቅ ተባለ፡፡ ከዚያም ምርጫ ተደርጎ በምርጫው ያሸነፈው ቡድን ሀገር እንዲያስተዳድር ተወሰነ፡፡ በዚህ መሰረት የኦነግ ጦር በመላው ኦሮሚያ በተዘጋጁለት ስምንት ካምፖች ጠቅልሎ ገባ፡፡ ኢህአዴግም ጦሩን ኦነግ ወደነበረባቸው ክልሎች አስጠጋ፡፡
===ከሚያዚያ ወር መጨረሻ እስከ ሰኔ አስራ አራት-1984===
የኦነግ ጦር ከገባባቸው ካምፖች መካከል አንዱ በኛ አካባቢ ነው የነበረው፡፡ ይህ ካምፕ ከገለምሶ በ45 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ባለው የኮቶራ ተራራማ አካባቢ የተዘጋጀ ሲሆን ወደ ካምፑ የገባው የኦነግ ጦር አስር ሺህ ያህል ይሆናል፡፡ ኦነግ ወደ ካምፑ የገባው በከተሞች የመሰረተውን የሲቪል አስተዳደር በስፍራው በመተው ነው፡፡ የኦነግ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጽ/ቤትም በኛ ከተማ እምብርት ላይ ነው የነበረው (ይህ ቤት በአሁኑ ወቅት የገለምሶ ከተማ 01 ቀበሌ ጽ/ቤት ሆኖ እያገለገለ ነው)፡፡ ዋነኛው የኦነግ የማዘዣ ጣቢያ ግን ከገለምሶ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና “ዳሮ አቦና” በሚባለው ስፍራ ላይ ነው የነበረው፡፡ ኦነግ በደርግ ዘመን በምዕራብ ሀረርጌ፣ በባሌና በአርሲ ዞኖች ሲያካሄዳቸው የነበሩትን የደፈጣ ጥቃቶች ይመራ የነበረው ከዚህ ማዘዣ ጣቢያው ነው፡፡ የያዛቸውን ክልሎች ለኢህአዴግ ለቆ ሲወጣም ዋና ዋና ካድሬዎቹና መሪዎቹ በዚህ ጣቢያ ነው የከተቱት፡፡
የኢህአዴግ ጦር ወደ ገለምሶ የመጣው በግንቦት ወር 1984 መጀመሪያ ላይ ይመስለኛል፡፡ በቅድሚያ የመጣው ጦር ብዛት 500 ያህል ሲሆን የሰፈረበት ስፍራ ደግሞ ከገለምሶ በስተምስራቅ አቅጣጫ በአምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለው “ዳሎ” የተባለ አነስተኛ መንደር ነው፡፡ በዚያን ጊዜ እንዳየሁት ከሆነ ጦሩ የህወሐትና የኦህዴድ (ኦፒዲኦ) ወታደሮች ቅልቅል ነው (በነገራችን ላይ ከ1986 በፊት በነበረው ዘመን የኢህአዴግ ጦር አንድ ወጥ አልነበረም፤ አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች የየራሳቸው ጦር ነበራቸው)፡፡ በኢህአዴግ ስር የነበረው ኦህዴድ (ኦፒዲኦ) በህዝቡ ውስጥ ተንቀሳቅሶ የፖለቲካ ስራ እንዲሰራ የተፈቀደለት በመሆኑ በከተማው መሀል አንድ ጽ/ቤት ከፍቶ ነበር፡፡ ሆኖም ኦህዴድ በፕሮፓጋንዳው ዘርፍ እንደ ኦነግ ሊቀናው አልቻለም፡፡
*****
ሁለቱ ሀይሎች እንዲህ ሲጠጋጉ ነገሮች በጣም ተባባሱ እንጂ ሊሰክኑ አልቻሉም፡፡ ሁለቱም በየራሳቸው መንገድ የሚያደርጉትን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ሲያጧጡፉ ነው የከረሙት፡፡ በተለይ የያኔው የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ የግንቦት ሀያ አንደኛ ዓመት በዓል ሲከበር ባደረጉት ንግግር “ኦነግን እስከ አሁን ታግሰነዋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ገደቡን እያለፈ ስለሆነ በዝምታ አናልፈውም” ማለታቸው የኦነግ መሪዎችንና ካድሬዎችን በከፍተኛ ደረጃ ነው ያበሳጨው፡፡ የያኔው የኦነግ ሬድዮ ጣቢያ የአቶ መለስን ንግግር “በኦሮሞ ህዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት” ብሎት ነበር፡፡
በአሜሪካና በኤርትራ ሸምጋይነት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ እየቀረበ ሲሄድ ደግሞ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የሚካሄደው የቃላት ጦርነት ከአስፈሪ ደረጃ ደረሰ፡፡ በሁለቱ መካከል ግጭት መካሄዱ እንደማይቀር ቢታወቅም የብዙዎቹ ጥያቄ “ማን ቀድሞ ያጠቃል?” የሚለው ነበር፡፡ በዚህ መሀል ነው እንግዲህ ለምርጫ የተቆረጠው ሰኔ 14/1984 ከተፍ ያለው፡፡
*****
አዎን! ዕለቱ እሁድ ነው፡፡ ቀኑም ሰኔ 14/1984 ነው፡፡ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ እንደ ወትሮው የእለት እንቅስቃሴውን እያካሄደ ነው፡፡ በአካባቢያችን ምርጫው እንደማይካሄድ ቀደም ብሎ የታወቀ በመሆኑ ወደ ምርጫ ጣቢያ ዝር ያለ ሰው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ማንም ሰው በዚያ ዕለት የተፈጠረው ነገር ይሆናል ብሎ አልጠበቀም፡፡ በርግጥም የኢህአዴግ ጦር በዚያን ጊዜ ወደ አካባቢያችን ባመጣው አነስተኛ ጦር ከተማውንና መላውን የሀብሮ አውራጃ ለመቆጣጠር ይሞክራል ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም፡፡ ነገሩ ግን በርግጥ ሆነ፡፡
የኢህአዴግ ወታደሮች ከተማውን ሲቆጣጠሩ ለገበያ የመጡ እንጂ ለዘመቻ የተሰማሩ አይመስሉም ነበር፡፡ እያንዳንዱ የኢህአዴግ ወታደር ለገበያ የሚሄድ በመምሰል ጠመንዣውን ይዞ በአምስት ሰዓት አካባቢ ወደ ከተማዋ ገባ፡፡ ከዚያም ግማሹ በከተማዋ ዋና መንገድ ላይ በሚገኙ መደብሮች ፊት ለፊት ተቀምጠው ከሚሸቅሉ ልብስ ሰፊዎች ዘንድ እየተጠጋ ልብሱን ያሰፋ ነበር፡፡ ግማሹም ወደ ከተማዋ ሻይ ቤቶች እየገባ ሻይ በዳቦና ሌሎችንም የምግብ ዓይነቶች ይበላ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ከዘለቀ በኋላ የተበታተኑት የኢህአዴግ ወታደሮች በቡድን በቡድን በመሰባሰብ በከተማዋ ዋና መንገድና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ መቆም ጀመሩ፡፡ በስምንት ሰዓት ገደማ ከተማዋ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር መግባቷን የሚያረጋግጥ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ይህም አንድ የኢህአዴግ ወታደር በሀብሮ አውራጃ ፖሊስ መምሪያ አቅራቢያ ኦነግ ካስታጠቀው የአካባቢ ሚሊሻ እጅ ጠመንዣ መንጠቁ ነው፡፡ ከአካባቢ ሚሊሻው ጋር ይሄድ የነበረ ሌላ ሰው ጠመንዣውን እንዲያስረክብ ቢጠየቅ በሩጫ አስነካው፡፡ የኢህአዴግ ወታደሮች ሰውዬን ለማስቆም ጥይቶችን ወደ ሰማይ ተኮሱ፡፡ ያቺ ጥይት አዲስ ክስተት መፈጠሩን አመላካች ሆነች፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት የኢህአዴግ ወታደሮች ወደ ቀድሞው የሀብሮ አውራጃ ኢሠፓ ጽ/ቤት በመሄድ በዚያ ያገኟቸውን የኦነግ ኪነት ቡድን አባላት ካባረሯቸው በኋላ ጽ/ቤቱን መያዛቸው ተሰማ፡፡
በዚያን ጊዜ የተፈጠረው ነገር ለብዙዎች ህልም እንጂ እውነት አልመስል ብሎ ነበር፡፡ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ግን ኢህአዴግ “ነገሩ እውነት እንደሆነ እመኑ” በማለት ተናገረ፡፡ አንዲት የኦህዴድ (OPDO) ካድሬዎችን የጫነች ፒካፕ በከተማው የተዟዟረች በቀበሌ ማይክራፎን “ኦነግ ምርጫውን እምቢ ብሎ ጦርነትን ስለመረጠ ኢህአዴግ ለህዝቡ ደህንነት ሲል ከተማዋን ተቆጣጥሯል” በማለት አወጀች፡፡ በዚያችው ሌሊት ወታደሮችንና መሳሪያዎችን የጫኑ በርካታ ኦራልና አይፋ መኪናዎች ወደ ከተማችን ገቡ፡፡ ከቦርዶዴ ወደ ገለምሶ በሚወስደው መንገድም በሺህ የሚቆጠር እግረኛ ጦር ወደ ከተማዋ መግባቱ ታወቀ፡፡
*****
እንግዲህ ይህ ክስተት በተፈጠረ በሶስተኛው ቀን ነው የመጀመሪያው የኦነግና የኢህአዴግ ጦርነት የተካሄደው፡፡ ጦርነቱ ምን ይመስላል?…. ከጦርነቱ በፊት ያሉት ክስተቶችስ ምን ይመስላሉ?… ከጦርነቱ በኋላስ ምን ተከሰተ?…..
በሁለተኛው ክፍል እንቀጥላለን፡፡
——
መስከረም 11/2007

No comments:

Post a Comment