Saturday, September 20, 2014

በህወሓት አገዛዝ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጅምላ ግድያ በጽኑ እናወግዛለን!!!


መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም.
የአገራችን የኢትዮጵያን በትረ ሥልጣን በጠመንጃ ኃይል የተቆጣጠረው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየወሰደ ያለውን እሥራትና ግድያ አጠናክሮ መቀጠሉን የሚያጋልጡ ማስረጃዎች በየጊዜው ከራሱ ከአገዛዙ እየሾለኩ በመውጣት ላይ ናቸው።
መስከረም 5 ቀን 2007 ዓም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን በምስል ተደግፎ የቀረበው በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከነዚህ ማስረጃዎች አንዱ ነው ።
የወያኔን አገዛዝ ይቃወማሉ የተባሉና በኦጋዴን ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ጋር ንኪኪ አላቸው የተባሉ እነዚያ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ ምስኪን ዜጎች አስከሬን መሬት ለመሬት እየተጎተተ አንድ ቦታ እንዲከማች ሲደረግ፤ አስከሬኑን ለመሰብሰብ ከታዘዙት የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ የገዛ ወንድሙ አስከሬን ከሚጎተተው መሃል እንደነበረ መስማት ህሊናን የሚሰቀጥጥና የወያኔ የጭካኔ እርምጃ አቻ የሌለው ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው።
በደርግ ዘመን ቤተሰብ የተገደለበትን ሰው አስከሬን ለማግኘት የጥይት ዋጋ ለመክፈል ይገደድ ነበር በማለት ሥርዓቱን በነጋ በጠባ የሚወነጅል አገዛዝ ከሚወነጅላቸው ሥርዓት በባሰ በኦጋዴን የገደለውን ንጹህ ዜጋ አስከሬን የገዛ ወንድሙ መሬት ለመሬት እንዲጎትተው አድርጓል። በዚህም ህወሓት በሰብዓዊነት ላይ ከቀደምቶቹ ሁሉ የከፋ የሚሰቀጥጥ ወንጀል ፈጽሟል። ቀደም ሲል በበደኖ፤ በአርሲ፤ በአርባ ጉጉ፤ በሃዋሳ ፤ በጋምቤላ እና ድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ነዋሪዎች ላይ በወያኔ ልዩ ትዕዛዝ ተመሳሳይ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። ይህ ሁሉ ወንጀል እየተፈጸመብን አስከዛሬ ወያኔን በጫንቃችን ተሸክመን ለመኖር የተገደድነው እነዚሁ ጥቂት ዘረኞች ሕዝባችንን በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት በመከፋፈላቸው አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ሲጠቃ ሌላው በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ይህንን አረመኔያዊ እርምጃ አጥብቆ ያወግዛል። ጊዜው ሲደርስ የዚህ ወንጀል ፈፃሚዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብሎ ያምናል። ስለሆነም ወያኔ ሕዝባችንን አቅም ለማሳጣት ላለፉት 23 አመታት በኅብረተሰባችን መካከል የገነባውን የጥርጣሬና የጥላቻ ግንብ በመናድ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኦጋዴንና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰቆቃና እልቂት ለማስቆም እንዲችሉ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
ኦጋዴን ውስጥ ለፈሰሰው የንጽሃን ደምና በሰብዓዊነት ላይ እየተፈጸመ ላለው ወንጀል ተጠያቂው ሥልጣንን በኃይል የሙጥኝ በማለት በአገርና በሕዝብ ሃብት ዘረፋ ላይ የተሰማራው ጥቂት የህወሃት አመራር መሆኑ አያጠያይቅም። ይህንን ወንጀለኛ ቡድን ለፍርድ ለማቅረብ ንቅናቄዓችን ግንቦት 7 የሚያደርገውን ሁለገብ ትግል ለፍትህ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ የቆመ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲቀላቀል በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ቀርቦለታል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment