Friday, August 22, 2014

ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ጥረት


የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በህሊናና የፓለቲካ እስረኞች ሁሉ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ መክበድ፤ በፀረ-ሽብርተኝነት ስም በሕዝብ ላይ የሚነዛው ወያኔያዊ ሽብር መብዛት፤ እስሩ፣ እንግልቱ፣ መሳደዱ፣ የሀብት ዘረፋው በየዕለቱ እየጨመረ መምጣት እና ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮ እየከበደ መምጣቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ጋር ወሳኝ የሆነ ትግል መግጠሚያ ወቅት ላይ መደረሱ አመላካች ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል መንፈስ መነሳሳት በተጨባጭ ከሚያረጋግጡ አመላካቾች አንዱ የግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አባል ለመሆኑ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመር ነው። ይህንን ለውጥ ተከትሎም ግንቦት 7 የአባላት ቅበላን ሥራ ለማፋጠን የሚረዱ እርምጃዎች ወስዷል። ሆኖም ግን በአባላት ቅበላ ወቅት ሊታለፉ የማይችሉ ጥንቃቄዎች መኖር እንዳለባቸው ደጋፊዎችም እጩ አባላትም ይረዳሉ ተብሎ ይታመናል።
በዚህም ምክንያት አሁንም እየጨመረ የመጣን ንቅናቄውን የመቀላቀል ፍላጎትን ለማስተናገድ፤ ለተግባራዊ ሥራዎች የተነሳሱ፣ ዓላማችንና ንቅናቄዓችንን የሚደግፉ ሆኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶች በድርጅት አባልነት መቀላቀል የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ አባላትን ለማሳተፍ የሚረዳ መዋቅር ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑ ታምኖበታል። ስለሆነም እነዚህን ወገኖቻችን የትግላችን አካል ብቻ ሳይሆን የንቅናቄዓችንም አካል ለማድረግ እንዲቻል በአባላት ጉዳይ ሥር የደጋፊዎች ማስተባበሪያ መዋቅር እንዲደራጅ ተደርጓል። ይህ አደራጀት ግንቦት 7ን ለማዘመን እና ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የተመቸ ድርጅት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አካል ነው። ይህ አደረጃጀት በአንድ በኩል የድርጅቱን ምስጢራዊት ለመጠበቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ባሉ ፍላጎቶች መካከል ያለውን ቅራኔ ለመቅረፍ የቀረበ መፍትሔ ነው።
በዚህም መሠረት በአባልነት ለመመዝገብ ስለእናንተ ምስክርነት መስጠት የሚችል የግንቦት 7 አባል ማቅረብ ለጊዜው ያልቻላችሁ፤ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያት የግንቦት 7 ደጋፊ እንጂ አባል መሆን የማትፈልጉ ወገኖቻችን ግንቦት 7 ፍላጎታችሁን የሚያሟላ መዋቅር ማዘጋጀቱን በይፋ ያበስራል።
የግንቦት 7 ደጋፊ በግንቦት 7 የውስጥ ጉዳዮች የመወሰን፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት አይኑረው እንጂ የንቅናቄው ሙሉ ተሳታፊና ባለቤት በመሆኑ በልበ ሙሉነት “እኔም ግንቦት 7 ነኝ” ማለት ይችላል። የግንቦት 7 ደጋፊ እንደማንኛውም አባል ድርጅታዊ ሥራዎች ሊሰጡት ይችላል።
በደጋፊነት ለመመዝገብ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ኢሜል፣ እድሜ፣ ጾታ፣ ከተማና የሚኖርበት ሀገር ብቻ የሚጠይቅ የድህረ ገጽ ቅጽ መሙላት ያስፈልጋል። ይህ ቅጽ በንቅናቄው ድህረ ገጽ ላይ ይገኛል። ደጋፊዎች እውነተኛ ስማቸውን የመስጠት ግዴታ የለባቸውም። አንድ ደጋፊ በየወሩ የሚፈቅደውንና የሚችለውን ያህል ገንዘብ እንደሚያዋጣ ይጠበቅበታል፤ ይህ የደጋፊነቱ አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ደጋፊ በሚኖርበት ከተማ በሚደረጉ የትግል እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ይጠበቅበታል፤ ይህም ሌላው የደጋፊነት መገለጫ ነው። ደጋፊዎች የንቅናቄው ሳምንታዊ ጋዜጣና ወርሃዊ ልዩ መልዕክት በግል ኢሜላቸው እንዲደርሳቸው ይደረጋል። ደጋፊዎች በተግባር በሚያሳዩት ተሳትፎ ከአባላት ጋር ቅርርብ በመፍጠር ወደ ከደጋፊነት ወደ አባልነት የሚሸጋገሩትን መንገድ ያመቻችላቸዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ራሳችሁን በህወሓትና ጀሌዎቹ መዋቅር ውስጥ ያገኛችሁና በወያኔ እኩይ ተግባራት የህሊና እረፍት ያጣችሁ የሕዝብ ወገኖች ይህንን መዋቅር ከግንቦት 7 ጋር በምስጢር ለመገናኛነት ተጠቀሙበት። በመከላከያና በፓሊስ እንዲሁም በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ይህንን መስመር በግኑኝነት መመስረቻነት ተጠቀሙበት። በወያኔ የስለላ ወዋቅር ውስጥ ያላችሁም እድሉን ተጠቀሙበት።
በድህረ ገጻችን ላይ http://www.ginbot7.org/supporter-form/ በቀጥታ በመመዝገብ የግንቦት 7 ደጋፊ መሆን ይቻላል። ድረገጹ በማይከፈትባቸው ቦታዎች በ supporter@ginbot7.org ይፃፉ።

No comments:

Post a Comment