ከዮሴፍ
ህወሃት ወያኔ በተደናገጠ ወይም በበረገገ ቁጥር አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ማለቱ የተለመደ ነው። በተለይም ህዝብ ከህዝብ ከፋፍሎ እና አጋጭቶም ሆነ ከትውልድ ስፋራው እያፈናቀለና እየገደለም ቢሆን የስልጣነ መንበሩን መነቃነቅ ባሸተተ ቁጥር ሁሌም ዛሬም ነገም ከዚህ አደጋ የሚወጣበትን መንገድ መፈልፈሉ የሚታወቅ ሃቅ ነው። እንደ 40/60 ኮንዶሚኒየም አሁን በተለይም በቅርብ ጊዜ ካየናቸው የፖለቲካ ትግሉን አቅጣጫ ለማስለወጥ ሟቹ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በአንድ ጀምበር ከተኙበት ባነው “አባይን መገደብ አለብን ህዝቤ ሆይ ተከተለኝ፣ አባይን የደፈረ… ብላችሁም ዘምሩልኝ” በሚል የአረቡ አለም የነጻነት አቢዎት በግብጽ፣ ሊቢያ እና ቱኒዚያ የተጀመረው አምባገነኖችን ጠራርጎ የወሰደው የነጻነት ወራጅ ውሃ እንዳይወስደው ግድብ ሊያበጅለት ዘንድ የአባይን ሳይሆን የነጻነት ጩኸትን ሊገድብ ዘዴ ፈጠረ። በዚህም የዲያስፖራውንና የሀገሩን ውስጥ ህዜብን ይህ እኮ ሀገራዊ ጉዳይ ነው በፖለቲካ ብንለያይ በአባይ ላይ ግን አንድ ነን በሚል ብልጣብልጥ ዘዴ ንጹሃንን የሚያስርበት፣ የሚገድልበት ገንዘብ ነገር ግን በአባይ ስም ልመና ሞከረ አልተሳካም እንዴውም በውጪ ለስብሰባ አዳራሽና ለባለስልጣኑ ትራንስፖርትና ሌሎች ተጨምረው ያወጣቸው ብሮች ለስራው ቢውል የተሻለ ነበር በሚል የውስጥ ወቀሳም ደረሰበት። ታዲያ ለጊዜውም ቢሆን survive ለማድረግ በመምሰል ቢንገዳገድም የገባበት አላማ ለእውነተኛ ግድብ ባለመሆኑ ዛሬ አለም አቀፍ ባለሙያዎች “ጥናት ያልተደረገበት ነውና ይደረግ” በሚል ሙያዊ ልገሳቸውን ቢሰጡም ይህን ችላ ብሎ ለሀገር ተቆርቋሪ በመመስል በሁሉም ዘርፍ የተጀመረበትን የትግሉን አቅጣጫ ለማስቀየር አሁንም እየሞከረ ነው።
በአንጻሩ ለሱዳን በጎንደር መተማ የነጻነት ሃይሎች የእምቢተኝነት ድምጻቸውን፣ ጉልበታቸውን አጠናክረው እንዳይመጡበት እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ስምምነት አደረግን በሚል May 21, 2008 መለስ ዜናዊ መሬት ለሱዳን መሰጠቱን እንዲህ ሲል ነገረን We, Ethiopia and Sudan, have signed an agreement not to displace any single individual from both sides to whom the demarcation benefits. We have given back this land, which was occupied in 1996. This land before 1996 belonged to Sudanese farmers. There is no single individual displaced at the boarder as it is being reported by some media. አቶ ስዪ አብርሃ በአንድ ወቅትም ይህ መሬት መሰጠቱን ለቪ.ኦ.ኤ ጋዜጠኛ እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል። አሁን ደግሞ ሃይለማርያም ደሳለኝ ቀጠሉበት። መከረኛ አማራው በየሄደበት መሬቱን እየለቀቀ እንዲሰደድም አደረጉ። ታዲያ ይህ እንግዲህ በጣም ቀላሉ ማንም የሚያውቀውን እውነት ነው።
ስለዚህ ይሄን ዘረኛ ሀገራዊ ራእይ የሌለው ቡድን ሁሌ በየጊዜው በሚሰጠን አጀንዳ እየታለልን ለምን የትግል መስመራችንን እንስታለን? ፖለቲከኞች የሚታገሉለትን እና የሚታገሉበትን ዘዴ በትክክል ይዘው ካልሄዱ፣ ባለሙያዎችም ይህን ተረድተው ብእራቸውን አስተካክለው መታገል ያለባቸውን ካላወቁ አውቀነውም ሆነ ሳናውቀው ለወያኔ የትግል ዘዴ እየተመቻችን ነው። ለዚህ አባባሌ ምክንያት የሆነኝ ሰሞኑን እነ ዶ/ር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ማሞ እና ዶ/ር ስይድ ስለ አባይ የጻፉት Misplaced Opposition to the Grand Ethiopian Renaissance Dam” ጽሁፍ ነው። በእኔ እምነት 50+ የሆነው ኢትዮጵያዊ ግድቡን አይቃወምም ነገር ግን መቅደም የሚገባውና መገደብ ያለበት የወያኔ የጥይት አፈሙዞች የሚተፉትን እሳት ነው። በመሆኑም ተቃዋሚው ጎራ የአባይ አጅንዳ የመጣው ለማደናበር መሆኑን በደንብ በተረዳበት ሰአት፤ በታቃዋሚው ጎራ የሚታወቁት ግለሰቦች ወያኔ እንኳን ከልቡ መገደብ ሳይፈልግና ብሄራዊ ተቆርቋሪ መስሎ ለመቅረብ ያሰበውን አጀንዳ ተቀብሎ ማጨብጨብ የትግሉን አቅጣጫ ማስለወጥ ተገቢ አይደለም። ሰሞኑን እንኳን ሰላማዊ ሰልፈኞችን ወደ 30 የሚያህሉ ንጹሃንን የገደለ መንግስት እንዴት ሆኖ ነው ብሄራዊነት የሚሰማው? እናም ብእራችሁ ማእበል ላይ ሆኖ መወዛዎዝ የለበትም። እናንተ የጻፍችሁት ጽሁፈ-ጥናት የወያኔ መንግስት የውጪ አምባሳደሮች ወይም የኢትዮጵያ ኢምባሲ በአሜሪካ ዌብሳይት ወይም አይጋ ፎረም ላይ የሚለጠፍ ጽሁፍ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ስለዚህ በኢትዮጵያ ህዝብ እና ሏኡላዊነት የሚደርሰውን በደል ማስቀደም ከተማሩ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ ነው። መጻፋችሁ ጥሩ ነው ነገር ግን እኛ እናንተን የምናውቃችሁ ደግሞ በተቃዋሚነት ነውና በማእበሉ ተናውጣችሁ ካልተቀየራችሁ በስተቀር እናንተ የኢትዮጵያን ልጆች ሃብት ናችሁ እና እባካችሁ የትግሉን አቅጣጫ አትለውጡት። የወገኖቻችሁ፣ የሀገራችሁ ህዝብ በመሬት ስንጠቃ፣ በግድብ ሰበብ ከቀዪው እየተፈናቀለ ነው እና ያንን እናተኩር። የዶ/ር አክሎግ ቢራራ ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶ አባይን መታደግ ይቻላልን? የሚለው ሙያዊ ገለጻ በሚገባ አስቀምጦታል። እርግጥም እንዳሉት ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶ አባይን መታደግ ይቻላልን? ባሉት ጽሁፋቸው “አባይ ፈንጅ የቀበረ ውሃ ነው”። እኛ የጠማን ውሃ ነው! እኛ ያጣነው መብራት ነው! ስለዚህ አባይ የኛ ነው!! ነገም ዛሬም ትላንትም! የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለወያኔ የስልጣን መቆያ እንጅ መንሻ እንዲሆን አንፈልግም። ኢትዮጵያኖች በወያኔ አጅንዳ ውስጥ ገብተን አንዋኝም። አጥቂዎች እንጂ ተከላካዮች አይደለንም። እናም ግድ የለም እናንተ የምትሉትን እነሱው ካወቁበት በዲፕሎማሲ ቋንቋ በተለመደ ውሸታቸው ይበሉት። እናንተ ግን የእኛ ናችሁ። ተሳሳትሁ እንዴ?
No comments:
Post a Comment