April 6, 2012
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮ ሚዲያ በተባለውና የትግራዩ ተወላጅ አቶ አብርሃ በላይ በሚያስተዳድረው ድረ ገጽ አማካይነት አቶ ሙሴ ተገኝ በድርጅታችን ላይ የከፈተውን ዘመቻ በተመለከተ ምላሽ ላለመስጠት ያደረግነውን ጥረት ወገን ሁሉ ይረዳዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ነገር ግን አቶ ሙሴ ተገኝ በጥቂት የአካባቢው ሰዎችና ጸረ ኤርትራ ህዝብ ጭፍን አመለካከት ባለቸው ግለሰቦች እየታገዘ በየዕቁብ ቤቱ ሳይቀር የከፈተው ጥቃት እየጨመረ በመምጣቱና የግለሰቡ ጉዞ ያበሳጫቸው ወገኖችም ለምን ምላሽ አይሰጠውም በሚል ባቀረቡልን ተደጋጋሚ ጥያቄ መሰረት ይህን መግለጫ እንድናወጣ ተገደናል።
አቶ ሙሴ ተገኝ ወይንም በተለምዶ አጠራር ፕሮፌሰር ሙሴ ሰሞኑን ከኤርትራ ለቀን ወጥተናል በማለት ራሱን እንደ ኢህአግ አባልና መሪ በመቁጠር የህይወት መስዋዕትነትን ዛሬም እየከፈለ ባለፈው አርበኛ ሰራዊት ደም መቀለዱን ስንሰማ የተሰማን ስሜት አስቆጪ እንደሆነ መግለጽ የተገባን ይሆናል።
በሰላማዊ ትግል ስም እየማሉና ከአምባገነኖች ጋር እየተሻሹ መቆየት ቀላል ሲሆን ጠመንጃ አንስቶ ለፍልሚያ መዘጋጀት አይደለም ጠመንጃ ካነሱ አርበኖች ጋር እንኳ ቆሞ ማውራት ብቻውን ምን ያህል ላብ ላብ እንደሚልና መች ከዚህ ቦታ ጠፍቼ እንደሚያሰኝ ያሳለፍናቸው ተሞክሮዎች አያሌ ናቸው።
ጠመንጃ አንስቶ ስርዓት ለመለወጥ የሚታገል ድርጅት ፋራ ነው እያሉ ሲሳለቁብን ከነበሩ የሰላማዊ ትግሉ ፋኖዎች አንስቶ ከአርበኞቻችን ጋር ፎቶ ግራፍ እየተነሱ አርበኛ አርበኛ ለመሽተት ብሎም “የመሃይምናኑ” አርበኞች መሪ ለመሆን በስተጀርባ ሲሯሯጡብን የነበሩትን በትግስት ያስተናገድንበትም ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ታግለው ባታገሉንና በትረ ስልጣኑን በጨበጡ እሰየው በነበረ ። ቅር የሚያሰኘውና እንባ እንባ የሚለው ግን በርቀት በሪሞት ኮንትሮል ካልተቆጣጠርናችሁ ማለታቸውን ጠልተን ፊታችንን ስናዞርባቸው በጠላትነት የሚፈርጁን ዝና በግዱ ግለሰቦች ለወያኔ ገመናችንን ማደላቸውና መረጃችንን ማሰራጨታቸው ይብሱን ጎዳን እንጅ።
በአዲስ መንፈስ ራሱን ያዘጋጀውና ወደ ወያኔ ጉያ ለመግባት ሰውነቱንን እያሟሟቀ የሚገኘው የዛሬውም አቶ ሙሴ ተገኝ ከነኝህ ከላይ ከጠቀስናቸው አንዱ ሲሆን በርዕሳችን ላይ እንዳመለከትነው ግለሰቡ ሲጀመርም የአርበኞች ግንባር እንኳን መሪ፤ ሙሉ አባል ያልነበረ የጤናው ሁኔታ እንኳ አጠራጣሪ በመሆኑ አርበኛው በሙከራ አባልነት በአስመራ ከተማ ነዋሪ በመሆን እንዲቆይ የወሰነበት ግለሰብ መሆኑን በቅድሚያ መግለጽ እንወዳለን።
ለዕለታዊ ኑሮ ቅመም መጨመርንና ለአንዲት ቀን አዳር ብትሆን ውበት መስጠትን የተካነበት ሙሴ ተገኝ የገንዘብ ምንጭንም ማፈላለግ እንዲሁ አብሮ አድጎበታልና ከአለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የመጀመሪያው የአስመራ ከተማ ኢንቨስተርና አካለ ስንኩላንን በስፖርት ማሰልጠን በሚል የረዴት ድርጅት አስተዳዳሪ ሆኖ የቆየ ሰው ነበረ።
የዛሬን አያርገውና በአስመራ ሲሶ መንግስት አለው እየተባለ በወቅቱ ይቀለድበት የነበረው አቶ ሙሴ ተገኝ ፕሮፌሰር በሚለው ስሙ ማልለን በአስመራ ከተማ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ወደኛ ድርጅት ያመጣልናል በሚል የአስመራና አካባቢው የአባላት ማደራጃ ጽ/ቤት ሃላፊ በማድረግና ማህተም በመስጠት ያሰማራነው ሰው ነበረ።
ከኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ አይደለም ከኤርትራውያንም ጭምር ገንዘብ በመቀበልና ማህበራዊ ሙስና ውስጥ በመዳከር ከሃገር ማስኮብለልን እንደተጨማሪ መተዳደሪያ በማድረግ እንዲህ እንደዛሬ ሳይታወቅና በኤርትራ መንግስት የወንጀለኛነት ማህደር ውስጥ ስሙ ሳይካተት የ1990ዎቹ መጀመሪያ ወቅት ነበረ ከግንባራችን አርበኖች ጋር ትውውቅ የፈጠረው።
ኢትዮጵያውያን ማለት የአባይ ተፋሰስ ሃገሮች ማለትም ጎጃም ጎንደርና ከፊል ወሎ ናቸው በማለትና በአባይ ጉዳይ ፈቃድ ልንጠየቅ የሚገባን እና ጎጃሜዎቹ ወይንም እንደሱ አጠራር ፈለገ ግዮኖቹ ብቻ ነን በማለት ጎሰኛ ድርጅት አቋቁሞ የነ መለስ ዜናዊን ዘረኛ ፖሊሲ ያቀነቅን የነበረው አቶ ሙሴ ተገኝ የአስመራ ከተማ ነዋሪ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ጥቂት አዱኛ ሰራሽ ደጋፊዎቹን በዙሪያው በማሰባሰብና የሌላውን አካባቢ ተወላጆች እርስ በርስ በማባላት የያዘው አባዜ ለኛም አርበኖች እንደተረፈ ለሚያዳምጠን ወገን ማካፈሉ ምን ያህል የመከራ ዘመን እንዳሳለፍን ያስረዳልናል የሚል እምነት ይኖረናል።
የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ ካሪዝማ ወይንም የደስደስ ቀድሞውንም ያልተፈጠረበት፤ ከትንሽ እስከትልቅ አክብሮት ተችሮት የማያውቀው፤ዛሬ አንድና ብቸኛ ባህርዩ ዜጎችን በገንዘብ የማማለል ክህሎቱ እንኳ ከላዩ ላይ ወልቃ የሾለከችበት አቶ ሙሴ ተገኝ ከውጭ የረድኤት ድርጅቶች በሚጎርፍለት ገንዘብ ሴት አካለ ስንኩላንን ጭምር ከማባለግ የዘለቀ አንድ ቀን ወንዶች ከዋሉበት ሊያውለው የሚችል ተግባር ላይ ሳይሳተፍ ራሱን አዋርዶ ኢትዮጵያውያንና ህዝቧን ያዋረደ ግለሰብ መሆኑን በድፍረት ለመናገር ግዴታችን ይሆናል።
የረድኤት ድርጅት ሃላፊ በመሆኑና በአስመራ ከተማ የኢሕአግን ደጋፊዎች ያስተባብርልናል በሚል ያስቀመጥነው ሙሴ ተገኝ በተለያዩ ጊዜያት አርበኞቻችንን ለመጎብኘት ወደ ግንባር ሲመጡ ከነበሩት ለምሳሌም ያህል ከሳይንቲስት ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ እንዲሁም አብርሃም ያየህ ጋር በመሆን ከአስመራ ይመጣ በነበረበት ጊዜ ነበረ ከሰራዊታችንና ከመሪዎቻቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የመሰረተው።
ለአርበኞች ግንባር ተዋጊዎች፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ማለት መሃከላቸው የሚተኛ አርበኛ ማለት ነው። ሳይገባ ወጣሁ፤ አባል ሳይሆን መሪ ነበርኩ በማለት ዛሬ ለያዢ እያስቸገረ ያለው ሙሴ ተገኝ ይዞ በሚንቀሳቀሰው የረድኤት መኪና አንዲት ቀን እንኳ አንድ አርበኛ ሳይሳፈርባት፣ ለአንዲት ምሽት እንኳ ከአርበኛው ጋር ጨረቃን ሳያይ፤ የአርበኛውን የሌሊት ህይወት ሳይካፈል ወደሞቀበት የከበርቻቻ መንደር ይመለስ የነበረ ሰው እንደነበረ ለወገኖቻችን መግለጽ የተገባ ነው።
በ1993ቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ምስረታ፤ በኋላ የግንባሩ መሪ ከሆነው መስከረም አታላይ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበረው በዕለቱ የክብር እንግዳ እንደነበሩት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት አይነት በክብር እንግድነት ተጋብዞ ተገኘ እንጂ እንደ ተራ የድርጅት አባል እንኳ አንዳችም ስፍራ እልዳልነበረው ለወገን ይፋ ማግድረግ ግዴታችን ነው።
ኤርትራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በሚያካሂዳቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ነውሮች በኢህአግ አባላት ዘንድ የተጠላው ሙሴ ተገኝ ከስራ አስፈጻሚ አባላት ጋር ወደ አርበኞቹ ማሰልጠኛ ይምጣ እንጂ ዛሬ ለጥፋት ተልዕኮ የሚጠቀምበትን ቪዲዮ ካሜራ ያጥፋ ያብራ እንጂ ፤ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ቃላት ብተና ላይ ሲንቀሳቀስ ይስተዋል እንጂ ለአንዲት ቀን እንኳ በላዩ ላይ የለጠፈውን ፕሮፌሰር የተሰኘ አንዳች የሚያክል ትልቅ ስም በአግባቡ ሲጠቀምበት ያልታየ ሰው እንደሆነ ማስረዳት አስፈላጊ ነው።
ዛሬም በጽ/ቤታችን ውስጥ ለላንቲካነት ተጎልታ የምትገኛውን ሰርታ የማታውቅ ዴስክቶፕ ኮምፒውተር ይዞ የተጠጋው ሙሴ ተገኝ ለግል ዝናው ይመቸው ዘንድ በወራት አንድ ጊዜ በማሰልጠኛው እየተገኘ የኢህአግንና የትህዴድ አባላትን በቪዲዮ ይቀርጽ የነበረ ሲሆን ጎጃም ፈለገ ግዮን የሚለው ጠባ ብሄረተኛ ፍልስፍናው ተቀባይ በማጣቱም ኢትዮጵያዊነት የሚል አዲስ መሰል ፍልስፍና በመስበክ ስሙን ለማረቅ የጀመረው በዚህ ወቅት ነበረ።
በ2004 አመተምህረት ከረን ከተማ ከምትገኝ ቡና ቤት ውስጥ ከወያኔ ከድተው ከመጡ የሰራዊት አባላት መሃከል በመንቀስ 6 የጎጃም ተወላጅ ወታደሮች ሰብስቦ ስለ ጎጃም ህዝብ የመገንጠል መብት መከበር ተገቢነትና አባይ የጎጃም ህዝብ ብቸኛ ሃብት ነው በሚል ያቀረበው ትምህርት ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም። የሚበትነው በሩ ሁሉ መልሶ እየለበለው እንደሆን የተሰማው ሙሴ ተገኝ ኢትዮጵያዊነትን ለመውደዱ ማረጋገጫ ይሆነው ዘንድ ኢትዮጵያኒዝም የሚባል ገመና መሸፈኛ ትምህርት ለጥቂት ቀናት በአርበኛው የመሰብሰቢያ ታዛ ስር ራሱን ከቪዲዮ እየከተተ ለመስጠት የሞከረውም የዛኑ ሰሞን ነበረ።
በ1996 አመተምህረት ኢህአግ ወደ ህብረት ሲመጣ ከቅርብ ጓደኛው መስከረም አታላይ ጋር በመቀራረቡ ብቻ አሁንም የኢህአግ የአስመራ ከተማ የድጋፍ ጽ/ቤት ሰራተኛና ከአባሎቻችን ላይ ገንዘብ ተቀባይ ሆኖ የሰራ ፤እንዲሁም ያለውን ትርፍ ጊዜ አጋጣሚ ይጠቀምበት ዘንድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎቻችንን ሲገናኝ የቆየ ሲሆን የመሃል ሃገር፤ የጎንደር፤ የአርማጭሆ፤ የወልቃይትና የጎጃም ተወላጆች በሚል የመከፋፈል አባዜ የተጠናወተው ሙሴ ተገኝ ተዋጊዎችን ከፖለቲካ ካድሬዎች፤ እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በማናቆር መሰሪ የመከፋፈል ተግባራትን በተፈጠረለት ትንሽ ቀዳዳ በመጠቀም ሲያከናውን የሰነበተ ፤ የድርጅቱን የአመራር አካላት በመከፋፈልም ገሚሱን ወደ ሱዳን ቀሪዉንም ወደ ሌላ ሃገር እንዲሄዱ አፍራሽ ተግባር ሲፈጽም የከረመ ነው።
በሺህ የሚቆጠሩ አርበኞቻችን የተሰዉለት ድርጅታችን ያለፈባቸው የመከራ አመታት የበዙ እንዲሆኑና በድርጅታችንም ውስጥ ለተፈጠሩት አሳዛኝ ክስተቶችም ዋነኛውንና ከፍተኛውን ሚና ሲጫወቱ ከነበሩት አንዱ ሙሴ ተገኝ መሆኑን ሳንወድ ዛሬ እንድንናገር ስንገደድ በድርጅታችን ውስጥ ለተሰሩ ወንጀሎች አቶ ሙሴ ተገኝና የቅርብ ጓደኞቹ ወደፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ሊፋረዳቸው የሚያስችል መረጃዎች ዛሬም በጽህፈት ቤታችን እንደሚገኙም በተጨማሪ መግለጽ አስፈላጊ ነው።
በጥቂት ተባባሪዎቹ አማካይነት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2000 ዓ/ም ወይንም እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር 2008 ላይ በተጠራው የድርጅቱ 1ኛ ጉባኤ ላይ ወደ ሙሉ አባልነት እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲሸጋገር ከቅርብ ጓደኞቹ በተደረገው ጥቆማ ሙሴ ተገኝ የአንድም አባል ድምጽ ሳያገኝ ጭራሹኑም ቁጣና ሁከት ተቀስቅሶ የነበረ ከመሆኑም በላይ ችግሮቹን ላንዴና ለመጨረሻ ለመቅረፍ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይም በጠቅላላ ድምጽ ከድርጅቱ እንዲወገድ የተወሰነበት ነው።
የፖለቲካ ቆሌ የራቀው ሙሴ ተገኝ ላለፉት አራት አመታት ባዘጋጀው ድረገጽ ላይ የአርበኞቻችንን ምስል በመለጠፍ ምስጢሮቻችንን ከአደባባይ በማኖርና የማሰልጠኛ ጣቢያዎቻችንን ሳይቀር ለጠላት በማስተዋወቅ የእጅ መንሻ እያደረገን የቆየ መሆኑን ወገን ልብ እንዲል እንወዳለን።
አዎ ኢሕአግ ዛሬም ወያኔን እያሳደዱ የሚቀጡ፤ የሚሰዉ፤ እንደወታደር የሚማረኩና የሰቆቃ ሰለባ የሆኑ አርበኞች ያሉት ድርጅት ሲሆን ሙሴ ተገኝ የወያኔን ቴሌቪዥን ገልብጦ ለህዝብ እንዳቀረበውም አምና በወያኔ ተማርከው አምልጠው በመውጣት ዘንድሮም አብረውት የሚፋለሙ አርበኞች ያሉት ድርጅት ነው።
እነ ሙሴ ተገኝ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኖች ግንባር ተዋጊ ኤርትራ ውስጥ የለም ማለታቸው እኛን ሁነው ማውራታቸው ከሆነ ትክክል ናቸው ለማለት እንደፍራለን። ምክንያቱም አዎ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ኤርትራ ውስጥ ምን ይፈይዳልና። የኢሕአግ ሰራዊት አባላት እየታገልን እየደማንና እየሞትን ያለነው በበቀልንበት ምድራችን፤ እትብታችን በተቀበረባትና አባቶቻችን ለዳር ድንበራቸው በወደቁባት መሬታችን ላይ ነው።
እኛ የኢሕአግ ሰራዊት አባላት እንደ አቶ ሙሴ ተገኝ አይነቱን የበሉበትን ወጭት ሰባሪና የክህደት አውራ ዋልጌ ግለሰቦች በጥብቅ እንጠላለን። በገዳዩ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ምክንያት ሃገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ዜጎች ከጅቡቲ ከሱዳንና ከመሳሰሉት አጎራባች ሃገሮች እየታነቁ ወደ ወያኔ እስር ቤት ሲጣሉ፣የኤርትራ ህዝብና መንግስት ግን ዛሬም ድረስ አቅፈው ደግፈው፣ያላቸውንም አቃምሰውንና አልብሰውን ፣ለነጻነታችንም እንበቃ ዘንድ አይዟችሁ በማለት እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ከጎናችን መሆናቸውን በድፍረት እንናገራለን።
የኢሕአግ ተራ አባል እንኳ ሳይሆኑ ከኤርትራ ለቀን ወጥተናል በማለት በየድረገጹና የመነጋገሪያ መድረኩ ያዙን ልቀቁን የሚሉት ግለሰቦች ቁጥራቸው የበዛ በመሆኑ ወገን ሁሉ እኒህን በድርጅታችን ስም የሚነግዱ፣ የድርጅታችንን ማህተም በመጠቀምም ከስደተኛ ወገኖቻችን ጭምር ሳይቀር ገንዘብ በመሰብሰብ መተዳደሪያቸው እያደረጉ ያሉትን ግለሰቦች ወጊዱ ይላቸው ዘንድ በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘብ እንወዳለን።
ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ ስምንት ሁነው በተሰበሰቡ በሳምንቱ ንፋስ የጣለውን የኤሌክትሪክ ቋሚ ፎቶ እያነሱ ሰራዊታችን ድልን እየተጎናጸፈ ነው ከሚሉ ሃሳዌ መሲሆች ኢትዮጵያዊ ሁሉ ራሱን እንዲያርቅ ስንመክር፤ በውን መሳሪያ አንስተው ገዳዩን ስርዓት በመፋለም ላይ ያሉ ወገኖች ካሉ ግን ዜጋ ሁሉ እገዛ ያደርግላቸው ዘንድ ጥሪያችን እናቀርባለን ። ምክንያቱም በመሳሪያ ሃይል ብቻ ነውና ዘረኛው አገዛዝ ከህዝባችን ጫንቃ ላይ ተሽቀንጥሮ የሚወድቀው፤ ብሎም እውነተኛ ሰላምና ዴሞክራሲ በሃገራችን ላይ ሊሰፍን የሚችለው።
አንድነት ሃይል ነው!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር
መጋቢት 27 ቀን 2004
No comments:
Post a Comment