በኦሮሚያ የተጀመረው ተቃውሞ መካረረ ስጋት ፈጥሯል
ኦህዴድ የተከፋፈለ አቋም ይዟል፤ ኢህአዴግ ጉልበት መርጧል
May 1, 2014
በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ድምጽ ለማሰማት በሞከሩና ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ሰልፍ በወጡ ወገኖች ላይ አገዛዙ የ”ከፋ” ነው የተባለ ሃይል መጠቀሙ ተሰማ። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ታስረዋል። ለተቃውሞ መነሻ በሆነው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ ኦህአዴድ ተመሳሳይ አቋም መያዝ አልቻለም። ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያልቻለው ኢህአዴግ ጉልበት መምረጡ አገሪቱ ውስጥ ካለው የተከማቸ ብሶቶች ጋር ተዳምሮ አለመረጋጋቱን ያሰፋዋል የሚል ስጋት አለ።
ከኦሮሚያ ክልል አስተዳደር የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት በአቀራረቡ ቢለያይም ከተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰሙት ዜናዎች ሊስተባበሉ የሚችሉ አይደሉም። በታችኛው እርከን የሚገኙትን ጨምሮ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በጥቅሉ፣ ገሃድ አይውጣ እንጂ በመዋቅር ውስጥ ያሉ ሰራተኞችና ካድሬዎች የተቃውሞው ተሳታፊና ደጋፊ መሆናቸውን ክልሉም ሆነ ኢህአዴግ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ አዲሱ ማስተር ፕላን በዙሪያዋ ያሉትን ስድስት የኦሮሚያን ከተሞችና ስድስት የገጠር ቀበሌዎች የተካተቱበት መሆኑ ያስነሳው ተቃውሞ ቀደም ሲል በክልሉ በምክር ቤት ደረጀ በካድሬዎች ተቃውሞ አጋጠመው። ይህንኑ ተከትሎ ከሳምንት በፊት በአንዳንድ የትምህርት ተቋማት ብልጭ ድርግም ሲል የነበረው ተቃውሞ እየጠነከረ መጣ። የክልሉ የጎልጉል ምንጭ “ተቃውሞው እንደሚጨምር፣ ካድሬውም የተቃውሞው ስውር አጋር እንደሆነ፣ በመረጃ ትንተና አስቀድሞ ይታወቅ ነበር። በዚሁ መሰረት አስቀድሞ አመጹን ማምከን ካልተቻለ የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴራልና ለመከላከያ አባላት መመሪያ ተሰጥቷል”።
የሰላማዊ ሰልፍ በሚጀመርበት አካባቢ ሌላውን “ሊያስተምር” የሚችል ከበድ ያለ የሃይል ርምጃ እንዲወሰድ በተላለፈው መመሪያ መሰረት ተግባራዊ ቢደረግም ረብሻውና የተቃውሞ እንቅስቃሴው እየሰፋ መሄዱን የጎልጉል መረጃ አቀባይ ይናገራሉ። ከከተማ ወደ ከተማ እየሰፋ የሄደው ተቃውሞ፣ የተቃውሞው አካል በሚመስሉ የስለላ ሰራተኞች በሚያቀብሉት መረጃ መሰረት ለማስታገስ ቢሞከርም አለመቻሉ ኢህአዴግ ውስጥ ጭንቀት ፈጥሯል።
የኦህዴድ አባላት በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉትን ጨምሮ ተመሳሳይ አቋም ያልያዙበት አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ በኦሮሚያ የተላዘበውን የፖለቲካ ችግር ሊያባብሰው ይችላል በሚል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢህአዴግ የፖሊስ የመከላከያ ሃይላት ከልዩ መመሪያ ጋር በተጠንቀቅ እንደቆሙ ምንጩ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ በኦህዴድ የታችኛው የቀበሌ መዋቅር ጭምር ተቃውሞው ስለሚደገፍ የአቋም መንሸራተት ሊፈጠር ይችላል የሚለው ስጋት ከፍተኛ መሆኑንንም አልሸሸጉም።
ከተለያዩ የማህበረሰብ አምዶች ሲደመጥ እንደሰነበተውና ሚያዚያ 22፤2006 (ኤፕሪል 30/2014) ቀን የአሜሪካ ሬዲዮ ከስፍራው ሰዎችን በማነጋገር እንደገለጸው ጅማ፣ አዳማ፣ ነቀምት፣ አምቦ፣ ሃሮማያ፣ ድሬዳዋ፣ በመሳሰሉት ከተሞችና የትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ ላሰሙት የተቃውሞ ድምጽ የተሰጣቸው ምላሽ ዱላና እስር ነው። ከአምቦ በስልክ ስለሁኔታው የተናገሩ እንዳሉት አላፊ አግዳሚው ሳይቀር “ተጨፍጭፏል”።
በተጠቀሰው ቀን ረፋዱ ላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ከሰዓት በኋላ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተቃውሞ ሲወጡ የመከላከያ አንጋቾችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በወሰዱት የሃይል ርምጃ በርካቶች መቁሰላቸውን፣ በነፍስ አውጪኝ አጥር ዘለው የሸሹትን በማሳደድ ጨፍጭፈዋቸዋል። እኚሁ ሰው በስልክ እንደተናገሩት “ሸሽተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው የመጡትን ተማሪዎች ለምን ቤትህ አስገባህ ተብዬ ተጨፈጨፍኩ፣ ነፍሴን ለማትረፍ መሬት እየተንከባለልኩ ጮህኩ። ሁለት ልጆቼን ወሰዱ” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል። የአምቦ ቤተመንግሥትም እስረኛ እንደሞላው አመልክተዋል።
ለማቅረብ ከያዟቸው ሶስት ጥያቄዎች መካከል አንዱ “ፊንፊኔ ያለው የአጼ ሚኒሊክ ሃውልት ይነሳ የሚል ነው” በማለት ፈርቶ እንደተሸሸገ የተናገረ ተማሪ ከአዳማ ለቪኦኤ ተናግሯል። የቪኦኤው ዘጋቢ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ሞክሮ እንዳልተሳካለት፣ በመጨረሻም ከኦሮሚያ ምክር ቤት ያገናቸው ሰው መልስ ሳይመልሱ እንደመሳቅ እያሉ ስልኩን እንደዘጉት በግብር አሳይቷል።
ከምርጫ 97 በፊት አዳማን የኦሮሚያ ዋና ከተማ መደረጓን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ችግር ከምርጫ 97 በኋላ ቀውሱ እልባት እንደተበጀለት ይታወሳል። በወቅቱ በሜጫና ቱለማ ማህበር አስተባባሪነት አዲስ አበባ ላይ የተካረረ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም አይዘነጋም። በዚያን ወቅትም የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ድሪቢን ጨምሮ በርካቶች ታስረው ነበር። ኢህአዴግ አቋሙን ለምርጫ ቀውስ ማርገቢያ በሚል ሲቀይር፣ ድርጊቱን አስቀድመው በመቃወማቸው የተገረፉ፣ የታሰሩና ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረጉ ካሳ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
አገሪቱ ላይ ከተንሰራፋው የተለያየ ችግር ጋር ተዳምሮ በኦሮሚያ የተጀመረው ተቃውሞ እንዳይካረር ስጋት የገባቸው ክፍሎች “ኢህአዴግ ጉልበት እየተጠቀመ የሚዘራውን ቂምና ቁርሾ ካላቆመ፣ ጠብመንጃ እጄ ላይ ነው በማለት የሚፈጽመውን ግፍ በማቆም ለእርቅ ካልሰራ አሁን ባለው ሁኔታ ነገሮች ከቁጥጥር ሊወጡ” እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ፤ ጂኒው አንዴ ከሳጥኑ ከወጣ በኋላ ልዩነት ሳያደርግ የሚያመጣው መዘዝ ለህወሃት/ኢህአዴግና በቅድሚያ ከዚያም ለሥርዓቱ ባለሟሎች በተዋረድ የሚባላ እሣት እንደሚሆን ታስቦ ካሁኑ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ይላሉ።
No comments:
Post a Comment