የታላቋ ቀን ልጅ
ሚያዝያ 1 2006 ዓ.ም.
ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ መዋቅሮች ባሉ መሪዎች ላይ ሰዎች ከፍተኛ አመኔታን ይሰጣሉ፡፡ ግን ብዙ ጊዜ ለአመኔታቸው አጸፋው መልካም ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ብዙም ጊዜ ወድቀትና ወርደት ይሆናል፡፡ ሁለቱም መዋቅሮች እጅግ የበሰለ አእምሮን፣ ቅንነትን፣ የሕዝብ እንደራሴ መሆንን የሚጠይቁ ቢሆም በብዙ የታሪክ ገጠመኞች ግን ተቃራኒው ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በአሁን ዘመን ደግሞ ከመቼውም የከፋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እነዚህ ከላይ የተጣለውን ሰይጣን የሚወክሉ ሰብዓዊ ፍጥረቶች በቅንነትና በበሰለ አእምሮ ለሕዝብና ለአገር ክብር የነበሩ ሰዎች ታሪካቸው እንዳይታወቅ፣ ከታወቀም ራሳቸው በፈጠሩት ሌላ ታሪክ የእነዚህን ባለታሪኮች ታሪክ በማጉደፍና የቀደመ ታሪክን የማያውቅ ሌላ እነሱን የመሰለ ትውልድ ተክቶ የታላላቅ ባለራዕዮችን ታሪክ ጨርሶ እንዲጠፋ በማድረግ የእነሱን ኑሮ ማደላደል አንዱ መገለጫቸው ነው፡፡
እኔ የምናገረው ከስሜተኝነት የተነሳ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ ግን የተረዳሁትን ያህል እናገራለሁ፡፡ ባለማወቅ ግን ልሳሳት እችላለሁ እኔ የተረዳሁት ስህተት ሊሆን ስለሚችል፡፡ የሚያርመኝ ካለም እቀበላለሁ፡፡ ደግሜ እናገራለሁ ከሥሜት የተነሳ አላወራሁም፡፡
በእኔ ግንዛቤና መረዳት በአለፉት አምስተ መቶና ምንአልባትም ከዚያም በላይ እንደ ኢትዮጵያዊው መሪ ሚንሊክ ያለ መሪ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካም ብቻ ሳይየሆን በአለም ላይ ነበረ የሚለኝን የታሪክ ምሁር ትንተና እሻለሁ፡፡ እኔ በአለፉት አምስት መቶ ከዚያም በላይ በሚሆን ዘመን እንደ ኢትዮጵያዊው ሚንሊክ ያለ ታላቅ መሪ እንዳልነበረ አስባለሁ፡፡ በእኛው ዘነድ ስለሚንሊክ ያለን ግንዛቤ ወይም ከላይ በጠቀስኳቸው የወረዱ አእምሮዎች የጎደፈ ወይም በእጅ የያዙት ወርቅ አይነት ብዙም ትኩረት ያልሰጠነው ይመስለኛል፡፡
ዛሬ በአብዛኞቻችን ዘንድ የሚንሊክ ታሪክ እንኳንስ የማንነታችን መገለጫ አድርገን የምንኮራበት በአንደበታችንም ለመናገር የሚቀፈን ሆኗል፡፡ ብዙዎቻችንም በመርዝ በተለወሰ ሌላ ታሪክ አእምሮአችን የታላቁን ሰው ታሪክ የሚያጎድፍ፡፡ በተለይም በኢትርዮጵያ ትልቅ ቁጥር አለው ተብሎ በሚታመንለት ኦሮሞ እየተባለ በሚጠራው አብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ዛሬ የሚንሊክ ጉዳይ ሲነሳ ያስበረግገዋል፤ እጅግ ያስቆጣዋል፤ ሥሙን አታንሱብኝ ይህን ሥም ከታሪክ ደምስሱት ጩኸት ያሰማል፡፡ ምክነያት ተብሎ ሲጠየቅ በዋነኝነት ብዙ ጊዜ የሚነሱት በሐረር የጨለንቆ ጦርነትና በአርሲ በሚንሊክ ዘመቻ ተፈጸሟል ተብሎ በዘበናውያን ታሪክ አዋቂዎች ነን ባሉ የተሰበከው የጡትና እጅ መቁረጥ (ሀርካ ሙራ ሐርማ ሙራ) ግፍ ነው፡፡
ሚንሊክን ታላቅ ከሚያሰኛቸው ታሪክ አንዱ ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን አገር አንድ በማድረጋቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉበት ሂደት ደግሞ አልጋ በአልጋ የነበረ ሳይሆን ከብዙ በየስፍራው በነበሩ መሳፍንቶች ጋር ተዋግተው ነው፡፡ በወቅቱ እንደአሁን ዘመን ዲፕሎማሳዊ ሂደት ብዙም የሚያስኬድ አልነበረም፡፡ ሆኖም ሚንሊክ እርግጥም ከዘመኑ በፊት የተፈጠሩ ታላቅ ሰው ስለነበሩ ዲፕሎማሳዊው ሂደት ሁል ጊዜም ቅድሚያ የሰጡት ነበር፡፡ አንድም መስፍን (የአካባቢ መሪ) የሚንሊክን ታላቅ ራዕይ ሳይቃወም ጦርነት የከፈቱበት የለም፡፡ በወቅቱ ግን በነበረው የመሳፍንቶች ኋላ ቀር አስተሳሰብ ከሚንሊክ የቀደመ አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ የሚንሊክን አገርን የመገንባት ሂደት የሚተባበር አልነበረም፡፡ የእነዚያ ኋላ ቀር የአካባቢ መሪ ተብዬዎች ሕልም ለራሳቸው ከርስ የሚሞላ ሕዝብን ከመግዛት ያለፈ የዕድገትና ብልፅግና ሕልም ከቶውንም አልነበራቸውም፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብና የአገር ውርደትና ኋላ ቀርነት እንደ እሳት ለአንገበገበው ሚንሊክ እንቅፋት ነበር፡፡ በመሆኑም ሚንሊክ የወደደውን በውድ ያልወደደውን በግድ ማሳመን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ከብዙ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ካላቸው የአካባባ መሳፍንት ጋር ጦርነት ገጥመዋል፡፡ በጦርነቶቹ ሁሉ የባለራዕዩ የበላይነት የግድ ቢሆንም ጦርነት ጦርነት ነውና ብዙ ጥፋቶች ጠፍተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የሰዎች ልጆች አልቀዋል፣ ተሰቃይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የሚንሊክ ፍላጎት ሳይሆን የመሳፍነቶቹ ምርጫ ነበር፡፡
በሀረር ጨለንቆና አርሲ የተከሰቱ ጦርነቶች ሚንሊክ አገርን ለመገንባት ካደረጓቸው ሁለቱ ናቸው፡፡ የጨለንቆው ጦርነት በአስከፊነቱ ብዙ ሕዝብ ያለቀበት ቢሆንም በጦርነት ከሚከሰቱ የተለመዱ ጥፋቶች ሌላ ለየት ያለ የታሪክ ጠባሳ ያቆየ አልመሰለኝም፡፡ የአርሲው ጦርነት ግን እስከዛሬም ድረስ እንዲረሳ አጋጣሚን ለመጠቀም በሚፈልጉ መርዘኞች እንደ መሣሪያነት እያገለገለ ነው፡፡
ሀርካ ሙራ ሐርማ ሙራ! በአማርኛ እጅ መቁረጥ ጡት መቁረጥ ማለት ነው፡፡ ይህ አሳቃቂ ግፍ በአርሲው የሚንሊክ ዘመቻ ተከስቷል እየተባለ ዛሬ ባለው ትውልድ ልዩ ስፍራ የተሰጠው አልፎም ሐውልት የቆመለት ጉዳይ ሆኗል፡፡ እኔ እንዲህ ያሉ ግፎች በዚያ ዘመን በነበሩ ጦርነቶች ሊከሰቱ ከሚችሉ አሳቃቂ ክስተቶች አንዱ ሊሆኑ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ ሆኖም በአርሲ ተከሰተ የተባለው እንዲህ ያለ ግፍ የታላቁ ሰው ሚንሊክ ትዕዛዝና ይሁንታ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ በብዙ ጦርነቶች እንደሚከሰተው፣ ይልቁንም በዚያ የጠበቀ የጦርነት የመምራት አቅምና ቅንጅት በሌለበት ዘመን ከተዋጊዎች አንዱ ወይም ከዚያም በላይ እንዲህ ያለውን ጥፋት ፈፅመውት ይሆናል፡፡ ሚንሊክ ግን እንዲህ ያደረጉትን ወታደሮች ማንነት ቢያውቁ የሚሸልሟቸው እንዳልሆኑ አምናለሁ፡፡ ይልቁንም በሞት ሳይቀር ሊቀጧቸው እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ ይህ የሚንሊክ እውነተኛው ልብ ነው! ሚንሊክ እውነተኛ ጀግና የሚባል ባሕሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ጀግና ደግሞ ጨካኝ አይደለም! ጀግና ጠላቶቹ የማይቋቋሙት እንጂ! እነኳንስ በሴቶችና አቅም በሌላቸው ላይ ሊያጠፋቸው የመጣን ጠላት እንኳን ከመግደል ይልቅ ከእነነፍሱ ይዘው ምህረትን ሊያደርጉለት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ጠላታቸውን እንኳን ገድለው በሬሳው ላይ የሚጨፍሩ አይደሉም፡፡ ይልቁንም አስቸጋሪና የተቋቋማቸው ጠላታቸውን ሲጥሉት ለአስከሬኑ ሳይቀር ክብርን የሚሰጡ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው ተቃራኒ ጠላት የሆነ ግን ጀግና አስከሬን ለውሻና ለአውሬ የሚሰጡ ሳይሆን በክብር የሚቀብሩ ውጊያውን የአላማ እንጂ የተፈጥሮ ጠላትነት እንዳልሆነ የሚያስቡ ናቸው፡፡ ሰውን በሰበዐዊነቱ የሚያከብሩ ልዩ አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ የእውነተኞቹ ጀግኖች ልዩ መገለጫ ነው፡፡ ሚንሊክ ይህ ባሕሪ ልዩ መገለጫቸው ከሆኑ አንዱ ነበሩ! በነዚህ መስፈርቶች መሠረት ግን ብዙዎች በኢትዮጵያ ጀግኖች እየተባሉ የተወደሱትን ማንነት ቴዎድሮስን ጨምሮ እጠራጠራለሁ፡፡ ይልቁንስ በቅርብ ታሪክ የምናውቀው ሕወሐት አባል የነበረው ኃያሎም አረአያ እነዚህ የጀግኖች ልዩ መገለጫ ያልኳቸው ባህሪያት እንደነበሩት ብዙ የሰማቸው ገድሎቹ ይናገራሉ፡፡
እንግዲህ በስሜትና በጥላቻ በመረቀዙ አእምሮዎች ሳይሆን እውነትን ለመጋፈጥ በሚደፍሩ አእምሮዎች እኔ የተረዳሁትን የሚንሊክን ማንነት አይደለም የሚል ካለ ለማደመጥ እወዳለሁ፡፡ ሚንሊክ ሩሩህና ይቅር ባይነታቸው ባደረቸው ጦርነቶች ሁሉ በደረሱ እልቂቶችና ጥፋቶች እጅግ ይጸጸቱ ነበር፡፡ ችግሩ አማራጭ ብቻ በማጣታቸው ጦርነቱ ግድ ሆኖማቸው እንጂ፡፡ በደረሰው ጥፋት ካዘኑባቸው ጦርነቶች አንዱ ደግሞ የአርሲው ጦርነት ነው፡፡ በጦርነቱ አሸንፈው አገሩን ከተቆጣጠሩት በኋላም ወታደሮቻቸውን ሕዝቡ ባለማወቁ ምክነያት የደረሰበትን እልቂት አሳዝኗቸው ወታደሮቻቸውን አሸንፌያለሁ በሚል በሕዝቡ ላይ ሌላ በደል እነዳያደርጉበት አዋጅ አውጥተው ሁሉ ነበር፡፡ ለወታደሮቻቸውም የአርሲን ሕዝብ ሲገልጹት ወንድምህ የአርሲ ሕዝብ እያሉ ነበር እንጂ እንደ ጠላት አልነበረም፡፡ ይህን እውነታ የታሪክ አዋቂ ነን የሚሉት ለምን ለሕዝብ ለማሳወቅ አልፈለጉም፡፡ ይልቁንስ የሚንልክ ትዛዛዊ ግፍ ለመሆኑ አጠራጣሪ ስለሆነው ሀርካሙራና ሀርማ ሙራ ማግዘፍን ለምን ፈለጉ፡፡ ሌላው የሚንሊክ ማንነት የተገለጸበት ጦርነት የወላይታው ከንጉስ ጦና ጋር የነበራቸው ጦርነት ነው፡፡ ንጉስ ጦናን አሸንፈው በእጃቸው ካገቡና አላማቸውን ከአሳመኗቸው በኋላ ንግሰናቸውን አጽድቀው እንደሾሟቸው ይነገራል፡፡ ከዚያም በላይ ጦና በጦርነቱ በመቁሰላቸው ምክነያት ሌላውን ሰው ባለማመን ሚንሊክ ራሳቸው እየተከታተሉ እንዲታከሙ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ሌሎችም አያሌ የሚንሊክን ሕይወት የሚናገሩ መዛግብቶች ሩሩሕና የጅግና ሰው ልዩ መገለጫ የሆኑትን ባሕሪያቸውን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ሚንሊክ ጋር በቀል የለም ጭጋኔም የለም የአላማ ጽኑነትና ታላቅነት እንጂ፡፡ ዘረኝነትም የለም ሰበዐዊነት እንጂ፡፡ በሚንሊክ አስተዳደር ወቅት ኢትዮጵያ ዘመናዊ በሚመስል ፌደራሊዝም ትተዳደር እንደነበር ስነቶቻችን እናውቃለን? አንዳንድ የሚንሊክን አላማ ለመረዳት እመቢ ባሉ መሳፍንት በቀር ከጦርነት በኋላ ሳይቀር ለእነዚያው የተዋጓቸው መሳፍንት ስልጣንን በሰጠት የራሳቸውን አካባቢ እንዲያስተዳድሩ ያደርጉ ነበር፡፡ በወቅቱ የተሸለ ግንዛቤ የነበራቸው እንደነ አባ ጅፋር የጅማው ያሉ የሚንሊክን አላማና ራዕይ ለመረዳት ስላልተቸገሩ በሠላም በአገር አንድ ማድረጉ ሂደት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የሚንሊክ እውነተኛው ታሪክ ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን አገር የፈጠሩ፣ አለም ላይ በእሳቸው ዘመን ኡሉ የተባሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ያስገቡ እነዚህም ስልክ፣ ኤሌክትሪክ፣ መኪና፣ ባቡር፣ ሌሎችም፣ አገርን በዘበናዊ አስተዳደር እንድትመራ የዋቀሩ (ሚኒስቴር መሠረት ያደረገ) ሌሎች ብዙ በአንድ ሰው እድሜ ሊሰሩ የሚችሉ የማይመሰሉ ብዙ ራዕዮችን በተግባር ያስጀመሩ ናቸው፡፡ ይህን ሁሉ ማድረጋቸው ሳያንስ ሚንሊክን ከቅርብ ወዳጅ እስከ ሩቅ ባላአንጣዎቻቸው እጅግ ፈታኝ መነቆዎች ነበሩባቸው፡፡ በወቅቱ ባለው ኋላቀር አመለካከት ምክነያት ብዙ የቅርብ የተባሉ የቤተመንግስቱና የቤተክህነቱ ሰዎች እንቀፋቶች እንጂ ለሚንሊክ አጋዥ አልነበሩም፡፡ በሚንሊክ የአገር አንድ የማድረግም ሆነ አገርን ወደ ዘመናዊነት መቀየር ሂደት በተሻለ ወሳኝ ሚና የነበራቸው የውጭ አገር ሰዎችና አንዳንድ የቅርብ አባሮቻቸው ናቸው፡፡ ከቅር አባሮቻቸው ደግሞ በተለይም አገርን አንድ በማድረጉ ሂደት የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ከየትኛውም የኢትዮጵ የሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪ በታሪካዊው የአድዋው የሚንሊክ ድልም እንደዛው ከሌሎች በተለየ ነበር፡፡
ዛሬ ላለው አብዛኛው የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ግን የሚንሊክም ታሪክ እነዛ የሚንሊክ የቀኝ ክንድ የነበሩት ኦሮምኛ ተናጋሪ ሸዌዎችም የሚታየው በበጎ ሳይሆን በጥላቻ ነው፡፡ ምክነያቱ ደግሞ የታላቅ ባለራዕዮች ሕልም የማይገባቸው፣ በተንኮል የነወረ አእምሮ ይዘው ታሪክን በማጉደፍ ትውልድን በእነሱ በተመረዘ አእምሮ ለመበከል ያሰራጩት መርዝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለአሁኑ ትውልድ የበለጠ የታሪክ ትውስታና ክፉውም ደጉም ከሞላ ጎደል ከሚታወቀው የደርግና የኃ/ሥላሴ ዘመን ስህተቶች ይልቅ የሚንሊክ ዘመን ስህተትን አቅርቦና አግዝፎ ለማሳየት የተመረዙ አእምሮዎች የሚፈጥሯቸው ሀተታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ምክነያቱ ግልጽ ነው አሁን ያለው ትውልድ የሚንሊክን ዘመን እውነተኛ ነገሮች በአካል የሚመሰክርለት የለውም ስለዚህ ምስክር በሌለበት በመሰሪዎቹ አእምሮው ሊመረዝ የሚችለው በቆየው ታሪክ እንጅ በአካል ያሉ መስካሪዎች ባሉበት ታሪክን ለመዋሸት ስለማይመች ነው፡፡ ሌላው ሚንሊክ የሠሩትን ታላላቅ ሥራዎች በበጎነቱ ማንሳቱ ራስን የሚያሶቅስ አደጋ ስላለው ነው፡፡ ዛሬ ላለው ትውልድ የሚንሊክ ዘመን ራዕይ ባለዕዳ አደርጎታልና ነው፡፡ በሚንሊክ ዘመን ራዕይ ይህች አገር ቀጥላ ቢሆን የት በደረሰች ነበር፡፡ ሌላው የሚንሊክ ራዕይ የአገር አንድነትና ብልፅግና ልዩ መሠረት ሥለነበር ይህንን መሠረት ሳያፈርሱ ስለዘረኝነት፣ ቀበሌ ዝቅ ብሎም ስለ ጎጥ እንዲያስብ ሕዝብን ማምከን አይቻልም፡፡
ዛሬ ከየትኛውም ክልል ትልልቅ ከሚባሉ ክልሎች በሚያሳዝን ሁኔታ የኦሮምያ ክልል በልማቱም ሆነ በመልካም አስተዳደሩ ወደ ኋላ መቅረቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ መሠረታዊ ምክነያቱ ሕዝቡን ከሌሎች ጋርም ሆነ እርስ በእርስ ትብብር እንዳይኖረው የጥላቻን ዘፈን እየዘፈኑለት የራሳቸውን ኑሮ በተፈጠረላቸው አጋጣሚ እንደ ልባቸው የሚኖሩ ኦሮሞ ነን ባይዮች አደገኛ ዜጎች ናቸው፡፡ ይህንን ከሚያክል ትልቅ ክልልና ሕዝብ አይደለም ኢትዮጵያን ሊመራ የሚችል ክልሉን ሊመራ የሚችል ሰው ታጥቷል፡፡ ኦሮሞ ነኝ የሚለው አብዛኛው የዛሬው ትውልድ ትልቁ እርካታው የሌሎች መውደቅ በተለይም ነፍጠኛ እያሉ የሚጠሩት የአማራውና አሁን በስልጣን ላይ በብዛት እንደተወከለ የሚነገርለት የትግራይ ሕዝብ ውድቀት እንጂ የራሱ ብልጽግና አይደለም፡፡ ለኦምኛ ተናጋሪው ክልል በልማትና በአስተዳደር ወደ ኋላ መቅረት ቁጭት ተሰምቶት ሊሰራ ከሚሞክር መሪና ትውልድ ይልቅ ከብዙ አመታት በፊት የተፈጠሩ የታሪክ ስሕተቶች ደግሞደጋግሞ በማላዘን ሌላ መርዛማና በጥላቻ የተበከለ ትውልድ ለማዘጋጀት ተግቶ የሚሰራው በዝቷል፡፡
ዛሬ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሆኖ ያለው ሕዝብ በዘር (በደም) አንድ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በደም ግንድ ከሆነ የወለጋና ሐረር ኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ከሚቀራረበው በላይ የጎጃ አማርኛ ተናጋሪውና የወለጋ ኦሮምኛ ተናጋሪው ይቀራረባሉ፡፡ የባሌና ሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከሚቀራረቡት በላይ የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪና የሸዋ አማርኛ ተናጋሪ የበለጠ የደም ትስስር አላቸው፡፡ በባህልም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ ዛሬ ዘረኝነትንና የቀበሌ አስተሳሰብን የሚሰብኩ ግን ቋንቋን ተመርኩዘው ግዙፉን ሕዝብ በአንድ ከአጨቁትና ከሌሎች ጋር ሕብረት እንዳይኖረው ከአወሩት በኋላ ወደታች ደግሞ በጎሳና፣ ቀበሌ፣ ዝቅ ብለው በጎጥ ይሸነሽኑታል፡፡ የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ከሌሎች በአካባቢው የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያልተጋጨው የለም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነበር፡፡ ሕዝቡ ለሌሎች ጥላቻ እንዲኖረው ስለሚሰበክ ነው፡፡ አልፎም ይሄው መለያየትን የሚሰብከው መዝሙር እርስ በእርስ ሳይቀር ጥላቻንና ግጭትን አስነስቶ አይተናል፡ እንደወንድማማች የሚተያዩት ጉጂና ቦረናን ሳይቀር ለከፍተኛ ደም መፋሰስ ዳርጓል፡፡
ይሄው ሃያ ምናምን አመት ሙሉ ስለቀድሙት ገዥዎች ጭቆናና በደል ሲነግሩን፡፡ የቀደሙትስ ጨቋኝና ጨካኝ ሆነው የኦሮሞን ሕዝብ ሲበድሉት ኖሩ ተብሎ ይታሰብ ዛሬስ የዚያን ዘመን በደል ሊያስረሳ የሚችል መሪ እንዴት ከዚህ ትልቅ ሕዝብ መካከል ጠፋ፡፡ እውነታው የቀደሙት ጨካኝና በደል አድርሰውም ከሆን ለኦሮምኛ ተናጋሪው የተለየ አልነበረም፡፡ ብዙ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ አማርኛ ተናጋሪ ከነበረው ይልቁንም የነገስታቱ ወገን ነው ተብሎ ከሚታመነው የሸዋ አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ በቀድሞ ነገስታት የተሻለ ተጠቃሚ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ሌላው ቀርቶ የነገስታቱ የቅርብ አጋር እየተባለ ዛሬም ድረስ በሌላው የኦሮምኛ ተናጋሪ በጥሩ አይን የማይታየው የሸዋው ኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ በነገስታቱ ዘመን አንዳች ተጠቃሚ እንዳልነበረ አእምሮ ካለን እናስተውላለን፡፡ ለእነዚህ ሕዝቦች ከሌላው በተሻለ የቀረላቸው ሀብት ቢኖር ሌላውን በጥላቻ አለመመልከት ለአገር አንድነትም ልዩ ፍቅር መኖር ነው፡፡
ሌሎች ክልሎች በአቅማቸው ልማታቸውንና የአስተዳደርም ችግራቸውን በፍታት ልዩ መንገድን እየሄዱ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የቀድሞው ገዥና ጨቋኝ ተብለው የተፈረደባቸው የአማርኛው ተናጋሪ ሕዝብ ክልል በቁጭት በሚመስል ሁኔታ እያደገ ለመሆኑ ግልጽ እየሆነና ልዩነቱንም ከሌሎች እያሰፋ መሆኑን እያሳየን ይገኛል፡፡ ትግራይ የገዥውን መንግስት ድጋፍ እያገኝ ስለሆነ ነው እየተባለ ቢታማም እውነታው የእድገት ጥማት ባላቸው መሪዎች ምክነያት እንጂ የማዕከላዊው መንግስት ተፅዕኖ ብቻ እንዳልሆነ እናያየለን፡፡ ደቡብና ሌሎች አናሳ እይተባሉ የሚጠሩ ክልሎች ሳይቀር ከኦሮምያ በተሻለ ዕድገት እያሳዩ ናቸው፡፡ በማዕከላዊውም መንግስት ያላቸው ተሳትፎ ከኦሮምያ ይልቅ የደቡብ የተሻለ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምክነያቱ ግልጽ ነው ኦሮምያ ኢትዮጵያን በሚወክል አመለካከት ይቅርና ክልሉን እንኳን በሚወክል አመለካከት የተገነባ ሰው ታጥቶበታል፡፡ በደቡብ ብዙ ሕዝቦች ኢትዮጵያዊ መሠረትን በደንብ ያደበሩ ናቸው፡፡ በኦሮምያ ሌሎችን በመጥላት የተጀመረው ሂደት ዛሬ ወርዶ ቀበሌ ደርሷል፡፡ ወለጋው ወለጋውን፣ አርሲው አርሲውን፣ ታች ወርዶ ደግሞ ሻንቡ ሀረቶ ምናምን እያለ የሚከፋፍል ነው፡፡ ይህ አይነቱ ባሕሪ በሌሎች ክልሎች አይንጸባረቅም ሳይሆን በንጸባረቅም ሌሎች ሌሎችን ጨምረው በሚያማክሉ ከፍተኛ ባለአእምሮዎች ይመክንና ቀበሌ ከሆነ ቀበሌ፣ ከፍ ብሎ በክልልም ከሆን ክልሉን ሳያልፍ ይመክናል፡፡ ኦሮምያ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ የወረደውን የጎጠኝነት ስሜትና አመለካከት የሚያመክን ጠፍቶ ትውልዱ በአብዛኛው በወረደው ጎጠኝነት ስሜት መክኗል፡፡
አሳዛኙ ነገር ተማርን የተሸለ የሕወት ልምድ አልን በሚሉት ይህ የአመለካከት ወርደት በርትቷል፡፡ በተለይም ደግሞ በተለያዩ መንገድ ወደ ውጭ ሄዶ በሚኖረው የኦሮምኛ ተናጋሪው ለሌሎች ያለው ጥላቻ እጅግ የከፋ ነው፡፡ አማራ ወይም ትግሬ የሚባለውን በመጥላት ሌሎችን ይጋብዛል፡፡ ሌሎችንም ወንድም እንደሆነ ሊሰብክ ይሞክራል፡፡ ይህ ጥላቻን ያዘለው ስብከት ከትልቋ ኢትዮጵያ እስከ ታች ተራ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በቅርቡ በቴዲ አፍሮ ምክነያት የበደሌን ቢራ ላለመጠጣት የተደረገው አድማ አንዱ ሕዝቡ እንዴትና በምን አይነት አመለካከቶች እንደሚመራ በሌላውም ላይ ያለው ጥላቻ ምን ያህል እንደሆነ ያመላከተ ነበር፡፡ ይህን ለሚያሕል አደማ ደግሞ ያደረሰው በሌሎች ከፍተኛ አደናቆትን ያተረፈው የቴዲ አፍሮ ጥቁር ሰው የሚለው ዘፈኑ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ የቴዲው ጥቁር ሰው ሚንሊክ ግን ለአፍሪካ ሳይቀር ኩራት እንጂ የሚያሳፍር አልነበረም፡፡ በጥላቻ የተመረዘው የእኛው ኦሮምኛ ተናጋሪ ግን ያንን የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ክብር የሆነውን ታሪክ ለመስማት አለመፈለግ ብቻም ሳይሆን ያንን ታሪክ የሚያነሱትን በሚያገኘው አጋጣሚ ሊበቀል እንዳለው አየን፡፡ አሁን ያለው እንዲህ የተመረዘው የኦሮምኛ ተናጋሪ ትውልድ ግን ስለሚንሊክም ሆነ በዘመኑ ስለነበሩ ክስተቶች በውል የሚያውቀው ነገር የለም መርዛማና የራሳቸውን ልዩ ፍላጎት በሕዝቡ ሊያሳኩ የሚያሴሩትን ስብከት ተቀበለ እንጂ፡፡
በቅርቡ የሀረካ ሙራ ሐርማ ሙራ መታሰቢያ በሚል አንድ ሐውልት ተመርቋል፡፡ እኔ እውነትም ይህ ክስተት በየትኛውም ስህተት ቢሆን ተከስቶ ከነበረ መታሰቢያ መቆሙ ክፋት አለው ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም ክስተቱ ተፈጠረ ከተባለ ከስንት ዘመን በኋላ ዛሬ ሀውልት ለማቆም የታሰበበት አላማ ያንን ክስተት ለማስታወስ የተደረገ ሳይሆን ይልቁንም ጥላቻን ለማጠናከር እንዲህ ያደረገሕ ሕዝብ ነበር ለማለት የቆመ ሀውልት ሆኖ ነው የተሰማኝ፡፡ አሁን አሁን እንደውም ያ አሳቃዊ ክስትት ሆን ተብሎ የተፈጠረ ታሪክ ነውም ብዬ እየተጠራጠርኩ ነው ከሌሎች ጋር ጥላቻ እንዲፈጠር የሚደረገው ሴራ ብዙ ነውና፡፡ ይህ ሀውልት በተመረቀበት በዚህ ሰሞን የሩዋንዳውም እልቂት ሃያኛ ዓመት የሚታሰበበት ነበር፡፡ ሲታሰብ ግን ልዩ መልዕክት የነበረው የተፈጠረውን ክስተት የሚያስረሳ ሰላምንና የአገር ብልጽግናን በዚያች አገር የማምጣት ራዕን ነው፡፡ ሐውልት እነኳን ለእነዚያ ዜጎች መታሰቢያ ማቆም ቢያስፈልግ ዳግም እንደዚያ ያለ አረመኔነት በዚያች አገር እንዳይከሰት ለትውልድ ማስተማሪያነት እንጂ ቂም በቀለኝነትን ለማቆየት አይሆንም፡፡ የኦሮምያው የሀርካ ሙራ ሐርማ ሙራ ሐውልት ግን ግልጽ መልዕክቱ ሌሎችን በመጥላት የተመረዘውን ብዙ የኦሮምኛ ሕዝብ የበለጠ ጥላቻ እንዲያድርበት ሌሎችም ሌሎችን በመጥላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ የታለመ ነው ብዬ አመንኩ፡፡
ብዙ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የወደፊት ብሩሕ ራዕይ ደስተኛ አይደለም፡፡ እነዚህ የሕዝቡ አካላት የኢትዮጵያን ውድቀት እጅግ የሚመኙ ናቸው፡፡ ሌላ ቀርቶ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ወይም እነሱ በጣም ከሚጠሉት አማራ ወይም ትግሬ ከሚባለው ሕዝብ ጋር የተያያዘ የራሳቸው ነገር እንኳን እርም ነው፡፡ የአባይ ወንዝን እንደምሳሌ ላንሳው፡፡ የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ብዙ ይነሳል፡፡ መነሻው ደግሞ ጎጃም የጮቄ ተራራ ነው፡፡ ሆኖም አባይን በውል የምታውቁት ካላችሁ አባይን አባይ ያደረገው የጮቄ ተራራ ወይም ከጣና የቀዘፈው ውሀ ሳይሆን ከኦሮምያ የሚነሱ ታላላቅ ወንዞች ናቸው፡፡ በተለይም ደዴሳና ዳቡስ፡፡ ይሄንን ለማስተዋል አሁን ግድብ እየተሰራበት ያለውን ቦታ የሚፈሰውን ውሃና ወደጎጃም ስትሻገሩ የምታዩትን ውሃ አስተውሉ፡፡ ግብጾቹም ይሁኑ ሌሎች እንቅልፍ የሚነሳቸው ጎጃም ያያችሁት አባይ አይደለም ደቡስና ዴዴሳ የደለቡት አባይ እንጂ፡፡ የአባይ ሥም ሲነሳ ግን ብዙ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ጥሩ ስሜት የለውም፡፡ ግድቡን ጨምሮ ሌሎች ለኢትዮጵያ ብልጽግናም ትልቅ ድርሻ ያላቸው ልማቶችም እንዲሁ በብዙ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ በመልክም አይታዩም፡፡ ግን ለምን? የሚንሊክን ታሪክና ዘመን እንዲህ በጥላቻ የሚያስመለክትስ በእውን የተጨበጠ ይቅር የማያሰኝ ስህተት አለ? ካለስ ይህ ትውልድ እነዴትና በምን ምክነያት እነዚያ ስህተቶች እንደተከሰቱ ምን ያህል ተረድቶ ነው እንዲህ በጥላቻ የተመረዘው?! ነው ወይስ አሁንም እያየን እንዳለንው የኢትዮጵያ ነገር ስለማያደስተው ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተቆራኘውን የአገሪቱን መስራች ሚንሊክን በስሜት ብቻ መጥላት ይሆን?
ኦሮምያ ውስጥ ባለፉት ሃያ ምናምን አመት ከተከሰተው ግፍ በላይ በቀደሙ የታሪክ ጊዜያት ለመከሰቱ ጥያቄ እያጫረብኝ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ! ኦሮምያ የሚባለውም ክልል ይሁን ኦሮምኛ ተናጋሪ የተባለው ሕዝብ ግልጽ በሚታይ ሁኔታ እየተቀደመ እንደሆነ ይረዳ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይህ ልዩነት ጎልቶ ሲታይ ይህችን መልዕክቴን ያነበቡ ያስታውሱ ይሆናል፡፡ ግን ለምን???!!
የታላቋ ቀን ልጅ ሚያዝያ 1 2006 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment