Wednesday, April 9, 2014

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ያልጠሩ ፓርቲዎችን አስጠነቀቀ

                   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በፓርቲያቸው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት በወቅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ፓርቲዎችን አስጠነቀቀ።
ቦርዱ ሰሞኑን ለፓርቲዎቹ አመራሮች ደብረዘይት በሚገኘው የስራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከሰጣቸው በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ የሚያሳስብ ደብዳቤ ሰጥቷቸዋል።
ቦርዱ በፓርቲዎቹ በበተነው ደብዳቤ እስካሁን በውስጥ ደንባቸው መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያሳለፉ ፓርቲዎች ጉባኤያቸውን በማካሄድ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል። ቦርዱ ጉባኤ አልጠሩም ላላቸው ፓርቲዎች የላከው ደብዳቤ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው።
ቦርዱ ለፓርቲዎቹ እስከ ሚያዚያ 30 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ ቢያዝም አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት እንደሚቸገሩ በመግለፅ ላይ ናቸው። አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች አንዴ ከተመሠረቱ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አመራር መምረጥ እንዳልቻሉ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ፓርቲዎቹ በሚመሩበት ሕገ-ደንብ መሠረት ጉባኤ በማካሄድ አመራር ከመመረጥ ይልቅ ልዩነት ሲፈጠር ብቻ ጉባኤ እንዲጠራ ቦርዱን እንደሚጠይቁ የታወቀ ሲሆን፤ ቀላል የማይባሉ ፓርቲዎች መሪዎቻቸውና የፓርቲዎቹ አድራሻ እንኳ የማይታወቅበት አጋጣሚ እንዳለም ለቦርዱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልፃሉ።
ባለፈው ዓመት በወቅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራትና አግባብ ያለው የሂሳብ ሪፖርት ላቀረቡ 13 ለሚሆኑ ፓርቲዎች ቦርዱ የምስጋና ደብዳቤ መፃፉ ይታወሳል። ቦርዱ ጉባኤ ያልጠሩ ፓርቲዎችን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሕግ ክፍተት መኖሩን አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል። ፓርቲዎቹ ሲመሰረቱ ብቻ እውቅና ለመጠየቅ ወደ ቦርዱ ከመሄድ ውጪ አንድ ጊዜ እውቅና ካገኙ በኋላ አድራሻቸው የሚጠፋበት አጋጣሚ እንዳለም እየተነገረ ነው። በአሁኑ ወቅት ጉባኤ ጠርተው አመራራቸውን ላላሳወቁ ፓርቲዎች ቦርዱ የፃፈው ደብዳቤ ከማሳሰብ ባለፈ ጥርስ እንደሌለው የሚገልፁ አሉ።
በአሁኑ ወቅት 79 ፓርቲዎች ሲኖሩ፤ 54 የሚሆኑ በክልል የተደራጁ ቀሪዎቹ 24 የሚሆኑ ደግሞ ሀገር አቀፍ መሆናቸው ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ቦርዱ ለፓርቲዎቹ ስለፃፈው ደብዳቤ ተጨማሪ ማብራሪያ የተጠየቀ ሲሆን፤ ማሳሰቢያው ለፓርቲዎቹ በማስታወቂያ እየተገለፀ መሆኑን በመግለፅ ወደፊት ከፓርቲዎቹ ጋር በመመካከር ምን ያህል ፓርቲዎች ጉባኤ እንዳልጠሩና እነማን እንደሆኑም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment